ቡና ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ከመሆኑም በላይ ለዘመናት የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ቆይቷል። ሆኖም ከማሳ እስከ ገበያ ድረስ ባለው ኋላቀር አሰራር ምክንያት አገሪቱ በዚህ የተፈጥሮ ፀጋዋ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ ሳትሆን ቀርታለች። ይህንን ችግር ለመፍታትና በዘርፉ የላቀ ተጠቃሚ ለመሆን ውስን ጥረቶች ቢደረጉም ይሄነው የሚባል ውጤት ማምጣት ያለመቻሉ የብዙዎች የዘመናት ቁጭት እንደሆነ እሙን ነው።
ከሰሞኑ ግን ልብን የሚያሞቅ ዜና ተሰምቷል። ይኸውም አገሪቱ የቡናን ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ፍፁም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 300 ሺ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷ ነው። በብዛትም ሆነ በጥራት ረገድ የተሻለ ምርት ይዞ በመቅረብ የማይደፈረውን የዓለም የቡና ገበያ ሰብሮ ለመግባት እንደተቻለ ከቡና ሻይ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ አርሶ አደር ‹‹በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ›› ዓለም አቀፍ ውድድር አንድ ኪሎ ልዩ ጣዕም ያለው ቡና በማቅረብ 884ሺ ዶላር ብር ማስገኘት መቻሉ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል።
ከዚህ በመነሳትም በተያዘው በጀት ዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘትና 45 በመቶ ብላጫ ያለው አፈፃፀም ለማስመዝገብ በመንግስት ታቅዷል። ይህንን እቅድ በምን መልኩ ማሳካት ይችላል? ካለፉት ዓመታት የተሻገሩ የተንዛዙ አሰራሮችንና ችግሮች በምን መንገድ መቅረፍ ይገባቸዋል? ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረናል።
የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ እንደሚሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዘርፍ የተገኘው ገቢ በበጀት ዓመቱ ይገኛል ተብሎ በዕቅድ ከተያዘውም ሆነ ከቀዳሚው ዓመት ጭምሬ ያሳየ ነው። ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በቡና የወጪ ንግድ ታሪክ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ብላጫ የተገኘበት ነው።
ይህ ውጤት ከመገኘቱ በፊት ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የቡና ወጪ ንግድ የተወሰኑ መሻሻሎች ቢታዩበትም፤ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት ሳይቻል ቀርቷል። አሁን ግን ከቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ መሻገር መቻሉ ትልቅ እምርታ ነው። በተያዘው በጀትም ዓመት ከ45 በመቶ በላይ ብልጫ ያለው ገቢ ለአገር ማሳገባት እንደሚቻል እምነት አሳድሯል።
የአሁኑ የቡና ወጪ ንግድ ገቢ ማደግ ዘንድሮ የታየው የዓለም ቡና ዋጋ በመጨመሩ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይነሳል። ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ግን የዓለም የቡና ዋጋ መጨመር አገሪቱ ላስገኘችው የላቀ ገቢ እንደ አንድ ምክንያት ቢጠቀስም በጥቅል ሲታይ ግን የሪፎርም ሥራው ትልቅ ለውጥ በማምጣቱ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በበጀት ዓመቱ የዚህን ያህል የውጭ ምንዛሬ ቡና ሊያስገኝ ከቻለባቸው ምክንያቶች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ እያደገ መምጣትና የብራዚልና የኮሎምቢያ ቡና በውርጭ መመታት እንደሆነ የዘርፉ ተንታኞች ያስረዳሉ። ዶክተር አዱኛ በበኩላቸው፤ ከቡና ምርት ጋር በተያያዘ በተሰራው ሪፎርም ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የቡና ምርት እያደገ መምጣቱም አንድ ምክንያት እንደሆነ ነው ያስረዱት።
የሪፎርም ስራውም የተሻለ ገቢ እንዲገኝ ወሳኝ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው፤ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ ግብይት ይፈፀም እንደነበረና ካለፈው ዓመት ጀምሮ ግን የተለያዩ የገበያ አማራጮችን በመፍጠር ገቢውን የዚያኑ ያህል ማሳደግ መቻሉን ያብራራሉ። በዚህ ሪፎርም መሠረት አርሶ አደሩ በተወሰነ መልኩ ተጠቃሚ እያደረጉት ስለሆነ ምርቱ ቶሎ ቶሎ እያወጣ እንዲሸጥ አስችሏል ይላሉ።
ቀደም ሲል በኮንትሮባንድ የሚወጣው ቡና አሁን ላይ አርሶ አደሩም ሆነ ሌላውም ተዋንያን የተሻለ ገቢ ስላገኘበት ወደዚህ ሥርዓት እየገባ በመምጣቱ ውጤቱ ተገኝቷል። በጥቅሉ በአገር ውስጥ የተሠራው ሪፎርምም ሆነ የዓለም የቡና ዋጋ መጨመርና እንደ ብራዚል ያሉ ዋነኛ ቡና ላኪ አገሮች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በገበያቸው ላይ የገጠማቸው ክፍተት ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል የፈጠረ ሆኗል።
የንግድና ኢንቨስትመንት አማካሪ አቶ አማንይሁን ረዳም፤ ባለፈው በጀት ዓመት የተገኘው ገቢ እንደትልቅ ስኬት የሚታይ መሆኑን ያምናሉ። በተለይ ባለፉት ዓመታት ከነበረው አፈፃፀም አንፃር ሲታይ ጥሩና የሚበረታታ እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህ ውጤት የብዙ ነገር ድምር ውጤት እንደሆነ አመልክተው፤ አንደኛው ምክንያት የሚላከው የቡና መጠን መጨመሩ እንደሆነ ያነሳሉ። ይህም ደግሞ የአርሶ አደሮች የልፋት ውጤት መሆኑ የማይካድ ሃቅ እንደሆነ ነው የተናገሩት። ዘርፉን የሚመሩት የመንግስት፤ የግል ባለሃብቶች እንዲሁም የልማት አጋሮች ርብርብ ማድረጋቸውም ሌላው አብይ ምክንያት እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
‹‹ዘንድሮ ደግሞ መንግስት ያቀደው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማምጣት ነው። ይሄ ማለት የባለፈውን ዓመት አፈፃፀም ወደ 45በመቶ ያህል ማሳደግ ማለት ነው። በእኔ እምነት ይሄ ይቻላል። ባለፈው ዓመት ምርት መጠኑ የጨመረበት ገቢ ያደገበትም ሁኔታ ሲታይ ዘንድሮ የታሰበው ገቢ የሚሳካ ነው›› ይላል።
ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ለቡና ከፍተኛ የሚመች አየር ንብረት፤ ሰፊ መሬት ያላት መሆኑ እንዲሁም ከማሳ ጀምሮ እስከ ግብይት ያለውን አሰራር ማዘመን ከተቻለ የማይሳካበት ሁኔታ እንደሌለ ይገልፃሉ።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በርካታ ወጣቶችን ወደ ግብርናው እንዲገቡ በማድረግ ዘመናዊ እርሻ ዘዴን ማስተማር ያስፈልጋል። ወጣቶቹን በደንብ እያስተማሩና እያሰለጠኑ ከምርምር ጣቢያዎች ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይገባል። የተሻለ ዝርያ ወደ አርሶ አደሩ ማሳ የሚገባበት ሁኔታ፣ የብድርና የግብርና ግብዓት አቅርቦት፣ የቴክኒክ ድጋፍ በደንብ ከተመቻቸና የቡና ተክል የሚስፋፋ ከሆነ፤ በሚቀጥሉት ዓመታት የተሻለ ምርታማ የማይኮንበት ምክንያት አይኖርም። ምርታማነቱ ባደገ ቁጥርም ከቡና ዘርፍ የሚገኘውም ገቢ በዚያው ልክ እያደገ ይመጣል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ባለ ልዩ ጣዕም (ስፔሻሊቲ ቡና) በስፋት ማምረት እንደሚገባ አቶ አማንይሁን ይናገራሉ። ‹‹ባለልዩ ጣዕም ቡናውም ሆነ መደበኛ ጣዕም ያለው በአንድ ማሳ ውስጥ የሚበቅሉ ናቸው። ልዩነቱ አያያዝ ነው›› ይላሉ። ባለልዩ ጣዕም ዘርፍ ያለ ቡና አስተራረሙም ሆነ በፀሐይና በዝናብ ጊዜ አያያዙ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት እንደሆነ ያነሳሉ። ፍሬው ከተለቀመ በኋላ ያለውን አሰራር ሲያስረዱም ‹‹ፍሬው የሚደርቅበት፣ የሚታጠብበትና አጠቃላይ ሂደቱ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው›› በማለት ይናገራሉ።
በተቃራኒው ደግሞ ኮሜርሻል ግሬድ የሚባለውና በመደበኛ መንገድ የሚከናወን የምርት ሂደት ግን በተለየ መልኩ ብዙ የማያደክም ቢሆንም ከገቢ አንፃር ለአገር ያለው ጠቀሜታ አነስተኛ መሆኑን ነው የሚያብራሩት። ‹‹ከገቢ አንፃር ግን ስንመለከተው ባለልዩ ጣዕም ቡና የሚባለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል። ስለዚህ አርሶ አደሮቻችን ባላቸው ማሳ የቡና አያያዛቸውን ዘዴ እንዲያዘምኑ ብናሰተምራቸው፤ ዘመናዊ የግብርና እውቀት እንዲኖራቸው በደንብ ቢሠራና ክትትል ቢደረግላቸው ገቢያቸውም በዚያው ልክ ሶስትና አራት እጥፍ ሊያድግ የሚችልበት ሰፊ እድል አለ›› ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ አቶ አማንይሁን ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው ቡና በዋናነት ከመደበኛ ጣዕም ያለው ወደ ልዩ ጣዕም ያለው ቡና የሚሄድበት ሁኔታ ከተመቻቸ የቡና ምርት መጠን እንኳን ባይጨምር የቡና ጥራቱ ከተሻሻለ ገቢያችን ይጨምራል። ለዚህ ደግሞ ምርቱ ምሳ ላይ እያለ በደንብ መንከባከብ ይገባል። አንዱን ከሌላው ምርት ሳይቀላቀል ተለቅሞ ታጥቦና ተዘጋጅቶ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ታሽጎ ቡናው ጣዕሙን እንደጠበቀ ተደርጎ መላክ አለበት። እያንዳንዱን ሂደት ደግሞ በአግባቡ የሚከታተል አካል ሊኖር ይገባል።
‹‹በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም እሴት ጨምረን ቆልተን ፈጭተን ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አሽገን ፕሪምየም ዋጋ ለሚገኝባቸው የአውሮፓ፣ የአሜሪካ የቻይና የጃፓን ገበያ የምናቀርብ ከሆነ በአንድ በኩል ለአገራችን ኢንደስትራላይዜሽን መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። በሌላ በኩልም ለወጣቶቻችንም የስራ እድል ይፈጥራል›› ሲሉ ቡናው ደግሞ እሴት ተጨምሮበት በሚላክበት ሰዓት የተሻለ ዋጋ የሚያሰገኝ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ የዛሬ 35 ዓመት አንድ የቡና ተክል የሌላቸው አገሮች ዘሩን ከኢትዮጵያ፤ ከኮሎቢያና ከብራዚል ወስደው ዛሬ ከዓለም ሁለተኛ ቡና ላኪ የሆኑ አገሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል ቪትናም በዋናነት የምትጠቀስ ሲሆን አገሪቱ በዓመት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች፤ አሁን ከብራዚል ቀጥሎ ትልቋ የዓለም ቡና ላኪ አገር መሆን ችላለች። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንደኛ፤ ከዓለም ወደ አምስተኛ ደረጃ ላኪ አገር እንደመሆንዋ ጥራት ላይ ትኩረት አድርጋ ስትሰራ በቅርቡ ከዓለም ሶስተኛ የምትሆንበት ሰፊ እድል አላት።
ይህ እንዲሆን በተለይ መንግስት ለቡና ልማት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ብቻ ሳትሆን አቅራቢ እንድትሆን የበለጠ መትጋት አለበት ይላሉ። በተጨማሪም የአገሪቱን ገፅታ ለማሻሻል ቡና ከነአፈላሉ ስርዓቱ የቱሪስት መስህብ የሚሆንበትን ሁኔታ በማመቻት በቡና ላይ የሚደረጉ ወርክሾፖች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረግ ይገባልም ባይናቸው።
‹‹ኢትዮጵያ በዘርፉ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን አሁንም ምርት የተሻለ ጣዕም ያለው ቡና ማዕከልነቷን ለዓለም በማሳየት፤ ቡና ልኮ ከሚገኘው ገቢ ባልተናነሰ በቡና ምክንያት ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ታሳቢ ማድረግና ማሳደግ ይቻላል›› በማለት ይናገራሉ። እቅዱ ግቡን እንዲመታ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብና የተቀናጀ የጋራ ጥረት ይፈልጋል።
እንደአቶ አማን ማብራሪያ፤ ከሁሉ በላይ ዘመናዊ የገበያ ስርዓትን መገንባት ላይ ትልቅ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል። በተወሰኑ የኮንትራት እርሻዎች የምርት ብክነትንም፤ የኮንትሮባድ ንግድንም ለማስወገድ እየተሰራ ያለውን ማስፋት ይገባል። በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ደግሞ አርሶ አደሮች በዩኒየናቸው፣ በህብረት ስራ ማህበራታቸው አማካኝነት ምርታቸውን ጥራቱን እያስጠበቁ፤ እያስፈተሹ ጥራቱን እያረጋገጡ አርሶ አደሩ በቀጥታ ገዢዎች በግልፅ ጨረታ የሚሳተፉበት የግብይት ስርዓት መጠናከር አለበት።
የብሔራዊ ባንክ በቅርቡ የወጣ መመሪያ አጋዥ እንደሆነም ይነሳል። ከወቅታዊው የዓለም የቡና ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በዚህ አጋጣሚ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን በቅርብ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባልተለመደ መልኩ ለቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች ባንኮች ብድር እንዲሰጡ ውሳኔ ላይ መድረሱ ነው። ብሔራዊ ባንክ የወሰነው ይህ ውሳኔ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ከሚገኘው የመጠባበቂያ ገንዘባቸው ላይ ሁለት በመቶውን በመውሰድ ለቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች ብድር ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን ነው። ይህም ዕድሉን ለመጠቀም መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ ይታመናል ይላሉ።
በዚህ ረገድ ቀደም ሲልም አርሶ አደሮች በተለይ በብድርና ቁጣባ፤ በስራ ማህበራት በኩል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በብድር ያገኙ እንደነበር አቶ አማን ይናሳሉ። ይሁንና ብድሩ ከፍተኛ ወለድ የሚከፈልበት መሆኑ ትርፋማነታቸው ላይ የራሱን ጫና አሳድሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። ‹‹ በነፃ ይሰጣቸው ባይባልም እንኳን የአስተዳደር ወጪን መሸፈን በሚያስችል መንገድ ዝቅተኛ ሆኖ መቅረብ አለበት›› ይላሉ። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በቀጥታ ለአርሶ አደሩ ባሉት ቅርንጫፎች የቁም እንስሳትን መያዢያ በማድረግ አበድራለሁ ማለቱ በጣም ጥሩ ውሳኔ እንደሆነ ይናገራሉ።
በበጀት ዓመቱ የቡና ዘርፍ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የተጣለበትን ሚና ይወጣ ዘንድ ከምንም በላይ ዘመናዊ አሰራር መዘርጋትና ወደ ተግባር መግባት ይጠበቃል። በተለይ ኢትዮጵያ የአርሶ አደር አገር እንደመሆንዋ፤ ኢኮኖሚውን በሻካራ መዳፉ ደግፎ የያዘ፤ ገጠሩን ከተማውን እየመገበ የሚገኝ የሕብረተሰብ ክፍል እንደመሆኑ ትልቅ ትኩረት መስጠት ሊሰመርበት ይገባል። ምክንያቱም ለአርሶ አደሩ የማትመች ኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ ልማትም ሆነ ሰላም አይኖራትም። ለአርሶ አደር የሚመች አገር መፍጠር ይገባል። ምርታማቱን እንዲያሳድግ ማስተማር ለነገ የሚታው አይደለም። ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ልናስተዋውቀውና አማራጭ የብድር መንገዶች ሊሰፉለት እንዲሁም በዝቅተኛ ወለድ ግብዓት እንደልብ የሚገዛበት፤ የገንዘብ አቅርቦትና የገበያ እድሎችና ትስስሮች መፍጠር ዘርፉን ለማሳደግ ወሳኝ መሆናቸውን በመፍትሄነት አመላክተዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2015 ዓ.ም