የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ የ15 ጊዜ ቻምፒዮኑ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ፈረሰኞቹ) ከአራት ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ቻምፒዮንስሊግ መድረክ ተመልሰው ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ይታወቃል። በዚህ የአህጉሪቱ ትልቅ የእግር ኳስ መድረክ የሚያደርጉትን ጉዞም ባለፈው መስከረም 01/2015 በድል ጀምረዋል። ፈረሰኞቹ የመጀመሪያውን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ባህርዳር ስቴድየም ላይ አድርገው የሱዳኑን ኃያል ክለብ አል ሂላልን በቸርነት ጉግሳ ሁለት ግቦች ታግዘው 2ለ1 ማሸነፋቸው አይዘነጋም።
ፈረሰኞቹ ነገ ከአል-ሂላል ጋር ላለባቸው የመልስ ጨዋታ ወደ ሱዳን መጓዝ ያለባቸው ቢሆንም ከቀናት በፊት አስቀድመው ለካፍ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል። ፈረሰኞቹ የመልስ ጨዋታቸውን ካርቱም ላይ እንዲያደርጉ ቀጠሮ መያዙ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከጨዋታው አስቀድሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል ለካፍ ደብዳቤ ልከዋል። በደብዳቤው መሠረትም ሱዳን አሁን ካለችበት ወቅታዊ የፀጥታ አለመረጋጋት በመነሳት በአገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ጨዋታውን ሱዳን ላይ ማድረግ ከደህንነት አንፃር ስጋት በመሆኑ ካፍ ጨዋታውን በገለልተኛ ሜዳ እንዲያካሂድ ፈረሰኞቹ ጥያቄ አቅርበዋል።
አል ሂላሎች በተመሳሳይ ባህርዳር ላይ የመጀመሪያውን ጨዋታ ከማድረጋቸው በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ምክንያት በማድረግ ካፍ ጨዋታውን ወደ ገለልተኛ ሜዳ እንዲወስደው ጥያቄ አቅርበው ነበር። ይሁን እንጂ ጥያቄያቸው በካፍ ተቀባይነት አላገኘም።
ፈረሰኞቹ ትናንት ረፋድ ላይ ወደ ካርቱም እንደሚያቀኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ የሚጓዙትን የ20 ተጫዋቾች ዝርዝርም ይፋ አድርገዋል። በዚህም ግብጠባቂ ቻርልስ ሉክዋጎ፣ ባህሩ ነጋሽ፣ ተከላካይ ምኞት ደበበ፣ ኤድዊን ፊሪምፖንግ፣ ሄኖክ አዱኛ፣ አማኑኤል ተርፋ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ደስታ ደሙ፣ ሱሌማን ሐምዲ ናቸው። አማካይ ተጫዋቾች ናትናኤል ዘለቀ፣ ጋቶች ፓኖም፣ በረከት ወልዴ፣ ሀይደር ሸረፋ፣ ዳዊት ተፈራ፣ ቢንያም በላይ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ዳግማዊ አርአያ፣ አብርሀም ጌታቸው ሲሆኑ አጥቂዎች ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ፣ ተገኑ ተሾመ መሆናቸው ታውቋል።
ከስብስቡ ጋር ልምምድ ሲሠሩ የሰነበቱት የተቀሩት አምስት ተጫዋቾች ደግሞ ከሌሎች የዕድሜ ዕርከን ከተውጣጡ ተጫዋቾች ጋር በመጪው ቅዳሜ በሚጀምረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቡድኑን ወክለው የሚሳተፉ ይሆናል።
የሁለቱን ክለቦች የመልስ ጨዋታ ሱማሌያውያን ዳኞች እንደሚመሩት ከቀናት በፊት ይፋ ያደረገው ካፍ ለፈረሰኞቹ ጥያቄም እስከ ትናንት መልስ አለመስጠቱ የፈረሰኞቹን ጥያቄ እንዳልተቀበለ ማረጋገጫ ሆኗል። የአል ሂላል ደጋፊዎች ክለባቸው በባህርዳሩ ጨዋታ መሸነፉን ተከትሎ የተለያዩ ሰበቦችን በመፍጠር ቅሬታዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲያሰራጩና ሲዝቱ ታይተዋል። ይህም የመልሱን ጨዋታ ለፈረሰኞቹ በሁለት መንገዶች ፈተና ሊሆን እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል። አል ሂላል በባህርዳሩ ጨዋታ ቢሸነፍም ፈረሰኞቹ ላይ አንድ ግብ ማስቆጠሩ በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን ቀልብሶ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ተስፋ አለው። ለዚህም በሜዳውና በደጋፊው ፊት ፈረሰኞቹ ላይ እግር ኳሳዊ ያልሆነ ተፅዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ስጋት ሆኗል። ፈረሰኞቹ የሚኖረውን ጫና ተቋቁመው በድምር ውጤት ማሸነፍ ከቻሉም ደጋፊዎች ያልተገባ ሁከት ሊፈጥሩ የሚችሉበት ዕድል ጠባብ አይደለም። ይህ ደግሞ ሱዳን አሁን ካለችበት የፀጥታ ሁኔታ አንፃር ለፈረሰኞቹ ስጋት ሊሆን ይችላል።
የፈረሰኞቹ አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከባርዳሩ ድል በኋላ ‹‹በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ጥሩ ነበርን፤ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ቀላል ስህተት ሠርተን ሁለት ለአንድ አሸንፈናል። ከሞላ ጎደል በጣም ጥሩ ነው ተጫዋቾቼ የሠሩት።» በማለት ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት ሰጥተዋል።
ፈረሰኞቹ በመጨረሻ ሰዓት ግብ ማስተናገዳቸው በመልሱ ጨዋታ ጫና ውስጥ እንዳይገቡ ስጋት ቢፈጥርም ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ዕድል አላቸው። አሰልጣኝ ዘሪሁን ወደ ጨዋታው ሲገቡ ቡድናቸው ግብ እንዳያስተናግድ አስበው እንደነበር ተናግረዋል። ነገር ግን ባለቀ ሰዓት ላይ በትንሽ የመከላከል ቅንጅት በሠሩት ስህተት ግብ አስተናግደዋል። ይህም በመልሱ ጨዋታ ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል አስተያየት ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ይህን ስጋት ለማስቀረት ፈረሰኞቹ ከባህርዳሩ ጨዋታ የተሻለ ነገር ሠርተው በድምር ውጤት ለማሸነፍ እንደሚዘጋጁ አስረድተዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚውን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈም በቀጣዩ ዙር ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስና ከደቡብ ሱዳኑ ዛላን ኤፍሲ ሩምቤክ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።
ውድድሩ ሱዳን ላይ መደረግ አለመደረጉ ዛሬ የሚታወቅ ቢሆንም ካፍ ይህን ተጠባቂ ጨዋታ እንዲመሩ አራት የሶማሊያዊ ዳኞች መመደቡም ይታወቃል። ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንዲመሩ የ29 ዓመቱ ዑማር አብዱልቃድር አርታን የተመረጡ ሲሆን፣ በረዳትነት ዳኝነት ሀምዛ ሀጂ እና ዓሊ መሐመድ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ሀሰን መሐመድ መመደባቸው ታውቋል። የሊቢያ ዜግነት ያላቸው ጋማል ሳሊ በበኩላቸው የጨዋታው ታዛቢ እንደሚሆኑ ካፍ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም