አዲሱን 2015 ዓ.ም ከጀመርን ቀናቶች ተቆጥረዋል። በየዘመናቱ በተለይም አሁን ካለንበት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ግማሽ ምዕተ ዓመት ወደ ኋላ ተመልሰን የነበሩ ኩነቶችን በየሳምንቱ የሚያስታውሰን የአዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን የቆዩ ዘገባዎችን ይዞ ቀርባል። በ1962 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ ታትመው ለንባብ ከበቁ የአዲስ ዘመን ጋዜጦች አስደናቂ የሆኑ ዘገባዎችን በዛሬው አምዳችን መርጠን አቅርበናል። እነዚህ ቆየት ያሉ የጋዜጣው ዘገባዎች ዛሬ ላይ ሆነን ስናነባቸው የሚያስደምሙ ናቸው። ከነዚህ መካከል፤ ዝንጀሮ ሰው በላ የሚለው ዜና ይገኝበታል። ሣር፣ ቅጠላ ቅጠል እና ፍራፍሬ የሚበላው ዝንጀሮው ምን አጥቶ ነው? ሰው ጋር የሚደርሰው የሚያስብል ክስተት ነው። ቀደም ብሎ ወደ 30 የሚደርሱ በጎችና ፍየሎችን በልቶ የነበረው ዝንጀሮ ነው፤ አደጋው ሲያድግ ሰው ወደ መብላት የተሸጋገረው።ይህም ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ያለማድረጋቸው ውጤት መሆኑን ዘገባው ይነግረናል። የአንበሳ አውቶቡሶች ማኅበር ተጨማሪ አውቶቡሶችን ለማስመጣት ማቀዱን መዘገቡም ባለፈው ሳምንት ወደ ሸገር ከገቡት አዳዲስ አንበሳ አውቶቡሶች ጋር የሚመሳሰል በመሆኑ መርጠነዋል።ሌሎች ዘገባዎችንም አካተን እንድታነቧቸው እነሆ ብለናል።
ዝንጀሮ ሰው በላ
ጅማ (ኢ ዜአ)፡- በከፋ ጠቅላይ ግዛት በሊሙ ኮሣ ወረዳ ግዛት በርቄ በተባለው ቀበሌ አንድ ዝንጀሮ የ፪ ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድ ልጅ መብላቱ ተነገረ።
ዝንጀሮው ሕፃኑን ልጅ ከበላ በኋላ በተጨማሪ አንዲት የ፫ ዓመት ዕድሜ ያላት ልጅ ለመብላት ሲሞክር ሰው ደርሶ አድኗታል።ሆኖም ልጅቷን ለመብላት መሬት ጥሎ በመቦጫጨቅ የመቁሰል አደጋ ያደረሰባት መሆኑ ከቀበሌው መልከኛ ተገልጧል ሲል የወረዳው ግዛት ጸሐፊ አቶ ለማ አዱኛ ገለጡ።
ዝንጀሮው አንዱን ልጅ በልቶ ሌላዋን ልጅ ያቆሰለው ልጆቹ በቤታቸው አቅራቢያ ሲጫወቱ አግኝቷቸው መሆኑን ዋና ጸሐፊው በተጨማሪ አረጋግጠዋል።
ይኸው ዝንጀሮ ልጆቹን ከመብላቱ በፊት ፤ከ፴ ያላነሱ በጐችና ፍየሎች በልቶ ወደ ጫካ እየተሸሸገ የኖረ መሆኑ ታውቋል።
(መስከረም 1 ቀን 1962 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
የአንበሳ ኦቶቢስ ማኅበር አዳዲስ ኦቶቢሶችን ሊያስመጣ ነው
ከሺፈራው መንገሻ
በኢትዮጵያ የተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር ግምታቸው ፰፻፹ ሺህ ብር የሆነ ፲፩ አውቶቡሶች ከኢጣልያና ከጀርመን አገር እንደሚያስመጣ የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ወርቅነህ ገለጡ።
የተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር በጠቅላላው ፩፻፷፩ አውቶቡሶች አሉት ።ከእነዚህም ፩፻፴ የሚሆኑት ለከተማ ሕዝብ አገልግሎት ሲቀርቡ ፴፩ዱ ለጠቅላይ ግዛት የተመደቡ ናቸው።
በ ፲፱፻፷፩ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየቀኑ ፩፻፮ አውቶቡሶች ፯፻፴ ሺህ መንገደኞችን አመላልሰዋል።
የተሽከርካሪ መኪናዎች አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር የተቋቋመው በ፩፻፺ ማኅበርተኞች ነው። ከነዚህም ውስጥ አንድ አራተኛው አክሲዮን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጐ አድራጎት ሥር የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሲሆን፤ ፩፴፭ አክሲዮን በኢትዮጵያውያን ፤ ፲፪ በውጭ አገር ዜጎች የተያዘ ነው።
ማኅበሩ ወደፊት ስላለው ዕቅድ ሥራ አስኪያጁ ሲገልጡ፤ ፩ኛ / በየመንገዱ ዳር በሚገኙት መሣፈሪያዎች መጠለያዎችን ለመሥራት፤ ፪ኛ/ማዘጋጃ ቤት የሚሠራውን መንገድ ድርጅቱ እየተከተለ አዳዲስ መኪናዎችን ለማቅረብ፤ ፫ኛ/ መንገደኛ በሚበዛባቸው መስመሮችና ከሥራ በመውጪያና በመግቢያ ሰዓቶች ላይ የአውቶቡሶችን ኃይል ለመጨመር፤፬ኛ/ የተሳፋሪውን ምቾት ለመጠበቅ የጽዳትና የጥበብ ሁኔታ የሚያስከትሉትን ጭነቶችም በማስቀረት ለማገልገል ከመታቀዱም በላይ እስከ የካቲት ወር መጨረሸ ድረስ ፲ የፊያት አውቶቡሶችና ፩ ልዩ ማርቸዲስ በጠቅላላው ፲፩ አውቶቡሶችን አስመጥተን የነበረው ችግር ለማስወገድ ነው ብለዋል።
(መስከረም 13 ቀን 19 62 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
በጊቱ ፫ እግር ያላት ግልገል ወለደች
ጎሬ(ኢ.ዜ.አ.)፡- በቡኖ በደሌ አውራጃ ግዛት በጮራ ወረዳ በሐሌሌ ምክትል ወረዳ ግዛት ልዩ ስሙ ሃኖ በተባለው ቀበሌ ንብረትነትዋ የአቶ ፈረጃ ሻጣሰው የሆነች አንዲት በግ ፫ እግር ያላት ግለገል ወለደች።
ይህችው የበግ ግልገል የተወለደችው ፤ባለፈው ነሐሴ ወር ፷፩ ዓ.ም ነው። ግልገሏ ከፊት 2 እግሮች ሲኖራት፤ከኋላ በኩል ደግሞ አንድ እግር ብቻ ያላት መሆኑ ታውቋል።
ይህችው ከተወለደች ከ፲፭ ቀን በላይ የሆናት ግልገል ፤ተራ በተራ ለመራመድ ባትችልም፤በዝላይ መራመድ መቻሏንና እስካሁንም በህይወት መኖሯን አቶ አብዲሳ ደኑ የቡኖ በደሌ አውራጃ ግዛት ጸሐፊ ገለጡ።
(መስከረም 4 ቀን 1962 ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ)
17,000 ጥቁር አሜሪካውያን ”የአፍሪካ ሬፑብሊክ‘ የተባለ ግዛት በአሜሪካ ውስጥ ይሰጠን ይላሉ
ከዱትሮይት፤ (ኤ ኤፍ ፒ)፡-ባለፈው በፈረንጆቹ ዓመት የተቋቋመው ‹‹አዲሱ የአፍሪካ ሬፑብሊክ››አሥራ ሰባት ሺህ ጥቁር አሜሪካውያን አባሎች፤ የአሜሪካ ዜግነታቸውን ሽረው በዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ ጠረፍ በኩል አንድ አዲስ የጥቁር ሕዝብ መንግሥት እንዲቋቋምላቸው ጠይቀዋል።
የአዲሱ ጥቁር መንግሥት አባት አሜሪካ በጥቁሮች ላይ ለፈጸመችው ለባርነትና ለዘር ልዩነት ጭቆና በደል 400ሚሊየን ዶላር ካሣ እንድትከፍል መንግሥቱን መጠየቃቸው ተረጋግጧል።
የአዲሱ ሬፑብሊክ ምክትል ፕሬዚዳንት በሰው እጅ የተገደሉት የጥቁር እስላሞች መሪ የማልኮልም ኤክስ ሚስት ሚስስ ቤቲይ ሻባዝ ሲሆኑ ፤የመከላከያ ሚኒስትሩ ራፓ ብራውን ፤የባህል ሚኒስትር ደራሲው ሌሮይጆንስ መሆናቸው በዜናው ተገልጧል።
(መስከረም 4 ቀን 19 62 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2015 ዓ.ም