በሁለት የተለያዩ ዘመናት ውስጥ፤ ፋሽን የዘመኑን መልክ አላብሶ ጉዞውን ቀጥሏል። ትናንት በራሱ ቅኝትና ጊዜው ባስገኘለት ልኬት የራሱን ቀለም ተላብሶ አልፏል። ዛሬ ደግሞ ሌላ የራሱን መልክ ይዞና ሌላ ቀለም ለብሶ ተገኝቷል። በእርግጥ አንዱ በሌላው ላይ አይገኝም አይባልም፤ የዛሬ መነሻው ትናንት ነውና። የዛሬው መልክ የትናንቱን መነሻ አድርጎ በተሻለ መልኩ ፈክቶ ዘመኑን መስሎ ተከስቷል።
ሰዎች በራሳቸው ዘመን ተፈጥሯዊ ውበታቸውን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ብዙ ጥረዋል፤ አሁንም ጥረታቸውን ቀጥለዋል። ይህ እራስን ወይም ሌሎችን የማስዋብ አልያም ውበት የማልበስ ተግባርና ዕውቀት ዛሬ ላይ ብዙዎች ሜክአፕ ወይም በአማርኛ ገጸ ቅብ በማለት ይጠሩታል። በዚያኛው ዘመን አልያም በዚህኛው ወቅት ይህ ጥበብ በራሱ ቀለም ሰዎችን አድምቋል።
በእርግጥ የሜካፕ ግብዓት በዘመን ሂደት ውስጥ ዛሬ ላይ ከፍተኛውን የፋሽን ኢንዱስትሪ ገበያ ተቆጣጥሯል። ልክ እንደዛሬው የሜካፕ ግብዓት በዘመናዊ መልክ ተመርቶ በገፍ ሁሉም ጋር ከመድረሱና በቀላሉ ማግኘት ከመቻሉ በፊት፤ ጥንት ሰዎች የራሳቸውን ውበት የውበት ዘመናቸው በፈቀደላቸው መልኩ የውበት መጠበቂያ ምርቶችን አዘጋጅተው ሲጠቀሙ ቆይተዋል።
ሜካፕ ትናንት
በተለይ በግብጽ በጥንት ዘመን ሰዎች ውበታቸውን ለመጠበቅና ገጽታቸውን ለማፍካት የተለያየ የውበት መጠበቂያዎችን ይጠቀሙ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በስነ ውበት ልሂቃን ዘንድ በዓለም የሜካፕ የጥበብ ታሪክ ውስጥ በጅምር ደረጃ ተደጋግሞ የሚነሳው ይኸው የግብፆች ጥንታዊ የውበት መጠበቂያ አዘጋጅቶ የመጠቀም ልማድ ነው።
ግብፃውያን ወይዛዝርት የፊት ቆዳቸውን ለመንከባከብና ያላቸውን የቆዳ ቀለም ለማስዋብ የተለያዩ ቅባቶች እንዲሁም በልዩ ልዩ የቆዳ ማስዋቢያዎች በመገልገል ይጠቀሙ እንደነበር የዘርፉ ሙያተኞች ያደረጉትን ምርምር በአስረጂነት ያቀርባሉ። ግብፃውያኑ በተለይ የፊት ቅባት ከተለያዩ ፍራፍሬዎች በማዘጋጀትና ዓይንና ቅንድባቸውን የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን በመቀላቀል በመቀባት ይዋቡ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌሎች አገራትም ሰዎች ተፈጥሯዊ ግብዓቶችን በመጠቀም የራሳቸውን ውበት ሲጠብቁ ኖረዋል። በተለይ በቻይና፣ ጃፓን፣ ሕንድና እና የሩቅ ምሥራቅ አገራት በዚህ የረጅም ዘመን ልምድ እንደነበራቸው ይጠቀሳል። በእነዚህ አገራት ሴቶች የቆዳ ውበታቸውን ለመጠበቅ ከሚቀቡት የተለያዩ ተፈጥሯዊ ቅባቶች በተጨማሪ ቆዳቸው ላይ የተለያዩ ነጠብጣቦች በመሥራትና ማጌጫዎች በማንጠልጠል ተውበው ዘመናትን ተሻግረዋል።
እኛም አገር እናቶች ለዘመናት የቆዳቸውን ውበት ለመጠበቅና ፀጉራቸውን ለመንከባከብ በራሳቸው የሚዘጋጁ ልዩ ልዩ ምርቶች፣ በተፈጥሮ የሚገኙ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች በመጠቀም በራሳቸው ጥበብ በማዘጋጀት ሲገለገሉ ኖረዋል። በዚህም ኢትዮጵያውያን እናቶችና ወጣት ልጃገረዶች ቆዳቸውን ለመንከባከብና ውበታቸውን ለማፍካት ለዘመናት የተለያዩ የቆዳ መንከባከቢያና መጠበቂያ ዘዴዎችን ይጠሙ እንደነበር ማሳያዎችን በመጥቀስ ማቅረብ ይቻላል።
ጥራጥሬዎችን ፈጭተው አትክልትና ፍራፍሬዎችን አዳቅለው ልዩ መልክ በማላበስና የቆዳና የፀጉር ውበታቸው በመጠበቅ አምረውና ፈክተው ዘመናት ተሻግረዋል። በተለይም ዛሬ ላይ በየመንደሩ ያሉ የውበት መጠበቂያ ምርቶች እንደፈለጉ ማግኘት በማይችሉበት ዘመን እናቶቻችን በየራሳቸው ጥበብ ተፈጥሯዊ ውበታቸውን ሲንከባከቡ ቆይተዋል።
እናቶቻችን እንደ እንሶስላ፣ ወይባ ጢስ፣ ቅቤ፣ ፊት ላይ የሚቀቡ ቀስል፣ ፍራፍሬዎችን እንዲሁም ለፊት ማሳመሪያ በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ባህላዊ የውበት መጠቀሚያዎችን አዘጋጅተው ሲጠቀሙ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ጭምር ነው። በእርግጥ አሁንም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ዛሬም ድረስ እነዚህ የውበት መገልገያዎች የሚጠቀሙ ብዙዎች ናቸው።
ዛሬም በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወጣት ሴቶችና እናቶች ቆዳቸውና ፀጉራቸው የሚጠብቁበትና የሚንከባከቡባቸው መዋቢያዎች ከራሳቸው አይለዩም። በተለይም ወጣት ሴቶች ወጣትነት አምረው የሚታዩበት ውብ ጊዜያቸው የሚታጩበት ወሳኝ ወቅት ነውና አምረው ለመታየት እጅጉን ይፈልጋሉ። ወጣት ሴቶች ፀጉርና ቆዳቸውን መንከባከብን ከእናቶቻቸው በተማሩት መልኩ ተፈጥሯዊ ግብዓቶችን ተጠቅመው መዋቢያ ምርቶችን አዘጋጅተው ይጠቀማሉ።
ኢትዮጵያውያን እናቶች በምንም መልክ ተውበው በማኅበረሰቡ ዘንድ መገኘት እንዳለባቸው ያውቃሉና እራሳቸውን መንከባከቡ ከቶም አይዘነጉትም። ይህንን ልማዳቸውም ለአመታት ሲገለገሉበት ኖረዋል።
ሜካፕ ዛሬ
ዛሬ ላይ ሁሉም ተቀይሮ የውበት መጠበቂያ ምርቶች በየመንደሩ ሲቸበቸቡ ይውላሉ። እንደ የቆዳ ክሬም፣ የፀጉር ቅባት፣ የሰውነት ሎሽን፣ ሊፒስቲክ፣ የፀጉር ቀለም፣ የጥፍር ቀለም፣ የተለያዩ ብሩሾች እንዲሁም የተለያዩ መዋቢያዎችን ማግኘት ብዙም የሚከብድ አይደለም።
እንደ ትናንቱ ፍራፍሬዎችን ከጥራጥሬዎች ጋር አዋህዶ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን ቀምሞና ቀላቅሎ መጠቀም አይጠበቅም። ዘመኑ የውበት መጠበቂያና ማድመቂያ ምርቶች የሚመረቱበት ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች የሚገኙበት ዋንኛ ሥራቸውም እነዚሁ የውበት መጠበቂያና መዋቢያ ምርቶች እያሻሻሉና እያዘመኑ ማቅረብ ሆኗል። ዛሬ ላይ የውበት መጠበቂያና መዋቢያዎች ለመጠቀም እጅግ በጣም ቀላልና ምቹ ሆነው በሚፈለገው መጠን ይገኛሉ።
የዛሬ ዘመን ሰው መዋብ ከፈለገ የግድ የገፀ ቅብ ባለሙያ መሆን አያስፈልገውም። አካባቢው ካለ አንድ የውበት ሳሎን ጎራ ብሎ የፈቀደውን ዓይነት ውበት በባለሙዎች ታግዞ መላበስ ይችላል። የገፀ ቅብ ባለሙያዎች ወይም ሜካፕ አርቲስቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሙያውን ተክነውበት ከዘመኑ ጋር የተሻሻሉ የስነ ውበት ሙያ አጋዥ መሣሪያዎች ተጠቅመው እጅን በአፍ የሚያስጭን ውበትን መፍጠርም ችለዋል።
በዘመናችን በባለሙያዎቹ የሚከወነው ሜካፕ ለእያንዳንዱ ውበት የተመጠነና በጥናት የተረጋገጠ በልምድም የዳበረ ውበትን ያላብሳሉ። የፊት ቅርፅ፣ የቆዳ ቀለም፣ የቆዳው ወዛማነት አልያም ደረቅነት መሠረት ያደረጉ መዋቢያዎችም በርክተዋል። በየ ኮስሞቲክስ መሸጫና ሱቆች ውስጥ የውበት መጠበቂያና ማድመቂያ ምርቶች በስፋት ማግኘትም ቀሏል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም