አዲስ አበባ፡- በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ባህላቸውን በመለዋወጥ ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ እንደሚረዳ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት «ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት» በሚል መሪ ቃል በአርባ ምንጭ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አከባበርን በተመለከተ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገመንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ ባንቺይርጋ መለሰ ትናት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፤ የበዓሉ በየዓመቱ መከበር ለአሁኑና ወደፊቱ ትውልድ ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር የጎላ ሚና አለው። በበዓሉ ላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባህላቸውን በመለዋወጥ ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያደርጋል ብለዋል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የፌዴራል ሥርዓቱን ለሚያጠናከር የወል ትርክት እንዲጎለብት ይረዳል ያሉት ወይዘሮ ባንቺርጋ፤ ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን የምናጠናክርበት ነው። ሰላማችን የምናጸናበት፣ አንድነታችን ሥር እንዲሰድ የምንተጋበት ነው፤ ለዚህ ደግሞ የበዓሉ መከበር ዴሞክራሲያያዊ አንድነትን ለማጠናከር ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ ሲከበር ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ የፌዴራልዝምና የሕገ መንግሥት አስተምሮ ሥራ ይሠራል ያሉት ወይዘሮ ባንቺይርጋ፤ የሰላማዊ ትግል መገለጫ የሆነውን የመመካከር፣ የመደጋገፍ፣ በሃሳብ ልዕልና የመወያየትና መደማመጥ እንዲዳብር በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም አውዶች አሸናፊ እንድትሆን የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመው፤ በዓሉ መግባባትን ባህሉ ያደረገ ህብረተሰብ ለመገንባት ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል
እንደ ጸሃፊዋ ገለጻ፤ በዓሉ ቀጣይነት ያለው ሠላም እንዲኖርና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቶች እንዲፋጠኑ ይረዳል። በ19ኛው በዓል ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕብረ ብሔራዊ አንድነታችን ዐሻራ ማሳያ በመሆኑ ለግድቡ የሚደረገውን ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ይሆናል። ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ ለማሻገር ህብረብሔራዊነት የሚኖረውን ዋጋ ማስገንዘብና የአብሮነት እሴቶች እያደጉ እንዲሄዱ የሚያስችል ተግባራት ይከናወናል።
ባለፉት 18 ዓመታት በዓሉ ሲከበር በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት ጸሐፊዋ፤ ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እንዲያፀኑ፣ በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አስችሏል። እንዲሁም የርስ በዕርስ ትውውቅና የባህል ልውውጥ መድረክ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት።
የክልሎች መሠረተ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ፤ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍፃሜ ለማድረስ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር የላቀ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።
እንደ ጸሐፊዋ ገለጻ፤ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል በብዝኃነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር በማድረግ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት ከበዓሉ የሚጠበቅ ውጤት ነው። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችና ትስስርና አንድነት የሚያጠናክሩ እንዲሁም የብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቱባ ባህሎቻቸውና መልካም እሴቶቻቸውን የሚያስተዋቁበት መድረክ እንደሚፈጠርም ጠቅሰዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት አርባ ምንጭ ከተማ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚዘጋጁ ሁነቶች የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥቷቸዋል። በዚህ መሠረት ህዳር 25 ቀን የወንድማማችነት፣ ህዳር 26 ቀን የአብሮነት፣ ህዳር 27 ቀን የደቡብ ኢትዮጵያ፣ ህዳር 28 ቀን የምክክር፣ ህዳር 29 ቀን፣ የኢትዮጵያውያን ቀን ተብለው መሰየማቸው ታውቋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም