ኢትዮጵያውያን ውብ ድብልቅ ማንነት ያላቸው ከቀሪው ዓለም የሚለዩዋቸው በርካታ ባህላዊ እሴቶች የያዙ ናቸው። አስተውሎ ሀገሪቱን ለመረዳት የሞከረ ሁሉ በህዝቦች ህብረት፣ አመጋገብ፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል፣ የቋንቋ፣ የአለባበስ፣ አመጋገብ፣ ስራና የተለያዩ የሃዘንና የደስታ ጊዜ ስርአቶቿ እጅግ ማራኪና ከሀገሪቱ ውጪ በሌላ አገር የማይገኙ ናቸው።
የጎዳና ላይ የጥምቀት፣ የጨምበላላ፣ የጊፋታ እና ሌሎችም ልዩ ልዩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርአቶቿ የኢትዮጵያውያንን እኛነት ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ እሴቶቻችን ናቸው። እነዚህን ሃብቶቻችንን ከበርካታ ሺ ዘመናት በላይ ማህበረሰቡ ሳይበረዙና ሳይጠፉ ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገረ እስከ አሁን ማስተላለፍ ችሏል።
በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡት መካከል መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች በድምቀት የሚያከብሯቸው የመስቀል ደመራና የጥምቀት በዓላት የማይዳሰስ ቅርስ ሆነው በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ሀብቶች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።
ሌላው “የኢሬቻ” በአል ነው። ይህ ፈጣሪን የማመስገኛ በዓል ከመላው ዓለም ቱሪስቶች ሊታደሙበት የሚፈልጉት ደማቅ ስነስርዓት ያለው ነው። የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ (ሪፕረዘንታቲቭ ሊስት ኦፍ ዘ ኢንታንጀብል ካልቸር ኦፍ ሒውማኒቲ) ኅዳር 2009 ዓ.ም መስፈሩ ይታወቃል።
ከላይ ካነሳናቸው ሃይማኖታዊና ባህላዊ የማይዳሰሱ ሃብቶቻችን በተጨማሪ በአዲስ ዘመን ማብሰሪያ የመስከረም ወር በድምቀት የሚከበረው የወላይታ ህዝብ ባህላዊ እሴት፣ የመላ ኢትዮጵያውያን ኩራትና ሃብት ምንጭ የሆነው የ”ጊፋታ” የአዲስ ዘመን መለወጫ በአል ነው።
ይህ የዘመን መለወጫ /ጊፋታ/ ዘንድሮ መስከረም 15 ቀን 2015 አም እሁድ ቀን ይከበራል። መላ ኢትዮጵያውያን በወላይታ ዞን እና በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በድምቀት በማክበር ይሳተፍበታል። የዝግጅት ክፍላችንም በዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምዱ ላይ “የወላይታ ብሄር የዘመን መለወጫ ጊፋታ”ን አስመልክቶ የዞኑ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ የባህል የታሪክና ቅርስ ስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ አዳነ አይዛን አነጋግሮ የክብረ በአሉን ስርዓት፣ ምንነት እና አጠቃላይ ባህላዊ ስነስርዓቶችን እንደሚከተለው በዝርዝር ይዞላችሁ ቀርቧል።
የዘመን አቆጣጠር
የወላይታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ (calendar) አለው። በወላይታ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው። የዘመን መለወጫ በዓልን ስናወሳ የዘመን አቆጣጠርን ነጥለን ማየት አንችልም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ የዘመን መለወጫ በዓል መነሻው የዘመን አቆጣጠር ነውና። የዓለም ህዝብ የጊዜ አቆጣጠር ስርዓት የፀሐይ (solar) ጨረቃ (lunar) ወይም ሁለቱንም አንድ ላይ የጨረቃና የፀሐይ (luni-solar) ኡደትን የተከተለ መሆኑ ይታወቃል።
በዚህ ዙሪያ በተደረጉ ጥናቶች እንደተረጋገጠው የወላይታ የዘመን አቆጣጠር በግማሽ ጨረቃና በግማሽ ፀሐይ ኡደት የተከተለ (Lunisolar) ነው። ወላይታዎች ቀኑን (Gallassa) ብለው ሲጠሩ ፀሐይ ስትጠልቅ ወይም ሲመሽ (Qammaa) ብለው ይጠራሉ። ቀንና ሌሊት አንድ ላይ ደግሞ አንድ ቀን (Issi wontta) ይባላል። ይህ አንድ ቀን 11 በሚሆኑ የጊዜ ክፍልፋዮች ይከፈላል። እነሱም፡-
• 11:00- 12:00 Jabbijoora/Daabidaaba/Wonttimaatta ጎህ ሲቀድ
• 12:00- 3:00 Guura-wonttaa ማለዳ
• 3:00- 5:00 Poo’uwa ረፋድ
• 6:00-7:00 Seeta Gallassaa ዕኩለ ቀን
• 7:00-10:00 Gallassaa ከሰዓት በኋላ
• 10:00-12:00 Omarssaa ማምሻ
• 12:00-2:00 Lemm’i lemm”aa/lenkkilenkka ማታ
• 2:00-4:00 Xumaa ምሽት
• 5:00- 7:00 Qammaa እኩለ ሌሊት
• 7:00-9:00 Bilahiyaa ውድቅት ሌሊት
• 9:00- 11:00 Henqeleela Belahiyaa ›› ›› በመባል ይታወቃሉ።
ወላይታዎች ሳምንታትን የሚቆጥሩት በአካባቢው የሚውለውን ትልቁን ገበያ መነሻ በማድረግ ከአንዱ የገበያ ቀን እስከሚቀጥለው የገበያ ቀን ያለውን ጊዜ እንደ አንድ ሳምንት ይቆጥራሉ። ይህም (Naa”u Giyaa) ወይም ሁለት ገበያ ማለት ነዉ። ለምሳሌ፡ – በአንድ አካባቢ የሚውል ትልቁ ገበያ ቅዳሜ ከሆነ እስከሚቀጥለው ቅዳሜ ድረስ ያለውን ጊዜ የመጀመሪያውን ቅዳሜ አንድ ብሎ ቀጥሎ በሳምንቱ የሚመጣውን ቅዳሜ ሁለት በማለት ሁለት ገበያ (Naa”u Giyaa)በማለት ይጠራሉ። በዚህም መሠረት አምስት ገበያ (Ichchashu Giyaa) አንድ ሙሉ የጨረቃ ኡደት አንድ ወር (Issi Aginaa) ይሆናል። ጨረቃዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየችበትን ቀን (Aginiyaa xeeraasu) በማለት አንድ ብሎ መቁጠር ይጀምራሉ።
በማህበረሰቡ ዘንድ ጨረቃ አዲስ ከመታየቷ በፊት ባሉት ሁለት ቀናት ውኃ ውስጥ ትውላለች የሚል እምነት አለ። እነዚህ ቀናት ጤሮ ጨገና (xeero ceggennaa) በመባል ይታወቃሉ። ይህም ህብረተሰቡ የጨረቃን መውጣት በመጠባበቅ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት ነው።
የአባወራዎች ተግባር
የጊፋታ በዓል ዝግጅት የሚጀምረው በቁጠባ (Qoraphphuwaa) ነው።
በጊፋታ ዕለት አባት ልጁን አስከትሎ በሬ ወደሚታረድበት ቤት በመሄድ ያደለቡትን በሬ በጋራ በማረድ በመደብ በመደብ ይከፋፍላሉ። በዚህ ሁኔታ ከሁሉም የሥጋ ብልቶች ትንሽ ትንሽ ቆርጠው በባለተራው ቤት በተዘጋጀው ማባያ ማለትም ቆጮ፣ቂጣ፣ዳታ በርበሬ ጋር ከቅርጫው አባላት (Amuwaa) ጋር ይቋደሳሉ፤ ይህም አንድነትን፣ፍቅር ማብሰሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ከዚያም የየራሳቸዉን ድርሻ ሥጋ ከመውሰዳቸው በፊት ለመጪው ዓመት በሬ መግዣ አሁን በታረደው በሬ ቆዳ ላይ ቁጠባ ይጀምራሉ። ይህም ሥርዓት የጊፋታ በዓል ከተሸኘ በኋላ በየሳምንቱ ይቀጥላል። በመጨረሻም ዓመቱ ሲጠናቀቅ ተሰብስበው በሬ ከገዙ በኋላ የሚተርፈውን ገንዘብ ለቤት ውስጥ ወጪ ይጠቀማሉ።
የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በዘር ወቅት መዝራት፣
መሰብሰብና ለጊፋታ ለይቶ ማስቀመጥ፣ በዓሉ ሲቃረብ ለልጆች አዳዲስ ልብሶችን መግዛት፣ ለማጣፈጫና ለቅመማ ቅመም መግዣ የሚሆን ገንዘብ ለእናቶች መስጠት እና ለጊፋታ የሚታረድ በሬ መግዛት የአባወራ ተግባራት ናቸው። ለእርድ ቀን ከሁለት ወር በላይ የሚሆን ጊዜ ሲቀረው በሬ በመግዛት እስከ እርድ ቀን ድረስ ለሚንከባከብ ተረኛ (Ariyawaa) ይሰጣል። ለበሬው ምቹ ቦታ ቀድሞ በዚህ ቤት እንዲዘጋጅ ይደረጋል።
የጊፋታ በሬ እንደሙሽራ ስለሚታይ ሰው እንዳያየው የተለየ ጋጣ ተዘጋጅቶ ሁሉም ቀዳዳዎች ከምግብ መስጫ ጠባብ በር ውጪ በደረቅ የኮባ ቅጠል (Qonashiyaa) ሙሉ በሙሉ ይሸፈናሉ። የአሙዋ አባላትም ስኳር-ድንች፣የበቆሎ አገዳ፣በቆሎ… በልጆቻቸው እያሸከሙ ወይም በአህያ እየጫኑ በየተራ በማምጣት ይቀልባሉ።
ቀጥሎም በየ15 ቀኑ ተሰብስበው በሬውን ወደ ውጪ በማውጣት ያለበትን ደረጃ በማየት በጣም እየወፈረ ከሆነ ተንከባካቢውን እያሞገሱ አስተያየት ይሰጣሉ፤ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የጊፋታ በሬ ይቀለባል። ሌላው በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከናወን የአካባቢ ጽዳትና የቤት እድሳት ሥራ ነው፤ ይህም በወላይታ ብሔር አዲስ ዓመት የመታደስ ምልክት ስለሆነ ሰዎች የቤታቸውን የሳር ክዳን በአዲስ ሳር መቀየር፣በቤት ውስጥ ያረጁትን ነገሮች ማለትም Qarxxaa, Quruxuwaa, Shakkuwaa, Gaaxaataa, Zazaluwaa, Gophphiyaa, Tuuqiyaa, Dizggiyaa, Kocaa፣Inddaa የመሳሰሉትን ከውጪ ደግሞ በቤቱ ዙሪያና በአካባቢው የሚገኙ ቆሻሻዎችን በማጽዳት በዓሉን ይቀበሉታል።
የእማወራዎች ተግባር
እማወራዎች ለጊፋታ በዓል ከሚያደርጉት ዝግጅቶች የመጀመሪያው ቁጠባ(qoraphphuwaa) ነው፤ ይህም የቅቤ እቁብ መጀመር ነው። በዚህም መሠረት ዓመቱን በሙሉ የቆጠቡትን በጊፋታ ሰሞን ሁለተኛ ሳምንት ገበያ (Bobbooda) አጥቢያ በቅቤ ዕቁብ ሰብሳቢያዋ ቤት የቅቤ ቡና ከጠጡ በኋላ የየድርሻቸውን ተከፋፍለው ይወስዳሉ።
ጊፋታ ካለፈ በኋላም ለቀጣይ ዓመት በየሳምንቱ ቁጠባውን ይቀጥላሉ። እናቶች ከሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ለተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ማለትም ለቆጮ፣ ለሙቹዋና ለባጪራ የሚሆኑ የደረሱ እንሰቶችን ከጓደኞቻቸውና ከሴት ልጆቻቸው ጋር ሆነው በመፋቅ ዝግጅት ያደርጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ ዳታ በርበሬን፣ የተለያዩ መጠጦች ማለትም ቦርዴ፣ጠላ፣ ጠጅ፣ቃረቦ እና ወተት በትልቅ እንስራ ያዘጋጃሉ።
ለ’ጋዚያ” ጨዋታ የሚሆን ሎሚ ገዝተው በቀዝቃዛ ቦታ ያስቀምጣሉ፤ የተለያዩ መዋቢያ ጌጣጌጦችን ይገዛሉ፤ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ የእህል
ዓይነቶችን ገዝተው ያጠራቅማሉ።ምስል–የዳታ በርበሬበጊፋታ የቤተሰብ የስራ ክፍፍል በጣም የጠበቀ በመሆኑ ሁሉም የራሱን ሥራ ያለማንም አዛዥ ወቅቱ ሲደርስ ያከናውናል።
ወጣት ወንዶች የጉሊያ እንጨት ከመቁረጥና ከማቆም ጀምሮ የከብቶችን ሣር በማጨድና በመከመር፣ እንጨት በመፍለጥ ለበዓሉ ጊዜ ከማስቀመጥ በተጨማሪ ከዘር እና ከአጨዳ ወቅት ጀምሮ ሁሉንም የጊፋታ ዝግጅት ሥራዎችን ከአባቶቻቸው ጎን በመሆን ይሠራሉ። ልጃገረዶች እንሶስላ ከመሞቅ፣የጋዚያ ጨዋታ ከመጫወት ከመሳሰሉ በግል ከሚፈጽሟቸዉ ተግባራት በተጨማሪ በሁሉም ሥራዎች እናታቸዉን ይደግፋሉ።
ዕዳ መክፈል
ከጊፋታ በዓል ቅድመ ዝግጅቶች አንዱ ያደረ ዕዳ መክፈል ነው። በወላይታ ብሔር ሰዎች ከዕዳ ጋር አዲሱን ዓመት አይቀበሉም። ምክንያቱም የግለሰብም ሆነ የመንግሥት ዕዳ ተሸክመው አዲሱን ዓመት የሚቀበሉ ከሆነ ዓመቱን በሙሉ በረከት አይኖረውም ተብሎ ይታመናል። በሌላ በኩል ደግሞ እዳውን ለመክፈል ዳተኛ የሆነ ሰው በማበረሰቡ ከፍተኛ ነቀፌታ ይደርስበታል። ስለሆነም አንድ ገንዘብ ወይም እህል ያስፈለገው ሰው ከሌላ ሰው ሲበደር አበዳሪው ይህ ዕዳ እጅግ ቢዘገይ እስከ ጊፋታ በዓል ድረስ እንደሚመለስ በጣም እርግጠኛ ሆኖ የሚበደረው በመሆኑ በብሄሩ ከጊፋታ በፊት ዕዳን አሟጦ መክፈል ነባር ባህል ነው።
የቤት እድሳትና የአካባቢ ጽዳት
የጊፋታ በዓሉ እየተቃረበ ሲመጣ ማህበረሰቡ አዲሱን ዓመት አዲስ ቤት በመሥራት ወይም አሮጌውን ቤት በማደስ መቀበል ነባር ባህሉ ነው፤ በመሆኑም ነባሩን አሮጌ ቤት አፍርሶ አዲስ የሚሠራ ከሆነ በደቦ ወይም በማህበር ያከናውናሉ። ነገር ግን የቤት ዕድሳት ብቻ ከሆነ አባወራው ከቅርብ ጓደኞቹ ወይም ለአቅመ አዳም ከደረሱ ልጆቹ ጋር ያከናውናሉ። በአሮጌው ዓመት ማብቂያ ቤታቸውን፣ ጓሯቸውንና አካባቢያቸውን በማጽዳት በዓሉን በተሟላ ንጽህና ይቀበላሉ።
የመንጻት ሥርዓት
በወላይታ ነባር ባህል የዘመን መለወጫ በዓሉ እንደነገ ሊከበር ማለትም ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ እኩለ ሌሊት ላይ አዲሱን ዓመት ከመቀበላቸዉ በፊት ሁሉም የማህበረሰቡ አባላት ከአሮጌው ዓመት እድፍና ቆሻሻ ጋር አዲሱን ዓመት አንቀበልም” በሚል እምነት ውኃ አሙቀው ገላቸውን ይታጠባሉ። ምክንያቱም ወላይታዎች ሁልጊዜ አዲሱን ዓመት የሚቀበሉት በሽታ፣ረሃብ፣ድርቅ የሌለበት መልካም ዝናብ የሚጥልበት፣መልካም ንፋስ የሚነፍስበት፣የጥጋብ ዓመት እንዲሆን ከአለፈው ዓመት ኃጥያት መንጻት አለብን ብለው ስለሚያምኑ ነው። ለህዝቡ አዲስ ዓመት ሁል ጊዜ አዲስ ተስፋ ይዞ ስለሚመጣ ንጹህ ሆነን መቀበል አለብን የሚል የፀና እምነት አለ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2015