የባሕር በር፤ ባሕር ኃይልና ኢትዮጵያ

ከዛሬ ሰላሳ አራት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ የራሷ ባሕር በር የራሷ ወደቦች እና በምሥራቅ አፍሪካ ጠንካራ የሚባል የራሷ ባሕር ኃይል የነበራት ሀገር ነበረች። ላለፉት ሰላሳ አራት ዓመታት ግን ሀገሪቷ ከሁለቱም ለአንድ ሀገር ወሳኝ የሆኑ ሀብቶች ተፋታ ቆይታለች። ይህን ያህል ዘመን ጉዳዩ በመንግሥት ደረጃ ሳይነሳ ቢቆይም የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የየእለት ጥያቄ ነበር ለማለት ይቻላል። ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆነው ለውጡን ተከትሎ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተጀመሩት ሁለቱም እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያውያን የሰጡት አበረታች ምላሽ ነው። መጀመሪያ የተስተናገደው ሃሳብ የባሕር ኃይል የማቋቋም ጉዳይ ነበር፤ ይህ ጅምር ብዙዎችን ያስገረመ ሲሆን ባሕር ኃይል ያለ ባሕር በር እንዴት ይታሰባል ? የሚል ጥያቄም አስነስቶ ነበር።

ሁለተኛውና ብዙ ጫጫታ ያስተናገደው ደግሞ የባሕር በር ባለቤት ልንሆን ይገባል የሚለው ነው። ይሄኛው ሃሳብ ጥቂት በማይባሉ የውጭ ኃይሎች ቀጥታ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ከኢትዮጵያውያን ወገን ግን የትኛው የባሕር በር ? እንዴትና መቼ ? የሚሉ ጥያቄዎች እንጂ የባሕር በር አያስፈልገንም ሲባል አልተሰማም። ለመሆኑ ባሕር በር፤ ባሕር ኃይልና ኢትዮጵያ ምንና ምን ናቸው? ስንል ሀገሪቷን ባለ ባሕር በርም፤ ባሕር አልባም ሆና የሚያውቋትን ነባር የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባላት አነጋግረን ያካፈሉንን እንደሚከተለው አቅርበናል።

ኮማንደር መኮንን መንበሩ ይባላሉ፤ ለ19 ዓመታት ያህል በነባሩ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አገልግለዋል። ረዥሙን ጊዜ ያሳለፉት የባሕር ጠለቅ ኮማንዶ አዛዥ በመሆን ሲሆን የጦር መርከብ 1068 ኮማንደር በመሆን ተመድበው እስከ 1983 ዓ.ም ሠርተዋል። በወቅቱ በሀገሪቱ የተከሰተውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ከአሰብ ወደብ 237 የባሕር ኃይል አባላትን በመያዝ ሞካ ወደሚባለው የየመን ወደብ አቅንተዋል። እዚያም ለየመን ባሕር ኃይል ተወካይ ኦሌኔል ወደቡን የባሕር ኃይሉን አስረክበዋል። ከዚያ በኋላ በስደት ሁለት ዓመት ቆይተው ቀሪ ጊዜያቸውን በገልፍ አካባቢ በንግድ መርከብ ላይ ሶስት ዓመት በቺፍ ኦፊሰርንት 18 ዓመት በካፒቴንነት በጥቅሉ ለ21 ዓመታት ሠርተዋል።

ኮማንደር መኮንን እንደሚያብራሩት ኢትዮጵያ ከሰላሳ ዓመት በፊት ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የባሕር በር ይዛ ከአንድም ሁለት ወደብ የነበራት ቢሆንም ዛሬ ሁሉንም አጥታ ተቀምጣለች። እንድታጣ የተደረገው ደግሞ በሴራ ነው። በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ ከአሰብ ወደብ 237 የባሕር ኃይል አባላትን በመያዝ ሞካ ወደሚባለው የየመን ወደብ በማቅናት ያስረከብኩት እኔ ነበርኩ። በወቅቱ አጠቃላይ አስራ ሶስት መርከቦች የሄዱ ሲሆን የተወሰኑት ያቀኑት ወደ ጅዳና ሳውዲ ነበር። በወቅቱ ትልቋ የኢትዮጵያ መርከብ የመን የደረሰችው 500 ባሕርተኞችን ይዛ ነበር። በዛን ጊዜ ንብረቱን በወቅቱ ይመለከታቸዋል ላልናቸው አካላት ስናስረክብ የኢትየጵያ የባሕር በር ጉዳይ እንዲህ በቀላሉ ይዘጋል የሚል እምነት አልነበረንም። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው መንግሥት ነገሩን በዝምታ አልፎታል።

ለየትኛውም ሀገር የባሕር በር አልባ መሆን የሚኖረው የኢኮኖሚ ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚኖሩ ግንኙነቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖም አለ። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በምጽዋ ወደብ የባሕር ኃይል ቀን ሲከበር አስራ አምስት ሀገራት በመርከብ የባሕር ኃይሎቻቸውን ይዘው በመምጣት ይሳተፉ ነበር። በዚህ መድረክ እንደ ባላንጣዎች ይተያዩ የነበሩት አሜሪካና ሶቪየት ሕብረትም የታደሙበት ወቅት ነበር። ይህ ለኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ረገድ የሚፈጠርው ከፍተኛ ተጠቃሚነት አለ። የራስ ወደብ መኖር በተለይም የጦር መሳሪያና ሀገራዊ ደህንነት የሚያስፈልጋቸውን እቃዎች ወደ ሀገር ቤት ለማስገባትም ከምንም በላይ ወሳኝ ነው።

በተጨማሪ ተደጋግሞ እንደሚነገረው የባሕር በር የኢኮኖሚ ምንጭ ነው። ዛሬ የባሕር በር ስለሌለን መርከቦች ቢኖሩንም ወደ ወደቡ በገቡ ቁጥር ክፍያ ይፈጸምባቸዋል። በተለያዩ ምክንያቶች በወደቡ በምትቆይበት ጊዜም በመርከቡ ቁመት ክብደትና እንደ ቆይታው እያንዳንዱ መርከብ የሚከፍለው ይኖራል። የአገልግሎት ክፍያም አለ። ይህ በውጭ ምንዛሬ የሚከፈል ሲሆን ክፍያውም ከፍተኛ ነው። የባሕር በር ቢኖር በየዓመቱ የሚወጣው በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርም ወደ ሌሎች ልማቶች ቢውል የሚኖረውን ጠቀሜታ መገመት ቀላል ነው።

የራስ ወደብ ሲኖር በራስ መገበያያ የሚከፈል መሆኑ፤ ክፍያው ዝቅተኛ መሆኑ፤ ክፍያው የሚከፈለው ለራስ ሀገር ገቢ መሆኑ፤ በወደብ ላይ ከጫኝና አውራጅ ጀምሮ የሚሠሩት ሥራዎች በሀገር ልጆች መሆናቸው የራስ የባሕር በር መኖር የሚኖረውን ጠቀሜታ እጥፍ ድርብ ያደርጉታል። በኢትዮጵያ ሁኔታ የጅቡቲንም የበርበራን ወደብ ብንጠቀም ከእነዚህ ወጪዎች አያድኑንም። ጎረቤቶቻችን ኤርትራ ጅቡቲ ሱዳን ግብጽ ሶማሊያ ኬንያ ታንዛንያ ሁሉ ወደብ አላቸው። ኢትዮጵያ ይህንን የሕዝብ ብዛት ተሸክማ ወደብ አልባ ሆና የምትቀጥል ከሆነ ከድህነት የመውጣቱ ጉዳይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ይሆናል። በመሆኑም የኪራይ ወይንም በሌላ በማንኛውም ሰዓት ሊፈርስ በሚችል ውል ሳይሆን ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ወደብ ያስፈልጋታል።

በተመሳሰይ የባሕር ኃይል መኖር ወሳኝ ነው። ባሕር ኃይል ብዙ ሙያዎች የሚገኙበት ትልቅ ዘርፍ ነው። ሌላው ቀርቶ የሕዳሴውን ግድብ በአግባቡ ለመጠበቅ የሚያስችል ኃይል ይሆናል። ከዚህም ባለፈ የባሕር በር ሲኖረን በአካባቢው ያለውን ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ፤ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የሽብር ጥቃት የመከላከል ብቃት ይኖረናል። ይህ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዚያ አካባቢ የሚንቀሳቀስ ንብረት ላላቸው ሀገራትም ዋስትና የሚሰጥ ይሆናል። ነባሩ ባሕር ኃይል አልጠፋም፤ ከነ እውቀቱ ዛሬም አለ። አሁንም ጊዜው ሳይረፍድ አዲሱን ባሕር ኃይል ለማቋቋም ነባሩን ባሕር ኃይል ያለውን እምቅ እውቀት መጠቀም ይገባል። ለዚህ ደግሞ በእኛ በኩል ዛሬም ዝግጁ ነን ብለዋል።

ሌላው እንግዳችን ማስተር ዋራንት ኦፊሰር አይቸው ማሞ ይባላሉ። በ1953 ዓ.ም ነበር ኮከበ ጽባሕ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቀው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይልን የተቀላቀሉት። መሠረታዊ የሚባሉትን የባሕር ኃይል ኮርሶች በሀገር ውስጥ በመከታተል አጠናቀዋል። ከዚያ በኋላ ከአሜሪካ መርከቦችን ለማምጣት ወደ አሜሪካ በመሄድ ከ250 ኢትዮጵያውያን መርከበኞች ጋር በመሰልጠን መርከቧን ይዘው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል።

‹‹ኢትዮጵያ በሁለቱ ወደቦቿ በወቅቱ ጠንካራ የሚባል በአካባቢውም ካሉት ግዙፍ የባሕር ኃይል የነበራት ሀገር ናት። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ሆኑ በደርግ ዘመን ይህ ኃይል ጠንካራ የሀገር መከታ ሆኖ የኖረ ነው።» የሚሉት ማስተር ዋራንት ኦፊሰር አይቸው አሁንም ነባሩን ዓይነት ጠንካራ ባሕር ኃይል መገንባት ይጠበቃል ይላሉ። ዛሬ ላይ ይህ ታሪክ እንዲደገም እና ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን መንግሥት እላይ ታች እያለ በትኩረት እየሠራ መሆኑን እያየን ነው። ይህ በጣም የሚያስደስት ጉዳይ ነው። ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን በመንግሥትም ሆነ በሕዝቡ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ፍሬ የሚታይበት ይሆናል። በአሁኑ ወቅት የባሕር በር ስለሌለን በምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን የአሁኑ ትውልድ ሙሉ ለሙሉ ይገነዘበዋል ብዬ አላስብም። የባሕር በርን ጥቅም ባሕር በር በነበረን ወቅት እዚያው ቦታው ላይ የነበረ ሰው የተሻለ ይረዳዋል።

እኛ ሀገሪቷ ሙሉ አቅም ሙሉ ተቀባይነትና ተሰሚነት ያላት ሀገር በነበረችበት ወቅት ደርሰንባት የባሕር በር ጥቅሙንም በአግባቡ ለመረዳት ችለናል። በዚያ ወቅት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የማይደርስበት የዓለም ክፍል አልነበረም። አሁን መንግሥት እየሠራ ያለው ይህ ደማቅ ታሪክ እንዲመለስ ነው። ዛሬ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ነገሮችን ከኃይል ይልቅ በውይይት በንግግር መፍታት እንደሚቻል የሚያመላክት ነው። የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚሁ አካሄድ የጀመረውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል ሀገሪቷን የባሕር በር ባለቤት እንደሚያደርጋት ሙሉ እምነት አለኝ። ኢትዮጵያ የባሕር በር ሳታገኝ የምትቀጥል ከሆነ የሕዝቡም የኑሮ ደረጃ የመንግሥትም ልፋት ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ስታነሳ ጉዳዩ የማይመለከታቸው በድንበር የማይገናኙን አንዳንድ ሀገራት ሁሉ ተቃውሞ ሲያስሙ ሰምተናል። ይህን የሚያደርጉት አንዳንዶቹ ጥቅማችን ይነካል ብለው በማሰብ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የሀገሪቱን እድገት ስለማይፈልጉ ነው።

ነባሩ ባሕር ኃይል በዛ ዘመን የኮንትሮባንድ ንግድን በመቆጣጠር፤ የኢትዮጵያውያን መርከቦች በየደረሱበት ጥቃት እንዳይገጥማቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የነበረ ነው። በአሁኑ ወቅትም መንግሥት እንደ አዲስ የባሕር ኃይል ለማቋቋም የጀመራቸው ሥራዎች አሉ። ይህ ይበል የሚያሰኝ ሲሆን በሚጠበቀው ደረጃ እንዲቋቋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሊያበረክት ይገባል። እኛ በዚህ ረገድ የሚጠበቅብንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

በራሻ በሚሳኤል ማስወንጨፍ ትምህርት የተማሩትና በአሰብ ወደብ የአየር ኃይል መደብ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ያገለገሉት አቶ ሙሉነህ ተረፈ በበኩላቸው «ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷና የባሕር ኃይሉም በመፍረሱ በርካታ ጥቅሞቿንም ክብሯንም አጥታ ቆይታለች» ይላሉ። አቶ ሙሉነህ እንደሚያብራሩት የባሕር በር ጉዳይ እስካሁን ጥያቄው ሳይነሳ መቆየቱ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት አስፈሪ የሆነበት ምክንያት ከጀርባ ብዙ ሴራ እንደነበር አመላካች ነው። በዚህ ምክንያት ዛሬ ላይ ያለው ትውልድ ስለ ባሕር በርም ሆነ ባሕር ኃይል የሚያውቀው ከየቦታው ከተሰባሰቡ መረጃዎች እንጂ የባሕር በር ተጠቃሚነትን እያየ ባለመሆኑ አዲስ ሊሆንበት ይችላል። በመሆኑም በጉዳዩ ላይ በድፍረት መምከር መነጋገር ታሪኩን ማወቅ ሕጉን ምን ይላል ብሎ ማንበብ መጀመር አለበት።

የቀይ ባሕር አካባቢ ለዓለም የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ወሳኝ ቦታ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ከሩቅ ምስራቅ እስከ አውሮፓና አሜሪካ ያሉት ሀገራት በዚህ አካባቢ በኪራይና በሌሎች መንገዶች ቦታ እየያዙ መቀመጣቸውን እናውቃለን። ይህ እውነታ እያለ ኢትዮጵያን ታክል ትልቅና በአካባቢው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ሀገር በቅርብ ርቀት እየተገኘች የባሕር በር ሳይኖራት ትቀመጥ ማለት ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም።

የባሕር በር አለመኖር አሁን ካለው በላይ አስፈላጊ የሚሆነው ለቀጣዩ ትውልድ ነው። የሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት በየወቅቱ እየጨመረ ይሄዳል። እንደ አቅማችን ለውጭ ገበያ የምናቀርብው ምርትም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል። ወደ ውጭ የሚላከውንም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ምርት በአግባቡ ለማስተናገድ የሚቆጣጠሩት እና የሚያስተዳድሩት የባሕር በር የግድ ይላል። ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆን ለኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ደህንነቷንም ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው።

ቀይ ባሕርና አካባቢው ዛሬም ድረስ በኮንትሮባንድም ሆነ በባሕር ላይ ዘራፊዎች ወንጀል የሚፈጸምበት አካባቢ ነው። በ1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እስከ ተበተነበት ጊዜ ድረስ በአግባቡ የተዋቀረ ጠንካራና አቅም ያለውና በአካባቢው የሚፈራም ነበር። ሌሎቹ ብቃትና አቅሞቹ ሳይነሱ ከ15 ኪሎ ሜትር አንስቶ ወደ መጨረሻው አካበቢ እስከ 75 ኪሎ ሜትር የሚደርሱ ሚሳኤሎችንም የታጠቀ አስፈሪ የሚከበር ኃይል ነበር። ይህ በዘመኑ የደረሰበትን የአቅም ደረጃ የሚያመላክት ነው።

አሁንም መንግሥት ባሕር ኃይሉን ለማደራጀት የጀመረውን ነገር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። መንግሥት አሁን ላይ የመሠረተውና በንቁ ወጣቶች እየተገነባ ያለው የባሕር ኃይል ለዚህ ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ እንደሚሆን አምናለሁ። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ያለውን የሰላም እጦት ለመፍታት የሚያስችል አቅም ኢትዮጵያ እንደሚኖራትም ተስፋ አለኝ።

የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በርግጠኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ አይቀርም። አሁንም በኢትዮጵያ ሕዝብ ተሳትፎና በመንግሥት ቁርጠኛ አመራር እንደሚሳካ ሙሉ እምነት አለኝ። ይህ ማለት የግድ ጦርነት ይታወጅ ማለት አይደለም። መንግሥት የጀመረው ሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ የባሕር በር የማግኘት እንቅስቃሴ ለዚህ ትክክለኛ መንገድ ነው። የባሕር ኃይል ግንባታውም ቢሆን ወቅቱን ያገናዘበ እና ተገቢ ነው። በመሆኑም ይህ ትልቅ ሀገራዊ ጅማሮ እውን እንዲሆን ሕዝቡ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ጎን በመቆም መንግሥት በጀመረው መንገድ እንዲቀጥል ጫና መፍጠር ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን  መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You