ያለፉትን ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹን) በአሰልጣኝነት ሲመሩ የቆዩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፤ ከቡድኑ ጋር እንዲቆዩ የሚያደርጋቸውን ተጨማሪ ኮንትራት ከቀናት በፊት መፈረማቸው ይታወቃል። ይህንን በሚመለከትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም አሰልጣኙ ከትናንት በስቲያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአሰልጣኙን ኮንትራት መራዘም በሚመለከት በተሰጠው ማብራሪያ፣ አዲሱ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮችን በቅድሚያ በማስቀመጥ ለሶስት ጊዜ መወያየቱን የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ገልጸዋል። እነዚህም የሌሎች አገራት ተሞክሮ፣ የአሰልጣኙ ስኬት እንዲሁም የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞችን በሚመለከት ያለው የገበያ ሁኔታ ላይ ውይይት መደረጉ ተጠቁሟል። እነዚህን ሃሳቦች መነሻ በማድረግ ኮሚቴው ባደረገው ውይይት እንዲሁም አሰልጣኙን በማነጋገርም ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል።
በዚህም መሰረት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከመስከረም 15/2015 ዓ.ም እስከ መስከረም 14/2017 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ዓመታት በወር የተጣራ 250ሺ ብር ደመወዝ እየተከፈላቸው ብሄራዊ ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ውሳኔ ላይ ተደርሷል። ለአሰልጣኙ ከደመወዝ ባሻገር ሌሎች ጥቅማጥቅሞች የተከበሩላቸው ሲሆን፤ ለአብነት ያህል ብሄራዊ ቡድኑ ጉዞ በሚኖረው ወቅት አሰልጣኙ በቢዝነስ ክላስ እንዲጓዙ፣ ስልጠናዎች ሲኖሯቸውም ፌዴሬሽኑ ወጪያቸውን ለመክፈል ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ጸሃፊው በሰጡት ማብራሪያ በአፍሪካ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ከፍተኛ እና ዝቅተኛውን ክፍያ የሚያገኙ አገራት እንዲሁም በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች የገበያ ሁኔታ በማነጻጸሪያነት በማስቀመጥ የአሰልጣኙ ደመወዝ ምክንያታዊ መሆኑ እንደታመነበት ተናግረዋል። በተጨማሪም ከሌሎች አገራት አንጻር የአሰልጣኙ የፊርማ ክፍያ ዝቅተኛ የሚባል መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን ከፍተኛ ሊባል እንደሚችል አስረድተዋል።
አሰልጣኙ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በሚቆዩበት ጊዜያትም እአአ ለ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ዋልያዎቹን እንዲሳተፉ የማድረግ እንዲሁም በቅርቡ ለሚካሄደው የቻን ውድድር ያለፈውን ቡድን ከዚህ ቀደም በመድረኩ ከተገኘው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዝገብ የማድረግ ግዴታዎች እንዳሉባቸው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ለአሰልጣኙ እንደ ግዴታ የተቀመጡት ጉዳዮች ካልተሳኩ አሰልጣኙ በቀጥታ ይሰናበታሉ ማለት ሳይሆን በሁኔታዎች ላይ በመመስረት በቀጣይ የሚሆነው ነገር እንደሚወሰን በመግለጫው ተመላክቷል። ከዋናው አሰልጣኝ ባሻገር ሌሎች የስልጠና ቡድኑ አባላትን በሚመለከትም ሁሉም ባሉበት የቀጠሉ ሲሆን፤ በቀጣይም ደረጃውን ለማሻሻል የሚሠራ ይሆናል። ባለሙያዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃት ያላቸው ሲሆኑ፤ የሌሎች አገራት ብሄራዊ ቡድኖችን እስከማማከር የደረሱ በመሆናቸው በቀጣይ ደረጃቸውን እንዲያሳድጉ ይደረጋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በበኩላቸው የታደሰውን ኮንትራት ተከትሎ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከሁለት ዓመታት በፊት ኮንትራት በፈረሙበት ወቅት ችግሮች ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠብቀው እንደነበርና በማስታወስ ያንን ስጋት እንዳለፉትም ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ በተለያዩ ክለቦች ጥያቄዎች ቢቀርቡላቸውም የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ከሚያገኙት ልምድ እና ጥቅም አንጻር ኮንትራቱን መፈረማቸውንም ገልጸዋል። ከምክትል አሰልጣኞቻቸው ጋርም በመቀጠላቸው ደስተኛ እንደሆኑ የገለፁ ሲሆኑ፤ ተጫዋቾችም ሆኑ የአሰልጣኞች ቡድኑ አባላት እንደ ብሄራዊ ቡድን ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ ወደ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በመጡበት ወቅት በርካታ ችግሮች እንደነበሩ የሚታወቅ ሲሆን፤ ተጫዋቾች በራሳቸው እንዲተማመኑ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ስራ እንደሰሩ አስረድተዋል። በቀጣይ ደግሞ ደረጃው ከፍ ያለ ቡድን ለመገንባት የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል። አያይዘውም ‹‹የተቀመጠውን ግዴታ የማስፈጸም ኃላፊነት አለብኝ፣ ነገር ይህን ካላደረክ እርምጃ ይወሰዳል የሚል የተቀመጠ ነገር የለም›› ብለዋል።
የብሔራዊ ቡድኑን ቀጣይ የወዳጅነት ጨዋታዎች በተመለከተ አሰልጣኝ ውበቱ በሰጡት ማብራሪያም ‹‹ከሊቢያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለመጫወት በቃል ደረጃ ብንስማማም ሳይሳካ ቀርቷል፣ ነገር ግን ከሱዳንና ጋር በመጪው ዓርብና ሰኞ በምናደርገው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ እንድትመለከቱን እጋብዛለሁ›› በማለት ተናግረዋል። አሰልጣኝ ውበቱ ለመገናኛ ብዙሃንም ‹‹ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያለእናንተ አልተጓዝንም፣ በቀጣዮቹ ዓመታትም ያለእናንተ አይሆንምና ለብሄራዊ ቡድኑ ገንቢ ሀይል እንድትሆኑን እጠይቃለሁ፣ አበረታቱን ክፍተት ካለ እየነገራችሁን እንደአገር ስራው የጋራ በመሆኑ አብረን እንስራ፣ ለእስከዛሬው ድጋፋችሁ አመሰግናለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2015 ዓ.ም