‹‹እጄን ልዘርጋለት እኔም ለወገኔ ሲወድቅ የሚያነሳው ማን አለው ያለኔ›› የሚለውን ሀሳብ ከሴቶች በላይ የሚረዳውም የሚተገብረውም የለም። በሕ.ወ.ሓ.ትና መሰሎቹ ካልሆነ በስተቀር። ምክንያቱም እነርሱ የበሉበትን ወጭት የሚሰብሩ ስለሆኑ በኢትዮጵያ ሀገራቸው ላይ ከአንድም ሶስት ጊዜ በከፈቱት ጦርነት የክፋታቸውን ጥግ አሳይተውናል። በየጊዜው በሚከፍቱት ጦርነት ‹‹ለወገን ደራሽ ወገን ነው›› የሚለውን ወገናዊ ጥሪ በመቃወም ድጋፍ የሚያደርጉትን ጭምር መግደላቸውን ተያይዘውታል። ይሁን እንጂ ሴቶች ደግነት ባህሪያቸው ነውና እየሞቱም ቢሆን ድጋፋቸውን ያደርጋሉ።
ሕብረተሰቡን በማስተባበር ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ ሕይወታቸውን ይገብራሉ። በጦርነቱ አካባቢ ባይኖሩ እንኳን አለንላችሁ ማለታቸውን አስተጓጉለው አያውቁም። በተለይ ለመከላከያ ሠራዊትና በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ያላቸው ድጋፍ የተለየ ነው። ምክንያቱም ከሁሉም ሰው ተጎጂ እነርሱ እንደሆኑ ይረዳሉና ድጋፋቸውን በማስተዋል ለተቸገረ፤ መከታ ለሚሆናቸው ሁሉ ያደርጋሉ። ከእነዚህ መካከልም የድሬ ሴቶች ይጠቀሳሉ። ለወገን በመድረስ ብቻ ሳይሆን ለአንድ አገር ሰላምም ሴቶች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ አምነው የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል።
የሀገርን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጡ ረገድ ያላቸው ሚና የጎላ እንደሆነ በተግባራቸው አረጋግጠዋል። በሀገራችን ላይ የመጣውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ከጸጥታ ኃይሎች ጎን ተሰልፈው በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋምና የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቁ ሂደት እየተጉ የሚገኙትን የድሬዳዋ ሴቶች በፌዴሬሽናቸው በኩል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉም ነው።
የፌዴሬሽኑ አባላት ሴቶች ሰርተው ሕይወታቸውን መለወጥ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር ለሰላም ዘብ መቆም ላይ ይሰራል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ አንዱ የሕ.ወ.ሓ.ት ቡድን ባደረገው ጦርነት የተጎዱ ወገኖችን ስፍራው ድረስ በመዝለቅ ያገዙበት ተግባር ነው። በቡድኑ አባላት ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እጃቸው ፤ እግራቸው ጡታቸው የተቆረጠና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በመከላከያ ሆስፒታል በህክምና ላይ ላሉ ወገኖችም የደረሱ መሆናቸው ሥራቸውን ከሚያጎሉት መካከል ነው።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ይፍቱ አባስ አህመድ እንደሚሉት፤ ይሄ አጋርነታችንና አይዟችሁ ባይነታችን እንዲሁም እንግዳ ተቀባይነታችን በአድ መሆን የለበትም። ሰፈርተኛና ብሔርተኛ ሊያደርገን አይገባም። ዜጋችን ብቻ ሳይሆን ሰው ለሆነ ሁሉ መድረስ አለበት። ነባሩን መልካምነቷን ነው ማስቀጠል ያለብን። የኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ መሆን ያለበት ያለፈውን መልካም ነገር ይዞ አዳዲስ መልካም ነገሮችን መፍጠር ነው። መልካሙን አስተሳሰብና ባህል በአዲሱ ዓመት ማሻገር ያስፈልጋልም።
‹‹በአገራችን በጠላት ላይ እንኳን የማይደረግ አሰቃቂና አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈጸም አይተናል፤ ሰምተናልም። እነዚህ ግፍና በደል የተፈፀመባቸው ወገኖች ደግሞ ኑሯቸው ቀላል አልነበረም›› የሚሉት ፕሬዚዳንቷ፤ በሆስፒታል የነበሩትን በጎበኙበት ወቅት ስቃያቸው የበረታ ቢሆንም ሙሉ ቤተሰባዊ ስሜትና ፍቅር እንዲሰማቸው ማድረጋቸው ነገሮችን ለጊዜውም ቢሆን እንዳስረሳቸው ይናገራሉ። ይህ ተግባራቸው ጦርነቱ ካሳደረባቸው የስነ ልቦና፤ ተስፋ የመቁረጥ የተለያዩ ተፅዕኖዎች እንዲወጡና መንፈሳቸው እንዲታደስ እንዳደረገም ያነሳሉ።
ወይዘሮ ይፍቱ እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ቡድኑ በተደጋጋሚ በከፈተው ጦርነት ምክንያት በርካታ ዜጎች መጎዳታቸውንም ያወሳሉ። ተወልደው ባደጉበት፤ ዕትብታቸው በተቀበረበት ሀገር ማደሪያ አጥተው ተንከራታች ሆነዋል። አርሰውና ዘርተው ከራሳቸው አልፎ ተርፎም ህዝበ አዳምን ከመመገብ ታግደዋልም። ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው ጎዳና ለመውጣት ተዳርገዋል። ስደተኞች ሆነዋል። ህልውናቸው ተደፍሯል። መብታቸው ተረጋግጧል። በአጠቃላይ በገዛ አገራቸው ውስጥ በገዛ ወገናቸው ለጠላት እንኳን የማይደረግ ግፍ ተፈፅሞባቸዋል። ይህ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ ነው ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። እንዴት ወደነበሩበት እንመልሳቸው የሚለውን እንድናስብ ያደርገናል ይላሉ።
ፌዴሬሽኑ ለእነዚህ ወገኖች እንደ ድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር አጋርነቱን ለማሳየት የተነሳው ነገሮችን በየአቅጣጫው ሄዶ በመመልከቱ እንደሆነ የሚያነሱት ፕሬዚዳንቷ፤ ሚናቸውን ሊያጎላው ያስቻለው በተለያዩ አደረጃጀቶች ገብተው በቅንጅት መሥራታቸው እንደሆነ ይጠቅሳሉ። በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብና በዓይነት በመደገፉ ረገድ ዓይነተኛ ሚና መጫወት የቻሉትም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ያብራራሉ።
አደረጃጀታቸው ደግሞ ሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ አቅም እየገነቡ እና መልካም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አስችሏል። በመንግስት በኩልም አስተዋጽኦውን ማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። የሰላምን ዋጋ ለማሳየትም አግዟል። በሀገራዊ ጉዳዮችና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረጉ ረገድ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያስቻላቸው መሆኑንም ይገልጻሉ።
ወይዘሮ ይፍቱ እንደሚሉት፤ ሀገራችንን ወደ አልተፈለገ ጦርነት ካስገባት ቡድንና ከሌሎች የጥፋት ኃይሎች ተልዕኮ ተቀብለው የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት ጭምር የሆነችውን ድሬዳዋን ሰላሟ እንዲደፈርስ የሚጥሩ አካላት ነበሩ። እነዚህ አካላት ደግሞ ሰላምን የማይፈልጉ፤ እኩይ ተልእኮ የሚያራምዱና ሃይማኖትን ተገን ያደረጉም ናቸው። በዚህም ድሬዳዋ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለወራት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት ከሌሎች ክልሎች ባልተናነሰ በርካታ ችግሮችን እንድታስተናግድ ሆናለች። ሁለት ግለሰቦች ፀብ የሚሰፋበት፤ ከብሄርና ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ ወደ ትልቅ ግጭት የሚያመራበት ሁኔታም በሰፊው ይታይ ነበር። ሆኖም በሰላም ሰባኪ ሴቶች ነገሮች እንዲረግቡና ወደቀደመው ማንነት እንዲመለሱ ሆኗል።
ሴቶች በየአካባቢዎቻቸው በሚደርሱ ችግሮች ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ናቸው። በድሬዳዋም የነበረው ይኸው ነው። ዛሬ ላይ መድረስ የቻሉትም ችግሮቹን እየተጋፈጡና ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ ሁሉም ሊረዳው ይገባል። ችግሮቹን በግንባር ቀደምትነት የሚፈቱትም ተጎጂዎች እነርሱ መሆናቸውን ስለሚያስቡ ነው። ስለዚህ ሁልጊዜ ሴቶች የጥፋተኞችን ዓይን ይሰብራሉ፤ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ይተጋሉ፤ሲፈጠሩም ጣልቃ ገብተው በማቀዝቀዝ ያስታርቃሉ። ጎረቤት ሲጣላ ግጭቶች ወደ ብሔርና ሃይማኖት ከፍ እንዳይል ይሰራሉ።
እንደ ፌዴሬሽን የሴቶች የሰላም ምክር ቤት አዋቅረው እየሰሩ እንደሆነ የሚናገሩት ፕሬዚዳንቷ፤ ምክር ቤቱ በእያንዳንዱ ቀበሌ የራሱ የሰላም ምክር ቤት አለው። ትልቁ ሥራውም ሰላም ላይ ያተኮረ ተግባር መከወን ነው። ለዚህ ደግሞ የተለያዩ አደረጃጀቶች አባል የሆኑት በጎ ፈቃደኛ ሴቶች ተጠቃሽ ናቸው። እነኝህ ሴቶች ሰላምን ለማምጣት ተራ ገብተው አካባቢያቸውን በሮንድ ጭምር ይጠብቃሉ። አሁን ቡድኑ ለሦስተኛ ጊዜ በከፈተውም ጦርነት ተመሳሳይ ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም ሕብረተሰቡን ከሃይማኖትም ሆነ ከብሄር ጋር የተያያዙ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ እንዳደረጉት ያስረዳሉ።
እንደ ወይዘሮ ይፍቱ ገለጻ፤ ሴቶቹ እየሰሩት ባለው ሥራ መልካም የሆኑ ጉርብትናዎች እየተፈጠሩም ነው። የትናንት የድሬዳዋ ማንነት ወደ ነበረበት እንዲመለስም አስችለዋል። አሁንም ሰላም አለ ብለው አርፈው ሳይቀመጡ ሰላማቸውን አብዝተው እየጠበቁ ይገኛሉ። ፌዴሬሽኑ ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል በየቀበሌው ምክር ቤቶችና በየኮሚቴው ሴቶች እንዲገቡ ያደረገበት ሁኔታም አለ። ይህ ደግሞ አብረው አጀንዳ እንዲቀርፁ በጋራ ጉዳያቸው ላይ ተቀምጠው እኩል እንዲነጋገሩ ያስችላቸዋልና ጥሩ መነቃቃትን ፈጥሯል።
በዚህ እንቅስቃሴ በከተማ ያሉት የዘጠኝ ቀበሌ እንዲሁም በገጠር ያሉ የ38 ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አባላቶቻቸው ይሳተፋሉ። እነዚህ ሴቶች ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በተሳተፈበት በባለፈው ሀገራዊ ምርጫም በምርጫው በተመራጭነት በመወዳደር እንዲሁም በመራጭነትና ምርጫውን በመታዘብም ተሳትፈዋል። ይሄም ከምርጫ ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ የፀጥታ ችግሮችን መከላከል እንዳስቻላቸው ይናገራሉ። የአመራርነት ብቃታቸው የተሻለ እንዲሆንም ይሰራል ይላሉ።
‹‹እኔ ለዚህ ቦታ የምከፍለው ዋጋ ለሀገር ሰላም ትልቅ ውጤት አለው›› በሚል እሳቤ አንዳንድ ውዝግብ የተፈጠረባቸው ቦታዎች ላይ እና ኮረጆ እስኪጫንና ውዝግቡ መፍትሄ እስኪያገኝ እዛው ምርጫው በሚካሄድበት ሥፍራ ለሁለት ቀናት ያደሩ ሴቶች እንደነበሩ የሚያወሱት ፕሬዚዳንቷ፤ ይህ ደግሞ ጉሊት ወጥታ ሽንኩርት ቸርችራ፤ ዳቦ ነግዳ ዕለታዊ ኑሮዋን የምትመራው ሴት ከሰላም ተጠቃሚ ነኝ ማለቷን ይመሰክራል። በዚህ ሁኔታ ሰርታ መኖር የምትችለው ሰላም ካለ የመሆኑ ግንዛቤዋ መስፋቱንም ያመላክታል ይላሉ።
ፌዴሬሽኑ እያንዳንዷ ሴት ላይ ‹‹ እኔ ለሰላም ዘብ መቆም አለብኝ›› የሚል እሳቤ እንዲያይ አድርጓል። ከዚህም ባሻገር ሴቶች በሰላም ጉዳይ ያለን መረዳት እዚህ ድረስ የሰፋው የማንንም በጀት ሳንጠይቅ በራሳችን ተነሳሽነት ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል መሥራታችን ነው። ለዚህም ማሳያው ‹‹አማራና አፋር ላይ ወልዳ የራባት እናት ወገናችን ናት በሚል ድጋፍ ልናደርግላት ይገባል›› ብለን ነው ከአንድ ሁለቴ ሕወሓት በከፈተው ጦርነት የተጎዱና የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ የተንቀሳቀስነው ሲሉም ክልሎች ድረስ እንዴት ወርደው እንደሰሩ የሚያነሱት።
በድጋፋቸው ግንባር ቀደም ሴቶቹ በየቤቱና ባለሀብቱ በሚገኝበት እየዞሩ ገንዘብ፤ ዱቄት፤ የተለያዩ አልባሳትና ቁሳቁሶችን በመሰብሰባቸው የተከወነ ነው። ከሰበሰቧቸው መካከል ዳይፐር ፤ሞዴስና የህፃናት ልብሶችም ይገኙበታል። እነዚህኑ ሦስት ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ንብረቶችን እስፍራው ድረስ በመሄድም አድርሰዋል። አሁን ላይም ፌዴሬሽኑ በተለይ በጦርነቱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱትን በአማራ ክልል ዋግ ህምራ ዞን ሰቆጣ አካባቢ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማገዝ ከየፋብሪካዎችና ከተለያዩ ባለሀብቶች የተለያዩ ምግቦች፤ ለአዋቂ፤ ለህፃናትና ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚሆኑ አልባሳት እንዳሰባሰበ ይናገራሉ።
በድጋፉ ዘጠኝ ቀበሌዎችን የአቀፈው ከተማ አስተዳደርና በአራት ክላስተር የተደራጀው የ38 ገጠር ቀበሌ ነዋሪ የሕብረተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ ያደረጉበት እንደሆነ የሚገልጹት ፕሬዚዳንቷ፤ የተሰበሰበው ድጋፍ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው። ነገር ግን ወደ ሰቆጣ በመዝለቅ ሊሰጡ ባሉበት ወቅት ሕ.ወ.ሓ.ት ለሦስተኛ ጊዜ በክልሉ ጦርነት ከፈተ። ስለዚህም ንብረቱ በመጋዘን ውስጥ በማስቀመጥ የተወሰነ መረጋጋት እስኪፈጠር እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ያነሳሉ። እንደ ፌደሬሽን በቅርቡ ድጋፉን ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ያብራራሉ።
‹‹ድሬዳዋ ላይ ትልቅ የመከላከያ ሆስፒታል አለ›› የሚሉት ፕሬዚዳንቷ፤ በዚህ ሆስፒታል እጃቸውን ከማጣት ጀምሮ ጡታቸው የተቆረጠ ፤እግራቸው የተጎዳና የተለያየ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በፌዴሬሽኑ ተጎብኝተዋል። ቅቤ በመቀባት መርሐ ግብር በማሳተፍም ፀጉራቸውን ቅቤ የመቀባት ዕድልም አግኝተዋል። ሳሙናና የፀጉር ቅባቶች ተሰጥቷቸዋል። እጃችንም ሆነ ጡታችንና እግራችን የተቆረጠው ለሀገራች ነው የሚል ስሜት እንዲፈጠርባቸውና እንዲጽናኑ አስችሏቸዋል።
አዲስ ዓመት ሲመጣ ቤተሰቦቻቸውን ስለሚያስታውሱ፤ በጦርነቱ መጎዳታቸውም ትዝ ስለሚላቸው መጥፎውን የጦርነት ስሜትና ትውስታ የሚቀይርላቸው የዘመን መለወጫ መርሐ ግብር ያስፈልጋቸዋል ያሉን ወይዘሮ ይፍቱ፤ በእነርሱ በኩል ይህ ተግባር ባለፈው ዓመት ተከናውኗል። ለመርሐ ግብሩ ባለሀብቶች የሰጡትን 10 ፍየሎች በመጠቀምና ዳቦ በማስጋገር ባንድ በማቆም ጭምር ትልቅ የእራት ግብዣ አዘጋጅተው በዓሉን እንዲያከብሩም አድርገዋል።
በፌዴሬሽኑ አነሳሽነት ከከንቲባው ጀምሮ የተለያዩ ባለሀብቶች በምሳና እራት ግብዣም ሆነ በተለያየ መንገድ በሆሲፒታሉ ለነበሩት ተጎጂዎች አጋርነታቸውን ያሳዩበት፤ ያፅናኑበት ጦርነቱ ከፈጠረባቸው አስፈሪ ትውስታ ውስጥ እንዲወጡ ያደረጉበት ሁኔታም እንደነበር። አሁንም ይህ ተግባር የሚቀጥል ይሆናልም ብለውናል።
እንደ ወይዘሮ ይፍቱ ገለጻ፤ ባለፈው ዓመት ተጎጂዎቹ በየፊናቸው ወደ ፊትም ለሀገራችን የበለጠ መስዋእት እንድንሆን አነሳስቶናል እስከሚሉ ደርሰዋል። ታክመው ከሄዱ በኋላም የቤተሰብ ያህል ቅርበት የፈጠረ ግንኙነትን ማጠናከር ተችሏል። ስለሆነም 2015ዓ.ም ይህ ነገር እንዲደገም ይደረጋል። ምክንያቱም ቤተሰባዊነት ከሁሉም ይበልጣል። ለሰላም መረጋገጥ ደግሞ ሚናው ቀላል አይደለም። ስለሆነም በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ለመፍጠር ይሰራል። እኛም የሴቶች ልምድ ይስፋ ወገንም በየትኛውም ሁኔታ በወገን ይደገፍ በማለት ጽሑፋችንን አሳረግን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2015 ዓ.ም