መልክና ቁመናዋን ላስተዋለ እንኳን አልቅሳ ተከፍታ የምታውቅ አትመስልም። በአትኩሮት ላያት ግን ጠይሙ ፊቷ ብዙ የሚናገር ይመስላል። ጥቂት ላሰበ በወይዘሮዋ እርጋታ ውስጥ የተደበቀ ማንነት እንዳለ መገመት አይቸግርም። በየአፍታው በዓይኖቿ የሚመነጨው ትኩሰ ዕንባ በህይወቷ ብዙ መከራ ማለፉን ያሳብቃል። ወይዘሮ መሰረት አርጋው ውልደትና ዕድገቷ አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ተክለሀይማኖት ከሚባል አካባቢ ነው። ኑሮዋን በጎዳና የላስቲክ ጎጆ ከማድርጓ በፊት እሷም እንደሌሎች ግድግዳና የቆርቆሮ ጣራ ከነበረው ቤት ውላ ታድር ነበር። የዛሬን አያድርገውና እንደአሁኑ ጤናዋ ሳይታወክ ህይወቷ በሰላም፣ ፍቷ በፈገግታ የተሞላ ነበር። መሰረት ወላጅ እናቷን በሞት ያጣችው ገና የአንድ ዓመት ህጻን ሳለች ነው። የዛኔ እሷን የማሳደግ ሀላፊነቱ የታጠለው በአክስቷ ትከሻ ሆነ። አክስት የአባቷ ታላቅ እህት ናቸው። የእናቷን መሞት ተከትሎ ከወንድማቸው የተቀበሏትን ህጻን ለማሳደግ በወሰኑ ጊዜ አባት ከስፍራው ርቀው ከዓይን ተሰወሩ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ የመሰረት ወላጅ አባት ልጅ ‹‹አለኝ›› ብለው አልተመለሱም። መሰረት ስለወላጆቿ ስትሰማ ያደገችው አንዳቸው በሞት፣ ሌላቸው በመጥፋት እንደተለይዋት ነው።
አክስቷን እንደእናት አባት ተቀብላ መኖር የጀመረችው ህጻን አንዳች ሳይጎድልባት በፍቅር አደገች። የሙት ልጅ ብትሆንም በቤቱ ያሉ የአክስቷ ልጆች እህት ወንድም ሆኑላት። ልጅነቷን አገባዳ ታዳጊነትን እስክትጀምር ህይወት አልጎረበጣትም፣ ባይተዋርነት፣ ብቸኝነት ይሉት ስሜት አልፈተናትም። የአስራ አራተኛ ዓመት ልደቷን ባከበረች ማግስት የመሰረት ህይወት ከፈተና ሊወድቅ ግድ አለ። በፍቅር ተንከባክበው ከልጆቻቸው ሰይለዩ ያሳደጓት አክስቷ በድንገት አረፉ። ይህኔ ክፉኛ ሆድ ባሳት፣ ሀዘኗ ከፋ፣ እስከዛሬ ውስጧ ያልነበረ ብቸኝነት ከበባት።
አሁን መሰረት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት። አክስቷን በሞት ካጣች በኋላ ህይወትን እንደቀደሞ ለመቀጠል ትፍጨረጨር ይዛለች። ውሎ አድሮ በቤቱ የተከሰተው አለመግባባት ግን ሰላም እየነሳት ነው፤ የአክስቷ ልጆች ከእናታቸው ሞት ማግስት እሷን ማየት እንደማይሹ ነግረዋታል። መሰረት ስለምን ብላ መወዛገብ አልፈለገችም። እነሱ ከእሷ የሚጋጩበትን ምክንያት አሳምራ ታውቀዋለች። ሰበብ እየፈለጉ የሚጣሏት በመኖሪያ ቤቱ መነሻ ነው። ቤቱ የቀበሌ ይዞታ መሆኑ ይታወቃል። እንዲያም ቢሆን የእሷን አለመወለድ ምክንያት ሆኖ እንድትልቅ ተገዳለች። የአክስቷ ልጆች ከእሷ በዕድሜ ይበልጣሉ። ታናሽነቷን አይተው ግን ማዘን አልፈለጉም። ከቤት እንድትወጣ ሲወስኑ በአንድ አይነት ቃልና ስሜት ነበር። ደጋግመው ቤቱ ለእነሱ ብቻ እንደሚገባ ነገሯት። መሰረት ምርጫ የላትም። የልባቸውን ሞላች። ያደገችበትን ቤት ላትመለስባት ተሰናብታ ከወዳጅ ዘመድ ተጠጋች። የመሰረት ጅምር ትምህርት እንደቀድሞው አልቀጠለም። በየዘመዱ ቤት ያለው እንክርት ህይወቷን ፈተነው። የዘመድ ቤት ኑሮ እንዳሰበችው አልሆነም። ውላ አድራ ከራሷ መከረች። ያገኘችውን እየሰራች ለእጇ ሳንቲም መያዝ እንዳለባት ወሰነች። ያሰበችው ሆነ። የአቅሟን ቤት ተከራይታ ራሷን መምራት ያዘች።
የወታደሩ ዓይኖች
አሁን መሰረት በአካል ጎልብታ በዕድሜ ጨምራለች። ዛሬ ከጎኗ የሚሆን ዕንባዋን የሚያብስ ዘመድ የላትም። የእናት አባቷን ፍቅር ሞልተው እንደ ልጅ ያሳደጓትን አክስቷን ካጣች ወዲህ ህይወት መልኳን ቀይራባታለች። እንደእህት ወንድም የምታያቸው የአክስቷ ልጆች በቤት ንብረት ሰበብ ክደዋታል። ማንም እንደሌላት የምታውቀው ወጣት አጋር እንደሚያሻት ልቧ ሹክ እያላት ነው። መሰረት ድንገት ካወቀችው ወታደር ጋር መግባባት ይዛለች። ወታደሩ አገር ለማስጠበቅ፣ ድንበር ለማስከበር ዝግጁ የሆነ ወጣት ነው። ባገኘችው ቁጥር ጎዶሎዋ የሞላ፣ ቀኗ የፈካ ይመስላታል። ስታየው ውስጧን ደስ ይለዋል። ሲያወራት ታደምጠዋለች። ሲያጫውታት ጊዜ ትሰጠዋለች። ዓይኑን የጣለባት ወታደር በዚህ ብቻ አልበቃውም፤ ልቧን ተረክቦ ልቡን አስረከባት። የሁለቱ ግንኙነት ፍቅር ቢያሸንፋ ቁምነገር አሰቡ። ትዳር ይዘው ጎጆ ቀልሰው መኖር ወደዱ። ጥንዶቹ በትዳር ዘልቀው ቤት ሲያቀኑ መተሳሰባቸው ነገን የሚያሻግር ሆነ። የአብሮነታቸው መስመር ጠንክሮ ዓመታትን በአንድ ኖሩ። ፍቅራቸው በመኖር ብቻ አልተጋመሰም። ሁለቱን በአንድ የሚያጣምር ፣ህይወት ኑሯቸውን የሚያሳምር ፍሬ አገኙ። ትዳራቸው በልጅ በረከት ታደሰ። የመጀመሪያ ልጃቸውን በፍቅር እያዩ አቅፈው ሳሙ። ዳግም ነገ የመኖር ተስፋቸው ለመለመ።
መሰረት ከልጇና ከባለቤቷ ጋር ህይወትን ቀጥላለች። ትናንት የሆነባትን አታስብም። ብቸኛ የሆነችባቸው ዓመታት አሁን በእጥፍ በሆኑ የደስታ ቀናት ተክሰዋል። ዛሬ ልጇና ባለቤቷ ጎዶሎዋን ሞልተው ፣ዓለሟን አሳምረዋል፣ ዕንባዋን አብሰው ፈገግታዋን መልሰዋል።
ድንገቴው ህመም..
መሰረት አልፎ አልፎ የሚሰማት ህመም ጤና ይነሳት ይዟል። የሚጠባ ልጇን እንደታቀፈች ስትስል፣ ስታስነጥስ መዋል ልማዷ ነው። ሁሌም የተለየ ድካም ይሰማታል፤ ልቧን እያስጨነቀ መተንፈሻ ያሳጣት ህመም አልጋ አያስያዘ ያስነሳታል። ‹‹ተሸሎኛል››ስትል እያገረሸ በውጋት ያሰቃያታል። መሰረት ህመሟ የሳንባ ቲቢ መሆኑን ካወቀች ሰንብታለች። መድሀኒት ታዞለት ዘወትር እየወሰደች ነው። ያም ሆኖ አልተሻላትም። አንድቀን ህመሙ ባስ ሲል ወደ ሀኪም ቤት አቀናች። ሀኪሞቹ የቀደመ ውጤቷን እያስተዋሉ ተጨማሪ ምርመራ እንድታካሂድ አዘዙ። መሰረት እንደተባለችው ሙሉ ምርመራ አካሄደች፣ ደም ሰጥታ ውጤት ጠበቀች። ጥቂት ቆይቶ ሀኪሙ እጅ የደረሰው የምርመራ ውጤት እንደተገመተው ሆነ። ጥርጣሬው ትክክል ነበር። መሰረት ከሚያሰቃያት የሳንባ ህመም በተጨማሪ በደሟ የኤችአይቪ ቫይረስ ተገኝቷል። ሀኪሞቹ ከውጤቱ በኋላ መሰረትን እያጽናኑ ማድረግ ስለሚገባት ጥንቃቄዎች ምክር ለገሱ። ወይዘሮዋ ሁለት ዓመት ያልሞላውን ህጻን ልጇን እያጠባች ነው። ከዚህ በኋላ ከቀድሞው የበለጠ ጥንቃቄና እንክብካቤ ያሻታል። ቫይረሱ በደሟ እንደተገኘ ሌሎች ጥያቄዎች ሊነሱ ግድ ሆነ። አሁን ህጻኑና ባለቤቷ ተመሳሳይ ምርመራ ማካሄድ አለባቸው። በተለይ ባለቤቷ በፈቃደኝነት የተመሰረተ ይሁንታው ያስፈልጋል።
የጭንቅ ቀናት …
መሰረት ውጤቱን ከሰማች በኋላ በከባድ ድንጋጤ ተዋጠች። ስጋትና ጥርጣሬ እየተመላለሱ አስጨነቋት። ትንሹ ልጇ በእርግዝናዋ ፣ ቆይቶም በማጥባት ጊዜ ከእናቱ ቫይረሱን ሊወስድ ይችላል። ይህን ስታስብ ጸጸቱ ዕንቅልፍ ነሳት። ሆስፒታል በነበረች ጊዜ ከህክምና ባለሙያዎቹ ልጁ አስቸኳይ ምርመራ ማካሄድ እንዳለባት ተነግሯታል። መሰረት የሀኪሞቹን ምክር ተቀብላ ህጻን ልጇን ለማስመርመር ከሆስፒታል ተገኝታለች። ትንሹ ልጅ በእናቱ እቅፍ ሆኖ ትንሽዬ ክንዱን ለምርመራው አዘጋጅቷል። የደም ናሙናው ሂደት ሲጠናቀቅ ለውጤቱ ቀጠሮ ተሰጣት። እናት መሰረት በአይኖቿ ሙሉ እያነባች ፈጣሪዋን ተማጸነች፣‹‹በኔ ይብቃ፣ በልጄ አይለፍ›› ስትልም ምህረት ፣ድህነቱን ተመኘች። የቀጠሮ ቀን
ወይዘሮዋ ዛሬ በቀጠሮዋ መሰረት ከሕክምና ማዕከሉ ተገኝታለች። ጊዜው ደርሶ ስሟ እሰኪጠራ ብዙ እያሰበች ነው። ከልጅነቷ ጀምሮ ያሳለፈችው ስቃይ ቀላል የሚባል አይደለም። ያለእናት አባት የኖረችበት ጊዜ ዋጋ አስከፍሏታል። ካደገችበት ቤት በግፍ መባረሯ አሁን ለቆመችበት ህይወትና ለደረሰባት ክፉ አጋጣሚ ምክንያቷ ነው። ያልተመቸ ኑሮዋ ለህመም አጋልጦ ሲያሰቃያት በደሟ የተገኘው የኤችአይቪ ቫይረሰ ለአንድ ልጇ ጭምር ስጋት ሆኗል። አሁንም እናት መሰረት ጭንቀት ውስጥ ናት፣ስለራሷ፣ስለባሏ በተለይ ስለትንሹ ልጇ እያሰበች የዓይኖቿን ዕንባ ታብሳለች። በድንገት ስሟ ሲጠራ ከዕንቅልፏ የባነነች ያህል ፈጥና ነቃች። ከአንድ ክፍል ገብታ እንደተቀመጠች ሀኪሙ በእጁ የያዘውን ካርድ እያገላበጠ እውነቱን ሊያሳውቃት ተዘጋጀ። መሰረት ሀኪሙ ተናግሮ እስኪጨረስ አፏ እየደረቀ አዳመጠችው። የተባለቸውን ሰምታ የሀኪሙን ምክር አድምጣ ከክፍሉ ስትወጣ እናት መሰረት ፊቷ በፈገግታ በርቶ፣ እርምጃዋ ከወትሮው ጨምሮ ነበር። አሁን ልጇ በደሙ የኤችአይቪ ቫይረስ እንደሌለበት ተረጋግጧል። መሰረት ይህን ስትሰማ በደስታ አነባች፣ የራሷን ህመም ረሳች፣ ፈጣሪዋን አመሰገነች።
ህይወት በሌላ መልክ…
መሰረት የልጇን ውጤት ካወቀች ወዲህ ጡት ማጥባት እንደሌለባት ተነግሯታል። አሁን ትልቁ ሸክም ከትከሻዋ ወርዷል። እንዲያም ሆኖ ሌላ ችግር አልቀረላትም። ባለቤቷ ተመርምሮ ኤችአይቪ እንዳለበት ካወቀ ወዲህ በእጅጉ ተስፋ ቆርጧል። በየቀኑ በመጠጥ ሱስ መናወዙም ህይወት ኑሯቸውን አመሳቅሏል፡ ፡መሰረት ከምትወስደው የቲቢ መድሀኒት ባለፈ በጀመረችው ተጨማሪ ህክምና ልዩ ትኩረት የሚያሻት ሆናለች። ከምንም በላይ ግን የባለቤቷ ሁኔታ ሰላም ነስቷታል። ስራውን ትቶ በየቦታው መታየቱ፣ ራሱን ጥሎ በተስፋ ማጣት መሰንከሉ ተስፋዋን አጨልሞባታል። መሰረት በዚህ ፈታኝ ህይወት ላይ ሆና ሁለተኛዋን ልጅ ወለደች። እንዲህ መሆኑ ከባሏ ስራ መፍታት፣ ከእሷ በህመም መጎዳት ጋር ተጣምሮ ኑሮን አስቸጋሪ አደረገው። መልካም ከሆኑ ሰዎች ግቢ ማድቤቱን ቤት አድርጋ ኑሮን ቀጠለች። ያለችበት ቤት በልማት ምክንያት ሲፈርስ ከስፍራው ልትወጣ ግድ ሆነ። እያደር እጅ ሲያጥር፣ ቤት ሲጎድል አማራጮች ጠበቡ። ለቤት ኪራይ የሚከፈል፣ ለዕለቱ የሚላስ የሚቀመስ ጠፋ። መሰረት ውሎ አድሮ ከነቤተሰቧ ከጎዳና ወደቀች። ላስቲክ ወጥራ፣ ከመንገዱ ደርቻ፣ ከአስፓልቱ ጥግ ኑሮ መሰረተች። አሁን ባለቤቷ ከእሷ አይደለም። በመሀላቸው በተፈጠረው ችግር ተለያይተዋል። ከጎኗ ረዳትና አጋዥ የለም፣ ልጆቿን ለማሳደግ፣ አስተምሮ ወግ ለማድረሰ ቀን ከሌት መስራት ግድ ይላታል። ለዚህ ብርታቱን የሰጣት ወይዘሮ ስለ ልጆቿ የማትሆነው የለም። በየቀኑ የሾፌሮችና የረዳቶችን ልብስ ታጥባለች፣ለትንሽ ትልቁ ትታዘዛለች፣ ከምታገኘው ገቢ ለልጆቿ ደጉሟ ለላስቲክ ጎጇዋ ትደርሳለች።
ሌላው ፈተና..
መሰረት ችግርን ከጽኑ በሽታ ይዛ አመታትን በችግር በገፋችበት የላስቲክ ቤት ህይወት በልጆቿ ተስፋ ታደርጋለች። የጎዳና ህይወቷ ክረምት ከበጋ ከፈተና አይወጣም። ጎርፍና ዝናብ ያስጨንቃታል። ብርድና ውርጩ ያስቸግራታል።
የልጇቿ አባት ከእሷ ባይሆንም ይጠያየቃሉ። እሱን ስታይ ይከፋታል። የትናንትናው መልኩ ዛሬ አብሮት የለም። በህመምና ችግር አካሉ ከስቶ ፊቱ ገርጥቷል። ልብሱ ቆሽሾ ራሱን ጥሏል። ገለልተኛ ሆኖ ከሰዎች ርቋል። እናም መሰረት እሱን ስታይ ይከፋታል ፣ ከልቧ ታዝናለች። ወይዘሮዋ ኤይችኤቪ ቫይረስ በደሟ መኖሩን ካወቀች ወዲህ ራሷን አሳምና መኖርን ለምዳለች። ከዓመታት ወዲህ የሚሰማት ሌላ ህመም ግን ሰላም እየሰጣት አይደለም። ሰውነቷን ክፉኛ ያሳክካታል። መላ አካሏን ላስተዋለ እሳት የበላው ይመስላል። የህመሙ መመላለሰ ያስጨነቃት መሰረት ከቀናት በአንዱ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተገኝታ ሙሉ ምርመራ አካሄደች። በወቅቱ የተገኘው ውጤት አስደንጋጭ ነበር። ወይዘሮዋ በካንሰር በሽታ ተጠቂ ሆናለች።
‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የመሰረት ጤንነት በሌላ ህመም መፈተኑ ለሚያውቋት ሁሉ አስደንጋጭ ሆነ። በምልልስ የኬሞቴራፔ ህክምናን የጀመረችው ሴት ህመሙ ከምትገኝበት፣ ካሳለፈችው ህይወት ተዳምሮ ኑሮዋን አስቸጋሪ አድርጎታል። የቀደመ ታሪኳን የሚያውቁና ችግሯን የተረዱ አንዳንዶቸ በማጽናናትና በምክር ቆማ እንድትሄድ አግዘዋታል። በተለይ በሆስፒታሉ ህክምናዋን የያዘው ዶክተር ዳኛቸው እሷንና ልጇቿን ከግል ኪሱ እየደጎመ ነገን አሻግረው እንዲያዩ ረድቷቸዋል። መሰረትም ለዚህ ሰው ያላት አክብሮትና ምስጋና ከሌሎች ሁሉ ይለያል። ዛሬም መሰረት የዘንድሮን ክረምት በጎዳናው ቤቷ አሳልፋለች። ህመም ከኑሮ ድካም ያንገላታት ወይዘሮ በእግሯ ላይ የሚሰማት ብርቱ ህመምና በሰውነቷ ላይ የሚስተዋለው ለውጥ ሲያውካት ይውላል። በውጭ አካሏ ላይ በግልጽ የሚስተዋለው የጓጓለ አይነት ምልክት ሁሌም እረፍት እንደነሳት ነው። ልብስ አጥባ ስትገባ እጇን ክፉኛ ያሳክካታል፣ ያቃጥላታል። አንዳንዴ የሚመላለስባት ቁርጥማት በእጅጉ ከባድ ነው። መሰረትን ሳገኛት ገጽታዋ የሕመምተኛ አይመስልም። መልኳ የተረጋጋ ፈገግታዋ የተመጠነ ፣የፊት ቀለሟ የሚያምር እንደሆነ አስተውያለሁ። ከእሷ ጥቂት ማውጋት እንደጀመርን ልብሷን አውልቃ መላ ሰውነቷን አሳየችኝ። መልከ ብዙ በሚባል አይነት ገጽታ ተዥጎርጉሯል። እግሯ፣ ባቷ፤ጀርባዋና ሆዷ ሳይቀር የተለየ መልክ አለው። ውስጤ አዘነ፣ መንፈሴ ተረበሸ፣ ዕንባዋን ተከትዬ ላለማልቀስ ከራሴ ታገልኩ ፡ለጊዜው ተሳካልኝ።
ዛሬም እንደትናንቱ..
መሰረት ዛሬም ከህመም እየታገለች ለልጆቿ መኖር ይዛለች። ኑሮዋ አሁንም ከጎዳና አልወጣም። ማንነቷን የተረዱ የወረዳ አካላት ቤት እንደምታገኝ ተስፋ ሰጥተዋታል። በተሰጣት ተስፋ ነገን ለማየት ዛሬን በችግር ልታልፍ ግድ ብሏታል።
የመሰረትን ልጆች ላየ ድህነት ያለባቸው አይመስሉም። ኑሯቸው ጎዳና ቢሆንም ንጹህ ሆነው ይውላሉ። ታሪኳን የሚያውቁ አንዳንዶች ልብስ ያመጡላታል፣ ከቤታቸው ጓዳ ቆርሰው፣ቆንጥረው ያጎርሷታል።
የመሰረት ሁለተኛዋ ልጅ ከአጠቃላይ ተማሪዎች አንደኛ በመውጣት እንዳኮራቻት ነው። ዛሬ አስራሰባት ዓመት የሞላው ወንዱ ልጇ፡ ትምህርቱን አቋርጦ ፤የእሷን ድካም ለመካፈል ሲበረታ ይውላል። በተደራራቢ የጤና ችግር ስትፈተን የምትውለው መሰረት ዛሬ በልደታ ክፍለከተማ በተገነባው የምገባ ማዕከል በቀን አንዴ እንድትመገብ ዕድል አግኝታለች። ሁሌም ከሚሰጣት ቋጥራ ለልጇቿ ታጎርሳለች። ልጇችዋ ለእሷ የጨለማዋ ብርሀን ናቸው። ነገን አሻግራ ታይባቸዋለች፡ ዛሬን በተስፋ ታድርባቸዋለች። ክንደ ብርቱዋ፣መንፈሰ ጠንካራዋ ወይዘሮ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም