‹‹ያኔ እኔ ራስ ቲያትር እሰራ በነበረበት ጊዜ የወሊድ ፈቃድ 40 ቀን ነበር። የአመት ፍቃዴን ተጠቅሜ የ40 ቀን ፍቃዴን ወሰድኩ፡፡ እንዲህም ሆኖ የመጀመሪያ ልጄን ወልጄ እተኛሁበት አራስ ቤት ቲያትር እንዳዘጋጅ ስክሪፕት ተላከልኝ›› ትላለች የዛሬዋ እንግዳችን፡፡
እንኳን ባል ቀርቶ ወጣ ወጣ ያለ እንደ ቲያትር ያለ ሙያን ወላጅ እንኳን በማይፈልግበት ማህበረሰብ ውስጥ አልፎና ራስን ሆኖ ለስኬት መብቃት እጅግ እንደሚከብድም ታወሳለች። ትዳር፤ ልጅ፤ ፊልምና የቲያትር ሥራ ውጪ በማምሸት፤ውጭ በማደር፤ ከአዲስ አበባ ውጭ በመውጣት የሚሰራ መሆኑ ክብደቱን ከመጠን በላይ እንደሚገዝፈውም ከራሷ ተሞክሮ ተነስታ ትመሰክራለች።
እንደ ዕድል ሆኖ እሷን ባይገጥማትም ቀናተኛ ባል ካለ ደግሞ የበለጠ ክብደቱ ይጎላል። ከባድ ቢሆንም ይሄን ጊዜ ጉልበት የሚሰጠው እግዚአብሔር እንዲሁም በቅርቡ በሞት የተለያት ባለቤቷና የሁለት ወንድ ልጆቿ አባት መልካምነት አግዟት በቲያትሩና በፊልሙ ዓለም ከ35 ዓመታት በላይ መናኘት ችላለች።
‹‹ማንም ሰው ቢያግዝ እናት እናትነቷን አትተውም›› ስትል ምንም በቲያትርና ፊልም ሥራ ጫና ውስጥ ብትኖርም በተለይ ለልጆቿ የሚያስፈልጋቸውን ሳታሰልስ ታደርግላቸው እንደነበር ትናገራለች። አሁንም ከጥበቡ ሳትወጣ በታምራት ፊልም ፕሮዳክሽን እየተሰራ ባለ ፊልም ላይ በፕሮዳክሽኑም፤ በፊልሙም የአክቲንግ ዳይሬክተር ሆና እየሰራች ትገኛለች።
ዛሬ እንግዳችን ያደረግናት አርቲስት ዓለምፀሐይ በቀለ ወሊድን ብቻ ሳይሆን ከሴትነት ጋር ተያይዞ በኪነጥበቡ ሙያ ዘርፍ ሊገጥሙ የሚችሉ ከባድ መሰናክሎችን ተሻግራለች። በአጫጭርና የሙሉ ጊዜ ቲያትሮች፤ የቴሌቪዥን ድራማዎች በዝግጅት፤ በትወና እና በመፃፍ ተሳትፋለች።
‹‹ወንድ አይገባም›› የሚለውንና ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ለመድረክ የበቃውን ጨምሮ ራሷ ጽፋና አዘጋጅታ ለመድረክ ባበቃቻቸው ስድስት ያህል ተወዳጅ ቲያትሮቿ ተለይታ የምትታወቀው አርቲስቷ አብዛኞቹን ቲያትሮች፤ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች በመሪ ተዋናይነት ነው የተጫወተቻቸው። ለሴት ልጅ በቲያትር መሳተፍ ከባድ ነው። ገና ልጃቸው በሙያው እንድትሰማራ ባለመፍቀድ ከወላጆች ይጀምራል። ሥራ ላይም ችግሮ ች ሊኖሩ ይችላሉ። ሆን ተብሎ ሳይሆን ግንዛቤ ካለመኖር ሊከሰት ይችላል። እሷ ይሄን ሁሉ ችላ በመሻገሯ በቅርቡ 10ኛውን የ2014 የበጎ ሰዎች ሽልማትን አግኝታለች። በሽልማቱ ዓለምፀሐይን ጨምሮ ከዘጠኝ የተለያዩ ዘርፎች 691 ለአገር በጎ ያደረጉ እጩዎች ቀርበው ነበር። በየዘርፉም ሦስት፤ ሦስት ተለይተው ቀሩ። በኪነጥበቡ ዘርፍ ከተለዩት ሦስት ለአገርና ለሕዝብ አርአያነት ያላቸው አሸናፊዎች መካከልም ዓለምፀሐይ በፊልም ዳይሬክተሪንግ ተሸላሚ መሆን ችላለች።
‹‹እቴጌ መነን የሴቶች ትምህርት ቤት እማር በነበረበት ጊዜ ወንድ ስለሌለ ሴቶች ነበርን እንደ ወንድ ሆነን በትምህርት ቤቱ በሚዘጋጁ ድራማዎች የምንተውነው›› የምትለው ዓለምፀሐይ አሁን ታዋቂ ወዳደረጋት የቲያትርና የፊልም ሙያ ለመግባት መነሻ የሆናትን ታስታውሳለች።ሁለት ወራት የቆየችበት የጋሽ ተስፋዬ አበበ የቲያትር ክበብም አስተዋጽኦ እንዳደረገላት ታነሳለች። ክበብ ውስጥ ሳለች የእጩ ተዋናይ ኮርስ በመምጣቱ ከክበቡ ወጥታ ለሁለት ዓመታት ኮርሱን ወስዳለች። ወደዚያው ራስ ቲያትር ተከፈተ። እሷን ጨምሮ ኮርሱን የወሰዱት ተማሪዎች በሙሉ አዲስ ሠራተኞች ሆነው በራስ ቲያትር ተቀጠሩ። አርቲስቷ እዚህ ቲያትር ቤት እዛም እዚህም እንድትሳተፍ የሚጋብዟት ሲበዛ በራሷ ፈቃድ መልቀቂያ አቅርባ እስከለቀቀች ድረስ ለ25 ዓመታት አገልግላለች። ከ30 በላይ የመድረክ ቲያትሮችን በተዋናይነት ተጫውታለች። ከራስ ቲያትር ከወጣች በኋላ ስድስት ያህል የሙሉ ጊዜ ቲያትሮች አዘጋጅታለች። ከዚህ በኋላም የቴሌቪዝን ድራማና ፊልም በስፋት አዘጋጅታለች። እንዲሁም እነዚህ ፊልሞችና ቲያትሮች ላይ በትወና ሰርታለች። ገመና የቴሌቪዚን ድራማ ላይ ከሦስቱ መምህራን አንዷ የነበረችበት ይጠቀሳል።
እንደምትለው ፊልምና ቲያትር ከትዳር፤ ልጅ፤ የቤት ኃላፊነቶች ጋር ውጭ በማምሸት፤ ውጭ በማደር፤ ከአዲስ አበባ ውጭ በመውጣት የሚሰራ በመሆኑ ይከብዳል። እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች በጣም አቅምና ጊዜ ይጠይቃሉ። አንዳንድ ጊዜ ቤታችንን በሀሳብ ጭምር ላናየው እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ ቤትም ውጭም እንሰራለን። በአርቲስቶች ላይ ሲሆን ይታይና ይጎላል እንጂ ሴቶች በአጠቃላይ የሥራ ሰው ሲሆኑ ይሄ ችግር ይገጥማቸዋል። ብዙዎች ለስኬት የበቁት ይሄን ሁሉ መሰናክል ተወጥተው ነው። በዚህ ሙያ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሙያ ቢሆን ሴት ምንም ነገር መሥራት ትችላለች። ይሄን ማንም ሰው ማመን አለበት። በመጀመሪያ መጠንከር፤ በቀጣይ እንደሚችሉ እርግጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል። የሴት ጭንቅላት ብዙ ነገር ማሰብ ይችላል። ትዳሯን፤ ልጆቿን፤ ሥራዋን፤ ሁሉን ነገር ማሰብ ትችላለች። ‹‹ሴቶች አእምሯችን ውስጥ የምንሰራው ሥራ ነጠላ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ በጣም የሚያጨናንቀን ሥራ ሊኖር ይችላል። ግን በድል መወጣት ይጠበቅብናል›› ትላለች። እንደ እሷ የቲያትር ፊልም ደራሲዎች ብዙ ጊዜ የወንድ ካራክተሮችን (ገፀ ባህሪዎችን) ነው አብዝተው የሚጽፉት። ለሴቶቹ አነስተኛ ነገር ነው የሚጽፉት። ብዙ ሴት ተዋናዮች ያልነበሩትም ለዚህ ነው። አሁን ግን እራሳቸው በሚያደርጉት ጥረት በዝተዋል። ‹‹ለምሳሌ እኔ አዘጋጅ የሆንኩት ከአንዲት ጓደኛዬ ጋር እስካሁን ድረስ ለወንዶቹ ረዳት አዘጋጅ ሆነን ብዙ ቲያትር ሰርተናል። አሁን ግን ራሳችንን ችለን ማዘጋጀት አለብን ብለን ጠይቀን ›› ነው ስትልም የራሷን ተሞክሮ አብነት ታደርጋለች። እንዳከለችው በአጋጣሚ በዚያን ጊዜ የነበረው ቲያትር ለሌላ ወንድ ተሰጥቶ ስለነበር የሚቀጥለውን ቲያትር ታዘጋጃለሽ ተብሎ የሚቀጥለው ቲያትር ተሰጣት። ከዛ ቀጥሎ የነበረውን ፤ ቲያትር ደግሞ ፕሮፖዛል አቅርባችሁ ያለፈ ሰው ያዘጋጃል ተባለ። አቀረበችና አለፈች አዘጋጀች። ቆየት ብሎም የቲያትር ክፍል አዘጋጅ ይመረጥ ሲባል የቲያትር ክፍሉ አባላት በድምፅ ብልጫ እሷን መረጧት። እንዲሁም የቡድን ዝግጅት ውስጥ ካለ ኮሚቴ እሷን የዝግጅት መሪ አድርገው መረጧት። እንዲህ እንዲህ እያለች ነው ራሷን ያበቃችው።
‹‹አሪፉ የነበረው ሁላችንም ተማሪዎች ስለነበርን ስሜታችን የሥራ ሳይሆን የትምህርት ቤት ዓይነት ነበር›› ስትል ዓለም ፀሐይ ያበቃትን የሥራ አሀዱዋን ታስታውሳለች። እንዳከለችልን ትምህርቷን አቋርጣ በገባችበት ራስ ቲያትር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራችው ‹አንድ ለአንድ››የሚል ቲያትር ነበር።
ይሄ በወላጆቿ መሰማቱ በሙያው ከገጠማት መሰናክል ቀዳሚ ሆነ። በጥብቅ ተቃወሟት። ዓለምፀሐይ በማህል አጎቷ ደርሶላት በብዙ ትግል አሳምኗቸው ባይፈቅዱላት በሙያው ገፍታ ዛሬ ላይ መድረስ ትችል እንዳልነበርም ታወሳለች። እንደ እሷ አሁን ላለችበት የባለቤቷና የቤተሰቦቿ አስተዋጽኦ ጉልህ ነው። ቤተሰቦቿ ትምህርቷን በማቋረጧና የማይፈልጉት ሙያ ውስጥ በመግባቷ የተቃወሟት ቢሆንም የአቅማቸውን ደግፈዋታል።
ቤተሰብ ቢደግፈንም ብዙ ጊዜ ወልደን በምንተኛበት ጊዜ ነው ለምሳሌ፦እኔ ስወልድ እናቴ ቤት እየሄድኩ ነበር የምታረሰው። ከዛም አልፎ ብዙ ጊዜ ታናናሽ እህቶቼ ሲመቻቸው መጥተው ያግዛሉ። ልጅ ያቅፋሉ። ወደ ቤት ይዘው ይሄዳሉ። ልጆቼን ከሰራተኛ ጋር ቤተሰቦቼ ቤት ወስጄ እንዲጠብቁልኝ በማድረግ ነበር ወደ ሥራ የምሄደው። ማታ ደግሞ ወደ ቤተሰቦቼ ጋር በመሄድ ልጆቼን ሰብስቤ ወደ ቤቴ እገባለሁ ስትል ድካሟን ትገልፀዋለች።
በተለይ የመጀመሪያ ልጇን ወልዳና የ40 ቀን የወሊድ ፈቃድ ብቻ ተሰጥቷት አራስ ቤት በነበረችበትና ይባስ ብሎ ቲያትር እንድታዘጋጅ አራስ ቤት ድረስ ስክሪብት በተላከላት ወቅት ትልቅ እገዛ አድርገውላታል። እገዛቸው በወሊድ ፈቃዷ ላይ የዓመት ፈቃዷን በመውሰድ ወጣ ገባ እያለች የተሰጣትን የቲያትር ዝግጅት የቤት ሥራ በስኬት እንድታከናውን ረድቷታል።
ሟቹ ባለቤቷ የሚያደርግላት እገዛም ቀላል አልነበረም። ሥራ በሌለው ጊዜ ልጆቹን ያጥባል። ልብሳቸውን ያዘጋጅና ያለብሳል። የቤት ሥራቸውን አስርቶ ይጠብቃታል። ያስተኛቸዋል። እሷ በእሱ ቦታ፤ እሱ በእሷ ቦታ ቢሆኑ ኖሮ አደርገዋለሁ ብላ የማትገምተውን መልካም ነገር ሁሉ አድርጎላታል።
አርቲስቷ ይሄን ከአንዳንድ በሙያው ውስጥ ያሉ ሴቶች በተለየ ከባለቤቷ ጋር ያላትን ትስስብ ከሌሎች ባሎች ጋር አታነፃፅረውም። ባለቤቴን እኔም አምነዋለሁ። እሱም ያምነኛል። አልዋሸውም ዕውነት ነው የምናገረው። ቅዳሜና እሁድ ሥራ እንዳለኝ ያውቀዋል። ፊልም ሲጀመር ፊልም እንደምሰራ ይረዳኛል። ሳመሽ እንዴውም ደውሎ ራት ይቀመጥልሽ ወይ ነበር የሚለኝ። አለዚያ እስከ ስንት ሰዓት እንጠብቅሽ ይለኝና የሚቻለውን ያህል ይጠብቃኛል ትላለች። አደውልና እናንተ ተኙ እኔ በጣም አመሻለሁ እላለሁ። መኪና ያደርስሻል ወይ ነው ጥያቄው። አዎ ያደርሰኛል እላለሁ›› ስትል ነግራናለች። የተከራዩባቸው የውጭ በር ቁልፍ ስለሰጧቸው በመጣችበት ሰዓት ከፍታ ትገባለች። በመሆኑም በባለቤቷ ላይ የቅናት መንፈስ አይታ አታውቅም። ‹እኔ እንዳልጎዳ ነበር የሚጠብቀኝ› ትላለች። ሌላው ቀርቶ ለምሰራው ሥራ ሁሌ ጉልበት የነበረኝ ባለቤቴ ነውም ባይ ነች። ዕድሉ ስለነበረው ለፊልምም ሆነ ለቲያትር ማንበብ የምትፈልገውን በአጠቃላይ ለምትሰራው ሥራ ይጠቅማታል ያለውን ከኢንተርኔት ላይ እያወረደ ይሰጣት ነበር። ቲያትር ወይም ፊልም ስራና ቀረፃ ኖሯት ስታመሽ እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከእንቅልፉ ጋር እየታገለ በትግስት ይጠብቃት እንደነበርም ታወሳለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው የቲያትሩንና የፊልሙን ዓለም ከተቀላቀለች በኋላ ከጓደኞቿ ጋር የማታ ትምህርት ተምረው መሆኑን የምትናገረው አርቲስቷ ካገባች በኋላ ዕውቀቷን እንድትጨምር በማድረጉ ረገድም ባለቤቷ ሚናው የጎላ ነበርም ትላለች። ባህል ሚኒስቴር ለቲያትር ቤቶች በሰጠው ዕድል ዩኒቨርሲቲ ገብታ ሦስት ዓመት ተኩል ስትማርም እገዛው አልተለያትም።
ባለቤቴ በተፈጥሮ የሚገባው፤ አውቆት ሳይሆን በማንበብ ወይም ተመልካች ሆኖም የሚያውቅ ሰው ዓይነት ነው ትላለች። አንዳንድ ጊዜ ታዲያ የምትሰራውን ሥራ ታወራዋለች። ይሄ እንዲህ ቢደረግ ይሻላል ይላታል። ልጆቻቸው ከፍ ከፍ ካሉ በኋላ እረፍት በሆኑ ቀን ራት እንደመብላት ወይም እንደሽርሽር ዓይነት ቦታ ተያይዘው ይወጡ ነበር። ለልጆቻቸውም እንዲህ ዓይነቱን ጊዜ ይሰጣሉ። ከባድ ሥራ በሚኖራት ጊዜ ባለቤቷ በደንብ ያውቃል። ስለዚህ በውጭ ምትሰማው ቢኖርም የቅናት ክፉ ስሜት እሷ ቤቷ ውስጥ ገብቶ አያውቅም። ጓደኞቿም አልገጠማቸው።
ራስ ቲያትር የነበርን ልጆች በሙሉ ከጓደኝነት አልፈን ልክ እንደቤተሰብ የምንተዋወቅ ነበርን። አንዱ አንዱ ቤት ይመጣል። የሌላውን ባል ወይም ሚስት ሌላው ያውቀዋል። የኛ ዘመን እንዳሁኑ ዓይነት አልነበረም። ምን አልባት ወደ ክፉ ሀሳብ የማንገባው ይሄ ነገር ረድቶን ይሆናል ብዬ አስባለሁ ትላለች ምክንያቱንም ስታብራራ።
አርቲስቷ እንዳወጋችን በእርግጥ ባለቤቷ የሚሰራው አዲስ አበባ ውስጥ ቢሆንም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ነበር። ድርጅቱ ገባ ወጣ ብሎ የሚሰራበትም አልነበረም። ፈቃድም ቢሆን ከአቅም በላይ ካልሆነ አይሰጥም። በመሆኑም ልጆች መውለድ ብቻ ሳይሆን ማሳደግ፤ ለልጆች የበለጠ ጥንቃቄና እንክብካቤ ጥበቃ ሲባል ከሰራተኛ ጋር ወደ ወላጆች ቤት መውሰድ፤ ከፍ ሲሉም ትምህርት ቤት ማስገባት፤ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት፤ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ማመላለስ፤ በትምህርት ቤት ያለውን መከታተል በእሷ ላይ ነበር የወደቀው። ‹‹እንደገና ቤቴ አለ። ቤቴ ውስጥ መአት ነገሮች ያስፈልጉኛል። እነዚህን ሁሉ የማሟላው እኔ ነኝ›› የምትለው ዓለምፀሐይ ይሄ ከከባዱና ፋታ ከማይሰጠው የቲያትርና ፊልም ሥራ ጋር ስደመር ሕይወቷን እጅግ ፈታኝ አድርጎት እንደነበርም ታወሳለች። በተለይ እስቴጅ (መድረክ) ላይ የነበረባትን ኃላፊነት ቤት ውስጥ ከነበረው ጣጣ ጋር አስታርቆ ለመሄድ ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል። ቤቷን የምታየው ከምሽቱ ስድስት እና ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከሥራ ስትመለስ ነው። ሰርክ ባለቤቷ የቤት ሥራቸውን አሰርቶ ጠረጴዛ ላይ የሚያስቀምጥላትን የልጆቿን ደብተር ታያለች። ትምህርት ቤታቸው በሚጠይቀው መሰረት ፊርማዋን ከማሳረፏ በፊት በትክክል መሰራቱን ማረጋገጥም ግዴታዋ ነበር። በዚህም ለእንቅልፍ የምትሰጠው ሰዓት ሁለት ሰዓት ሆኗል። ምግብ የምታዘጋጅ ሰራተኛ ብትኖራትም ልጆቿ ዩኒቨርሲቲ እስኪገቡ ድረስ ምሳቸውን የምትቋጥረው ራሷ ነበረች። በመሆኑም በብዙ ደክማለች። ሆኖም የትኛውም የቲያትርም ሆነ የፊልም ሥራዋ ላይ ‹ያደረገባት ተፅዕኖ አልነበረም። መሸለም ያስቻላትም ይሄው ስኬቷ ነው። የእሷም ሆነ የሌሎች ሴቶች ስኬት ደግሞ ለሌሎች አርአያ ይሆንና ያነሳሳል። ሴት ትችላለች የሚለውን ያሳያል የሚለው ሀሳቧ ነው። መልካም ንባብ!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2015 ዓ.ም