መንግሥት ከ2012 በጀት አመት ጀምሮ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። በዚህም የአስር አመት መሪ እቅድ ወጥቶ እየተሠራ ይገኛል። የአገር የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስቀጠል፣ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ምህዳር እንዲሁም ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ማሻሻያው አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጣቸው ክፍለ ኢኮኖሚዎች ማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ ይጠቀሳሉ። የማዕድን ዘርፍ በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር የሚገቡ የማዕድን ውጤቶችን፣ የማዕድን ኢንዱስትሪ ግብአቶችን በአገር ውስጥ መተካትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ለአገር ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጥቂቶቹ ናቸው። ዘርፉን በዋናነት የሚመራው ማዕድን ሚኒስቴር ይህን መሠረት በማድረግ ዘርፉ ለኢትዮጵያ የመጪዎቹ አመታት የብልጽግና ጉዞ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እንዲሁም በ2022 ዓ.ም የማዕድን ሀብት የብልጽግና መሠረት ሆኖ ማየት የሚል ተልዕኮ ይዞ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ሚኒስቴሩ በማዕድን ክፍለኢኮኖሚ የ2015 በጀት አመት የእቅድ ሰነዱ አመልክቷል።
በዘርፉ የተሳኩ ተግባራትን ለማከናወን በ2014 በጀት ዓመት በሪፎርምና በሠራቸው ሥራዎች ተጨባጭና ትልቅ ተስፋ ያላቸው ውጤቶች ማስመዝገቡን ሚኒስቴሩ በሰነዱ አስታውሷል። ያለፈ ስኬቱን መነሻ በማድረግ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አዘጋጅቷል። ለበጀት አመት እቅዱም የተለያዩ መነሻዎችን መሠረት አድርጓል።
አንዱ መነሻው የ2014 በጀት ዓመት አጠቃላይ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተሰጡ ግብረ- መልሶችን እንደ ግብዓት ተጠቅሟል። እነዚህ መሠረቶች ለአዲሱ በጀት አመት የእቅድ ሥራው የነበሩበትን ክፍተቶች ለመለየትና አስፈላጊዎቹን የማስተካከያ እርምጃዎች ለመውሰድ በማገዛቸው የተሻለውን አሠራር በእቅዱ በማካተትና ክፍተቶቹን በማረም የዘርፉን ራዕይ አንግቦ ተቋማዊ ተልዕኮ ለመፈፀም ተዘጋጅቷል።
ከሰነዱ መረዳት እንደሚቻለው፤ የዘርፉን የቀጣይ አስር አመታት ዕቅድ መሠረት በማድረግና በአዲስ መልክ ፕሮግራሞችን በመቃኘት በ2015 በጀት ዓመት ለመተግበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል። በዚሁ መሠረትም የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ በአምስት ፕሮግራሞች ተዘጋጅቷል። ይህም የዘርፉን ተቋማዊ አቅምና ብቃት የማጎልበት፣ የስነ-ምድር መረጃን ለልማትና ለኢንቨስትመንት የማመንጨት፣ የማዕድን ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት፣ የማዕድን፣ ነዳጅ እና የጂኦተርማል ኢንቨስትመንትን የማስፋፋትና የማጎልበት እንዲሁም የማዕድን፣ ነዳጅ እና ጂኦተርማል ምርት አቅርቦት ድጋፍ ፕሮግራሞች በሚል ተከፋፍሎ ተዘጋጅቷል። ለየፕሮግራሙ ስኬትም አግባብነት ያላቸውን ውጤት አመላካች ተግባራትን ታሳቢ ጉዳዮችንም አካቶ ቀርቧል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በእጥረት የተለዩ ጉዳዮችን የማሻሻል እቅዶችንም በ2015 በጀት አመት አቅዱ አካትቷል። ከእነዚህም መካከል የማዕድን ልማት የሚካሄድባቸው ቦታዎችን የፀጥታ ስጋት ለመፍታት ከፌዴራልና የክልል የፀጥታ መዋቅሮች ጋር እንዲሁም ከአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ጋር በቅርበት የሚሠራውን ሥራ እና የማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚውን ውጤታማነት ለማጎልበት እንዲሁም ከአደረጃጀት ጋር ተያይዞ ያሉትን ክፍተቶች ለመቅረፍ ከክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር፤ የቁልፍ ውጤት አመልካች ተግባራትን በሚመለከት ያሉ ውስንነቶችን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር በመወያየት ዕቅዱን ወቅታዊ ለማድረግ በጋራ መሥራት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች በመንግሥትና በኩባንያዎች አቅም እንዲገነቡ በትኩረት መሥራት የሚሉት ይገኙበታል።
በበጀት ዓመቱ የክፍለ ኢኮኖሚውን ውጤታማነት ለማጎልበት የሚከተሉት የትኩረት አቅጣጫዎችም በሰነዱ ተመላክተዋል፤ የወጪ ንግድ ማዕድናትን በዓይነት፣ በመጠንና በብዛት ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ፤ የማዕድን ኢንዱስትሪ ግብአቶችን እና የማዕድን ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት በተለይም የድንጋይ ከሰል፣ ማዳበሪያ፣ ብረት እና የግንባታ ማጠናቀቂያ (finishing Materials) ግብአቶች ላይ በልዩ ትኩረት ይሠራል።
ዘመናዊ የማዕድናት ግብይት ሥርዓት መዘርጋት፣ በዘርፉ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የሥነ-ምድር መረጃ በጥራትና በሽፋን በማበልፀግ የፕሮጀክት አዋጭነትን የሚያሳዩ የማስተዋወቅ ሥራዎች በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መዳረሻዎች በስፋት በመሥራት ግዙፍ ኩባንያዎች በዘርፉ ማሰማራት የሚሉትም ከትኩረት አቅጣጫዎቹ መካከል ይገኙበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ በዘርፉ የተሰጡ ነባር የማዕድን ልማት ፕሮጀክቶችን ድጋፍና ክትትል በማጎልበት የፕሮጀክቶችን የውል አስተዳደርና አፈፃፀም ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት መሥራት፤የሚከናወኑ ኢንቨስትመንቶች የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ያጎለበቱ እንዲሆኑ ማድረግ፤ የማዕድናት ዕሴት ማበልፀጊያ ኢንተርፕራይዞችን ማስፋትና ማጠናከር፤ በባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከክልሎች ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር የመዘርጋት ሥራዎችን መሥራት፣ በክፍለ ኢኮኖሚው የተማረ የሰው ኃይል በጥራትና በብዛት እንዲኖር መሥራት የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
ቁልፍ ከሚባሉ ባለድርሻ አካላት ጋርም ቅንጅታዊ ሥራ ለመሥራት ስላስቀመጠው አቅጣጫም ሰነዱ እንዳመለከተው፣ የማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚ ለአገር ሁለንተናዊ እድገት ያለውን አስተዋጽኦ እንዲወጣ፣ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ የማዕድናት ምርትን በብዛት፣ በጥራትና በዓይነት ማምረት፣ ከውጭ የሚገቡ የማዕድን ኢንዱስትሪ ግብአቶችና የማዕድን ውጤቶችን በአገር ውስጥ መተካት እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራ ተልዕኮዎችን ለማሳካት ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት የሆኑት ክልሎች፣ ኩባንያዎች፣ የባህላዊ ማዕድናት አምራቾች እንዲሁም ልዩ ልዩ ተግባርና ኃላፊነት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት ናቸው።
ከዚህ አኳያ የክልል ባለድርሻ አካላትን በሚመለከት ከክልል ቢሮዎች፣ የከተማ መስተዳድሮች ጋር በመሆን በጋራ ከዕቅድ ዝግጅት እስከ አፈፃፀም መሥራት፣ የባህላዊ ማዕድናት አምራቾችንና የተለያዩ ባለፈቃድ ኩባንያዎችን በመደገፍ ለሥራ ምቹ ሁኔታዎችን እንዲፈጠር ማድረግ፣ በዘርፉ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ሕገወጥ የማዕድናት ግብይትን በመቆጣጠር የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባ ተገልጿል።
ኩባንያዎች በገቡት የውል ስምምነት መሠረት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚጠበቅ ሲሆን፣የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በየወቅቱ በመከታተል የጋራ መፍትሔ በመስጠት ውጤታማነታቸውን ማጎልበት፤ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ማዕድናትን በማምረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙትን የባህላዊ ማዕድናት አምራቾችን አሠራራቸውን፣ አመራረታቸውን እንዲሁም አደረጃጀታቸውን ማሻሻል ትልቅ ትኩረት መሰጠቱ በሰነዱ ተጠቅሷል።
ይህን የሚያግዝ የባህላዊ ማዕድናት አምራቾች አደረጃጀት፣ አመራረትና አሠራር ማሻሻያ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ትግበራ መግባቱ ተመልክቷል። በመሆኑም ለዚህ የሚያግዙ ማሽነሪዎችን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል፤ በባህላዊ የማዕድን ማውጣት ዙሪያ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመለየትና አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም ለፖሊሲ ግብአትነት ጥናትና ምርምር እንዲደረግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተደረገውን የጥናት ስምምነት አጠናክሮ ማስቀጠል፤ ከትምህርት ሚኒስቴር እና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ በመሥራት የማዕድን ዘርፍ በቴክኖሎጂና በምርምር እንዲደገፍና ዘርፉ በተማረ የሰው ኃይል እንዲመራ የማዕድን የትምህርት ክፍሎች ተጠናክረው ጥራት ያለው የተማረ የሰው ኃይል በስፋት ማበርከት እንዲችሉ በጋራ መሥራት የሚልም በሰነዱ ተመልክቷል።
ሚኒስቴሩ የማዕድንና ነዳጅ ሥራዎች ግልጸኝነት የሰፈነበት፤ ዘመናዊነትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው እንዲሆን ተቋማዊ የማስፈጸምና የመፈጸም አቅም አድጎና በልጽጎ ለዘርፉ ዓበይት ተግባራት ውጤታማነት የተሻሻለና ብቃቱ የተረጋገጠለት የመልካም አስተዳደር ችግሮች የቀነሱበት፤ ዘላቂነት ያለው ተቋም ማድረግ ከዋና ዓላማ ተግባራቶቹ መካከል መሆኑን በሰነዱ አብራርቷል።
ሚኒስቴሩ በበጀት አመቱ ያቀዳቸውን ሥራዎች ለመፈጸምም የያዘውን በጀትም ከእቅዱ ጋር አያይዞ በዝርዝር አስቀምጧል። የበጀት አመቱን ዕቅድ ለመፈፀም ለመደበኛ ሥራዎች መተግበሪያ ብር60 (ስልሳ) ሚሊዮን እንዲሁም ለካፒታል ፕሮጀክቶች ብር 60 (ስልሳ) ሚሊዮን በድምሩ ብር 120.00፣ ሚሊዮን በጀት ተይዟል። በተጠሪ ተቋማት ማለትም ለኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት መደበኛ ሥራዎች መተግበሪያ ብር 85 ነጥብ 162 ሚሊዮን፣ ለካፒታል ብር 200 (ሁለት መቶ) ሚሊዮን በድምሩ ብር 285 ነጥብ 162 ሚሊዮን የተያዘ ሲሆን፣ ለማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መደበኛ ሥራዎች መተግበሪያ ብር 81 ነጥብ 04 ሚሊዮን፣ ለካፒታል ብር 60 ሚሊዮን በድምሩ ብር 141ነጥብ04 ሚሊዮን መያዙ ተጠቁሟል። በአጠቃላይ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና በተጠሪ ተቋማት ለሚከናወኑ መደበኛ ሥራዎች መተግበሪያ ብር 226ነጥብ20 ሚሊዮን እንዲሁም ለካፒታል ሥራዎች ማስፈፀሚያ ብር 320.00 ሚሊዮን በአጠቃላይ ብር 546ነጥብ20 ሚሊዮን በጀት ተደግፏል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መልካም አጋጣሚዎች፣ ስጋቶችና የማስፈጸሚያ ስልቶች ብሎ በሰነዱ ካሰፈራቸው መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል። በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማዕድን ክፍለ ኢኮኖሚ በተሰጠው ልዩ ትኩረት መንግሥት ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ዘርፉን ለመደገፍ ቁርጠኝነት አሳይቷል።
ኢትዮጵያ ዕምቅ የማዕድን ሀብት ያላት አገር መሆኗ፤ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልጉ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ፍላጎት መጨመር፤ አንዳንድ ማዕድናት በዓለም ላይ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ በመልካም አጋጣሚ ይጠቀሳል። በስጋት ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከልም በማዕድን አምራች አካባቢዎችና ኩባንያዎች የሚከሰት የፀጥታ ችግር፤ ሕገ-ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ መኖር፤ ወደ ምርት ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ ፍቃዶች በሚፈለገው ፍጥነት ወደ ምርት አለመግባታቸው እና የኩባንያዎች የአቅም ውስንነት፤ ከፍተኛ ችግሮች ላለባቸው የማዕድን ውጤት አምራች ኢንዱስትሪዎች በአገር ውስጥ የማይገኙ የግብዓት፣ የአላቂ ዕቃዎች እና ለመለዋወጫዎች የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ግቦችን ሊያሳኩ የሚያስችሉ ብሎም ሊያጋጥሙ ይችላሉ የተባሉትን ስጋቶችን በመቀነስ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የሚከተሉትን የመፍትሄ አቅጣጫዎች መተግበር ወደ ውጤታማ አፈጻጸም ሊያመጣ እንደሚችል ሚኒስቴሩ ያመነባቸውንም እንደሚከተለው አስቀምጧል። የፀጥታ ችግር እንዲሁም የሕገወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድ በተመለከተ ማዕድን የሚመረትባቸው ቦታዎች ከሚመለከተው ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ እንዲሁም ከክልል የፀጥታ ተቋማት ጋር እየተሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል፣ እንዲሁም የግብይት ማዕከላት በአቅራቢያቸው እንዲከፈቱ ከሚመለከታቸው ጋር መሥራት፤ ኩባንያዎች በገቡት የውል ግዴታ መሠረት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን ማጠናከር፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሬ የሚያገኙበት ሁኔታዎች ላይ ከሚመለከታቸው ጋር በቅርበት መሥራት የሚሉት በዝርዝር ሰፍረዋል።
2015 በጀት አመት በዘርፉ ፕሮግራሞች፣ ዋና ዋና ውጤት አመልካች ተግባራትና ግቦች እንዲሁም የሚጠበቁ ውጤቶች የበለጠ እንዲጎለብቱ ከተጠሪ ተቋማት፣ ከክልሎችና ከከተማ መስተዳድር የዘርፉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት የማዕድን ክፍለ-ኢኮኖሚው በአገራዊ ብልፅግና ያለውን ፋይዳ ለማሳደግ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ሚኒስቴሩ አመላክቷል።
የማዕድን መረጃዎች በአግባቡ እንዲሰበሰቡ፣ እንዲጠበቁ፣ ለተጠቃሚዎች እንዲቀርቡ፤ ለማዕድን ፍለጋና ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የማዕድን ኢንቨስትመንትን ማበረታታት፣ በማዕድን፣ ፔትሮሊየምና ጂኦተርማል ፍለጋና ልማት ለሚሰማሩ የግል ባለሀብቶች ፈቃድ በመስጠት፣ ባለሀብቶቹ በገቡት ውል መሠረት ሥራቸውን ማካሄዳቸውንና የክፍያ ግዴታቸውን መፈጸማቸውን በመቆጣጠር፣ በባሕላዊና በአነስተኛ ደረጃ የሚመረቱ የከበሩ ጌጣጌጥ ማዕድናት ግብይት ሕጋዊ መስመር እንዲይዝ በማድረግ፤ የማዕድንና ተፈጥሮ ጋዝ ልማትን ለማፋጠን የሚረዱ የምርምርና የማሠልጠኛ ተቋሞችን እንደ አስፈላጊነቱ በማቋቋም ሚኒስቴሩ በአዋጅ የተሰጠው ስልጣንና ተግባራት እንደሆነ በሰነዱ ተብራርቷል።
ለምለም ምንግሥቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2015 ዓ.ም