የምናብ ታሪካችን ወደ አንድ ትልቅ መኖሪያ ጊቢ ይወስደናል። የጊቤው ባለቤቶች እና ተከራዮች የፈጠሩት አነስተኛ ቀበሌ። እኒህን በአንድ ጊቤ ውስጥ የሚኖሩ ቤተሰቦችን በምናባችን እያሰብን ከመካከላቸው እንገኝ። ከጊቢው ትልቅነት የተነሳ ተከራዮቹ አይደለም እርስ በእርሳቸው በቤቱ ባለቤቶች በሙሉ እንኳን በወል አይተዋወቁም። ከብዛታቸው የተነሳ። ብዙ ተከራይ፤ ብዙ የቤተሰብ አባላት፤ ምናልባት ድሮ ድሮ ቢሆን አንድ ቀበሌ ነዋሪን ያክሉም ይሆናል።
በዚህ ትልቅ ጊቢ ውስጥ አንድ ቀን ማምሻው ላይ አንድ ነገር ሆነ፤ አስደንጋጭ ነገር። ሰው ሁሉ ከአዋቂነት ወደ ልጅነት ተቀያይሮ የሚታይበት ቀን። አንዱ ሰው ሌላውን ሰው የሚያየው የልጅ መልክ ሆኖ የሚታይበት ቀን።
ባልና ሚስት ሲተያዩ ሁለቱም የሚታያቸው በእድሜ የገፋ የትዳር አጋራቸው ሳይሆን የትዳር አጋራቸውን አለባበስ የለበሰ፤ አረማመድ የሚራመድ፤ ተመሳሳይ መልክ ያለው ነገር ግን እድሜው ልጅ የሆነ ሰው። በተከራዮቹም ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ። የቤት ኪራዩን ሊከፍል ወደ አከራዮቹ ቤት ጎራ ያለ ሰው አከራዮቹን አጥቶ የሚገጥመው አከራዮችን መሳይ ልጆች የሆነበት ቀን። ብሩን የሚቀበለው ሲያጣ ለልጆች ልክፈል አልክፈል ብሎ ተከራይ ግርታ ውስጥ የሚሆንበት ማምሻ። አከራዩ ደግሞ ተከራዩን የሚመስል ሰው ሲያይ “እንዴት እራሱ መጥቶ ኪራዬን አይከፍለኝም፤ ምኑን ልጅ ነው የላከብኝ” ብሎ የሚጠይቅበት ቅጽበት።
ባል “ቁጭ ሚስቴን የምትመስል ልጅ” ይላል፤ ሚስትም “ቁጭ ባሌን የሚመስል ልጅ” ትላለች፤ ሁሉም እርስ በእርሱ እንደ እዚያ ይተያያል። ተመልካቹ አዋቂ፤ የሚመለከታቸው በሙሉ ልጆች። በግርታ ውስጥ የሚተራመስ ጊቢ፤ በጥያቄ ውስጥ የተሞሉ የጊቢው ነዋሪዎች። መልስ መስጠት የሚችል ሰው የሌለበት የእውር ድንብር ጉዞ። በሬዲዮ የሚነገረው፤ በቲቪ የሚሰራጨው፤ በሞባይል የሚታየው ሁሉም ባለበት ነው። የእይታው ድንግርታ ያለው እርስ በእርስ ባለው መተያየት ውስጥ ነው።
ይህን የመሰለ እንግዳ ነገር ሲሆን ግርታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው። ግርታው እንዴት ሊፈታ ይችላል? አንባቢው ራሱን ሊጠይቀው የሚገባ ጥያቄ ነው። ግርታው ሲፈታ ምን ሊሆን ይችላል? ደስታ ወይንስ ሃዘን። ወይንስ እንዲሁ መገረም፤ የስሜት መዘበራረቅ።
የጊቢው አባላት ግርታ ውስጥ ቢሆኑም የግርታውን ምንጭ መረዳት ያልቻሉበት ምክንያት መረዳት ቀላል ነው፤ ምክንያቱም ተመልካቹ ራሱን እንደ አዋቂ የመመልከቱ ምስል አብሮት ያለ መሆኑ ነው። ሁሉም ሰው አዋቂ መሆኑን የራሱን ምስል ያውቀዋል፤ ችግሩ ሌሎችን ሲያይ የሚይበት መንገድ ነው። በሌላው ሰው ዘንድ እንደ ልጅ ቢታይም ራሱን የሚያየው ግን እንደ አዋቂ ነውና ጉዳዩ ለመረዳት አስቸጋሪ ሆነ። በሬዲዮ የሚነገረው፤ በቲቪ የሚሰራጨው፤ በሞባይል የሚታየው ሁሉም ባለበት መሆኑ ግርታውን ለመመርመር እድል የማይሰጥ ሆነ።
“ውይ አባወራውን የሚመስል ልጅ” ስትል እናት አባወራው ደግሞ “አንቺ ምን ሆነሻል ቁርጥ ሚስቴን የምትመስይ” ይላል፤ ሁሉም ሊግባባ አልቻለም። በሁሉም ውስጥ ግን መጠበቅ አለ፤ ልጁን የሚመስለው እውነተኛው ሰው እንዲመጣ መጠበቅ። ጥበቃው እየገፋ ሲሄድ አዲስ ነገር አልገለጥ ማለቱ ነው ችግሩ። አባት ስለ ሚስቱ ሲያስብ “ምናልባት ወደ ጎረቤት ሄዳ ነው ስትመጣ እርሷን የምትመስላውን ልጅ ከየት እንደመጣች ታስተዋውቀኛለች” ብሎ ይጠብቃል፤ ሚስትም እንደእዚያው። ሁሉም እየጠበቀ ሰዓቱ ነጎደ። የታሰበው ለውጥ ግን አልነበረም።
እንዲህ ባለ ጊቢ ውስጥ አንድ ሁኔታውን በአግባቡ የተረዳና የጊቢውን ነዋሪዎች ከግርታ ሊያወጣ የሚችል ሰው ወደ ጊቢው ቢገባ ሊል የሚችለውን መገመት ጥሩ ነው። ይህም ሰው “እይታችሁ ላይ ችግር አለ፤ ሌላ የሚመጣ ሰው የለም ሁላችሁም ችግራችሁ እይታችሁ ላይ ነው” ቢል ሊያምኑት ይችሉ ይሆን? አይመስልም። ቀኑ እየጨመረ ሲመጣ ሊግባቡ አለመቻላቸውን ሲያውቁ የግለሰቡን አስተያየት እያመኑ ይመጡ ይሆናል። የበለጠ የሚያምኑት ከመካከላቸው እይታው የተቀየረለት ሰው ምስክርነት መስጠት ቢችል ነው። ግለሰቡን የሚያዩት በልጅነት ሳይሆን በአዋቂነት ከሆነ። በሂደትም የሁሉም እይታ እየተቀየረ ሲመጣ “ምንድን ነበር የሆነው!” የሚለው የመገረም ጥያቄ የሁሉም ጥያቄ ይሆናል። እዚያው ድረስ ግን አንዱ ሌላውን እንደ ህጻን ወይንም እንደ ልጅ እየተመለከተ በግርታ ውስጥ ይኖራል። ወደ ትክክለኛው እይታ ለመመለስ የሚመጣውን አንድ ሰው እስኪያገኝ ድረስ። ድንግርታው ሳያደናግረው እንደ እብድ እየተቆጠረም ቢሆን ወደ እይታ መቀየር ሌሎችን የሚመራው ሰው። እንግዳ ነገር ሲሆን፤ …
እንግዳ ነገር በሃዘንም ሆነ በደስታ እንዲሁም በአጠቃላይ ድንግርታ ውስጥ ሊገለጽ ይችላል። ድንግርታውን ለምደነው መደበኛ ሕይወታችን አካል እስካለደርግነው ድረስ በእንግዳ ስሜት ውስጥ እንኖራለን። በሀዘን እና ደስታ የእንግዳ ወቅት ማሳያዎች አልፈን ግርታ ሲያጋጥም እንዴት ልንወጣው እንደሚገባ ወደሚያሳስበው ነጥቦች እናምራ።
አንዱ ድንግርታ ወደ ሌላ ድንግርታ፤ አንዱ የስሜት ትርጉም ለሌላው እያቀበለ በስሜት ማእበል ውስጥ እየተላጋ የሰው ልጅ በምድር ላይ እየኖረ አለ። በእውቁ ገጣሚ ኦስካር ዊልድ አባባል መሰረት አንድ ስሜት ፈጽሞውኑ ሊደገም የማይችል ነው፤ ሌላኛው ስሜት ይከተል ይሆናል እንጂ። ጥያቄው በድንግርታ ውስጥ ስንገኝ ወይንም እንግዳ ነገር ሲገጥመን እንዴት ተቀብለን እናስተናግደዋለን ነው፤ የምናተርፍበት ወይንም የምንከስርበት የሚሆንበት አግባብ።
ሀዘን
አንባቢው በሃዘን ስሜት ውስጥ ይገኝ ይሆን? በምን አይነት ሃዘን? በጥልቅ ወይንስ በመለስተኛ? እንግዳ ነገር ከሚፈጠርባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ሃዘን ነው። ሀዘን ሰዎች ጠብቀውትም ሆነ ሳጠብቁት የሚገጥም ነገር ነው። ሃዘን እንደ ሃዘኑ አጠባበቃችን ክብደቱን ቅለቱ ይወሰናል። ለረጅም ጊዜ በህክምና ሲረዳ የቆየ ሰው ከህክምናው ሁኔታ ተነስቶ ሊገጥመው የሚችለውን የከፈ ነገር ልንገምት እንችላለን። ታማሚው እየደከመ በሄደ ቁጥር አስታማሚው ቤተሰብ ለሃዘን እየተዘጋጀ ሲቆይ የሀዘን ስሜቱ እየቀለለ ይሄዳል። እንዲህ በመሰለ መንገድ የሚመጣ ሃዘን እየተጠበቀ ሊመጣ ስለሚችል እምብዛም ድንገተኛ ላይሆን ይችላልና እንግዳ ነገር ላይሆን ይችላል። ከእዚያ በተቃራኒ ግን የሚገጥም የሃዘን አይነት አለ፤ ፍጹም ድንገተኛ የሆነ የሃዘን አይነት ነው። ጠዋት ተሰናብቶን ወደ ስራ የሄደ ሰው መንገድ ላይ የመኪና አደጋ ገጥሞት ሕይወቱን ቢያጣ የሚሰማን ስሜት እጅግ አሳዛኝና እጅግም ድንገተኛ ነው። በሕይወታችን ላይ የሚፈጥረው ግርታ ሊገባን እስካይችል ድረስም ይደርሳል፤ ነገሮች በሙሉ ጨለማ ሆነው የሚታዩበት ድባብ።
እንዲህ አይነት ድንገተኛና ሀዘንን የምንቀበልበት መንገድና ሌሎችን የምንቀበልበት አንድ ሊሆን አይችልም። እንዲህ አይነት ሃዘን ሲገጥመን ምን እናደርጋለን? ምናልባት ዛሬ ላይ ማሰብ አንፈልግም ይሆናል። በተጨባጭ ግን በሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚደርስ መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም። ድንገተኛ ሃዘን የሚፈጥረው እንግዳ ነገር ሕይወታችንን ወደ ምን አቅጣጫ ይወስደው ይሆን? የሚያምኑት ሰው ድንገት እምነት አጉድሎ ሲገኝስ፤ መቀበል አቅቶን የምንወስደው እርምጃ ላይስ ምን እናስባለን? የቅርብ የምናውቃው የትዳር አጋሩን የገደለ ምናልባትም ራሱንም የገደለ ሰው ወደ አእምሮችን ይመጣስ ይሆን? እንግዳ ነገር ሲሆን ሰው ፈጽሞ እገኝበታለሁ ብሎ ባላሰበው መንደር ውስጥ ሊገኝ ይችላል፤ ግርታው መርቶ የሚያደርሰው ቦታ። በሃዘን ስሜት የሚገለጽ እንግዳ ነገር ደግሞ ከሌላው የተለየ ነው። ከባድ ስሜት፤ የውስጥ ጥንካሬን የሚፈትን፤ ውስጥን እንደ አለት አጠንክሮ መጓዝን የግድ የሚል።
የሀዘን ተቃራኒው ደስታ ሌላው የግርታ ስሜት ውስጥ የሚጨምር ነው፤ ከቀላል እስከ ውስብስብ ግርታ፤ የሕይወትን አቅጣጫ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ ሊያስኬድ የሚችል።
ደስታ
ያልተጠበቀ ሃዘን እንዳለ ሁሉ ያልተጠበቀም ደስታ አለ። ሎተሪ የቆረጠ ሰው ሎተሪው ለምን አልደረሰኝም ብሎ የማዘን እድሉ አነስተኛ ነው። ምክንያቱም ሎተሪ የመድረስ እድሉ ፈጽሞ ዜሮ በሚባል ደረጃ ስለሆነ ብዙም የሚጠብቀው ስላልሆነ። ነገር ግን አንድ ሰራተኛ የወር ደመወዝ እንደማይከፈለው ቢነገረው የሚሰማው ስሜት ቀላል አይሆንም፤ ትልቅ ግርታ። ምክንያቱም የሰራው ስራ እንዲከፈለው የሚጠብቀው በመሆኑ። ለሎተሪ የከፈለ ቢሆንም ሎተሪ የወጣለት ሰው ደስታው እንግዳ ሆኖ የሚገለጽ ነው፤ ያልጠበቀው ስለሚሆን። ከሎተሪም በላይ ፈጽሞ ድንገተኛ የሆነ የደስታ አይነትም አለ፤ ያልጠበቁት ሲሆን የሚፈጠር ደስታ። ለምሳሌ በውትድርና ላይ የተሰማራ የቤተሰብ አባል ሕይወቱን የማለፉ መርዶ ከተሰማ እና ቤተሰብም እርሙን ካወጣ በኋላ ሞቷል የተባለው ግለሰብ በአካል ሲመጣ የሚፈጥረው ስሜት ከባድ ነው። ኢትዮጵያ ለዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አለፈች ቢባል ወይንም የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን ብታነሳ ስሜቱ ፈጽሞ ለማንም ሰው ቀላል ሊሆን የሚችል ስሜት አይደለም፤ ፍጹም እንግዳ ነገር እንጂ። ለረጅም አመታት ልጅ እምቢ ብሏቸው የቆዩ ጥንዶች ልጅ ሲያገኙ የሚሰማቸው ስሜት ምን ሊሆን እንደሚችል እንዲሁ መገመት የእንግዳው ነገርን ትርጉም መረዳት ያስችላል። ያልታሰበ ደስታ ነውና ትርጉሙ ብዙ ነው።
በሀዘንም ሆነ በደስታ የሚገለጽ ልዩ ትኩረትን የሚስቡ ነገሮች በርካታ ናቸው። ከበርካታ ነገሮቹም መካከል አንባቢው የሚቆጥረው የራሱ ክስተት ይኖረዋል። ሕይወት እንዲህ ባለወቅት ውስጥ በምትሆንበት ጊዜ ወቅቱን ተቆጣጥሮ ማለፍ መቻል እርሱ ብልሃት ነው። አንዳንድ ሰሞን ካልጠበቅነው ሁኔታ ጋር አገናኝቶን ሊሆን ይችላል፤ ፈጽሞ ካልጠበቅነው። ጥያቄው ሁኔታው ወዴት እንደመራን የሚጠይቅ ነው። ወደ እድገት ወይንስ ወደ ቁልቁለት።
በሁለቱም የእንግዳ ነገር ማሳያዎች ውስጥ የጋራው ነገር፤ ስሜት ነው። ስሜት በደስታም በሃዘንም ጊዜ ትርጉም አለው። የአንድ ሰው ብስለቱም ሆነ ጥንካሬው የሚታየው ስሜቱን በማረቅ ውስጥ እንደሆነ የዘርፉ አጥኚዎች ይገልጻሉ። በውሳኔዎቻችን ውስጥ ስሜት ያለው ቦታ ትልቅ ነው። በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ስንሆን ልንሰራ የምንችለው ውጤታማን ስራ ታሳቢ በማድረግ ለስሜት እድገት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለብን እንረዳለን።
ስሜትን መግራት ማለት የስሜት መዋዠቅ በሚያጋጥም ጊዜ አዎንታዊ እርምጃ/positive action/ እንድንወስድ የሚረዳን ተግባር ነው። ለሕይወት ጠቀሜታ ያለውን አዎንታዊ እርምጃ መውሰድ ባለብን ጊዜ መውሰድ በመቻል ውስጥ አትራፊነት አለ። በሕይወት ጉዞ ውስጥ ትርፋማ ለመሆን ስሜትን መግራት ያለውን ቦታ በሚገባ መረዳት አስፈላጊ ነው።
አልበርት አንስታይን የመጀመሪያው የመቻልን አቅም የሚሰጠን ስሜት ከመንፈሳዊነት የሚቀዳው ስሜት እንደሆነ ያምናል። በመንፈሳዊነት ውስጥ አዎንታዊነት፤ ቀናዊነት፤ ስለሌሎች ማሰብ፤ ከምድር ስሌት ውጭ በሆነ ነገር ውስጥ የውስጠኛው አካላችንን እርካታ ማግኘት አለ። ሰዎች ሲሞቱ በቀብር ስነስርዓቱ ላይ የሚነበበው የሕይወት ታሪክ የአንድን ሰው የሕይወት ዘመኑን መንፈሳዊ ስሜትን የሚያንጸባርቁ ሆነው እናገኛቸዋለን። ይህ ስሜት ከውስጥ ወደ ውጭ የሆነ ስሜት ነው፤ ፈጽሞ በውጫዊው ነገር ላይ ያልተመሰረተ ስሜት፤ ከልብ ውስጥ የሚገኝ። ሔለን ኬለር “የዓለማችን ምርጡና ውብ የሆነው ነገር በአይን የሚታይ እንዲሁም የሚዳሰስ አይደለም ነገር ግን በውስጥ ልብ የሚሰማን ነው” ያለችውን ማስታወስ ይገባል። ዋጋቸው ውድ የሆኑ በእጅ የሚዳሰሱ፤ በአይን የሚታዩ፤ በምላሳችን የምናጣጥማቸው ወዘተ በርካታ ነገሮች አሉ፤ ገበያው የሞላው፤ ብዙ ብር የሚጠይቁን። ነገር ግን ከእዚህ ሁሉ ዋነኛው ከውስጥ የሆነ ነው፤ ከልብ ውስጥ።
የልብ እና የስሜት ቁርኝት ቀጥተኛ በመሆኑ ልብን የሰበረው ነገር ጉዟችንን ይሰብራል፤ ልብን የሚያሞቀው እርምጃችንን ያሞቃል፤ እንግዳው ነገርም ከእዚህ አንጻር የሚታይ ነው። እንግዳ ነገር እንዲገጥመን አስበን የምናደርገው ነገር የለም፤ እንግዳው ነገር ስሜትን በግልጽ አካል ለብሶ እንዲታይ የሚያደርግ በመሆኑ ጠቀስነው።
ከእንግዳ ነገር በተጨማሪም አቅደን ማከናወን በቻልናቸው ነገሮች እንዲሁ ልባችን ውስጥ የሚተከል ነገር አለ። ድርጅት መስርቶ ውጤታማ ማድረግን አቅዶ እርምጃ የጀመረና በተግባርም ማድረግ የቻል ሰው በተጨባጭ ወደፊት እንዲራመድ ያሳካው ነገር ምክንያት ይሆነዋል። ማሳካት ያልቻለው ነገር ደግሞ ስሜቱን ተቆጣጥሮ ወደ ነገው ለመሻገር ይቸገረዋል።
ዛሬ አቅደን በምንተገብረው ነገር ውስጥ የልብን አቅም መገንባት እንድንችል ከትንሽ ጀምረን አቅዶ የመተግበርን ባህል ማዳበር ያስፈልጋል። ይህ እንግዳን ነገር ሳይሆን በተፈጥሮ ሰው የመሆናችንን አቅም ተጠቅመን ልናደርገው የሚገባውን የሚያሳይ ነው። እንግዳ ነገር ግን ከእዚህ ተቃራኒ ነው። በደስታም ሆነ በሀዘን ውስጥ ምእራፉ የሚጀመር ልብን የመግራት፤ ስሜትን የመግራት አቅም ላይ ካልሆንን ደስታውም ሀዘኑም አሉታዊ ሆነው ሊመጡብን እንዲችሉ የሚያደርግ።
ጠንካራ ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲያልፉ የሚፈጥሩት ነገር ለሌሎች ነገርን ማቅለል የሚችሉበት ምእራፍ ውስጥ መድረስ ነው፤ ነገሮች በቀለለበት መንገድ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች ደግሞ ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የመግባት እድላቸው ሰፊ ነው። ይህ ምልልስ በሕይወት ውስጥ በብዙ ግለሰቦች ሆነ ቤተሰብ ውስጥ የሚታይ ነው። ስሜትን በመግራት፤ ልብን በአግባቡ በመያዝ በድምር ውጤቱ ሕይወትን በትክክለኛው መንገድ ውስጥ የማድረግን አስፈላጊነት የሚያሳይ። ድህነትን ታግሎ ያለፈ አባት ለልጆች በቀላል መንገድ ውስጥ ማለፍን ሲያጎናጽፍ እነርሱ በቀላሉ መንገድ ውስጥ አልፈው ጠንካራ ከመሆን ፈንታ በተቃራኒው እንዲገኙ የሚያደርግ ምልልስ ነው። በማግኘት ምክንያት ማጣት፤ በደስታ ምክንያት ሃዘን፤ በገንዘብ ምክንያት ድህነት፤ ወዘተ ማለት ነው።
ግርታ ሲፈጠር፤ ያልተጠበቀው ሲሆን፤ በስሜት ተነድቶ ከመሄድ እየሆነ ያለውን በአንክሮ በመመዘን ወደ ልባችን የመመለስ ጥበብ። በተጨባጭ ሊበዛልን የተገባው፤ ለዛሬ፤ለነገም።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2015 ዓም