በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ከ1950ዎቹ መባቻ ጀምሮ የነበሩ ጋዜጦች ተመልክተናል። ብዙዎቹ ጋዜጦች በወቅቱ ይዘው የወጡት ዜና ትንግርት ነክ ክስተቶች ነበሩ። እነዚህ ዜናዎች በጋዜጣው ሲዘገቡ ግን በአንድ አንቀጽ ብቻ የተገደቡ ነበሩ። እነዚህን ዘገባዎች ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከታቸው የአንባቢን ጥያቄ ወይም የዜናን መሥፈርት ላያሟሉ ይችላሉ። በዚያን ወቅት የጋዜጠኝነት ሙያ በአገራችን ገና ካለመዳበሩ ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል ዘገባዎቹ ሲነበቡ ከዚያስ፤ እና ምን ይጠበስ ? ሊያስብሉ የሚችሉ ናቸው። ያንን ዘመን ዛሬ ላይ ሆነን እንድናይ የሚያስችሉን አንድ የታሪክ አካል በመሆናቸው ግን ትንሽ ዘና ሊያደርጉን ይችላሉ ብለን በማሰብ እንደሚከተለው መርጠን ለትውስታ አቅርበናቸዋል።
ጎንደር በመብረቅ አደጋ የሞተ ወንጀለኛ
ጫቅሉ መስፍን የተባለው ወንጀለኛ በጎንደር አውራጃ አርማጭሆ ወረዳ ግዛት ውስጥ ጃግሬ ሚካኤል ቀበሌ አቶ ገበየሁ ካሣ የተባለውን ሰላማዊ ሰው መጋቢት በ ፲፩ ቀን ፵፱ ዓ.ም ከሌሊቱ ባልታወቀ ሰዓት ከመኖሪያ ቤቱ ውስጥ እንደተኛ በግፍ በአንድ ጥይት ገድሎት አምልጦ ፖሊስ በጥብቅ በመከታተል ሐምሌ ፳፭ ቀን ላይ ሣለ ፵፱ ዓ.ም ከቀኑ ፲ ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በዚሁ ወረዳ ግዛት ከች ባጄና በተባለ ምክትል ወረዳ ግዛት ውስጥ ከተደበቀበት ቦታ የመብረቅ አደጋ የገደለው መሆኑን ከጠቅላይ ግዛት ፖሊስ ጽ/ ቤት ዋና ጸሐፊ ከመቶ አለቃ ግርማ እንዳልካቸው በደረሰን ወሬ ተገልጿል።
የቤጌምድርና ስሜን አዛዥ አዣንስ
(ጳጉሜ ፪ ቀን ፵፱ ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ጅብን ከሰውና ውሻ ማላመድ
ኗሪነታቸው በወሎ ጠቅላይ ግዛት በደሴ ከተማ የሆነ አቶ በየነ ገብሩ የሚባሉ የጦር ሠራዊት ባልደረባ አንድ የጅብ ግልገል ከዱር አግኝተው ይዘው እቤት ካሏቸው ውሾች ጋር በማላመድ በዕረፍት ጊዜያቸው ውሻውንና ጅቡን ባንድ ጋሪ አሳፍረው ሲንሸራሸሩ ለሕዝብ ሲያሳዩ ይታያል። ይህ ጅብ ስንት ጊዜ ከሳቸው ጋር እንደቆየ ብጠይቃቸው ጥቅምት ፲፬ ቀን ፩ሺህ፱፻፶ ዓ.ም ሲደርስ አንድ ዓመቱ መሆኑንና በዚህም ጊዜ ውስጥ በግልገልነቱ የከብት ወተት በጡጦ እየጠባ ከአደገ በኋላ ግን እንጀራ መመገቡን ገልጸውልናል። ከዚህም በላይ እርስዎ አንድ ወታደር ነዎት፤ ይህ ጅብ እንደ አንድ ቤተሰብ የምግብ ወጪ ይጠይቅዎታል፤ ደግሞስ ምን ሊሰጥዎት ነው እንዲህ የሚደክሙት ? ብዬ ብጠይቃቸው እንደሚከተለው መልስ ሰጥተውኛል።
ሰው በተስፋ ይኖራል፤ እኔም በወታደርነቴ መጠን ከማገኘው ደሞዝ ቀንሼ ይህን ጅብ በማሳደግ ከሰውና ከውሻ አላመድኩት፤ አሁን እርስዎ በእጅዎ ዳሠው እንዳዩት ሁሉ በሌላውም ዓለም ክፍል ብዙ ዓይነት የዱር አውሬዎች እንደዚሁ ለማዳ በመሆን ብዙዎች ለሥራ አገልግሎት ጥቅም ሲውሉ፤ ብዙዎቹ ደግሞ በአንድ ሥፍራ ተከማችተውና በደንብ ተይዘው ሰው ሠራሽ ቲያትርና ሲኒማ እንደሚታየው ሁሉ በእግዚአብሔር የተፈጠሩትን አውሬዎችና እንስሳዎች አብልጠው በማፍቀር አገር ጐብኚዎችም ሆኑ ተወላጆች እንደ ትንግርት ማየታቸውን ስለምሰማ፤ እንደዚህ ያለውን ለአገር ጥቅም መንግሥት ሳይከታተለው አይቀርምና በበላይ አለቆቼ አማካይነት አቅርቤ አንድ ሽልማት የማገኝ ስለመሰለኝ በተስፋ አሳድጋለሁ ሲሉ መልስ ከሰጡኝ በኋላ፤ እኔም በኚሁ አረጋዊ ሰው ሐሳብና ንግግር በመገረም አይቼና ሰምቼ ዝም ከማለት ያላዩ እንዲያዩ፣ ያልሰሙ እንዲሰሙ ስለሚያስፈልግ በዚሁ ዓምድ ለአንባቢዎች እገልጻለሁ።
በየነ ዘመንፈስ
(መስከረም 16 ቀን 1950 ታትሞ ከወጣው
አዲስ ዘመን)
የነፋስ ኃይልና ማዕበል
በፍቼ አካባቢ ደገም ምክትል ወረዳ ግዛት ውስጥ ሐምሌ ፲፱ ቀን ፩ ሺ፱፻፵፱ዓ.ም ከምሽቱ ፩ ሰዓት ላይ ነፋስ ተነስቶ የሰላሣ ቤቶችን ክዳን ገፎ ሣሩን ወዴት እንዳደረሰው አልታወቀም። ትልልቅ ዛፎችም ጥሏል። በሰው ላይ አደጋ አላደረሰም።
በዚሁ ሌሊት ውስጥ፤ በዚሁ ቦታ በቀኝ አዝማች ገለልቻ መልከኝነት ከባድ በረዶ ጥሎ እህልና አትክልት በጣም አጥፍቷል ሲሉ የወረዳው ገዥ ግራዝማች በቀለ አሸብር ነሐሴ ፲፭ ቀን ፩ ሺ፱፻፵፱ ዓ.ም በቁጥር ፩ሺህ ፱፻፶ በተጻፈ ደብዳቤ አረጋግጠውልናል።
(መስከረም ፳፭ ቀን ፶ ዓ.ም ከታተመው
አዲስ ዘመን)
አንድ ጊደር መንታ ወለደች
በደገም ምክትል ወረዳ ልዩ ስሙ ቦስታ በሚባለው ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አቶ አፈወርቅ ቸኮለ ነሐሴ ፲፯ ቀን ፵፱ ዓ.ም አንድ ጊደር ሁለት ጥጆች ወልዳ የተወለዱትም በሕይወት አሉ። ከብቷም ደህና ነች ሲሉ እመሥሪያ ቤታችን ድረስ መጥተው ገልጸውልናል ።
(መስከረም ፳፭ ቀን ፶ ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ባለ አራት እግር የዶሮ ጫጩት
በሐረር ከተማ ውስጥ ሸንኮር በሚባለው ሠፈር በማመድ ዩሱፍ ቤት አራት እግር ያላት የዶሮ ጫጩት ተፈልፍላ ኖሮ በመስከረም ፳፱ ቀን በ፶ ዓ.ም በክፍሉ ሠፈር ሹም አማካይነት በሙሳ ገበሬ እጅ ለሐረር ከተማ ሹምና አውራጃው ገዥ ድረስ መጥተው ከተመለከቷት በኋላ ለጊዜው ጫጩቷ ማዘጋጃ ቤት የቆየች መሆኗን ከሐረር ጠቅላይ ግዛት ማዘጋጃ ቤት የደረሰው ወሬ አረጋግጧል።
የሐረር ጠቅላይ ግዛት አዣንስ
(ጥቅምት ፱ ቀን ፩ ሺህ ፱፻፶ ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ልጆች ለተጧሪዎች ልብስ ገዙ
አዲስ አበባ (አ-ዜ-አ-) በመካከለኛ ወረዳ ግዛት አካባቢ የሚገኙት ተማሪዎች በሠፈሩ ለሚኖሩት ተጠዋሪ ሽማግሌዎች ልብስ ገዝተው ጥቅምት ፫ ቀን ፲፱፷፩ ዓ.ም አለበሱ።
ተማሪዎቹ ለልብስ መግዣ ገንዘብ የሰበሰቡት በዕረፍት ጊዜያቸው በገዛ ኃጢያቴ ሲኦል ሆነ ቤቴ በሚል አርዕስት ያዘጋጁትን ቲያትር ለወላጆች በማሳየት ባገኙት ገቢ ነው። ከዚሁ ቲያትር ተማሪዎቹ ያገኙት ገቢ ፹፰ ብር ከ፸፭ ሳንቲም ሲሆን፤ ለአራት ችግረኖኞች ሽማግሌዎች የቀንና የሌሊት ልብስ ገዝተው አልብሰዋል።
ተማሪዎቹ ቲያትሩን ባሳዩበት ጊዜ በወረዳ ግዛቱ የተቋቋመው የዕድር ማኅበር ድንኳን በመስጠት የረዳቸው መሆኑ ተገልጧል። ከዚሁ በቀር ተማሪዎቹ ወላጆች ላደረጉላቸው ድጋፍና ርዳታ ምስጋና አቅርበዋል።
(ጥቅምት 7 ቀን 1961 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2015 ዓ.ም