“የማን ነው እንዲህ እየፈረሰ ያለው ? በጥይት በሏቸው።
“እሺ እሺ ! እየተጠራቀመ ነው ። እዛ ያለው የኔ ፣ ያንተና የሌሎች ነው “
“ቢሆንም በሉት ። ትግራዋይ የሆነ ሁሉ ለትግራይ የማይወድቅ ከሆነ በጥይት በሉት”
“ተቀብለናል ። 65 እየሰማህ ነው? “
“65 እያዳመጥከኝ ነው? “
“አቤት “
“ትግራዋይ ሁኖ ለትግራይ የማይወድቅ ካለ በሉት በጥይት “
“እሺ”
“በጥይት በሉት ! ይሄ ይሉኝታ አያስፈልገውም፤ ሞት ፈርቶ ነው እየለቀቀ ያለው፤ ሞት እዚህም እንዳለ አሳዩት “
“እሺ”
“እየወረዱ ያሉትን በጥይት በሏቸው”
“እንመልሳቸዋለን “
“ዝም ብለህ በላቸው እያልኩህ ነው “
“ሁሉም ነው እየፈረሰ ያለው እኮ‼”
“ነገር ተበላሽቷል‼”
ይህ በሕወሓት ጦር ከፍተኛ አዛዥና በበታች አዛዦች መካከል በትግሬኛ የተደረገ የሬዲዮ መገናኛ ምልልስ ሰሞኑን ከውጡ አስደንጋጭ የሕወሓት ገመናዎች አንዱ ነው ። በኢቲቪም “ስለሀገር” ላይ በማህበራዊ ሚዲያውም ሲዘዋወር ስመለከት ማመን ነው ያቃተኝ ።
ከፍተኛ አዛዡ ብርጋዴር ጀነራል ተክላይ አሸብር/ወዲ አሸብር/ሽብርተኛው ሕወሓት ከትግራዋይ ጉያ ነጥቆ ያለበቂ ስልጠናና መሳሪያ የማገዳቸውንም ሆነ ፤ በቂ ስልጠና ወስደውና በታሪካዊ ጠላቶቻችንና ለ27 አመታት የዘረፈውንና የቀበረውን መሳሪያ እስካፍንጫቸው የታጠቁ የልዩ ኃይሉና የኮማንዶ አባላቱ የጀግናውን ጥምር ኃይል ምት መቋቋም ተስኗቸው ሲፈርሱ ፣ ሲሸሹና ሲያፈገፍጉ ነው እንግዲህ ባልተወለደ አንጀቱ በጥይት ቁሏቸው ! አርግፏቸው ! የሚለው ። ይሄኔ የእሱ ልጆችና ሚስቶች ከሀገር በተዘረፈና በሸሸ ዶላር በአሜሪካና በአውሮፓ ውድ ትምህርት ቤቶች እየተማሩ ፣ የተቀናጣ ኑሮ እየመሩ ነው የሚሆነው ። ይህንን የምትሰማ ትግራዋይ ሆይ ! ሕወሓት ከዚህ በላይ ምን እንዲያደርግህ ነው !? በፍርሀት ቆፈን ተይዘህ ዛሬም ዝም የምትለው !? በተለይ ተምሬያለሁ ፊደል ቆጥሬያለሁ የምትለውስ ነገ ትውልድም ታሪክም ሲጠይቅህ ምን ልትመልስ ነው !?
ይህ “በሏቸው!”ትግራዋይን የወላድ መካን ፣ ጧሪና ቀባሪ አልባ ካደረጉ ቁንጮ አሸባሪዎች አንዱ ነው ። የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ምክትል የነበር ሲሆን ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አኩርፈው ከሀገር ይልቅ የግል ጥቅማቸውንና ስልጣናቸውን አስቀድመው ፤ በቀቢጸ ተስፋ፣ በሴራም ፣በደባም፣ በጦርም ብለን ተመልሰን እንገዛለን ብለው በመማጸኛ ከተማቸው መቀሌ ከመሸጉ በላዔ ሰዕቦች አንዱ ነው ። በነገራችን ላይ የሕወሓት ገዢዎች ድምጽ ሳያሰሙ ፣ ጭራቸውን ቆልፈው ተያይዘው መቀሌ የገቡት ተመልሰው ገዥ እንደሚሆኑ እርግጠኛ ስለነበሩ ነው ።
ጦርነቱ ከሚካሄድበት ግንባር በ50 ፣ በ100ና ከዚያ በላይ ኪሜ ርቆ ምን አልባትም መቀሌ ሆኖ ያለሀፍረት በጭካኔ”…ትግራዋይ የሆነ ሁሉ ለትግራይ የማይወድቅ ከሆነ በጥይት በሉት …”ሲል በሰው ልጅ ህይወት ሞት ይፈርዳል ። የሚገርመውና የሚያሳዝነው አይደለም የአሁኑ ጦርነት ለ17 አመታት ከደረግ ጋር የተካሄደውና በመቶ ሺዎች የሞቱለትና የቆሰሉለት ጦርነት አንድን ቤተሰባዊ ቡድን ወደ አገዛዝ ለማምጣትና ለማበልጸግ እንጂ ለትግራይ ሕዝብ ነጻነትና ተጠቃሚነት አለመሆኑን ለ27 አገዛዝ ላይ እያለ አረጋግጦልናል ። የትግራይን ሕዝብ በስሙ እየማለና እየተገዘተ ከተረጅነት ፣ ከድህነት ፣ ከርሀብና ከቸነፈር አላወጣውም ።
የሞኝ ዘፈን ሁል ጊዜ አበባየሁሽ እንዲሉ ፤ ለማይረካው የስልጣን ጥሙ ፣ ለማይጠረቃው ከርሱና ለ27 አመታት በፈጸመው ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና ዘረፋ ከተጠያቂነት ለማምለጥ እና የጋላቢዎቹንና የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ተልዕኮ ለማስፈጸም የቀሰቀሰውን ጦርነት ለትግራዋይ ስል ነው በማለት ማደናገርን ቀጥሎበታል ።የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢ ሙሉቀን ታደገ በዚያ ሰሞን ከወልቃይት ግንባር ባጠናቀረው ዜና ማየት የተሳናቸውን አዛውንት ፣ መነኩሴ ፣ ህጻናትንና አዛውንቶችን ቦምብ አስታጥቆ ከፊት ለጥይት ማብረጃ እንዲሆኑ እየማገዳቸው እንደሆነ እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎችን ዋቢ አድርጎና በፎቶ አስደግፎ አስመልክቶናል ።
ዘጋቢው ካነጋገራቸው ምርኮኞች መካከል እማሆይ ማይጠምቱ አንዷ ሲሆኑ የ75 ዓመት መነኩሲት ፤ እንደማንኛውም መነኩሴ የጸሎት ማድረሻ መቁጠሪያ አንገታቸው ላይ ያደረጉ ፤ የምንኩስና ቆብም የደፉ ናቸው። የሽብር ቡድኑ ቦምብ አሸክሞ የላካቸው ሌላው የ72 ዓመቱ አዛውንት አቶ ተክለሃይማኖት ተስፋዬ ደግሞ አይነ ስውር ናቸው ። ደም ምሱ ፣ ነውር ጌጡ የሆነው ሽብርተኛው ህወሓት አይነስውር አረጋውያንን በ7ና በ8 አመት ህጻናት እያስመራ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚወስድ ፤ በተፋፋመ ውጊያ መሐል እነሱን ማግዶና ተገን አድርጎ እሱ ከኋላ ይከተላል ። ባልበላ ጎናቸው ፣ በእርጅና በደከመ ጉልበታቸው አጓጉዞ የእሳት ራት ያደርጋቸዋል ።
ህይወታቸውን እንዲገብሩለት ለሚያሰልፋቸው አረጋውያንና ህጻናት እንኳ በስማቸው የቀላወጠውን የእርዳት እህል ሰጥቷቸው እንደማያውቅ ላነጋገራቸው ጋዜጠኛ ምንም ሳይደብቅ ነግረውታል ። ወጣቱን ፣ ጎልማሳውን ጨርሶ ህጻናትንና አረጋውያንን እየማገደ ትውልዶችን እየፈጀ ፤ ክልሉን የመናፍስት ክልል እያደረገው ይገኛል ። ታዲያ ትግራዋይ ከሕወሓት በላይ ምን ጠላት አላቸውና ነው አፈሙዝ የማያዞርበት !? በቃህ የማይሉት !? አሽቀንጥረው የማይጥሉት !?
አሸባሪው ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ታሪክም ትውልድም ይቅር የማይሉት ክህደት በመፈጸም የሰሜን ዕዝን በማጥቃት ትጥቁንና ስንቁን ከመዝረፍ ባሻገር በሺህ የሚቆጠሩ የሰሜን ዕዝ አባላትን በመጨፍጨፉና በማጥቃቱ አገራችን ተገዳ ወደ ጦርነት ገብታለች ። እፉኝቱ አሸባሪው ሕወሓት በሕዝባዊ ተቃውሞና በኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠሩ የለውጥ ኃይል የተናበበና የተንሰላሰለ ትግል ኢ-ፍትሐዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ከነበረው ከማዕከላዊ መንግሥት አገዛዙ ሲነሳና በልክህ ሁን ሲባል በእኩልነትና በፍትሐዊነት ላይ አኩሩፎ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ በመመሸግ ዕቅድ “ለ”ውን ከመሳቢያው አቧራውን አራግፎ በመሳብ እንደ አፄ ልብነ ድንግል መሬትን 40 እየገረፈ ጦር አውርድ እያለ የጦርነት ነጋሪቱን መጎሰም ጀመረ ።
በዚህም ብዙዎች አለቁ ። ዳግም አብረን የማንኖር እስኪመስል በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ሰቆቃና ግፍ ፈጸመ ። በሀገርና በሕዝብ ሀብት ላይ ሰፊ ዘረፋና ውድመት አደረሰ ። ይህ አልበቃ ብሎት 3ኛ ወረራ ፈጽሙ ትግራዋይን በፕሮፓጋንዳም በግዳጅም እየማገደ ፤ የአማራና የአፋርን ንጹሐን በከባድ መሳሪያ እየፈጀ ይገኛል ።
በየግንባሮች ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ እንደ ቅጠል የረገፈውን የቆሰለውን ፤ ትግራዋይ ባሰብሁ ባሰላሰልሁ ቁጥር የትግራይን ሕዝብ ምንም እንኳ በሕወሓት የአንድ ለአምስት ጥርነፋ የታፈነ ቢሆንም በቃ ለማለት እንዴት እንጥፍጣፊ ወኔ ያጣል ፤ አብዛኛው የትግራይ ልሒቃንስ ይሄን እልቂት እያየና እየሰማ እንዴት በቃ ማለት ይቅርና ከአመክንዮና ከተጠየቅ በዚህ ደረጃ ወርዶ ከእብሪተኛው ጋር የጦርነት ነጋሪት ይጎስማል ። ሕወሓትን በቃ ለማለትስ ዋጋው ስንት ነው !? በጠላቱ ሕወሓት ላይ አፈሙዝ ለማዞር የአሉላ አባ ነጋ ወኔና ጀግንነት እንዴት ስንቅ ሊሆነው አልቻለም !?
የአምስትና የስድስት ዓመታት ሕጻናት ለሌላ ዙር እልቂት እስኪማገዱ !? ወይስ ከመጪው ትውልድ “ተበድሮ” ሕዝባዊ ማዕበል እስኪያስነሳ !? መቼም ምድር ከፍ ሰማይ ዝቅ ቢል እብሪተኛው ሕወሓት ይሄን ጦርነት አያሸንፍም ። ለዛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ የተፋው ጭላጭ እንኳ ማህበራዊ መሠረት የሌለው ሕወሓት። የሚያሳዝነው ነበልባሉን ከስር ከስር በትግራዋይ ብላቴናዎች የሚቆሰቁሰው የሽብር ኃይሉ አመራርም ሆነ ልጆቹና ቤተሰቦቹ ዳር ቆሞ ተመልካች መሆናቸው ነው። ከፍ ብሎ ለማንሳት እንደተሞከረው ፤ ልጆቹና የቅርብ ዘመድ አዝማዶቻቸው በአውሮፓና በአሜሪካ ከሕዝብ በተዘረፈ ሀብት የተቀማጠለ ኑሮ ይመራሉ ። እዚህ ተራው ትግራዋይ እብሪትና ማንአህሎኝነት በፈጠረው ጦርነት በረሃብ በእርዛት ይገረፋል።
የትግራይ ሕዝብ ከአምላኩ፣ ከተቀረው ኢትዮጵያዊና ከኤርትራዊ ወገኑ በጥል ግድግዳ የለየውን የሽብር ኃይል በቃ ብሎ ለመነሳት ምን እንዳያጣ ነው ዝምታን የመረጠ የሚለው ጥያቄ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አእምሮ ይመላለሳል ። ልጆቹን ክብሩን እምነቱን ህልሙን ራዕዩን ወዘተረፈ የነጠቀው ኃይል ምን ከዚህ የከፋና የባሰ ነገር እንዳያመጣበት ነው በቃ ! ለማለት ድፍረት ያጣው !? በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በ30 የዓለም ከተሞች ጣልቃ ገብነትን ሽብርን ውሸትን በቃ ! ሲሉት የከሀዲውና የሽብር ቡድኑ የቅድሚያ ቅድሚያ ገፈት ቀማሽ የሆነው ትግራዋይ በቃ ለማለት ድፍረት ያጣው ምን የከፋ ነገር እንዳይመጣበት ነው ? ለዘመናት በክፉው በደጉው ቀን አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብለህ ተጋብተህና ተዋልደህ ከኖርኽው ከአማራና ከመላው ኢትዮጵያዊና ከኤርትራውያን ጋር እንድትቆራረጥ አደረገህ ።
በየሰዓቱ ጠላት እየቀፈቀፈልህ በጥርጣሬ እንድትተያይ አደረገህ ። በገዛ አገርህ ባይተዋርነት ፣ ባዕዳነት እንዲሰማህና እንድትሸማቀቅ አደረገህ ። በአገርህ በወገንህ ተስፋ እንድትቆርጥ አሴረብህ ። አጥንትህን ከስክሰህ ደምህን አፍስሰህ ባቆምካት አገር ላይ እንድትነሳ ሸፍጥ ሰራብህ ።ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ ብሎ ተማምሎ ማገደህ ። እንግዲህ ምን ቀረኽና ምንስ የባሰ ሊመጣ ነው በቃ ለማለት አንደበትህ የተያዘው !? የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዳግም ጭቆና የማይንበረከክ መሆኑን እና አሸባሪው ሕወሓት ዳግም አይደለም ኢትዮጵያን ትግራይን እንደማይገዛ እያወቅህና ይሄን ኅልቆ መሳፍርት ዋጋ ከከፈልክ በኋላ በቃ ያላልኸው የበቃ ዋጋው ስንት ቢሆን ነው ? በሰሞነኛ ወረራው ደግሞ ጸሎት አድራሽ፣ ፈጣሪን ተለማማኝ ጨርሶ ሊያሳጣህ አይነ ስውራንና መነኩሴዎችን በህጻናት እያስመራ ለእሳት እየማገደ ይገኛል። ትግራዋይ ሆይ እንግዲህ ምን ቀረህ !?
የትግራይ ሕዝብ ሆይ ! ዛሬም በቃ ! ለማለት አረፈደምና ንቃ ! ተደራጅ ! ተነስ ! በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች የምትኖር ትግራዋይ ሆይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን ቆመህ ሰንኮፉን የምትነቅልበት ጊዜው አሁን ነውና ሕወሓትን በአንድ ድምጽ በቃ በለው ። እጣ ፈንታህ ከኢትዮጵያና ከሕዝ ጋር እንጂ ነገ የታሪክ አተላ ከሚሆነው አሸባሪ ጋር አይደለም ። በቃህ ! በለው ። አፈሙዝህን አዙርበት ። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም እንደትናንቱ ከጎንህ ነውና ። ለትግራዋይ ህይወት ግድ የሌለው ሕወሓት ለ3ኛ ጊዜ ጦርነት ከፍቶ አሁንም በየግንባሩ እያስጨረሳቸው ይገኛል ። ይህ አልበቃ ብሎት ከጦርነቱ የሚያፈገፍጉትንም በሏቸው እስከማለት ደርሷል ።
ጦርነትን እንደ ጣኦት የሚያመልከው ሽብርተኛው ሕወሓት ፤ ምሱ ደም ነው ። የትግራዋይም ሆነ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ደም የዶሮ ደም ያህል ግድ የማይሰጠው ሕወሓት ከፍጥርጥሩ ጀምሮ ደም እንደጠማው ዛሬ ድረስ አለ ። ይህ የደም ጎርፍ አንድ ቀን ጠራርጎ እንደሚወስደው አያጠያይቅም ። የዘገየ ቢመስልም አይቀርለትም ። ሆኖም ደግሜ ሕወሓትን ትግራዋያንም ሆኑ ኢትዮጵያውያን ስንት ጊዜ ሲሞቱ ነው የሚበቃው ስል እጠይቃለሁ ። ሕወሓትስ መቼም አንድ ትግራዋይ ቢቀረውም በቃኝ አይልምና የትግራይ ሕዝብስ መቼ ነው በቃ የሚለው !?
አሁን ደግሞ ከበባውን እሰብራለሁ ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን በጉልበቴ አስጀምራለሁ እያለ ልጆችህን ለዚህ የጥፋት እብሪት ምስ እያደረገ ነው ። ለ27 አመታት በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የፈጠረው ቁስል ሳይጠግግ በማይካድራ በጋሊኮማና በአጋምሳ በፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ቁስላቸው ሳይሽር በአማራ ክልል በቆቦና አበርገሌ ፤ በአፋር ክልል በያሎ ላይ ዘግናኝ ግፍና ሰቆቃ እየፈጸመ ነው ። በስምህ እየማለና እየተገዘተ የግል ጥቅሙን ሲያሳድድ የኖረ ስብስብ ከፌደራል ስልጣኑ በፈጸመው ሕልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና ዘረፋ ምሬት የተነሳ አላግባብ ይዞት ከነበረ መንበር ሸርተት ሲል ክፉ ሀሳቡን በልቡ ይዞ ወደ መቀሌ መሽጎ ትግራዋይን በማገትና እንደ ሰብዓዊ ጋሻ በመጠቀም ጣዕር ሞቱን ለማራዘም እየተጋጋጠ ይገኛል ።
የሚላክልህን የዕለት ደራሽ እህል ፣ አልሚ ምግብና ነዳጅ ለጦርነት እያዋለ በርሀብ መግደሉ ሳያንስ ልጆችህን ደግሞ ከጉያህ እየነጠቀ በመማገድ ከአንድ ጊዜም ሁለት ጊዜ በላይ ደጋግሞ እየገደለህ ካለው ሽብርተኛ ሕወሓት ውጭ ጠላት የለህምና ተነስ አምጽ ፤ አፈሙዝህን አዙርበትና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትክሻህ አውርደህ ፈጥፍጠው ። እምቢ ! በቃ ! በለው ። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ትላንቱ ከጎንህ ነውና አይዞህ ! በርታ !
በ17 አመቱ የትጥቅ ትግል ከ60ሺህ በላይ ልጆችህን ህይወት ገበርህ ፤ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዘለውና ሩጠው ያልጠገቡ የአብራክህ ክፋዮች አካል ጉዳተኛ ሆነው ያመጡትን “ነጻነት” ከጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር/ደርግ/የከፋ ፈላጭ ቆራጭና አምባገነን በሆነው ህወሓት ተነጠቅህ ። በአንድ ለአምስት ጠርንፎ እርስ በርስህ እንዳትተማመን ፤ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገንህ ጋርም በጥርጣሬ እንድትተያይ ፤ ይህ አልበቃ ብሎት ልጆችህን ትርጉም ለሌለው ለኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግዶ ከሀዘንህ ሳትጽናና ከልህን ሳትቀይር ፤ ሰሜን ዕዝን በመክዳትና በውድቅት ሌሊት በመጨፍጨፍ 50 አመት ባልሞላ ጊዜ ለ3ኛ ጦርነት ማገደህ ።
መንግስት የተናጠል ተኩስ አድርጎ ሲወጣ ለ4ኛ ጊዜ፤ ሰሞኑን ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ የአንተው አልበቃ ብሎ ነፍስ የማያውቁ ህጻናት ልጆችን ከጉያህ እየነጠቀ በሀዘን ላይ ሀዘን እየደረበብህ ፤ የወላድ መካን እያደረገህ ፤ ያለጧሪ ቀባሪ እያስቀረህ ይገኛል ። እንግዲህ ምን ቀረህና ትፈራዋለህ !? ልጆችህን ጨርሶ ወደ አንተ እየመጣ ፤ ትግራይን ምድረ በዳ እያደረጋት ነውና ተነስ በቃህ ! በለው፤ አፈሙዝህን አዙርበት ፤ ከሕወሓት በላይ ሌላ ጠላት የለህምና ።ትግራዋይ ሆይ ትግራይ በሕወሓት ትውልድ አልባ ከመሆኗ በፊት በቃ ! በል ፤
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2015