የአሸባሪው ትህነግ በቅጥፈት የታጀበ የሴራ ጉዞ ከጫካ እስከ ከተማ የዘለቀ ብቻ ሳይሆን፤ ለሴራው ማሳለጫ የሚሆን የሃሰት ጩኸቱን የሚያግዙትና የሚያስተጋቡለት አያሌ አጋሮች በአገር ውስጥም በውጪ አገራትም ያሉት የጥፋት ኃይል ነው። ቡድኑ በትግራይ ሕዝብ ስም ነጻ አውጪ ብሎ ራሱን በመሾም የአንዳንድ ምዕራባውያን አገራትና ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ተልዕኮ ተሸክሞ ጫካ ሲገባ፤ የተልዕኮው ዳር ማድረሻ አቅም የሚሆነውን ሁሉ የሚያገኘው በህዝቡ ላይ በሚሰራቸው እኩይ ሴራዎች ላይ በመመስረት ከጋላቢዎቹ በሚዘረጋለት ዳረጎት ነበር።
ለምሳሌ፣ የ77ቱ ድርቅ ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ትህነግ ቀጠናውን የጦር አውድ በማድረጉ ዜጎች ተረጋግተው ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳያገኙ በማድረጉ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ከወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ አካባቢው የሚላከው ሰብዓዊ ድጋፍ ለትግራይ ሕዝብ እንዳይደርስ እክል በመፍጠር የትግራይን ህዝብ ለከፋ ረሃብ ዳርጎት ነበር። ይሄ ብቻም ሳይሆን ትህነግ የትግራይ ሕዝብ ባለበት ቆይቶ ድጋፍ የሚያገኝ ከሆነ ያቀደው ሴራ እንደማይሰምርለት በማወቁ፤ ከራያ አካባቢ ጀምሮ ህዝቡ ወደ ሱዳን እንዲሰደድ በማስገደድ “የማዕከላዊው መንግስት ለትግራይ ህዝብን ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረሰ ባለመሆኑ ህዝቡ ለከፋ ረሃብና ስደት ተዳርጓል” በሚል ማደናገሪያ ወሬና “መንግስት በትግራይ ሕዝብ ላይ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው” የሚል ቅጥፈትን አሰራጭቷል።
ከውጭ ሆነው የሚጋልቡትና የሚደግፉት ኃይሎችም ምንም እንኳን እውነቱን የሚያውቁት ቢሆንም፤ ዓላማቸው ኢትዮጵያን ማንኳሰስና የኢትዮጵያ መንግስትን ማስወገድ በመሆኑ ይሄንኑ የትህነግ ቅጥፈት በስፋት አስተጋብተዋል። አስተጋብተውም ዝም አላሉም፤ ከፍ ያለ የሰብዓዊ ድጋፍና ገንዘብ እንዲገባለት አድርገዋል። ቡድኑም ይሄን ገንዘብና ሰብዓዊ ድጋፍ ለህዝቡ ሳይሆን ለቡድኑ አቅም ማጠናከሪያና የጦር መሳሪያ መግዣ አውሎታል። አጋሮቹም ለምን ብለው ሳይጠይቁ የቀደመውን ረሃብን የጦር መሳሪያ ትርክት እንደ ገደል ማሚቶ ማስተጋባቱን፤ ድጋፉን በአናት በአናቱ በህዝቡ ስም ማቀበሉን በመቀጠል ተጋግዘው ለስልጣን አብቅተውታል።
ይህ የቀደመ ታሪክና ተግባራቸው በተለይ አሸባሪው ትህነግ ከማዕከላዊው መንግስት ተገፍቶ ወደ ትግራይ ክልል ገብቶ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት በአገር ላይ ያለውን ጥልቅ ክህደት ካረጋገጠበት እለት ጀምሮ፤ የረሃብ ፖለቲካውን በትኩረት እየሰሩበት ይገኛል። በዚህ ረገድ መንግስት ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ የሚያደርገውን ጥረት ለማስተጓጎል ቢሳናቸው እንኳ፤ ወደ ክልሉ የገባው ድጋፍ ለህዝቡ እንዳይደርስ እና ሽብር ቡድኑ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዲውል በማድረጉ ሂደት ተናብበው እየሰሩ ይገኛሉ።
በዚህም የትግራይ ሕዝብ የሚላክለት ሰብዓዊ ድጋፍ ሳይደርሰው በረሃብ እንዲቀጣና ለከፋ ስቃይ እንዲዳረግ የፈረዱበት ሲሆን፤ በአንጻሩ መንግስት የትግራይ ህዝብ እንዲራብ በማድረግ “ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው” የሚል የጅራፉን አይነት ጩኸት ሲያስተጋቡ ይደመጣሉ።
ለአብነት፣ መንግስት በተለያየ ጊዜና መንገድ ወደክልሉ የሚያስገባቸውን ሰብዓዊ ድጋፎች በነዳጅ እጥረት ምክንያት ለህዝቡ ማድረስ አልቻልንምና ነዳጅ ይግባልን በሚል ሰበብ በመጋዘን አከማችተው ሕዝቡን ሲያሰቃዩ ታይቷል። መንግስትም ቀደም ሲል በክልሉ በመጠባበቂያነት ካስቀመጠው ነዳጅ በተጨማሪ ነዳጅ እንዲደርስ እየሰራ ባለበት ወቅት፤ ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው አሸባሪው ትህነግ ለጦር ጉዞው ማሳለጫ እንዲሆን ከተከማቸው ነዳጅ ከ570ሺ ሊትር በላይ አንስቶ ሲወስድ የተከዱ የመሰላቸው ተባባሪዎች ትህነግ ነዳጅ ዘረፈ ሲሉ ባወጡት መግለጫ ቀድሞውንም ሰብዓዊ ድጋፉ ያልደረሰው በነዳጅ እጥረት ሳይሆን በአሸባሪው ትህነግና ተባባሪዎቹ የሴራ ትስስር ምክንያት የትግራይን ሕዝብና የፌዴራሉን መንግስት ለማቃቃር ባላቸው ጽኑ መሻት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር አደረጉት።
ይሄ መንገዳቸው የከሸፈባቸው አሸባሪው ትህነግ እና ተባባሪዎቹ ታዲያ ከሰሞኑ ሌላ አጀንዳ በተጠባባቂነት ካስቀመጡበት ይዘው የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን “ጥናት ሪፖርት” በሚል ብቅ ብለዋል። “ሪፖርቱ” እንደ ቀደሙቱ ሁሉ የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኖ እንዲያገለግል የተዘጋጀ ነው። ይሄን የኮሚሽኑ “ሪፖርት” የኮሚሽኑን ወገንተኝነት እና የተሰጠውን ፖለቲካዊ ተልዕኮ ለማሳካት በሚያስችለው መልኩ ስለመዘጋጀቱ ከሚያረጋግጡ ነጥቦች መካከል፤ የመጀመሪያው፣ “ሪፖርቱን” ያዘጋጀው ኮሚቴ የተቋቋመው ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸውን አገራት እና ተቋማት ጥቅም ለማስጠበቅ መሆኑ ሲሆን፤ ይሄም ሉዓላዊት በሆነች አገር እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀን የሽብር ቡድን “የትግራይ ኃይሎች” “የትግራይ ሰራዊት” በሚል የክብር ስም መጥራቱ ነው።
ሁለተኛው ነጥብ፣ ኮሚቴው ይህን “ሪፖርት” ሲያዘጋጅ ጥናቱ ከሚከናወንባት አገር ኢትዮጵያ ውጭ ሆኖ አከናወንኩ ማለቱ ነው። ይህ ደግሞ ሽብርተኛ ቡድኖች በሚፈነጩባቸው አገራት ሳይቀር በቦታው እየተሄደ የሚሰራን ጥናት በኢትዮጵያ ሲሆን በርቀት እንዲከናወን ማድረጉ፣ ያውም ሊጠቀስ የሚችል የመረጃ ምንጭ ሳይዝ መፈጸሙ፤ በድምዳሜውም የአሸባሪውን ትህነግ ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ ጥቃቶች በወታደራዊ ስነ-ምግባሩ፣ በግዳጅ አፈጻጸም ብቃቱ፣ በህዝባዊነቱ እና በተላበሰው የወገናዊነት ባህሪው ተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ ምስጋና እና እውቅና ሲቸረው ለቆየው ለኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መስጠቱ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚጠቀሰው ሶስተኛው ነጥብ፤ የሽብር ቡድኑን ሀሰተኛ መረጃዎች ስታስተጋባ የቆየችው የባለሙያዎች ምርመራ ቡድን አባሏ ካሪ ሙሩንጊን በኮሚሽነርነት መመደቧ ሲሆን፤ ሴትየዋ ቀደም ባሉት ጊዜያት በሽብር ቡድኑ ሲሰራጩ የነበሩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት አጋርነቷን ስትገለጽ መቆየቷን ከግል የቲውተር አካውነቶቿ የተገኙት መረጃዎች መጠቆማቸው ነው። ከዚህም በላይ ቀደም ሲል በተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ የተጠናውን የጥናት ውጤት እና ምክረ- ሃሳብ ለመጠቀም ፈቃደኛ አለመሆኑ የተልዕኮ ተሸካሚነቱን የሚያረጋግጥ ነው።
በተመሳሳይ መንግስት በጋራ ኮሚሽኖቹ የጥናት ምክረ- ሃሳብ ላይ ተመስርቶ ያቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል የምርመራ እና የክስ ኮሚቴ በአማራና በአፋር ክልሎች ያከናወነውን ጥናት እና ያገኘውን ውጤት እንዲሁም ያስቀመጠውን ምክረ-ሃሳብ በግብዓትነት ለመጠቀም ፈቃደኛ ስላለመሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ። በአንጻሩ፣ በትግራይ ክልል ተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያረጋግጡለት በመረጃ ምንጭነት የተጠቀማቸው ሰዎችም የሽብር ቡድኑ አባላት፣ ታጣቂዎች፣ ፖለቲካዊ አመራሮች፣ ችግሩ ከመፈጠሩ አስቀድሞ ጭምር የፌዴራል መንግስትን ሉዓላዊ አገራዊ ስልጣንና ኃላፊነት በማጣጣልና በማዛባት ጭምር ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ እና ከለላ ሲሰጡ የነበሩ ካድሬ የህክምና ባለሙያዎች፣ በክልል በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች እና ስመ መምህራን ናቸው።
ለምርመራውም ትክክለኛ የመረጃ ምንጮችን ሳይጠቅስ ከታማኝ ምንጮቼ ባሰባሰብኩት አስተማማኝ መረጃ በሚል የተለመደ የማወናበጃ ስልት መጠቀሙ የኮሚሽኑን ገለልተኝነትና ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ “ሪፖርት” ስለመሆኑ ያመላከቱ ሃቆች ናቸው።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን መስከረም 12 ቀን 2015 ዓ.ም