ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር መድረክ ፕሪሚየርሊግ ተሳታፊ ከመሆን አልፎ ቻምፒዮንና የዋንጫ ተፎካካሪ መሆን የቻለው ፋሲል ከነማ አገሩን ወክሎ በአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ ሆኗል። በተለይም አፄዎቹ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫና ቻምፒዮንስሊግ ውድድሮች አገራቸውን በመወከል በተሳትፎ ደረጃ የተሻለ ስኬት አስመዝግበዋል። በነዚህ ሦስት ዓመታት ሁለት ጊዜ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ አንድ ጊዜ ደግሞ በቻምፒዮንስሊግ መድረክ መቅረብ ችለዋል። ካቻምና የፕሪሚየርሊጉ ቻምፒዮን በመሆን በአፍሪካ ቻምፒዮንስሊግ ኢትዮጵያን የወከሉት አፄዎቹ አምና ሁለተኛ ሆነው በማጠናቀቅ ዘንድሮ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ መሆናቸው ይታወቃል።
በዚህ መድረክ የቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ባለፈው ሳምንት በባህርዳር ስቴድየም ያደረጉት አፄዎቹ ካለፉት ዓመታት የተሻለ አጀማመር አሳይተዋል። አፄዎቹ ባለፈው አርብ የቡሩንዲውን ክለብ ቡማሙሩን 3ለ0 በማሸነፍ ጣፋጭ ድል ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ዛሬ የመልሱን ጨዋታ ያከናውናሉ። አለምብርሃን ይግዛው፣ ፍቃዱ አለሙ፣ ታፈሰ ሰለሞን አፄዎቹ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጉዟቸውን በድል እንዲጀምሩ ግቦችን ከመረብ ያሳረፉ ተጫዋቾች ናቸው። ባለ ድሉ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽም አፄዎቹ በጨዋታው የነበራቸው የበላይነት የጠበቁትና ቡድናቸው ከዚህም የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ አቅም እንዳለው ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት ሰጥተዋል።
አፄዎቹ ዛሬ ከቡማሙሩ ጋር ላለባቸው የመልስ ጨዋታ በአዲስ አበባ ሲዘጋጁ የቆዩ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት ጨዋታው ወደ ሚካሄድበት ገለልተኛ አገር ታንዛኒያ አቅንተዋል፡፡ ቡሩንዲ የመልሱን ጨዋታ ለማስተናገድ በካፍ ፍቃድ የተሰጠው ስቴድየም የሌላት በመሆኑ ቡማሙሩ ክለብ አፄዎቹን በገለልተኛ ሜዳ ለመግጠም ተገደዋል። የመልሱ ጨዋታ የሚካሄደው ደግሞ በታንዛኒያ አዛም ኮምፕሌክስ ሜዳ ላይ ነው፡፡ ጨዋታው በገለልተኛ ሜዳ መካሄዱ አፄዎቹ በሜዳቸው በሰፊ ግብ ልዩነት ከማሸነፋቸው ጋር ተደምሮ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ይጠበቃል፡፡ አፄዎቹ ይህንን ጨዋታ በድምር ውጤት የሚያሸንፉ ከሆነ በቀጣይ የቱኒዚያውን ሴፋክሲየንን እንደሚገጥሙ አስቀድሞ የወጣው መርሐ ግብር ይጠቁማል።
የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ዋና አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ከክለቡ ማህበራዊ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ‹‹ባህርዳር ላይ ጨዋታችንን ከማድረጋችን በፊት ከተጫዋቾቼ ጋር ተነጋግረናል። የተነጋገርነውም በተቻለ መጠን በሜዳችንና በደጋፊያችን ፊት ውጤቱን ጨርሰን ለመውጣት የምችለውን ለማድረግ ነበር። በተነጋገርነው መሠረትም እቅዳችንን አሳክተናል። ዛሬ የምናደርገውን ጨዋታም ቢቻል አሸንፈን አለበለዚያም ውጤታችንን አስጠብቀን የምንወጣበትን መንገድ ነው የምናስበው፣ ነገር ግን ዋነኛው አላማችን ቡድናችን ጨዋታውን አሸንፎ ወደሚቀጥለው ዙር እንዲያልፍ ማስቻል ነው። ያንን ለማድረግ ሁላችንም ዝግጁ ነን›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከመጀመሪያው ጨዋታ ውጤት አንፃር የዛሬው ጨዋታ ያለቀ ሊመስል ይችላል ያሉት አሰልጣኙ፣ የእግርኳስ ውጤቶች በባህሪያቸው አይታወቁምና ቡድናቸው በጥንቃቄ እንደሚጫወት ገልፀዋል፡፡ በቡድናቸው ቅርፅ ዙሪያ ግን ጨዋታው እስከሚደረግበት ሰዓት ድረስ የተጫዋቾችን ደህንነት ተመልክተው መጨረሻ ላይ እንደሚወስኑ አስረድተዋል፡፡
የቡድኑና አጠቃላይ የተጫዋቾቹ መንፈስ እንዲሁም መነቃቃት ጥሩ ነው ብለው እንደሚያስቡ የገለፁት አሰልጣኙ፣ የመጀመሪያውን ጨዋታ ከማድረጋቸው በፊትም የተጫዋቾቹ የመጫወት ፍላጎትና ውጤት ለማምጣት ያላቸው ተነሳሽነት በጣም ጥሩ እንደነበር አስታውሰዋል። በዛሬው ጨዋታም ያንን መንፈስ ለማስቀጠል በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
‹‹በ2015 የውድድር ዘመን ካቀድናቸው ዋነኛ እቅዶች መካከል አንዱ አሁን በምንወዳደርበት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ረዥም የሚባል ጉዞን ማድረግ ነው። በዚህ መነሻም የመጀመሪያውን ዘጠና ደቂቃ በጥሩ ውጤት ጨርሰናል። በቀጣይም የሚኖሩን ጨዋታዎችን በድል በመወጣት በክለቡ የታሪክ መዝገብ ላይ አዲስ ነገር ለማስፈር እናስባለን። ነገር ግን ቅድሚያ የምንሰጠው በእጃችን ላይ ያሉ ጨዋታዎችን በድል ለመቋጨት በትኩረት መንቀሳቀስ ላይ ነው። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ በተጫዋቾችም ሆነ በአሰልጣኞች ውስጥ ጥሩ መነቃቃት አለ›› በማለት አሰልጣኙ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ቢወክሉም የመጀመሪያዎቹን ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ግን ማለፍ እንዳልቻሉ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ግን ይህን ታሪክ ለመቀየር ጥሩ አጀማመርና ተነሳሽነት አሳይተዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2015 ዓ.ም