በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅ በሆነው የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሶስቱ ምርጥ ተጫዋቾች በነበራቸው ፉክከር የስፖርቱን ዓለም ይበልጥ አድምቀውት ቆይተዋል። የሜዳ ቴኒስ ስፖርት የምንጊዜም ኮከብ ተጫዋቹ ሮጀር ፌደረር፣ ራፋኤል ናዳል እና ኖቫክ ጆኮቪች። ከዚህ በኋላ ግን በእነዚህ ኮከቦች አጓጊ የውድድር ዓለም ውስጥ የስፖርት ቤተሰቡ አንዱን እንቁ የሚመለከተው አይሆንም። ምክንያቱ ደግሞ ከሰሞኑ ከተሰሙ የስፖርቱ አለም ከዋክብት ስንብቶች መካከል አንዱ የሜዳ ቴኒስ ኮከቡ ሮጀር ፌደረር ራሱን በቅርቡ ከውድድር እንደሚያርቅ በይፋ በመናገሩ ነው።
የስፖርቱ ዓለም ከዋክብት ለዓመታት ተወዳጅነትን ከተቀዳጁበትና የስፖርት ቤተሰቡን ሲያስፈነድቁ ከቆዩበት ውድድር ራሳቸውን የማግለላቸው ዜና ሲነገር ለደጋፊዎቻቸው አስደንጋጭም አሳዛኝም ነው። ጥቂቶች በጉዳትና ሌሎች የጤና እክሎች ምክንያት ስፖርተኝነታቸው እስከወዲያኛው ሲገታ ሌሎች ደግሞ በዕድሜያቸው ምክንያት ውድድር በቃኝ ይላሉ። የሜዳ ቴኒስ ፈርጡም ፌደረር ከእንግዲህ ይብቃኝ ብሎ ራኬቱን ለመስቀል ወስኗል። የፌደረርን ስንብት ተከትሎም ተቀናቃኙ ራፋኤል ናዳል ‹‹ጓደኛዬና ተፎካካሪዬ፤ ይህ ቀን መቼም ባይመጣ ምኞቴ ነበር፤ ምክንያቱም ይህ ዜና ለእኔ እና ለስፖርት ቤተሰቡ አሳዛኝ ነው›› ሲል ስሜቱን ገልጿል።
ይህ የሜዳ ቴኒስ ቁንጮ ስፖርተኛ ከስፖርቱ ዓለም ለመራቅ መወሰኑን ተከትሎ በርካቶች በቀሪ የህይወት ዘመኑ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥመው ምኞታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። እኛም የሮጀር ፌደረርን የስፖርት ህይወት በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ከብዙ በጥቂቱ ልንዳስሰው ወደድን።
ፌደረር በስዊዘርላንድ ባዜል በተባለ ስፍራ እአአ 1981 የተወለደ ሲሆን፤ ለወላጆቹ ሁለተኛውና የመጨረሻው ልጅ ነው። እንደበርካቶቹ ታዳጊዎች በተወለደበት አካባቢ የሜዳ ቴኒስ ስፖርት ኳስ አቀባይ ሆኖ ነው ያደገው። በልጅነቱ ይበልጥ የሚወደውና የሚያዘወትረው የእግር ኳስ፣ ባድሜንተን እና የቅርጫት ኳስ ስፖርቶችን ይሁን እንጂ፤ መክሊቱ ያለው በሜዳ ቴኒስ ስፖርት በመሆኑ አካሉ በቅጡ ሳይጠና ከራኬት ጋር ከመተዋወቅ አልፎ ውድድሮችን ወደማድረግ ተሸጋግሯል።
እአአ በ1996 ፌደረር በ14 ዓመቱ የታዳጊዎች ውድድር ላይ ተሳታፊ በመሆን ተስፋውን ያሳየ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በታዳጊዎች ዘርፍ የዓለም ቁጥር አንድ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል። ይህ ብቃቱ ቀስ በቀስ ወደ ፕሮፌሽናል ተወዳዳሪነት በማደግ እአአ በ2003 የዌምብልደን ግራንድ ስላም አሸናፊ በመሆን የስፖርቱን ዓለም ከፍተኛ ስኬት ሊቀላቀል ችሏል። በዚያው ዓመት በተካሄደው የቱር ውድድር ላይም ሰባቱን ተከታታይ ውድድሮች አሸናፊ በመሆን ስኬታማነቱን ይበልጥ ማንጸባረቅ ችሏል።
ቀጣዩ ዓመትም በቴኒስ የዓለም ቀዳሚ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ መሆን የቻለበት ነው። በአንድ የውድድር ዓመት ሶስት ግራንድ ስላም ውድድሮችን በማሸነፍ ክብረ ወሰኑን ከማትስ ዊላንደር (አአአ 1988) መጋራት ችሏል። ይኸውም ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሮፌሽናል የሜዳ ቴኒስ ውድድር የዓለም ቁጥር አንዱ ተጫዋች እንዲሆን አድርጎታል። እአአ 2005 የዌምብልደን እና ዩኤስ ኦፕን አሸናፊ ቢሆንም በሌሎች ሁለት የግራንድ ስላም ውድድሮች ግን ድል ሊቀናው አልቻለም ነበር። ቀጣዮቹ ዓመታትም በተለመደው ሁኔታ በስኬትና በጠንካራ ተፎካካሪነት አለፉ።
እአአ 2008 ግን ፌደረር ካለፉት ጊዜያት ይልቅ በጉዳት የተፈተነበት እንዲሁም የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በጥንድ ያሸነፈበት ዓመት ሆኖለታል። በውድድር ዓመቱ አጋማሽ የገጠመው የጉሮሮ ህመም ለተወሰኑ ውድድሮች መሰናክል ሆኖበታል፣ በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ ጀርባው ላይ ጉዳት አስተናግዶ ነበር። እንደዛም ሆኖ ግን የዩኤስ ኦፕን ግራንድ ስላም እንዲሁም በኦሊምፒክ የጥንድ ውድድር አሸናፊ በመሆን ዓመቱን በስኬት አጠናቋል። እአአ የ2012 ኦሊምፒክ በግል የብር ሜዳሊያውን አጥልቋል።
በጉልበት ጉዳት ምክንያት ያለፉትን ሶስት ዓመታት አስቸጋሪ ጊዜያትን ያሳለፈው ፌደረር፤ በውድድር ህይወቱ 6 የአውስትራሊያ ኦፕን፣ 1 የፈረንሳይ ኦፕን፣ 8 ዌምብልደን እንዲሁም 5 ዩኤስ ኦፕን ክብሮችን ማጣጣም የቻለ ስኬታማ ተጫዋች ነው። በዓለም የሜዳ ቴኒስ ፌዴሬሽን ለ310 ተከታታይ ሳምንታት የዓለም ቁጥር አንድ ተጫዋች ሆኖ የቆየው ፌደረር፤ ከእነዚህ መካከል በ237 ለተከታታ ሳምንታት ነበር የበላነቱን መያዙ በክብረወሰንነት የተመዘገበለት።
ፌደረር ከቀናት በፊት እነዚህን ታላላቅ ክብሮች ይዞ ከውድድር ገለል እንደሚል አውጇል። ‹‹ያለፉት ሶስት ዓመታት በጉዳት ምክንያት የተፈተንኩባቸው ናቸው። ወደ ውድድር ለመመለስም ጠንክሬ ስሰራ ቆይቻለሁ። ነገር ግን ሰውነቴ እያስተላለፈልኝ ያለው መልዕክት ግልጽ ነው። አሁን 41 ዓመቴ ነው፤ ከእነዚህ ውስጥ ያለፉትን 24 ዓመታት 1ሺ500 ጨዋታዎች አድርጌያለሁ። ቴኒስ አልመው ከነበረው የበለጠ ነገርን አድርጎልኛል፤ ይሁንና አሁን የተወዳዳሪነት ጊዜዬ የተጠናቀቀ ይመስለኛል። በእርግጥ በርካታ የቴኒስ ውድድሮችን በቀጣይ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን የቱር እና የግራንድ ስላም ደረጃ ያላቸው ታላላቅ ውድድሮች ላይ አልሳተፍም›› በማለት ስንብቱን በትዊተር ገጹ ላይ በመለጠፍ ለስፖርት ቤተሰቡ አስታውቋል። በዚህ ሳምንት የሚደረገው የላቨር ካፕም የመሰናበቻ ውድድሩ እንደሚሆንም ገልጿል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2015