በግሌ ስለ አሸባሪው ትሕነግ እኩይነት፣ ክፋትና ሸር፣ ሰላም ጠልነት፣ ያለጦርነት መኖር አለመቻል፣ ውሸት፣ አስመሳይነት…መስማትም መናገርና መጻፍም ሰልችቶኛል። ምክንያቱም እንኳንስ እዚሁ አብረነው የኖርነው ዓለም ላይም ቢሆን ይህን የማያውቅ አለ ብዬ አላስብምና። አሁን ማወቅ የምፈልገው ከዚህ በላይ ነው፤ ስለተሠራበት መሠረቱና ስለሆነው እሱነቱ፣ ስላደረገውና ስለኖረው ታሪኩና ድርጊቱ፣ ስለጸባዩና ግብሩ ሳይሆን ለዚህ ሁሉ መሆኑና ማንነቱ መንስኤ የሆነውን እውነተኛውን የፍጥረቱን ልክ ማወቅ ነው የምፈልገው። ይህም ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነፍስ ካወቁበትና ስለትሕነግ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ ዕድሜ ልኬን ስፈልገው የኖርኩት እውነት ነው። እናም የትሕነግን ትሕነግ መሆኑን ሳይሆን «ለምኑን» (ማለትም ከትሕነግ ትሕነግን ሆኖ የመፈጠር ጀርባ) ያለውን ምስጢር ለማወቅ ለዘመናት ስደክም ኖሬያለሁ። አቅሜ የፈቀደውን ያህልም ጉዳዩን ለመመርመርና ለማጥናት ሞክሬያለሁ። በዛሬው ጽሑፌ በምርምሬ የደረስኩበትን ግኝትና የጥናቴን ውጤት ላካፍላችሁ ወደድኩ።
የጥናቱ መነሻ
ሰው ከምድር ፍጥረታት ሁሉ ልቆ የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር ነው ብዬ አስባለሁ። ሰው ሆኖ መፈጠርም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የሆነ ታላቅ ክብርን የሚያቀዳጅ የታላቁ ፈጣሪ ልዩ ስጦታ መሆኑንም አምናለሁ። የሰውን አፈጣጠር በተመለከተ በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊው ጎራ የፈለቁና የሚታመንባቸው እሳቤዎች የሚያረጋግጡልንም ይህንኑ እውነታ ነው። መንፈሳዊው ወይም ሥነ ፍጥረታዊው ዕይታ እንደሚያስረዳው ፈጣሪ ይህን ዓለምና በውስጡ የሚኖረውን ፍጥረት በፈጠረበት ወቅት በታላቁ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር ሌላውን ፍጥረት ሁሉ «ይሁን» እያለ በቃሉ ብቻ የፈጠራቸው ሲሆን ሰውን ግን በቅዱስ እጁ «ኑ ሰውን እንደ አምሳላችን እና እንደ አርዓያችን እንፍጠር» በማለት ከአራት ባህርያተ ሥጋና ከሦስት ባህርያተ ነፍስ በአጠቃላይ ከሰባት ባህርያት አዋህዶ በቅዱስ እጆቹ አበጅቶታል። በግዕዙ «ሰብዕ» የሚለው ቃልም ይህንኑ የሚያመለክት ሲሆን ትርጓሜውም ሰባት ባህርያት ያሉት ማለት እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ።
ከዚህም በአሻገር እግዚአብሔር ሌሎችን ፍጥረታት በሙሉ ሥራው ይታወቅበትና ይደነቅበት ዘንድ ለአንክሮና ለተዘክሮ የፈጠራቸው ሲሆን ሰውን ግን «ስሙን ለመቀደስ፣ ክብሩን ለመውረስ ፈጠረው» ይላል። ይህም ለሰው ልጅ ምን ያህል ክብር እንደተሰጠው የሚያሳይ ነው። በተለይም «ክብሩን ለመውረስ» የሚለው ቃል ሰው በአግባቡ ተፈጥሮውን አውቆ ከተንቀሳቀሰ ከምድራውያን ፍጥረታት በልጦ መገኘት ብቻ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር የመሆን ዕድል እንዳለውም ያሳያል። ይህም ብቻ አይደለም፤ ሰው የተፈጠረው ከእርሱ ውጪ ያሉ በምድር ላይ የሚኖሩ ሌሎች ፍጥረታትን ሁሉ ይገዛ ዘንድ ታላቅነትን ብቻ ሳይሆን አለቅነትንም ጭምር ይዞ ሁሉን በሚችለው ፈጣሪ የዚህች ምድር ታላቅ ፍጡር ሆኖ መፈጠሩንም በመንፈሳዊው የሥነ ፍጥረት እሳቤ ዘንድ ዋነኛ ማጣቀሻ ሆኖ የሚያገለግለው መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ ቋንቋ በግልጽ መዝግቦት ይገኛል።
ስለሰው ልጅ አፈጣጠርና አመጣጥ የሚያትተው የሳይንሱ ክፍልም ቢሆን አጠቃላይ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሕይወት ከሌላቸው ቁስ አካላት መገኘታቸውንና የሰው ልጅም ከጦጣ መሰል ፍጡር መምጣቱን ይናገራል። ይሁን እንጂ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት በርካታ ችግሮችን እያሸነፈ የመጣና በሂደት ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ማድረግ የቻለ ከፈጣሪው በታች ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚችል ኃያል ፍጡር መሆኑን ይመሰክራል። ሰውን የምድራችን ታላቁ ፍጡር እንዲሆን ያስቻለውና ለዚህ ክብር ያበቃው ደግሞ ክፉና በጎን፣ ስህተትና ትክክልን፣ እውነትና ሃሰትን፣ ልማትና ጥፋትን፣ ሞትና ሕይወትን የተሻለውን አመዛዝኖ እንዲመርጥበት ከፍጥረት ሁሉ ተዳልቶ ለእርሱ ብቻ ተዳልቶ በተሰጠው «አዕምሮ» በተባለ ውድ የፈጣሪ ስጦታ መሆኑንም ጠንቅቄ እረዳለሁ። እናም ምንም እንኳን የሰው ልጅ እንደ እንስሳ ስጋዊ ጠባይ ቢኖረውም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ አምላካዊም፣ መለኮታዊም የመሆንን ዕድል በማግኘቱ እንደፈጣሪው መልካምና ርህሩህ ፍጡር ነውም ብዬ አምናሁ።
ይሁን እንጂ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለማድረግ ይቅርና ለማሰብ የሚዘግንኑ፣ ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠሉ እጅግ የሚከብዱ የክፋትና የጭካኔ ድርጊቶችን በሰው ልጆች ላይ ሲፈጽም የኖረው ትሕነግ የሚባለው የሰው ጉድ ስለሰው ልጅ አፈጣጠርና ማንነት ካለኝ አስተሳሰብና እምነት በተቃራኒው ቆሞ መመልከቴ ዕድሜዬን ሙሉ «ለምን?» የሚል ጥያቄን በአዕምሮዬ ውስጥ ሲያመላልስብኝ ኖሯል። ሁኔታውን በአጽንኦት እንድመረምረውና በጉዳዩ ላይ የራሴን ጥናት እንዳደርግ ያስገደደኝም ከሰው ልጅ ተፈጥሮ በተቃራኒ የቆመው ይኸው የአሸባሪው ትሕነግ ድርጊትና ማንነት ነው።
የጥናቱ አሁናዊ ዳራ
በሊቢያ የሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ አይ.ኤስ. አይ.ኤስ በተባለ ወንጀለኛ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ላይ ከተፈጸመው እጅግ ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊት የባሰ ጭካኔ በሚለው ቃል ብቻ ሊገለጽ የማይችል ዓለማችን አይታው የማታውቀው ሌላ ዓይነት ጭካኔ እዚሁ በራሳችን ታህተ ሰብዕ ጨካኞች በትሕነግና በትሕነጋውያን አማካኝነት በተደጋጋሚ ተፈጽሟል። አሸባሪው ትሕነግ በማይካድራ የዕለት ጉርሳቸውን፣ የዓመት ልብሳቸውን ለማሟላት ቀያቸውን ጥለው ለጉልበት ሥራ የሄዱ፣ ቀን በሃሩር ሌሊት በቁር ያለእረፍት ላባቸውን እያፈሰሱ የነበሩ፣ እጅጉን በሥራ የደከሙ ምስኪን የቀን ሠራተኞችን ፍጹም አሰቃቂ በሆነ መንገድ በአካፋና በዶማ ቀጥቅጦ ገድሏቸዋል። ሞቼልሃለሁ፣ ተሰውቼልሃለሁ እያለ በሃሰት በስሙ የሚነግድበትን በተግባር ግን ዕድሜ ልኩን ሲገድለውና ለጥቅሙ ሲሰዋው ለኖረው ትሕነግ «ሕዝቤ» ለሚለው የትግራይ ሕዝብ ሕይወታቸውን ሰጥተው ሃያ ዓመታትን ከጠላት ሲጠብቁት የኖሩትን፣ ከማትበቃ ደመወዛቸው እየቀነሱ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ የገነቡለትን፣ ሃያ ዓመት አብረውት የበሉትን የጠጡትን ጋሻ መከታ ወንድሞቹን በተኙበት አርዷል።
በአፋር በጋሊኮማ መንቀሳቀስ የማይችሉ በሰው የሚወጡ የሚገቡ አረጋውያን እናቶችንና አባቶችን እና ሕፃናትን በከባድ መሣሪያ በጅምላ ጨፍጭፏል። በሰሜን ወሎ አጋምሳ የተባለች ወረዳን ነዋሪዎቿን በጅምላ ጨፍጭፎ፣ ምድሯን ሳይቀር አቃጥሎ ሙሉ በሙሉ አውድሟል። ሽንፈቱንና ውርደቱን ለመደበቅ በሚል በጦርነት የሞቱበትን የራሱን አመራሮች ሳይቀር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አንገታቸውን ቆርጦ ደብቋል። ትሕነጋውያን ጦርነት ምን እንደሆነ ምኑንም የማያውቁ፣ አውቀውም የማይሸሹ፣ ሸሽተውም የማይደበቁ፣ የማይናገሩ፣ የማያስቡ፣ የማይማከሩ «ነፍሰ እግዚአብሔር» የሚባሉ የቤት እንስሳትንም ገድለዋል፣ አቃጥለዋል። ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ደግሞ እጅግ አሰቃቂ በሆነ፣ እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የሰውን ልጅ አሰቃይተዋል፣ ገርፈዋል፣ ሰውን ከእባብና ከጊንጥ፣ ከአንበሳና ከጅብ ጋር አንድ ላይ አስረዋል፣ የሰውን ልጅ ከእነ ነፍሱ ቀብረዋል፣ የወንድ ልጅን ብልት አኮላሽተዋል፣ በሴት ልጅ ብልት እንጨት…።
በአጠቃላይ ትሕነግ ቅድስት አገር በምትባለው በኢትዮጵያ ላይ ይቅርና ምንም ዓይነት ሃይማኖት የሚባል ነገር በሌለበት በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ እንኳን ሊፈጸሙ የማይችሉ፤ ታይተው ተሰምተው የማይታወቁ እንኳንስ ለሰው ልጅ ለፍጡር ሁሉ እንግዳ የሆኑ፣ ብዙ፣ ብዙ ተዘርዝረው የማያልቁ አሳፋሪ ርኩሰቶችንና አሰቃቂ ጉዶችን በሰው ልጆች ላይ ፈጽሟል።
የጥናቱ ዘዴ
በዚህ ጥናት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው ዘዴ እስካሁን ድረስ የተነበቡ የትሕነግ ማንነት ታሪኮችን በቅርብ ጊዜ ከቀሰቀሰው ወረራና ጦርነት ጋር በማገናዘብ ጥልቅ የማሰብና የማብሰልሰል ዘዴን በመጠቀም የትሕነግን ሁለንተናዊ ማንነት መመርመር ነው።
ትንተና
የራስን ችግር ለመፍታትና የተሻለ ሰው ሆኖ ለመገኘት ማሰብና መፍጨርጨር ለሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ ተፈጥሯዊ ባህሪይው ነው። መነሻና መድረሻውም ሕይወትን ማፍቀርና ማሳመር ነው። እናም ይኸው ንጹህ የማደግና የመሻሻል ፍላጎት የወለደው ንጹህ የፍቅር የኃይል ሚዛናዊ በመሆኑ ሂደቱ አንድና ቀጥተኛ ግቡም አንድነትና ስምምነት ነው። መሠረቱ ለሕይወት ያለ ንጹህ ፍቅር ነውና፤ ሕይወት ደግሞ የእያንዳንዱም የሁሉም፣ አንድም ብዙም፣ ግለሰብም ኅብረተሰብም፣ ራስም ሌላም፣(የራስም የሌላውም፣ የሁሉም)፤ ናትና። ሰው ራሱ አንድነትም ብዙነትም ነውና፣ ሰው የሚለው ቃል ራሱ የአንድም የሁሉም ስያሜ ነውና፣ አንዱም ሰው፣ አጠቃላይ የሰው ዝርያ(ስፒሽየስ)ም የሚጠራው «ሰው» ተብሎ ነውና።
ለምሳሌ «አንተ ሰው»፣ «ያ ሰው» በሚሉት አገላለጾች ውስጥ ያለው ሰው አንድ ወይም ነጠላ ሲሆን «የሰው ልጅ»፣ «በምድር ላይ የሚኖር ሁሉም ሰው ሊያውቀው የሚገባ ጥብቅ ጉዳይ»፣ «ሰው ለተባለ ፍጡር ሁሉ፣ ሰው ሁሉ፣ አገር ያለ ሰው» …ወዘተ በሚሉት ሐረጎች ውስጥ የሚገኘው «ሰው» የሚል ቃል ደግሞ ብዛትን የሚያመላክት ነው። ስለሆነም ሰው መሠረቱን ፍቅር ላይ አድርጎ የእርሱ ከሆነው ከራሱ ሰውነት ላይ ተነስቶ ሕይወቱን ለማሻሻል ሲሠራ ሰውነትም ሕይወትም የጋራ ስለሆኑ ሰው ለተባለ ፍጡር እየሠራ ነው ማለት ነው። ፍቅርም የጋራ የሰው ሁሉ ናትና ለሁሉም ይሠራል ማለት ነው።
በሌላ አባባል ሰው ራሱን ትቶ ከሌላው ጋር አነጻጽሮ ሲነሳ ግን ምንም እንኳን ራሱን ያነጻጸረው ከሰው ጋር ቢሆንም እንኳን ራሱን ትቶ ከሌላው በመነሳቱ ራሱን ክዷል ማለት ነው። ራሱን ከካደ ደግሞ የሌላውንም ሰው ማንነትም ይክዳል ማለት ነው። ሁለተኛ ነገር ወደሌላው ሰው የተመለከተው ያንን ሰው ለመጥቀም ሳይሆን ከዚያ ሰው አኳያ እርሱ ያለውንና የሆነውን ለመመዘንና በምን ይበልጠኛል፣ እኔስ በምን እበልጠዋለሁ፣ እኔ ከእርሱ በምን አንሳለሁ፣ እርሱስ ከእኔ በምን ያንሳል የሚሉትን በእርሱና በሌሎች መካከል አሉታዊ ክፍፍል የሚፈጥሩ፣ አላስፈላጊ የመበላለጥና የበላይነትና የበታችነት ስሜትን የሚፈጥሩ አፍራሽ ስሜቶችና የጉድለት ስሜትን የሚፈጥሩ ስሜቶችን የሚያመጡና ያን የተዛባ የኃይል ሚዛን ለመመለስ ለማስጠበቅ ወደፉክክርና ሽኩቻ የሚወስዱ የጥፋት መንገድን በማሰብ በመሆኑ ነው።
ስለዚህም ሌላውን መሠረት አድርጎ የሚነሳ ሰው በመጨረሻም በዚህ የተሳሳተ አካሄዱ ሰውን መጉዳቱ አይቀሬ ነው። እናም እንዲህ ዓይነቱ ሰው ራስ ወዳድ ሳይሆን ራስ ጠል ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ራስን ለመመልከትና ከራስ ለመነሳት ራስን መውደድ ያስፈልጋል። ራሱን ተመልክቶ ከራሱ ተነስቶ ቢሆን ኖሮማ ራሱንም ስለሚወድ ሌላውንም ይወዳል። ስለሆነም ሌላውን ሰው የሚጎዱ ሰዎች በተለምዶ እንደሚባለው ራስ ወዳድ ሰዎች ሳይሆኑ ራሳቸውን ክደውና ጠልተው ራሳቸውን ከሌላው አንጻር ለመመልከትና ለመቅረጽና በዚያ መንገድ ለመኖር የሚሠሩ ራስ ጠል ሰዎች ናቸው ማለት ነው። ወይንም እነዚህ ሰዎች ማለትም ከራሳቸው ሳይሆን ራሳቸውን ከሌላው ጋር አነጻጽረው ኑሮን ለመምራት የሚነሱ ሰዎች ራስ ጠል ናቸው ወይንም ራስ ወዳድ ሳይሆኑ ራስን ብቻ ወዳድ በሚል ሊገለጹ ይችላሉ።
ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቶቹ ራስ ጠል ሰዎች ሕይወታቸውን ለመምራት ወደሰው የሚሄዱት ራሳቸውን ስለሚጠሉ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ብቻ ስለሚወዱም ሊሆን ይችላል። ማለትም ከራሳቸው አብልጠው ወደሰው የሄዱት ራሳቸውን ብቻ ስለሚወዱ በዚያም ሁሌም እነርሱ ብቻ ከሌላው የበላይ ሆነው ለመኖር ከሌላው ሕይወት ላይ ተነስተው ማለትም ሌላው ሰው ባለውና በሌለው፣ በሆነውና ባልሆነው ነገር ላይ ተመሥርተው ሌላው የሌለውን ለእነርሱ ለመፍጠር ሌላው ያልሆነውን እነርሱ ለመሆን የሚያስችላቸውን ራስን ብቻ የማስበለጥ ወይንም የመውደድ ብልጣብልጥ ስሌት ሊሆን ይችላል።
ሆኖም ፍቅር በባህሪው ለብቻ የማይዙት፣ ለራስም ለሌላውም የሚሰጡት፣ ከራስ አፍልቀው ለሌላው የሚሰጡት የሚካፈሉት እንጂ እንደበሽታ ለብቻ የሚሸከሙት ባለመሆኑ «ራስን ብቻ መውደድ» የሚባለው አገላለጽ በራሱ የተሳሳተ አገላለጽ ወይንም ስያሜ ነው። ስለሆነም እነዚህ ሰዎች ምንም እንኳን ራሳቸውን ብቻ በመውደዳቸው ራስ ብቻ ወዳዶች ተብለው ሊገለጹ የሚችሉ ቢሆንም አንድም ከስያሜ ተገቢነት አኳያ የማያስኬድ በመሆኑ፣ የስያሜው ኢተገቢነት የመነጨው ደግሞ ከጽንሰ ሃሳቡ ስሁትነት በመሆኑ ማለትም ራስን ብቻ እየወደዱ ራስ ወዳድ ወይም ፍቅር የሚያስገኘውን ሰላም እያገኙ መኖር የማይቻል በመሆኑ ራስን ብቻ መውደድ በራሱ ከፍቅር ይልቅ የጥላቻ መገለጫ በመሆኑ ራስ ጠል የሚለው ይበልጥ ይስማማቸዋል።
ራሱን ብቻ የሚወድ ለራስ ብቻ የሚሰጥ ፍቅር ባለመኖሩ ፍቅርም በባህሪው ለራስ ብቻ የማያገለግል በመሆኑ እንዲሁም ራስን ብቻ ወዳድነት አስማሚና አንድነት ፈጣሪ ሳይሆን አግላይና ከፋፋይ በመሆኑ ራስን ብቻ ወዳድነት ራስንም ሌላውንም የሚጎዳ ራስ ጠልነት ነውና! ራሱን ብቻ የሚወድ ሌላውን ይጠላልና፤ ሌላውን የሚጠላ ደግሞ ራሱንም አይወድምና፤ እንዲያውም ራሱን የሚጠላ ነውና! የትሕነግ እውነተኛ ስሪትና ባህሪም እንዲሁ ነው። ለምን?
ምክንያቱም አሸባሪው ትሕነግ ገና ሲወለድ የራሱን ማለትም ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ክዶ ነው የተወለደው። ማንነቱን ክዶ የተወለደው «የትግራይ ሕዝብ» ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) በአጥንትና በደም ተሳስረውና ተዋህደው ፍጹማዊ በሆነ ፍቅርና መቻቻል የማያልቅ ሕብረትና አንድነት ፈጥረው ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ዥንጉርጉር መልካቸውን ይዘው፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን ጠብቀው፣ የተከበረና አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ አገር መስርተው የኖሩ ኢትዮጵያውያንን አባቶቹንና እናቶቹን ማንነት ክዶ ነው የተወለደው። ራስን መካድ ደግሞ ራስን መጥላት ነው። ከዚህ በተጨማሪም በኢምፔሪያሊዝም የዘር ሾተላይ የእርግዝና ዘመኑን ሳይጨርስ የሰውነት ደረጃ ላይ ሳይደርስ ከኢትዮጵያ ምድር የተወለደው ጭንጋፉ ትሕነግ ከምን ጊዜውም በላይ የሰው ልጆች ወደ አንድነትና ትብብር እየመጡ ባሉበት በሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ሰዎችን፣ ያውም የአንድ አገር ዜጎችን የሚለያይ የአጥንትና የመንጋ ፖለቲካ ይዞ ነው የተወለደው።
የራሱንና የአገሩን የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ማንነት አውልቆ ጥሎ ለኢትዮጵያውያንና ለራሱ ሌላ አዲስ የሃሰት ማንነት ለመፍጠር ነበር ትሕነግ በጫካ የተወለደው። በመጨረሻም «ኢትዮጵያ የአማራ ገዥዎች ሌላውን ብሔርና ብሔረሰብ በኃይል አስገድደው የፈጠሯት አገር ናት፤ ትግራይም የኢትዮጵያ አካል ሳትሆን ራሷን የቻለች አገር ናት፣ እናም ትግራይም ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም ማንነታቸውን ለማስከበርና ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር በጨቋኙ የአማራ ብሔር ላይ በጋራ መነሳትና መታገል አለባቸው» የሚል የጥላቻና የሃሰት ትርክት አዘጋጅቶ የጥፋት መርዙን ቋጥሮ ነበር ከጫካ የወጣው። እናም ትሕነግ ራስ ጠል ነው።
በዚህ መንገድ ለብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተቆረቆረ መስሎ ግን ደግሞ ማንነታቸውንና የአገር ባለቤትነት መብታቸውን ነጥቆ ኢትዮጵያን ለአንድ ብሔር ብቻ ጠቅልሎ የሚሰጥ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ዥንጉርጉርነት ተፈጥሯዊ ማንነትን ክዶ የሚያስክድ እጅግ አደገኛ የክህደት፣ የውሸትና የጥፋት አጀንዳን ያለእረፍት እየፈጸመና እያስፈጸመ ግማሽ ክፍለ ዘመናትን በሕይወት ቆይቷል። ራስ ጠል በመሆኑ በክህደት ተወልዶ በውሸት ያደገው አሸባሪው ትሕነግ ዛሬም በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ከስህተቱ የማይማር፣ ከጥፋቱ የማይመለስ፣ በእርኩሰቱ የሚደሰት፣ እየተገረፈ የሚስቅ፣ ለቅሶ ተቀምጦ ከበሮ የሚደልቅ፣ መቃብር ውስጥም ሆኖ የሚፎክር ሳጥናኤልን የሚያስንቅ ከንቱ የእብሪተኛ ቡድን በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘር በሙሉ ኃፍረትም ነው። እናም እንዲህ ዓይነት ራስ ጠል ታህተ ሰብኦች ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘር ሁሉ ጸሮች ናቸውና ከምድረ ሰው እንዲወገዱ ዓለም ሁሉ ሊተባበር ይገባል የሚለው የአጥኚው ምክረ ሃሳብ ነው።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም