አሸባሪው ትህነግ በደርግ ውስጣዊ ድክመትና በዓለም የፖለቲካ አሰላለፍ ለውጥ በለስ ቀንቶት አራት ኪሎ የገባው በትግራይ ሕዝብ ሁለንተናዊ ትግል ነው። ቡድኑ የተረከበውን በትረ- መንግሥት አስጠብቆ በቆየባቸው አመታትም ሰርቀው የማይጠግቡት አመራሮቹ ሕይወት ተቀይራል።
ይሁንና በመርዘኛ የውሸት ንቃተ ህሊና መመሪያ፣ ሕጎችን እና ሂደቶችን በመታለል ቡድኑን አራት ኪሎ ለማስገባት በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆቻቸውን ሳይቀር የገበሩት የትግራይ እናቶች ሕይወት አልተለወጠም።
የሚያስገርመው ግን ዘመን ያላስተማራቸው፣ ስልጣን ያልገራቸው የቡድኑ አመራሮች ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ከሥልጣን ሲባረሩም መጠጊያ የሆናቸው የትግራይ ሕዝብ ነው። አመራሮቹ ወደ መቀሌ ከፈረጠጡና በወንጀላቸው ተፈልገው ለፈጸሙት ጥፋት ዋጋ ለመክፈል ሲቃረቡ ትዝ ያላቸው የትግራይ ሕዝብ ነው።
የቡድኑ አመራሮች ዓይናቸውን በጨው አጥበው መቀሌ ከመሸጉ በኋላም ፍርፋሪ እየወረወሩ ያሰማራቸው ባንዳ ደጋፊዎቻቸው በትግራይ ሕዝብ ስም እያጭበረበሩ ሕዝቡ የአገዛዙ ጭፍን ደጋፊና የሥርዓቱ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርገው በተደጋጋሚ ሲነግሩን ቆይተዋል።
በኢትዮጵያዊነት የሚያምን፣ ከጥንት ጀምሮ ለአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር የላቀ ዋጋ እየከፈለ የኖረ እና ምን ጊዜ ቢሆን ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ የማያውቀውን የትግራይ ሕዝብ፣ ከሚወዳት አገሩ ጋር እንዲኳረፍ ብዙ ደክመዋል።
የትግራይን ሕዝብ የውስጥ ቅኝ አገዛዝ ወይንም internal colonialism ስር በማስገባት የፈለጉትን ኢትዮጵያን የማፍረስ ፍላጎት ለማስፈፅም ብዙ ድንጋይ ሲፈነቅሉም ከርመዋል። በመጨረሻም የሥልጣን አባዜ በሚያመጣው እብደት «ከእኛ በላይ ላሳር» በሚል ትእቢት ተወጥረው፣ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነትን ከፍተዋል።
የሚሠጠውን ሰላም አማራጭ እና የሚከፈትለትን የሰላም በር በመዝጋት የኃይል የበላይነት አለኝ ብሎ ባመነበት ጊዜ ሁሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ ጦርነት የሚከፍተው ትህነግ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያለውን አላማ ለማስፈፀም ነፍስ ያለው ሁሉ እንዲታጠቅና እንዲሞትለት የክተት አዋጅ በመለፈፍ ሰላም ሳይሆን ጦርነት እና ጦርነት ብቻ ፍላጎቱ መሆኑንም በተደጋጋሚ አስመስክሯል።
ጦርነት መሄድ አለመሄድ የግል ምርጫ ነው። ለጦርነት አልወጣህም ተብሎ ወላጅን ማሰር ግን በዓለም ታሪክ ታይቶ የሚታወቅ አይደለም። ሕወሓት በአንፃሩ ቢያንስ ከቤተሰብ አንድ ሰው ወደ ጦርነት መላክ አለበት የሚል ሕግ በማውጣት፣ ለዓላማው የማይተባበሩትን እስከ ማሰር እና እስከ መረሸን መሸጋገሩን ሰምተናል።
ብቻዬን አልሞትም በሚል ስሌት በእናት ማህጸን ውስጥ የሚገኝ ጽንስ እስኪቀረው ድረስ ለስክሪፕቶና እርሳስ ያልጠነከረን እጅ ክላሽ እንዲጨብጥ በማድረግ በአዶልፍ ሂትለር ዘመን የመጨረሻዎቹ ወራት እንደሆነው በሰው ጎርፍ በሕፃናት ማዕበል ጦርነትን ለመሸነፍ ሲጋጋጥም ከርሟል። በሀሽሽ የናወዙ የትግራይ ሕፃናትና አዛውንቶች ጥይት ወደሚጮኽበት፡ የመትረየስ ላንቃዎች ወደሚያስካኩበት ጦርነት በደመነፍስ በማግተልተል የእሳት እራት አድርጓል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአንፃሩ የትግራይ ሕዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስና አስፈላጊው ሰብዓዊ እርዳታና መሠረታዊ አገልግሎቶች ማግኘት እንዲችል፤ አያሌ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ከጦርነት ይልቅ ሰላም ይሻላል ከጦርነት የሚያተርፍ የለም በሚል ለሰላም እጁን እስከመዘርጋትም ተሻግሯል።
ይሁንና እብሪተኛው ቡድን ለሰላም ሲለመን፤ ጦርነት ይብቃ ሰላም ይሻላል የሚለውን የመንግሥት ተማፅኖ ረግጦ ከሰላም ዘንባባ ይልቅ ጥይት ማወዛወዝን ምርጫው አድርጓል። በዚህ ተግባሩም ከማንም በላይ ለትግራይ ሕዝብ ምጽዓት ይዞ የመጣ ታላቅ መርገምት መሆኑን በሚያስመሰክር መልኩ ዳግም ጦርነት ከፍቷል።
ቡድኑ በእብሪተኝነት ስሜት ተወጥሮ በለኮሰው እሳት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያዊ ጥምር ጦር ራሱ መለብለብ ጀምሯል። ምንም እንኳን አንዳንድ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የቡድኑን እስትንፋስ ለማስረዘም የሰላም አምባሳደር መስለው እዚህም እዚያም እየተራወጡ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ትህነግ ወደላይም ሆነ ወደጎን መሄድ አይችልም። አሁን ላይ የቡድኑ ፀሐይ እየጠለቀች ነው።
አሸባሪው ትህነግ በታሪክ ገጽ ላይ ከጥቁር ገጽታው ጋር ተከትቦ የሚሰናበትበት ዋዜማ ላይ ደርሷል። የተነቃነቀ ጥርስ እንዲሉ በቅርቡ መውለቁ አይቀርም። ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ እንደተወገደው ሁሉ ከትግራይ ምድርም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊሰናበትና ከእነቆሻሻ ስብዕና ታሪክ ሆኖ ግብዓተ መሬቱ ሊፈፀም ተቃርቧል።
በቡድኑ ተደጋጋሚ እብሪት ያልተገባ መስዋትነት የሚከፍለው የትግራይ ሕዝብ፣ ከዚህ እኩይ ስብስብ ለአንዴና እና ለመጨረሻ ጊዜ መለያየት የሚችልበት ትክክለኛ ጊዜም አሁን ነው። ከሁሉ በላይ የትግራይ ሕዝብ ከትህነግ ቀንበር ለመፈታት የአስተሳሰብ ባርነቱን ማስወገድ አለበት።
የአስተሳሰብ ለውጥ ከሌለ ችግሩን ለመፍታትም ሆነ ከችግሩ ለማምለጥ አይቻልም። ሳይንቲስትና ፈላስፋ አልበርት አይንስታይን ‹‹ we cannot solve our problems with the same thinking we used when we created them›› እንደሚለው ማለት ነው።
በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ በሚል ዘግይቶም ቢሆን ከነባራዊው እውነታ ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ የአፓርታይዱን ቡድን የሚሸሹና የሚቃወሙ የትግራይ ልጆችን እየተመለከትን እንገኛለን።
አፈናና ጭቆናው አንገሽግሹአቸው ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በጎራባች ክልሎች የተጠለሉና በዳግም ጦርነቱ ተማርከው ለኢትዮጵያ ጥምር ጦር እጃቸውን የሠጡ የትግራይ ልጆችም ቡድኑ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጠላት አድርጎ ጥላቻ ቢሰብካቸውም ሕዝቡ በፍቅር ተቀብሎ እያስተናገዳቸው እንደሆነና ጠላታቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ለስልጣን ጥሙ ግፍና መከራ የሚፈጽምባቸው ትህነግ እንደሆነም እያረጋገጡ ናቸው።
የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የመቆራረጫው ጊዜው አሁን ነው። ተባበረው ይህን የሽብር ቡድን አንኮታኩቶ የመጣል ጊዜው ነገ ሳይሆን ዛሬ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ግድ ይለዋል። ቡድኑ ከሚነዛው ጠባብ መንደርተኛ አስተሳሰብና ጨለምተኛነት ራሱን አፅድቶ፣ ወዳጅና ጠላቱን ለይቶ፣ ጥንካሬና ድክመቱን መዝኖ ከትናንት ስህተቱ መማር ይኖርበታል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም