የዛሬዋ የዘመን እንግዳችን በግብረ-ሰናይ እንዲሁም በአገራዊ እርቅና ሰላም ሥራቸው ለረጅም ዓመታት ሕዝብና አገራቸውን ያገለገሉ እናት ናቸው። እኚህ ሴት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት ለመታደግና ኑሮ ለመለወጥ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ቢሆኑም የልፋታቸውን ያህል ያልተዘመራቸው ታታሪ ሰው ስለመሆናቸው የሚያውቋቸው ይመሰክሩላቸዋል። እንግዳችን ውልደታቸውም ሆነ እድገታቸው አዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም ለጥቂት ጊዜ በድሮ አጠራር ሲዳሞ ክፍለሀገር ኖረዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ነው የተማሩት። ብርሃን ዛሬ ነው በተባለ ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው ክፍለ ጊዜ ገብተው እየተማሩ ጎን ለጎንም በጽሕፈት ሥራ እዚያው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያገለግሉም ነበር። ሆኖም በወቅቱ ትዳር ይዘው ስለነበረ ባለቤታቸው ለሥራ ሲንጋፖር በመመደባቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው ከባለቤታቸው ጋር ለመሄድ ተገደዱ።
በሄዱበት አገርም በሕፃናት አስተዳደግ ዙሪያ የተለያዩ ስልጠናዎችን የወሰዱት እኚሁ ሴት በአሜሪካም በኢንትሪየር ዲዛይን የትምህርት መስክ ተምረውም ነበር። ሆኖም ሁለተኛ ልጃቸውን ወልደው ስለነበር ብዙም ሳይገፉበት ሙሉ ትኩረታቸውን ልጆቻቸውን ወደ ማሳደግ አዞሩ። ይህም ቢሆን ጎን ለጎን ራሳቸውን በእውቀት ለማበልፀግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር። በተለይም ሴቶችን የማማከር የተፈጥሮ ፀጋቸውን እያጎለበቱ በመምጣት የተጎዱ አናቶችን በሃሳብና በተለያዩ ነገሮች በመደገፍ የበኩላቸውን ሚናም ተጫውተዋል። በባለቤታቸው የሥራ ፀባይ ምክንያት የተለያዩ አገራትን የመጎብኘት ዕድሉን ያገኙት እኚህ ሴት በውጭ አገራት በቆዩባቸው 38 ዓመታት በተለይ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በመደገፍና በችግራቸው ሁሉ ቀድሞ በመድረስ የበጎ አድራጎት ሥራ ያከናውኑም ነበር። በዋናነትም የወያኔ አገሪቷን መቆጣጠር ተከትሎ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ጥለው ወደ ኬንያ የተሰደዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት በመታደግና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ረገድ ያበረከቱት አስተዋፅ ተጠቃሽ ነው።
ወደአገራቸው ከተመለሱ በኋላም በደማቸው ኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ያለባቸው በርካታ ሴቶች የሕክምና፣ የሥነ-ልቦና የስልጠና ድጋፍ እንዲያገኙ አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ራሳቸውን እንዲችሉ የሙያ ስልጠና በመስጠትና በማህበር እንዲደራጁ በማድረግ የመኖር ተስፋቸውን ያለመለሙ አገር ወዳድ ሴት ስለመሆናው በሥራቸው አስመስክረዋል። ከዚህም ባሻገር በወህኒ ቤት ያሉ ሴት ታራሚዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ላይ ፕሮጀክት በመቅረፅና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር እገዛ እንዲያገኙ አድርገዋል። ካለፈው ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን የተደፈሩ 100 ሴቶች ከደረሰባቸው የሥነ-ልቦና እና የአካል ጉዳት እንዲወጡ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በብዙዎች ዘንድ ትልቅ አክብሮትን አስችሯቸዋል። እነዚህና ሌሎች በርካታ የበጎአድራጎት ሥራቸውን በሚመለከት የቤዛ ኮምዩኒቲ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን መሥራች የሆኑትን ወይዘሮ ሶፊያ አሰፋን አነጋግረናቸው እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- እርሶና ባለቤትዎ ኬንያ በምትኖሩበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ሕይወት በመታደግ ከፍተኛ ሥራ ማከናወናችሁ ይነገራል። እስቲ ስለዚህ ሥራችሁ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
ወይዘሮ ሶፊያ፡- እንደምታስታውሽው የደርግ ሥርዓት እንዳበቃ በርካታ ሕዝብ ወደ ኬንያና ወደ ሌሎች አገራት ተሰዶ ነበር። በተለይ ወደ ኬንያ የፈለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ20 ሺ በላይ የሚልቅ ነበር። በናይሮቢ መጠለያ ጣቢያ ከሰፈሩት ውጪ ቲካ በተባለ በረሃ ላይ የወደቀውና የሞተው፤ የአውሬ እራት የሆነው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነበር። ከእነዚህም መካከል የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ጀነራሎች፣ ኮሎኔሎች፣ ሚኒስትሮች ነበሩ። የኬንያ መንግሥትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀበላቸው እንጂ እርዳታ አልነበራቸውም። በነገራችን ላይ መጠለያ ጣቢያ የገቡት የታወቁ የደርግ ባስልጣናት ሲሆኑ ሜዳ ላይ ደግሞ ዝም ብሎ የፈሰሱ በርካቶች ነበሩ። ናይሮቢ ከተማ ጎዳና ላይ ወድቆ በረሃብ የሞተም አለ። በየመንገዱ ስንሄድ የተጎሳቆሉ ኢትዮጵያውያንን ስንመለከት ልባችን ክፉኛ ይሰበር ነበር። በኋላ ይህንን እያየን ዝም ማለት ስላልቻልን በአቅማችን ለመርዳት ተነሳን። የኬንያ መንግሥትን አስፈቅደን ናይሮቢ ባለ መጠለያ ጣቢያ ላይ ቦታ ተሰጥቶን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን የሥነልቦና እና መንፈሳዊ ትምህርት እንሰጣቸው ነበር። ከትምህርቱ ጎን ለጎን ቤተ-መጽሐፍት ገንብተን የሚያነቡበትና ከተስፋ መቁረጥ ወጥተው አዕምሮቸውን የሚያበለፅጉበት ሁኔታን አመቻችተንላቸው ነበር። ይህም በተለይ ያሳለፉትን መጥፎ ታሪክ እንዲረሱ አድርጓቸዋል የሚል እምነት አለኝ።
ከዚህ በተጨማሪ በቲካ ካምፕ ውስጥ በበዓላት ጊዜ ደግሰን እናበላቸው ነበር። ናይሮቢ ከተማ ውስጥ ያሉት ደግሞ በጣም ብዙ ስለነበሩ በቀን እስከ 100 ሰው ድረስ በነፃ እናበላ ነበር። ዲቱር ወይም መመለስ በሚል መርሃግብራችን ደግሞ ወደ አውሮፓ ከሚሄዱት በተጨማሪ ወደ አገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ስደተኞች የተለያዩ ስልጠናዎች በመስጠት ሲመለሱ የራሳቸውን ሥራ የሚሠሩበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥረንላቸው ነበር። እውነቱን ለመናገር ይሄ ፕሮግራም ባይዘጋጅ ኖሮ ብዙዎች ይሞቱ ነበር። በየቀኑ መቶ ሰው ማብላት ማለት ቀላል አይደለም። በነገራችን ላይ ከየትኛውም ድርጅት ድጋፍ ሳናገኝ በራሳችን ገቢ ነበር ይህንን ሁሉ ሰው እንመግብ የነበረው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ አገርዎ ከተመለሱ በኋላስ የበጎ አድራጎት ሥራ የጀመሩበት አጋጣሚ ምን ነበር?
ወይዘሮ ሶፊያ፡- በመሠረቱ ይህ ለሰዎች ችግር ቀድሞ የመድረስና መርዳት ከልጅነት ጀምሮ ያደገብኝ ባህሪ እንደሆነ ነው የምረዳው። ሆኖም በተለይ እኔና ባለቤቴ ለ25 ዓመታት ኬንያ ናይሮቢ ከቆየን በኋላ የፈጣሪ ምሪትን ተቀብለን ነው ወደ አገራችን ለመመለስ የወሰነው። በተለይም ‹‹አገር በፅድቅ ይወረሳል፤ ፅድቅ ደግሞ አገርን ከፍ ከፍ ታደርጋለች›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃልን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያን መለወጥ አለብን ብለን ነው የተመለስነው። ልክ የዛሬ 17 ዓመት እንደመጣንም እንጦጦ ኪዳነ ምህረት አካባቢ ወደ አራት ሺ የሚሆኑ ሰዎች ላስቲክና ዛፍ ስር ወድቀው ተመለከትን፤ አንዳንዶቹም ልጆች አላቸው፤ በርካታ ወጣት ሴቶችና በዕድሜ የጠኑም ነበሩ። ሁሉም ሰዎች ታዲያ ኤች አይቪ እንዳለባቸው ሲያውቁ ብቻ ነው ለፀበል ብለው የመጡት። የሚበሉትም ሆነ የሚለብሱት አልነበራውም። የነበረውን አሳዛኝ ሁኔታ ስናይ በጣም ደነገጥን። ከዚያ ከኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ጋር በመተባበር ማሰልጠኛ ቦታ ሰጥተውን በመጀመሪያ ስለኤች. አይ.ቪ ማስተማር ጀመርን። በተለይም ራሳቸውን ከጠበቁ መኖር እንደሚችሉ፤ ከእነሱ ቀድሞ በሌላ በሽታ የተያዘ የሚሞትበት ዕድል ስለመኖሩ የሥነ-ልቦና ትምህርት ስንሰጥ ነበር።
እርግጥ እንደጀመርን ከፍተኛ ችግር አጋጥሞን ነበር፤ በተለይ ቄሶቹ ስለመድኃኒት እንድናስተምር የማይፈልጉ መሆናቸው ፈተና ሆኖብን ነበር። ምክንያቱም በዚያ ጊዜ መድኃኒቱ ብዙ አልታወቀም ነበር። በሂደት ግን በጥቂቱ መድኃቱን እየጀመሩ መጡ። ትምህርቱንም እየወሰዱ በሥነ ልቦናም እየታነፁ ትንሽ መጠናከር ጀመሩ። ከዚሁ ጎን ለጎን የሙያ ስልጠና እንዲሰጣቸው ተደረገ። በተለይም ከቡና ፍሬ ልዩ የሆነ ጌጣጌጥ ሥራ ስልጠና ወስደው እየሠሩ በመሸጥ ራሳቸውን ይደጉሙ ነበር። በባዛርና ውጭ አገር እስከመላክ የደረሱበት ሁኔታም ነበር። በኋላ ግን ሥራውን የጀመርነው በበጎ አድራጎት ድርጅት መልኩ ስለነበር የበጎ አድራጎት ድርጅት ደግሞ ገቢ በሚያመጡ ሥራዎች ላይ መሥራት አይችሉም ተባለና ተከለከልን።
በዚህ ምክንያት ድርጅቱን በቦርድ ይመሩ የነበሩ አንድ ግለሰብ ሥራውን ተረክበው ለብቻቸው ማካሄዱን ቀጠሉበት። ያም ቢሆን በርካታ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ሥራውን ገፍተውበት በግላቸው ሱቅ ከፍተው የቀጠሉ አሉ። በሽመና፤ ጡብ እና በተለያዩ ሙያ ነክ ሥራዎች ተሰማርተው የሚገኙትም ጥቂት አይደሉም። ከዚህ ባሻገር ተደራጅተው እንዲሠሩ የቁጠባ ማህበርም እንዲያቋቁሙ ድጋፍ አድርገንላቸዋል። አሁን በሚሊዮን የሚቆጠር ካፒታል ባለቤት ሆነዋል። ከእነሱ አልፎ ልጆቻቸውን እናስተምራለን፤ የተለያዩ ድጋፎችም እናደርግላቸዋለን። አሁን ላይ ኮሌጅ የደረሱት ልጆች ደግሞ ለሌሎቹ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ያግዙናል።
ከዚህ በተጨማሪ ጋይንት የሚባል አካባቢ ሥነ- ምህዳሩና ተፈጥሮው እህል ለማብቀል በጣም አስቸጋሪና ድንጋያማ መሬት ያለ በመሆኑ ሕዝቡ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እንደሚኖር መረጃው ደረሰን። በተደጋጋሚ ረሃብ ስለሚያጠቃቸውም በሴፍትኔት ነው የሚኖሩት። የአካባቢው ነዋሪ ራሳቸውን በምግብ የሚችሉባቸውን በርካታ ፕሮጀክቶችን ነድፈን ወደ ሥራ ገባን። ከእነዚህም መካከል 100 የሚሆኑ የአካባቢው ሴቶች ባላቸው አነስተኛ መሬት ማረስና ምርታማ መሆን እንዲችሉ የሚያደርግ ስልጠና ከውጭ ባለሙያ በማምጣት አሰልጥነናቸዋል። በቤታቸው ማዳበሪያ በማዘጋጀት ነዋሪዎቹ ከጓሯቸው ጀምሮ አትክልትና ፍራፍሬ አምርተው ውጤታማ ሆነዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን የፈትል ሥራ በስፋት እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥረንላቸዋል። ልጆቻቸውም ትምህርት ቤት እንዲማሩ ተደረገ። ከኅብረተሰቡ ጋርም በጠንካራ ትብብር ነው የምንሠራው። መንግሥትም ይህንን ሥራ እንድናሰፋው ጠይቆናል። በተጨማሪም የተለያዩ ሙያዎችን በማሰልጠን ሥራ እንዲፈጥሩ አድርገናል። የተለያዩ የዕደ-ጥበብ ውጤቶችና ሌሎች ምርቶች ባዛር በማዘጋጀት እንዲሸጡ አመቻችተንላቸዋል።
በሌላ በኩል ሱርማ ማህበረሰብ ላይ የምንሠራው ሌላ ፕሮጀክት አለን። እነዚህ ማህበረሰቦች እንደሚታወቀው ከዘመናዊ አኗኗር ዘይቤም ሆነ ከልማት ወደኋላ የቀረ ከሚባሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ዋነኞቹ ናቸው። አሁንም ድረስ ራቁት ሆነው የሚንቀሳቀሱ፤ በማደንና እርስ በርስ በመገዳደል የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። በተከታታይ ጊዜ ኋላቀር የሆነውን የመገዳደል ባህላቸውን ጎጂነት ግንዛቤ እናስጨብጣለን፤ በትራኮማና በሌሎች የጤና ችግሮች እየተሰቃዩ ያሉ ነዋሪዎችንም የህክምና ቡድን ይዘን በመሄድ ህክምና እንዲያገኙ እናደርጋለን፤ አልባሳትና የተለያዩ ቁሳቁሶችንም እዚህ ያለውን ማህበረሰብ በማስተባበር ድጋፍ እናደርግላቸዋለን።
አዲስ ዘመን፡- በወህኒ ቤቶችም የተለያዩ ሥራዎች እንደምትሠሩ ሰምተናል። እስቲ ስለዚህ ሥራችሁ በጥቂቱ ያጫውቱን?
ወይዘሮ ሶፊያ፡- በወህኒ ቤቶች በዋናነት የምንሠራው የግብረ-ገብ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው የሥነ-ልቦና ትምህርት ነው የምንሰጠው። ይህም ታራሚዎቹ ትክክለኛ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡና ከእስር ሲወጡ ከማህበረሰቡ ጋር በሰላም መኖር እንዲችሉ የሚያደርግ ነው። ሴት ታራሚዎች ጋር በተለይ ዕድሉ ሲገኝ የንፅህና መጠበቂያዎችን እንሰጣቸዋለን። ይህንንም የምናደርገው ከዚህ ቀደም ሴት እስረኞች የንፅህና መጠበቂ እጥረት ስላለባቸው ብርድልብሳቸውን ቀደው እንደሚጠቀሙ ሰምቼ ልቤ ክፉኛ ስለተነካ ነው። አንድ ክረምት ላይ እንዲያውም ጨርሶ ብርድልብስ የሌላቸው ሴት እስረኞች አጋጥመውናል። ስለዚህ ለእያንዳንዱ እየታጠበ ዳግመኛ መጠቀም የሚያስችል የታሸገ የንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) እናከፋፍላለን። ይህንን የንፅህና መጠበቂያ ደግሞ የሚሠሩት እኛ የምንረዳቸውና አሰልጥነን ሥራ የፈጠርንላቸው ሰዎች ናቸው። እስካሁን ገና ሁለት ወህኒ ቤቶች ላይ ብቻ ነው የሠራነው። በመጀመሪያው ዙር 60 ሴት ታራሚዎችን ፤ በሁለተኛው ደግሞ 40ዎቹን የግንዛቤ ማስበጫና ድጋፍ ነው ያደረግንላቸው።
ከዚህ በተጨማሪ ዝዋይ ላይ የጎዳና ልጆችን በመሰብሰብ ትምህርት የምናስተምርበት መርሃ ግብር አለ። በተለይ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ ጠንካራና ተከታታይ ሥራ ነው የሚሠራው። ልጆችን ብቻ ሳይሆን ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ እናቶችንም እንረዳለን። ይህም በጣም አበረታች ለውጥ እያመጣን ካለንበት ሥራዎች መካከል የሚጠቀስ ነው። እነዚህ እናቶች ከወንዶቹ በላይ ተጎጂ በመሆናቸው ነው በዋናነት ትኩረት የምናደርገው።
እንዳልኩሽ ከሴቶች ጋር መሥራት ከጀመርን በጣም በርካታ ዓመታት አስቆጥረናል። እንደእኔ የሴቶች ጉዳይ የሚያሳስባቸውና ሴቷ ተጠቃሚ እንድትሆን ፅኑ ፍላጎት ካላቸው የተለያዩ ሰዎች ጋር በየጊዜው ዓለምአቀፍ ጉባኤ እናደርጋለን። እስካሁን በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ በስፋት ተከናውኗል። በዚያ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ አገራት ሴት ኢትዮጵያውያን ተሰባስበን ሴት በአገር እድገት ያላትን ዋጋ ለሁሉም ማሳወቅና በተግባርም ማረጋገጥ በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ እንመክራለን። በተለይ ባህል የተማረችውንም ሴት ሳይቀር ተፅዕኖ የሚፈጥር እንደመሆኑ ሠርታ ማደግ፤ አገርን በብቃት መምራት እንደምትችል በተጨባጭ ለማሳየት እገዛ የምናደርግበት መድረክ ነው። ከዚህም አልፎ ጤነኛና ብቃት ያላቸውን አገር ተረካቢ ልጆችን የማፍራት ኃላፊነት በዋናነት የእኛ የእናቶች እንደመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ እንመክራለን።
በኢትዮጵያ ደግሞ ‹‹ቡና ጠጡ›› የሚል መርሃ-ግብር አለን። እርግጥ የዚህ መርሃ-ግብር መነሻው የማህበረሰባችን ቡና የመጠራራት የቆየ የማህበራዊ እሴት አካል ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ ይህ የቡና መጠጣት ሥርዓት የውይይት መድረክ የሚፈጥርና በዚህም ብዙ ችግሮቻችንን የምንፈታበት ትልቅ ባህላዊ እሴታችን ነው። እኛም ይህንን ባህላዊ የመገናኛ መድረክ በመጠቀም ሴቶች ያለባቸውን ችግር አቅርበው የመፍትሄ ሃሳብ እንዲመነጭ ይደረጋል፤ በየጊዜው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመምከር ግንዛቤ እንፈጥራለን። ላለፉት 17 ዓመታት በየሦስትና አራት ወራት በየጊዜው እየተገናኘን ቡና እየጠጣን ነው የምንመክረው። በቅርቡ ባካሄድነው የቡና ጠጡ መርሃ-ግብር አጀንዳ አድርገን ያነሳነው በወላጆችና በአዲሱ ትውልድ መካከል የአስተሳሰብ ክፍተት ላይ ነው ።
በተለይም ከዘመን አመጣሽ መጤ ባህሎች ተጋላጭነት እንዴት መታደግ እንደምንችል እንዲሁም ልጆቻችን በምን መልኩ ልናስተምር እንደሚገባ ሰፊ ውይይት አድርገናል። በዋናት በማህበራዊ ሚዲያው አማካኝነት በእምነትም ሆነ በባህል ውግዝ የሆነው ግብረ-ሰዶምያዊነት ተጋላጭ እየሆኑብን ስለሆነ እኛ በቂ እውቀት ይዘን እንዴት ልጆቻችን መታደግ እንደሚገባ በስፋት ተመካክረናል። ከዚህ ቀደም ደግሞ በባህል አልባሳት ትውልዱ በምን መልኩ ሊያዘወትር ይገባል? በሚል ርዕሰ ዙሪያ ውይይት ካደረግን በኋላ ለአንድ አራት ሴቶች ዲዛይን እንዲሠሩ ተደረገ። ትውልዱ በየዕለቱ ሊለብሳው በሚችል መልኩ በዘመናዊ መንገድ ተሠርተው ለገበያ ቀርበዋል።
አዲስ ዘመን፡- እንደማንኛው ኢትዮጵያዊ እናት ልጆችዎን በማሳደግና ለቁምነገር ለማድረስ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል፤ ግን ደግሞ ተስፋ ሳይቆርጡ ያልዎትን አቅምና ችሎታ ወገኖችን ለመርዳት ተጠቅመው ውጤታማ ሆነዋል። ለመሆኑ ይህንን ማሳካት የቻሉበት የተለየ ምስጢር ይኖር ይሆን?
ወይዘሮ ሶፊያ፡– እውነት ለመናገር ስለእኔ ማንነትና እዚህ መድረስ ሳስብ ከሁሉ በላይ ፈጣሪዬን ነው ማመስገን የምፈልገው። ምክንያቱም እግዚአብሔርን ከሚፈራ ቤተሰብ ስለመጣሁ እሱን በመፍራትና እንደሚገባኝ ቤተሰቤን እየመራሁ የኖርኩት። በሁለተኛ ደረጃ ለእኔ ሕይወት እንደትልቅ አርዓያ የማየውና መሠረት የጣለው ወላጅ አባቴ ነው። ምክንያቱም አባቴ ብዙ ሰዎች ያላገኙትን በፍቅርና በእውቀት ቀርፆ ነው ያሳደገኝ። ማንኛውም ነገር እንደምችልና በራሴ እንድተማመን ያበረታታኝም ነበር። ሴት በመሆኔ ተስፋ እንዳልቆርጥ ይደግፈኝ ነበር። በመሠረቱ ለእኔ ልጆቼን ማሳደግና ለቁም ነገር ማድረሱ በራሱ ከዲግሪም ሆነ ከስልጣን በላይ ነው። ልጆቼ አሁን ለደረሱበት ከፍተኛ ቦታ የእኔ መስዋዕትነት መክፈል ግድ ስለነበር ነው። እኔ በወቅቱ ራሴ ላይ ብቻ ባተኩር ኖሮ አሁን የደረሱበት ቦታ አይደርሱም ነበር።
ልክ እንደእኔ ብዙ እናቶች ጥቅማቸውንም ሆነ ፍላጎታቸውን ለቤተሰባቸው በመስጠትና በመኖር ለሌሎች መስዋዕት ሆነዋል። ያ ምንአልባት ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰው ባለስልጣን እኩል በማህበረሰብ ዘንድ ባያስመለክተንም ያንን ከፍተኛ ባለስልጣን ያለበት ደረጃ ያደረስነው እኛ እናቶች ስለመሆናችን ሊዘነጋ አይገባም። ብዙ ጓደኞቼ ዶክተርና ሌላም ነገር መሆን ችለዋል፤ እኔም ከፈጣሪ የተሰጠኝ ልጆች በመልካም ሥነ-ምግባር የማነፅና የማሳደግ ተልዕኮ በስኬት በማጠናቀቄ በዚህ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል።
ማንኛዋም እናት የጎላ የገንዘብ ችግር ከሌለባት በስተቀር ልጆቿን በሞግዚት እንዲያድጉ መፍቀድ የለባትም። ምክንያቱም ራሷ ቀርፃ ያላሳደገችው ልጅ ነገር አገር ተረካቢ ትውልድ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ይህ ማለት ሴት መማርና ወጥታ መሥራት የለባትም እያልኩኝ አይደለም። ሴት በጣም መማርና ራሷን ማሳደግ እንዳለባት አምናለሁ። ግን ደግሞ ከዚሁ ጎን ለጎን ወደዚህ ምድር ላመጣቻቸው ልጆች የበለጠውን ኃላፊነት ወስዳ ማሳደግ ይገባታል ባይ ነኝ። ደግሞም የትኛውም ሴት ብትሆን ልጆቿን ራሷን መስዋዕት ማድረጓ ሊቆጫት አይችልም። አሁን እኔ ለልጆቼ ያን ያህል መስዋዕትነት ከፍዬ በማሳደጌ ልጆቼ ከፍተኛ የሚባል ደረጃ ደርሰውልኛል፤ አገራቸውን የሚወዱና ወገኖቻቸውንም የሚደግፉ ናቸው። በሚሠሩት ሥራ ለበርካቶችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። ስለዚህ ትምህርት ቤት ብቻ በመሄድ እውቀት አይገኝም። በየዕለት ተዕለት ኑሯችን ራሳችንን ማስተማርና ማሳደግ ይቻላል ብዬ አምናለሁ። እኔ እስካሁን ተማሪ ነኝ ብዬ ነው የማስበው። መጽሐፍት በማንበብም ሆነ በሕይወት ተሞክሮ መማር ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ድርጅታችሁ በጦርነት የተጎዱና የተደፈሩ ሴቶችን እየረዳ መሆኑ ይታወቃል። እስኪ ስለ ሥራችሁ ያብራሩልን?
ወይዘሮ ሶፊያ፡- ስለእነዚህ ሰዎች በመጀመሪያ የሰማሁት ጎንደር ጋይንት አካባቢ ሄዶ ሴቶች ያሉበትን ሁኔታ ከተመለከተ ሰው ነው። እነዚህ የተደፈሩ ሴቶች የደረሰባቸው በደል አልበቃ ብሎ በማህበረሰቡ ተገልለው በር ዘግተው በችግር መቀመጣቸውን ስስማ ክፉኛ ልቤ አዘነ። በምን መልኩ ላግዛቸው እንደምችል አሰብኩና ዓለምአቀፉ ቤዛ ኢንተርናሽናል ማህበር አባላትን በዙም ስብሰባ ጠርቼ አማከርኳቸው። ሁላችንም ገንዘብ አዋጣንና ጋይንትና ንፋስ መውጫ ባለን ጽሕፈት ቤታችን አማካኝነት ገንዘብና ‹‹አንቺም አርበኛ ነሽ፤ አሸንፈሻል›› የሚል ጽሑፍ ያለው ሜዳሊያ እንዲደርሳቸው ተደረገ። ይህንን ያደረግንበት ምንክያት እነዚህ በአሸባሪ ቡድኑ የተደፈሩ ሴቶች በጦርነት ሜዳ ላይ ከተዋጋው ወታደር እኩል ለአገራቸው ዋጋ የከፈሉ ናቸው ብለን ስለምናምን ነው።
እነሱ ላይ የደረሰው ነገር የጦርነቱ ጠባሳ ነው። ልክ ወታደር አገሩን ለማዳን ሲል አካሉን እንደሚያጣ ሁሉ እነዚህም ሴቶች በወራሪው ኃይል ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሆኖም በጥቃቱ አልሞቱም፤ አሸንፈው ዛሬም በሕይወት መኖራቸው ትልቅ ድል እንደተቀናጁ ነው ሊቆጠር የሚገባው። የሥነልቦና ባለሙያዎችን በመላክም የተጎዳ ሥነልቦናቸው እንዲጠገንና ያለእፍረት ቀና ብለው እንዲሄዱ እገዛ አድርገንላቸዋል። ማህበረሰቡም እነዚህ ሴቶች ለአገር የከፈሉት ዋጋ መሆኑን ተገንዝቦ እነሱን እንዳያገል ተከታታይ ትምህርት ሰጥተናል። በዚህ ስልጠና ላይ 100 የሚሆኑ ሴቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበን 70ዎቹ ናቸው የተሳተፉት። እኛ በነበረው አለመረጋጋት በአካል እዚያ ባንገኝም በተወካዮቻችን አማካኝነት ለእነሱ ያለንን ፍቅርና ያለንን አክብሮት የሚገልፅ ደብዳቤ ልከን እንዲነበብላቸው ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ተገዳ ለሦስተኛ ዙር ስለገባችበት ጦርነት ያለዎት ምልከታ ምንድን ነው? በዚህች አገር ዘላቂ ሰላም ለማምጣትስ ምን መሠራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ወይዘሮ ሶፊያ፡– ጦርነቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ጎድቷል። አርሶአደሩም ምርቱን አጥቷል፤ ነጋዴው ኪሳራ ውስጥ ገብቷል፤ ንፁሃን ከየቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል፤ ቆስለዋል፤ ሞተዋል። በተለይ የሴቶች ጉዳት እጅግ ከባድ ነው። በዚህ ጦርነት እናት ዘጠኝ ወር ተሸክማ፣ አምጣ ወልዳና አጥብታ፤ ለፍታ ያሳደገቻቸውን ልጆቿን አጥታለች፤ የቤቷ መሪ የሆነው ባሏን መስዋዕት አድርጋ ብቻዋን ቀርታለች። በዚህም ዘላቂ ለሆነ የሥነ- ልቦና ጉዳት ሰለባ ሆናለች። አርሶ እና ሸምቶ የሚያበላቸውን ባለቤታቸውን አጥተው ለረሃብና ለእንግልት ተዳርገዋል። እነዚህ ሰዎች ልባቸው በልጅ ኀዘን የተመታና በመንፈስም የጎበጡ ናቸው። እንዳልኩሽ ደግሞ ይህ ሁሉ ግፍ ደርሶባቸው ሳለ የሚረዳቸው ወገን አጠገባቸው የለም። አሁን በየከተማውና ሜዳ ላይ ወድቀው ሲለምኑ የምናያቸው ሴቶች ኢትዮጵያ ተገዳ በገባችበት ጦርነት ምክንያት ቀያቸውን ለቀው የወጡ ናቸው። በጦርነቱ ልጇንና ባሏን ማጣቷ አልበቃ ብሎ አሁንም የሚጠባ ሕፃን ይዛ በሰቆቃ እየተገረፈች ያለችው ይህችው ምስኪን እናት ናት። ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ተደፍራ ላላስፈላጊ እርግዝና እና በሽታ የተዳረገችውንም ማሰብ ከባድ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የበኩሉን ጥረት ቢያደርግም በአሸባሪው ቡድን በኩል የሰላም ፍላጎት ባለመኖሩ ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት ጀምሯል። ይህን የሕወሓትን እብሪት እንዴት ያዩታል ?
ወይዘሮ ሶፊያ፡- እኔ ፖለቲከኛ ስላልሆንኩኝ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አልፈልግም። ግን ደግሞ ለእዚህ ቡድን ጦርነት እንዲያቆሙ ነው ጥሪ ማስተላለፍ የምፈልገው። እንዳልሽው ወደ ጦርነት ላለመግባት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት በመንግሥት በኩል እየተደረገ የነበረውን ጥረት ሁሉ አደንቃለሁ። ሰላም ለማስፈን ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የተሠሩ የልማት ሥራዎችም መንግሥትን የሚያስመሰግኑ ናቸው። በተለይ በአረንጓዴ ልማትና በምግብ ራስን ለመቻል የተሠሩት ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡-ቀረ የሚሉት ማስተላለፍ የሚፈልጉት ሀሳብ ካለዎት ዕድሉን ልስጥዎት?
ወይዘሮ ሶፊያ፡– ከዚህ ጋር አያይዤ መናገር የምፈልገው ነገር በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ስለመጣው ሌብነት ጉዳይ ነው። በግሌ በግልፅ ያጋጠመኝ ነገር ባይኖርም በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች የሚያልፉበትን ነገር በየቀኑ አያለሁ። ከዚህ ከነበረው በበለጠ ሁኔታ ሁሉም ነገር በጉቦ ነው እየተሠራ ያለው። የትኛውም ተቋም ላይ ሄደሽ ያለጉቦ የሚገኝ አገልግሎት የለም። ይህ ደግሞ እንደሕዝብ ትልቅ የአስተሳሰብ አዘቅት ውስጥ ነው የከተተን። አሁን እኮ አይን ያወጣ ሌብነትነው በመንግሥት ባለሥልጣናትና ፈፃሚዎች ላይ የምናየው።
ለእነዚህ ጉቦ ለሚጠይቁ ሁሉ ሰዎች ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር ከሕዝብ ጉሮሮ ነጥቆ ከመብላት አፀያፊ ተግባራቸው እንዲታቀቡ ነው። ሞኝነት ነው እንጂ ሕዝብ እያስራቡና እያስቸገሩ ለብቻ የትም መድረስ አይቻልም። ያማረሩት ሕዝብ ነገ መልሶ እነሱ ላይ መነሳቱ ስለማይቀር ከዚህ ተግባራቸው በአፋጣኝ ሊወጡና ሕዝቡን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ነው። ደግሞም ከሕዝብ አግበስብሶ በስርቆት የተወሰደ ነገር ሰላምም ሆነ በረከት የለውም። ሁልጊዜ የህሊና ወቀሳ የሚያስከትል በመሆኑ ሌባው ግለሰብ ጤና አይኖረውም። በመሠረቱ ሌብነት ለራስ ዋጋ አለመስጠት ነው። ስለዚህ ከዚህ መጥፎ ተግባር መውጣት ለራስም ህሊና ነፃነት ይሰጣል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ሶፊያ፡- እኔም ሃሳቤን እንድገልፅ ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም