‹‹መሃይም!›› የሚለው ስድብ በጣም ይከብዳል አይደል? ነውርም ነው! ግን አንዳንድ ስድቡ የሚመጥናቸው ሰዎች አሉ። በምኖርበት አካባቢ ካስተዋልኩት በጣም ቀላል ከሆነ ትዝብት ልነሳ።
በየበሩ ላይ ‹‹ቆሻሻ መጣል የሚቻለው ረቡዕ እና እሁድ ብቻ ነው›› ተብሎ ተለጥፏል። በአዲስ አበባ ደረጃ ቢያንስ መጻፍና ማንበብ የማይችል ማህበረሰብ አለ ተብሎ አይታሰብም፤ ምናልባት ሊኖር እንኳን ቢችል ቢያንስ ከአንድ ግቢ ውስጥ አንድ ወይ ሁለት ሰው ብቻ ነው።
ረቡዕና እሁድ ቆሻሻ የሚያነሱ ሰዎች ከሚጣልበት ቦታ እየመጡ ያነሳሉ። በእነዚህ ቀናት ግቢ ውስጥ በፌስታል ወይም በየትኛውም ማጠራቀሚያ ነገር የተጠራቀመውን ቆሻሻ አውጥተው ይሰጧቸዋል። በእነዚህ ቀናት በጡሩንባ ነው ‹‹ቆሻሻ አውጡ!›› እየተባለ የሚነገር።
ሰራተኞቹ ቆሻሻውን ሲያነሱ ቆይተው ይሄዳሉ። ልክ ከሄዱ በኋላ ማታ ከየቤታቸው ቆሻሻ አውጥተው የሚጥሉ አሉ። ከረቡዕና እሁድ ይልቅ በሌላው ቀን የሚጣለው ቆሻሻ ይበዛል። በዚያ ላይ የማስቀመጫ ቦታው ላይ ሳይሆን በየሜዳው ይበትኑታል። ከግቢ ታስሮ የወጣውን ቆሻሻ ከርቀት ይወረውሩትና ተፈቶ ወይም ፌስታሉ ፈንድቶ በሜዳው ሙሉ ይበተናል።
ታዲያ ይሄ መሃይምነት አይደለም?
በአንዳንድ ትልልቅ መስሪያ ቤቶች ሳይቀር የምታዘበውን ልጨምር። በዚህ ዘመን በትልልቅ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ከዲግሪ በታች የትምህርት ደረጃ ያለው ብዙም የለም፤ ዲግሪው ቢቀር ቢያንስ መጻፍና ማንበብ የማይችል አይኖርም። አገር ለመለወጥ በተማረ ኃይል የተቋቋመ እንዲህ አይነት መስሪያ ቤት መጸዳጃ ውስጥ የሚታይ ነገር ያሳፍራል። ውሃ ሳይኖር የሚታየውን ነገር አላልኩም! ቢያንስ ውሃ እያለ እንኳን በሥርዓት መጠቀምና የጋራ ንጽህናን መጠበቅ ስላልቻሉት ነው።
ውሃ ከፍቶ ትቶ የሚሄድ አለ፣ ውሃ እያለ መጸዳጃ ቤቱ ላይ ሳይደፋ የሚሄድ አለ፣ በግፊት የሚሰሩ የሲንክ መጻዳጃ ቤቶች ላይ ውሃውን ሳይገፋ ትቶ የሚሄድ አለ። እነዚህን በጣም ቀላልና ተራ ነገሮች ናቸው፤ ዳሩ ግን የሚፈጥሩት መጥፎ ሽታ ደግሞ አደገኛ በሽታ ያመጣል።
ታዲያ ይሄ መሃይምነት አይደለም? ምንም ወጪ በማያስወጣ እና ጉልበት በማያደክም ነገር ሰው እንዴት በሽታ ይጋብዛል? እንዴት ራሱን ይረብሻል?
የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ ጥፋቶች የሚጠፉት ‹‹የተማረ›› በሚባለው ወገን መሆኑ ነው። የቀለም ትምህርት ያልቆጠሩት እንዲያውም ይፈራሉ። በየመስሪያ ቤቶችም ሆነ በጋራ መኖሪያ አካባቢዎች ጥፋት የሚበዛው ጭራሽ የተማረ በሚባለው ወገን ነው።
ይህን ሁሉ እንዲያስታውስ ያደረገኝ የባለፈው ሳምንት የበዓል ሰሞን ነው። በዓል ጥሩ ነገሮች የሚደረጉበትና ጽዳት የሚታይበት ነው። በተለይ አዲስ ዓመት ሲሆን ደግሞ ተፈጥሮ ራሱ አዲስ ነው። ሰማይ ምድሩ ንፁህ ሆኖ ነው የሚታይ።
ዳሩ ግን ምን ዋጋ አለው አንዳንዶቻችን ከመሃይምነት አልተላቀቅንም! ከፍተኛ የሆነ ግደለሽነትና ንዝህላልነት አለብን።
የእንቁጣጣሽ ዕለት ምሽት 11፡00 አካባቢ የእግር ጉዞ ለማድረግ ወጣሁ። በእንዲህ አይነት የበዓል ቀን የከተማውን ድባብ ማየት ያስደስተኛል። ዳሩ ግን ምን ዋጋ አለው ደስታዬን የሚረብሹ ነገሮች በዙ። ከበዓል ድባብነቱ ይልቅ ስለማስተውላቸው መጥፎ ነገሮችና ስለማህበረሰባችን የግንዛቤ ደረጃ ማሰላሰል ጀመርኩ።
ቀኑ የዕርድ ቀን ስለነበር እዚህም እዚያም የሚታየው የእንስሳት ተረፈ ምርት ነው። ቆዳ፣ ደም፣ የእንስሳት የውስጥ ዕቃ (ፈርስ፣ አንጀት…)፣ አጥንት… የመሳሰሉት በየመስመሩ ዳር ተጥለዋል። እነዚህን ተረፈ ምርቶች ደግሞ የጎዳና ውሾች ከዚያ ወደዚህ ያገላብጧቸዋል።
ለዓይን ምቾት ካለመስጠታቸው በሻገር መጥፎ ሽታ ይፈጥራሉ። በተለይም ውሎ ሲያድር ከፍተኛ የሆነ መጥፎ ሽታ ነው የሚፈጥር። በዓልን በደስታና በፌሽታ ለማሳለፍ ተብሎ የተደረገ ነገር በሽታ ማምጫ ሆነ ማለት ነው።
ታዲያ ይሄ መሃይምነት አይደለም?
ቢቻል ቢቻል እነዚህን ቆሻሻዎች ወደ ሀብት መቀየር ነበረብን፣ እሱ ቢያቅተን ግን እንዴት የበሽታ ምንጭ እናደርጋቸዋለን? በዚህ ዘመን እንዴት ቆዳ መንገድ ላይ ይጣላል? ለመሆኑ የቆዳን ዋጋ ልብ ብለነው ይሆን?
የምንለብሰውን ጃኬት፣ የምናደርገውን ጫማ፣ ዘመናዊ ቦርሳዎች ከቆዳ እንደሚዘጋጁ ማንም ያውቃል፤ ዳሩ ግን እኛ ጋ በየሜዳው ይጣላል። በየሜዳው ከጣልነው ቆዳ የተዘጋጀውን ምርት ብዙ ሺዎች አውጥተን እንገዛዋለን። ይባስ ብሎ ግን ለጤና ጠንቅ በመሆን መንገድ መጣላችን ደግሞ ከድህነትም በላይ ለበሽታ እየዳረገን ነው። በነገራችን ላይ በአንድ ዘመን የቆዳ ዋጋ ከከብትና ፍየል ዋጋ በላይ ሆኖ እንደነበር ቤተሰብ ውስጥ ሲወራ ሰምቻለሁ። በዚህም ምክንያት ለቆዳው ሲባል ፍየል ወይም በግ ይታረድ ነበር።
የመጥፎ ሽታ ነገር በከተሞቻችን ውስጥ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። በተለይም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፣ የዓለም እንግዶች ማረፊያ፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችው መዲናችን አዲስ አበባ ደግሞ ይህ ነገር ሊታይባት አይገባም ነበር።
ተቋማዊ በሆነ መንገድ ከመንግሥት ብዙ ቢጠበቅም ለውጥ የሚመጣው ግን እንደ ማህበረሰብ ስንለወጥ ነው። በሁለት ወይም ሦስትና አራት ወር ውስጥ የሚደረግ የጽዳት ዘመቻ ችግሩን አይቀርፈውም፤ ችግሩን የሚቀርፈው ከግለሰብ ጀምሮ ለውጥ ሲመጣ ነው፤ የተማረ የሚባለው የህብረተሰብ ክፍል አርዓያ መሆን ሲችል ነው።
መስከረም በተፈጥሮ የንፅህና መለያ ነው። ሁሉ ነገር እንደ አዲስ የሚጀመርበት ነው። ልብስ እና የመገልገያ ዕቃዎች ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ መንፈስ ራሱ አዲስ የሚሆንበት ነው። በተፈጥሮ ጋራው ሸንተረሩ አዲስ የሚሆንበት ነው። ዳሩ ግን ይህን ሁሉ ፀጋ በሰው ሰራሽ ችግር እያበላሸነው ነው፤ እያቆሸሽነው ነው። በሽታዎቻችን ሰው ሰራሽ በሽታዎች ናቸው። በንጽህና ጉድለት የሚመጡ ናቸው።
ጉንፋን ብዙ ሰው ይያዛል፣ ብዙ ሰው ሳይነስ አለበት። እነዚህ ሁሉ የሚመጡት በመጥፎ ሽታ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ በወንዝ ወይም በመንገድ ዳርቻ የእግር ጉዞ ማድረግ የማይቻል እየሆነ ነው፤ አዙሮ የሚደፋ መጥፎ ሽታ ነው ያለው።
በመንግሥት የተጀመረው ‹‹ሸገርን ማስዋብ›› ፕሮጀክት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ከመንግሥት በላይ ዕድሉ ያለው ሕብረተሰቡ ውስጥ ነው። ለውጥ የሚመጣው በአንድ ወይም ሁለት ፕሮጀክት ሳይሆን በአስተሳሰብ ለውጥ ነው። ይሄ ለማንም ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን የእያንዳንዳችን ግዴታ መሆን አለበት። አለበለዚያ ‹‹ኩሩ ሕዝቦች ነን፣ የሥልጣኔ አስጀማሪዎች ነን፣ የአባቶቻችን ልጆችን ነን….›› እያሉ መፎከር አገር በክብር ያቆዩ ቅድመ አያቶቻችንን ማሳነስ ነው፤ በእነርሱ ለመኩራት እንኳን የማንበቃ እየሆንን ነው።
ሰው እንዴት ትንሿን ነገር የግልና የአካባቢዎን ንፅህና መጠበቅ ያቅተዋል? ለምርምር ይሆናል ተብሎ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማርን ሰዎች እንደ 1ኛ ክፍል ‹‹የግልና የአካባቢ ንፅህና›› የሚል ትምህርት ይሰጠን?
ኧረ እንፈር!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2015 ዓ.ም