ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የህክምና መሣሪያዎችን ለሆስፒታሎች አስረከቡ

አዲስ አበባ፡- ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው 41 የአእምሮ ሁኔታን በተለይም የሚጥል በሽታ ለመለየት እና ለመመርመር የሚያስችሉ የህክምና መሣሪያዎችን ለሆስፒታሎች በስጦታ ለግሰዋል።

የህክምና መሣሪያዎቹን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኙ ሰባት ሆስፒታሎች በስጦታ መለገሳቸው ተገልጿል።

ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የተለያዩ ሆስፒታል ዳይሬክተሮች በተገኙበት በትናትናው ዕለት 41 የአእምሮ ሁኔታን በተለይም የሚጥል በሽታ ለመለየት እና ለመመርመር በተጨማሪም ሌሎች የአእምሮ ችግሮችን ለመመርመር የሚያስችሉ የህክምና መሣሪያ ናቸው በስጦታ የተበረከቱት።

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከሚሠራቸው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ የአእምሮ ጤና ግንዛቤ ማሳደግ፣ ጥራቱንና ተደራሽነቱን የጠበቀ የህክምና እና ክብካቤ አገልግሎት እንዲሰጥ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ መሆኑም ተመላክቷል።

ጽህፈት ቤቱ የአእምሮ ጤና ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን በመሠራት ላይ መሆኑንና ከዚህ በፊትም ለአማኑኤል የአእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ለጎንደር ሆስፒታል የህክምና መሣሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉን የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You