ለግብርናው ዘርፍ ከሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብቶች መካከል ፀረተባይ አንዱ ነው። ይህም ግብርና የሚከናወንበትን ወቅት ጠብቆ በዓይነትና በመጠን መቅረብ ይኖርበታል። ግብአቱም እንደየሰብሉና እንደሚከሰተው የተባይ ዓይነት የተለያየ በመሆኑ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ግብአቱን ማሟላት ይጠበቃል።
አዳዲስ ሰብልን፣ አትክልትና ፍራፍሬን በየጊዜው የሚያጠቃ ተባይ የሚፈጠር በመሆኑ፣ ይህን ተለዋዋጭ የሆነ የተባይ ክስተት ለመቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ማድረግም ያስፈልጋል። እስካሁን ባለው ተሞክሮ የግብአት አቅርቦቱ በአገር ውስጥም ከውጭ በሚደረግ ግዥም ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።
አሁን እንደ አገር በገጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና በየጊዜው በሚከሰተው የዋጋ መናር ጸረ ተባይ ኬሚካል ከውጭ በግዥ ለማስገባት ያስቸግራል፤ በመሆኑም የውስጥ አቅምን በማጠናከር ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም።
በአገር ውስጥ ፀረተባይ ኬሚካል በማምረት ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው አዳሚቱሉ ፀረተባይ ማዘጋጃ ፋበሪካ መሆኑ ይጠቀሳል። ይህ ተቋም ካለው የረጅም ጊዜ አገልግሎት አንጻር ተለዋዋጭ የሆነውን ተባይ መቋቋም የሚችል ፀረተባይ በማምረትና በግዥ ከውጭ የሚገባውን ፀረተባይ በአገር ውስጥ ለመተካት እንዲሁም ስለአጠቃላይ የተቋሙ እንቅስቃሴ በአዳሚቱሉ ፀረተባይ ማዘጋጃ ፋበሪካ የምርታማነትና የተቋማዊ ለውጥ ተጠባባቂ ኃላፊ ከሆኑት አቶ ገመቹ ጣፋ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናዋል።
የፋብሪካው ምርቶችና ግብአቶች
አዳሚቱሉ ፀረተባይ ማዘጋጃ ፋበሪካ ለግብርና እና ለጤናው ዘርፍ በማምረት የ25 አመት ተሞክሮ ያለው መንግሥታዊ የልማት ተቋም ነው። የተለያዩ ሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም እንስሳትን የሚያጠቁ ተባዮችን የሚያጠፉና የሚከላከሉ 26 ዓይነት ምርቶችን በማምረት ለተጠቃሚው ያቀርባል። አንዱ የመድኃኒት ዓይነት ብቻ የተለያዩ ተባዮችን ለማጥፋት ጥቅም ላይ የሚውል ጭምር በመሆኑ ጠቀሜታው ሰፊ ነው።
ከውጭ በግዥ የሚገቡናበአገር ውስጥም የሚገኙትን ግብአቶች ይጠቀማል። በተለይም ዱቄት ፀረተባዮችን ለማምረት ዲያቶማይት የተባለውንና ዘይት ነክ የሆኑትን ከአገር ውስጥ ጥሬ ግብአት ማግኘት ይቻላል። ዲያቶማይት (አፈር) ግብአት ባቱ በሚባለው አካባቢ ከአምስት እስከ አስር ኪሎ ሜትር ጥልቀት በቁፋሮ ይገኛል። ግብአቱ በጎተራ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ምርት በነቀዝ ተባይ እንዳይጠቃ ለመከላከል የሚረዳ ነው።
አንዱ ምርት ከአንድ በላይ ግብአት ማሟላት የሚጠይቅ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ማሟላት የማይቻልበት ሁኔታ ስላለ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ መተካት የማይቻለውን ከውጭ በግዥ በማስገባት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል። አሁን ላይ ግን እንደ አገር ባጋጠመው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግር አስፈላጊ ግብአቶችን ከውጭ በግዥ ለማስገባት አዳጋች እየሆነ ነው። ምንዛሬ ግኝት ቢሻሻል የፀረተባይ ተደራሽነትን ማስፋትም ማረጋገጥም ይቻላል።
የማምረት አቅም
ፋብሪካው በአመት በዱቄት ፀረተባይ አቅርቦት እስከ አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ኪሎግራም፣ በፈሰሻ ደግሞ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር ፀረተባይ የማምረት አቅም አለው።
በግብርና ሚኒስቴር ተመዝግበው ከውጭ ወደ 382 ዓይነት ፀረተባዮች አገር ውስጥ እንደሚገቡ ይነገራል። በወጪ ደረጃም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይወጣል። በዚህ ምክንያት የፋብሪካው ድርሻ እያነሰ፣ ከውጭ የሚገባው ከፍ እያለ ነው።
ፋብሪካው የውጭ ምንዛሬ የማግኘት እድሉ ሰፊ ቢሆንም፣ ከውጭ የሚገባውን በአገር ውስጥ በማምረት የአርሶ አደሩን አቅም ባገናዘበ ማቅረብ ይቻላል። በቴክኖሎጂ በመታገዝ ፀረተባይ ለማምረት ፍላጎቱም ዝግጁነቱም አለው። በአሁኑ ጊዜም ፋብሪካው ከቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት ጋር ግንኙነት በመፍጠር በተሻለ ለማምረት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። ግብርና ሚኒስቴርም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ድጋፍ በማድረግ እያገዘን ነው። ለተለያዩ ፀረተባይ ኬሚካሎች ማምረቻ የሚውል ጥሬ ዕቃ ማስመጪያ ወደ ሰባት ሚሊዮን ዶላር መንግሥት ፈቅዶልናል። ትኩረቱ በዚህ ከቀጠለ ከውጭ ጥገኝነት መውጣት ይቻላል።
ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ጸረ ተባይ የማምረት ዝግጁነት
አዳዲስ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገነዘበ ጸረ ተባይ ለማምረት ጥረት እየተደረገ ነው። ለአብነትም ለጤና ሚኒስቴር ለወባ በሽታ መከላከያ ኬሚካሎች እያመርተ ያቀርባል። ጤና ሚኒስቴር ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመዳሰስ ወቅታዊ ግብአት እንዲቀርብለት ጥያቄ ያቀርባል። ጥያቄው በፈሳሽ ወይም በዱቄት መልክ ይመረትልኝ የሚል ሊሆን ይችላል። በቴክኖሎጂ ምክንያት በሚፈልገው መልኩ ማቅረብ ካልቻልን ገበያው ወደ ሌላ ሊሄድና ከፋብሪካው እጅ ሊወጣ ይችላል።
በግብርናው ዘርፍም እንዲሁ በተመሳሳይ በምዕራብ አፍሪካ የታየ ተባይ ምሥራቅ አፍሪካ አይደርስም ብለን ካልተዘጋጀን ተባዩ ደራሽ ሆኖ ሊያጠፋን ይችላል። ለዚህም በደቡብ አሜሪካ ተከስቶ ኢትዮጵያ ውስጥም ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎ የነበረውን የበቆሎ ትል ማስታወስ ይቻላል። እንዲህ ያሉ መረጃዎችን በመከታተል በወቅቱ ለመድረስ በፋብሪካው በኩል ጥረት ተደርጓል።
ነገር ግን የሚፈጠረው ተባይ ፀባይ ስፔሻላይዝ አደረገ የሚባለው ዓይነት ደረጃ ላይ የደረሰ ሆኖ ሲገኝ የሚዘጋጀውም ፀረተባይ እንደ ባህሪው የተመረጠ መሆን ይኖርበታል። ይህን በምሳሌ ለመግለጽ፣ ከፍተኛ የምርት ብክነትና ማነስ የሚያስከትል የሣር ዓይነት አረም ቢሆን፣ በፋብሪካው ለአረም ተብሎ እየተዘጋጀ የሚቀርበው ቱ ፎር ዲ የሚባለው አያገለግልም። የግድ የተመረጠ ፀረአረም ማምረት ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ ቴክኖሎጂ መኖር አለበት።
ከተለያዩ ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ጋር በመሥራት የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በፋብሪካው በኩል የተጀመረ ሥራ አለ። ቴክኖሎጂ ካፒታል ኢንቨስትመንት ወይንም የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። ለዚህ ነው መንግሥት በልዩ ትኩረት ለዘርፉ እንዲደግፍ የሚፈለገው።
ለቆላና በጋ መስኖ ልማት ያለውን የትኩረት አቅጣጫ መሠረት በማድረግ የፀረተባይ ምርቶችን በማምረት የማስተዋወቅ ሥራ ተከናውኗል። ለአብነትም የቆላ የበጋ መስኖ ስንዴ ሲዘራ፣ ዘሩ በፈንገስ እንዳይጠቃ ለመከላከል የሚያስችል ምርት ተመርቷል። በአረም እንዳይጠቃም እንዲሁ በተመሳሳይ ምላሽ ተሰጥቷል።
የአንበጣ ወረርሽኝ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። ፋብሪካው ከሦስት መቶ ቶን በላይ ፀረተባይ በማምረት ወረርሽኙን ለመቋቋም ጥረት አድርጓል። ፋብሪካው በቅርብ ወደ ገበያ የሚያወጣው ምርትም አዘጋጅቷል። ምርቱ በተለይ በጥጥ እርሻ ላይ የተለያየ ጉዳት የሚያስከትሉ ተባዮችን ለማጥፋት የሚያገለግል ነው። ምርቱ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ በኋላም በማሳ ላይ የማረጋገጥ ሥራ በማከናወንና ከተጠቃሚዎችም ግብረመልስ በመሰብሰብ የማሻሻል ሥራ ለመሥራትም በፋብሪካው በኩል ዝግጁነቱ አለ።
የፋብሪካውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግም ይሰራል። በተደረገ የገበያ ዳሰሳ ችግሩ ስለተደረበት የፋብሪካውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርብ ወይንም የሚያሰራጭ አካል እንዲኖር የጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል።
ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ ግንኙነት
ፋብሪካው የምርምር ክፍል አልነበረውም። በ2013 ዓ.ም ላይ በተደረገው የመዋቅር ጥናት የጥናትና ልማት ክፍል አዋቅሮ ባለሙያዎች አሟልቶ የጥናትና ልማት ሥራ ለመሥራት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ጋር በትብብር በመሆን ግብርና ሚኒስቴር በሚፈቅደው የፍቱንነት ማረጋገጫ ማዕከላት የምርት ሙከራ ሥራ ተጀምሯል።
ፋብሪካው ከመልካሳ የምርምር ማዕከል እንዲሁም በግብርና ምርምር ሥር ከሚገኘው ሰበታ ካለው የምርምር ማዕከልም ጋር በተመሳሳይ ይሠራል። የሰበታ ምርምር ማዕከል ከእንስሳት ጥገኛ ተህዋስ (አኒማል ሄክቶ ፓራሳይት)ጋር በተገናኘ በሚከሰት የጤና ችግር ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ነው። ፋብሪካው የምርት ናሙና ወደ ማዕከሉ በመላክ ምርመራ እንዲካሄድ ያደርጋል። የተላከው ናሙና የምርመራ ሂደቱን ካለፈ በኋላ የብቃት ማረጋገጫ ምዝገባ ለማግኘት ያስችለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአክሊሉ ለማ ምርምር ማዕከል፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና ላይ የሚያስፈልጉ ምርቶች ፍቱንነታቸውን በማረጋገጥ ላይ ያግዛሉ። መልካሳ ምርምር ማዕከልና ጎንደር ዩኒቨርሲቲም የጥጥ እርሻን የሚያጠቁ ተባዮችን በተመለከተ ባደረጉት እገዛ ፋብሪካው የምርት ምዝገባ ለማካሄድ ችሏል።
ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር ደግሞ በመጋዘን ወይንም በጎተራ የተከማቸ ምርት የሚያጠቃ ነቀዝን ለመከላከል በሚረዳ ምርት ፍተሻና ምርምር፣ እንዲሁም ከወንዶ ገነት ደን ኮሌጅ ጋርም በመአዛማ እጽዋት ላይ በጋራ ሠርተናል። ከነዚህ ተቋማት ጋር በተከናወነው ሥራ ከፀረተባይ የፀዳ የሥጋ ምርት ለውጭ ገበያ ለመላክ የሚያስችል ከመአዛማ እጽዋት የመከላከያ ምርት ማምረት ተችሏል።ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋርም በመሆን የእንስሳት ጥገኛ ህዋሳትን ለመከላከል የጋራ ሥራ ተሠርቷል።
ተግዳሮቶችና መፍትሄዎች
አንዳንድ ከአንድ በላይ በሆነ ግብአት የሚዘጋጁና የተለየ ፀረተባይ ለማምረት የሚውሉ መስሪያ ማሽኖች ባለመኖራቸው ከውጭ አገር በግዥ ማስገባት ይጠበቃል። መሥሪያ ማሽኖቹን በግዥ አስመጥቶ ለመትከል ደግሞ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። ለምሳሌ ለአበባ፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ አልሚዎች የሚውል ፀረተባይ ማምረት እንፈልጋለን። ነገር ግን ለማምረቻ የሚውል ፕላንት ወይንም ማምረቻ ማሽን ለመትከል ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ አምርተን ማቅረብ አልቻልንም።
ፋብሪካው በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል አቅም መፍጠር ያልቻለው ከምርቱ የሚያገኘው ገቢ ለተወሰነ አገልግሎት ከዋለ በኋላ ቀሪው ለመንግሥት ፈሰስ ወይንም ገቢ የሚደረግ በመሆኑ ነው። አሁን ላይ ግን ፋብሪካው የሚያገኘውን ትርፍ መልሶ አቅሙን እንዲገነባበት ወይንም ለኢንቨስትመንት እንዲያውለው ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረለት ነው። ወደፊት ለውጦች እንደሚኖሩ ተስፋ አለ።
ሌላው እየቸገረን ያለው በፀረተባይ ምዝገባ ሂደት ወቅት ያለው የአሠራር መጓተትና የአቅም ውስኑነት ነው።በፋብሪካው ተመርተው የሚወጡ አዳዲስ የፀረተባይ ምርቶች ገበያ ላይ ከመዋላቸው በፊት አስፈላጊነታቸው፣ ጥራታቸው፣ አካባቢ ላይ ብክለት አለማስከተላቸው ወይም የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌላቸው፣ በአጠቃላይ ለታለመው ዓላማ መዋል ስለመቻላቸው በሚያረጋግጠው አካል ተፈትሸውና ተመዝግበው ሕጋዊ ከሆኑ በኋላ ነው ለገበያ የሚውሉት።
ይህን ሂደት ለማስፈፀም መጓተትና የሚፈለገውን ፍተሻ በማድረግ የማረጋገጥ የአቅም ውስኑነት ከፍተት መጓተቶችን አስከትሏል። ናሙና ውጭ ልኮ ለማሠራት ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ ይጠይቃል። ለአብነት ለጤና አገልግሎት የሚውል ምርት አምርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ በውጭ ምንዛሬ ክፍያ ተፈጽሞ ናሙና ቤልጅየም አገር ተልኮ ነው የጥራት ማረጋገጫ ውጤት የሚመጣው። ፋብሪካው በዚህ ረገድ ያለበትን ችግር ለግብርና ሚኒስቴር አቅርቦ የተወሰነው ምርት እንዲመዘገብ ማድረግ ተችሏል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2015 ዓ.ም