‹‹ኢትዮጵያ ልትወጣው ወደማትችለው የኢኮኖሚ ችግር መግባትዋ ቢያሳዝነንም እውነታው ግን ልንክደው የማንችለው ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በርከት ያሉ ዜጎች የኑሮ ውድነቱን መቻል አቅቷቸዋል። ከባድ ፈተና ውስጥ እንዳሉ ብዙ ማሳያዎች አሉ። በትግራይ ያለው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ፋሺስቱ ዓቢይ የትግራይ ሕዝብ በችግር እንዲያልቅ ባለው ፍላጎት እየተቀጣጠለ ቢሆንም፣ ከሌሎች ጦርነት ካላገኛቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚታየው ችግር አንፃር ሲታይ እንደሚባለው ሰፊ ችግር እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል›› ይላል ሰሞኑን ከሕወሓት ጉያ ሾልኮ የወጣው የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ በሚል ተከትቦ የተገኘው መረጃ ።
ሕወሓት በኢትዮጵያ ውስጥ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን በመፈብረክ የሀገሪቱን ሠላም ማደፍረስ ዋነኛ ዓላማው ማድረጉ ይታወቃል። በዚህም ማንኛውንም ዓይነት ማህበራዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ሳንንቅ ወደ አደባባይ እንዲመጡ ፣ ጥያቄዎቹ ሕዝባዊ ቁመና እንዲላበሱ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲል መነሳቱም ይታወቃል።
እነዚህ ጉዳዮች ተገቢ ትኩረት እንዲያገኙ ሚዲያዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች አጀንዳውን የማቀጣጠል ሚናቸውን በሚገባ እንዲወጡ በማገዝ የፋሺስት ዓቢይን ውድቀት ሊያፋጥኑ ይገባል ሲል የኢኮኖሚ አሻጥር ላይ ትኩረት ማድረጉን ሰነዱ ያብራራል።
ለመሆኑ ይህ ቡድን፤ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚታየው ኢኮኖሚያዊ ችግር አንጻር የትግራይ ክልል የኑሮ ሁኔታ የተሻለ ነው ለማለት የሚታትረው ማንን ለማታለል ይሆን ?በስቃይና በእርዳታ ኑሮውን እየኖረ ያለውን የትግራይን ህዝብ ወይንስ ሌላውን?
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት፤ ይህን ድርጅት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ወደ መንበር ስልጣን ከመጣም በኋላ ሲያደርግ የነበረው ትክክለኛ መፍትሄ መስጠት ሳይሆን ሀገር እንዲበጠብጥ የተፈጠረ ነው። አሸባሪ የሕወሓት ቡድን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማያከብር የቡዱኑና የግለሰቦች የጥቅም ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው። በህዝብ እንደራሴዎች አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው ይህ ቡድን የሀገር ሉዓላዊነት ከመዳፈር በዘለለ አንዳች የፈየደው ነገር የለም። አካሄዱም ዓለም አቀፍ ህጎችን የሚጣረስና በውሸት ብቻ የተካነ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ህወሓት በአንድ በኩል ህዝቡ በችግር እያለቀ ነው፤ ችግር በዝቷል እያለ ይለፈልፋል።እርዳታ እየገባልን አይደለም ሲል ይደመጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ታጋዮቻችን ትጥቅና ስንቅ የሟሟላት ሥራ በዋናነት በነፃነቱ የማይደራደረው ሕዝባችን ተግባር ይሆናል ይላል። በትግራይ የሚገኙ የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሰብዓዊ ድጋፍ ማከማቻ መጋዘኖች ፋሽስቱን ለማስወገድ በምናደርገው ትግል የስንቅ አቅርቦት እንዳይጓደል በቁጥጥራችን ሥር ልናደርጋቸው ይገባል። ይሄም ከዓለም አቀፍ የዕርዳታ አስተባባሪዎች አወንታዊ የሆነ ግንኙነቶች በማጠናከር ረሃብና ተረጅነት ከሕዝባችን ትከሻ ላይ ለማውረድ ለምናደርገው ትግል ደጋፊ እንዲሆኑና ከጎናችን እንዲቆሙ ልናደርግ ይገባል ሲልም በሰነዱ ይገልጻል። ይሄ የህወሀት የመቀላመድ ተግባር ነው።በአንድ ራስ ሁለት ምላስ እንደሚባለው ነው ።
ታዲያ ይህ የአሸባሪው ሕወሓት አካሄድ አዲስ አይደለም። የተለመደ የቡድኑ ቅጥፈት አካሄድ መሆኑን የሚናገሩት አቶ እንዳለ፤ የእርዳታ እህልን በኩራት የሚቀበል ለክብሩ ፈጽሞ የማይጨነቅ ነው። በተለይም የእርዳታ እህል እየወሰዱ ለመዋጋት መሞከር በሰብዓዊነት ላይ እንደ መቆመር ነው፤ ይህም በታሪክም ከመወቀስ በሞራል እና በህግ ከመጠየቅም አያድንም ባይ ናቸው።
ውጊያ ብዙ ዓይነት ነው የሚሉት አቶ እንዳለ፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ አውቆ ማደናገር ነው። በመሆኑም ሕወሓት እየተናገረ ያለው ከሞራልና ኢትዮጵያዊ ሥነ-ምግባር ውጭ ሲሆን፤ በትግራይ ክልል የተደላደለ ኑሮ ያለ ለማስመሰል የሚሄድበት አካሄድ በታሪክ ይቅር የማይባል ነው። ይህን ያክል ለስልጣን የሚጋጋጠውም ለራሱ ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያንን አለቆቹን ለማስደሰት ጭምር ነው። ቡድኑ አለቆቹን ካስደሰትም የውሸት ዓይነት ሁሉ ይዋሻል፤ የጥፋትን ጥግ ይፈጽማል። ይህን በማድረግ የቆየ ልምድ ያለው ቡድን ሲሆን ከደደቢት ዋሻ ጀምሮ የተካነበት ስለመሆኑም ይናገራሉ። እናም ባወጣው ሰነድ ላይ በትግራይ ችግር የለም በሚል በችግር ውስጥ ያለውን ሰው ማሞኘት ነው የያዘው ፤ ሌላውንም ህዝብ ጭምር።
ምዕራባውያንም ነጭ ውሸት የሚከተሉ ሲሆን፤ ዓይናቸው እያየ፤ ጆሯቸው እየሰማ እና አሸባሪው ቡድን ዘግናኝ ነውሮችን እየፈፀመ እንዲሁም ለሰብዓዊ እርዳታ የተባሉትን ድጋፎች በሙሉ ወደ ጦርነት ቀጣና ሲወስድ ዝምታን መርጠዋል። ይህም የሚሳየው ዓላማቸውን ለማስፈጸምና ለመፈጸም ህወሓት ምን ያክል ታማኝ እስረኛቸው እንደሆነ ነው። ሌላው ቀርቶ በኑሮ ክፉኛ እየተጎዳ የሚገኝን ማህበረሰብ፤ የተረጋጋ ኑሮ እየኖረ ነው፤ ማህበራዊ መሰረቱም መልካም የሚባል ነው የሚል ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጨ ነዋሪዎችን ሲያደናግር አግባብ አለመሆኑን፤ የሚሰጡት እርዳታ እንደ ማጣቀሻ አድርገው ማቅረብ ይችላሉ። ይሁንና የሚፈልጉትን ዓላማቸውን በሚገባ እስካሳካላቸው ድረስ ሕወሓት ውሸትን እንደፈለገው ቢናገር ሊገስፁ፤ እየፈፀመ ያለውም ተግባር ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ ስለመሆኑ ለመናገር አይደፍሩም። ምዕራባውያን የሚዋሹትን ነጭ ውሸት ሕወሓትም ሲዋሽ ሲመለከቱ የሥራችን ውጤት ፍሬ እያፈራ ነው ብለው ከመደሰት የዘለለ፤ ለዕውነት ይቆማሉ፤ ሚዛናዊ አዕምሮም ይኖራቸዋል ብሎ መጠበቅም በእጅጉ የዋህነት ነው።
እንደ አቶ እንዳለ ገለፃ፤ ምንም እንኳ ሕወሓት ግፍና ውሸትን ባያቋርጥም መንግስት ግን እንደ ሀገር ኃላፊነት አለበት ይላሉ። የትግራይ ህዝብ የኑሮ መሰረት የተደላደለ ነው፤ ኑሮውም የተረጋጋ ነው በሚል የውሸት ወሬ ህዝብ ላይ ወንጀል እየፈጸመ ቢሆንም እውነት አለመሆኑን ማወቅና ማሳወቅ ይገባል። ከዚህም በዘለለ መንግስት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች በሙሉ አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ መሥራት ይጠበቅታል ሲሉም ይመክራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሓት የገንዘብና ስንቅ ድጋፍ የሚያደርጉለት ምዕራባውያንና ኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተው ይበቃሃል እስካላሉት ድረስ ጸረ ሰላምነቱን የሚያቆመው የለም። እነዚህ አካላት ደግሞ የኢትዮጵያን መዳከም የሚፈልጉ በመሆኑ ይህን የማድረግ ሞራልና ፍላጎት የላቸውም። ይሁንና መንግስት አሁንም የዲፕሎማሲውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉም ይመክራሉ።
ሕወሓት በአሁኑ ወቅት እየሠራ ያለውም ለትግራይ ህዝብ ነው የሚለው ድራማ መሆኑ በግልፅ የሚታወቅ መሆኑን የሚናገሩት ምሁሩ፤ ከአሸባሪው ቡድን በስተጀርባ ያሉ አካላትንም ለመነጠል በሚገባ መሥራት ይገባል። መንግስትም ለትግራይ ህዝብ ሲል ዋጋ እየከፈለ መሆኑን በተቻለ መንገድ ሁሉ ማሳወቅና ቀጣፊነት አሸባሪን ቡድን መገለጫ ባህሪ መሆኑንም ያሳስባሉ።
አሸባሪው ሕወሓት ሰሞኑን፤ ‹‹የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ›› ብሎ በነደፈው ሰነድ የተገኙት መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የሚጠብቀን ረጅምና መራር ትግል በመሆኑ ለዚህ የሚመጥን ከወታደራዊ፣ ከሥነ-ልቦናዊ፣ ከሎጂስቲክስ ላይ እየሰራን ነው የሚል ሲሆን፤ የኢትዮጵያን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረቶችን ማቃወስ የመጀመሪያ አጀንዳው አድርጎ መነሳቱም በስትራቴጂው በዝርዝር ማስቀመጡ ይታወቃል።
የሠላም አምባሳደር ምዑዝ ገብረህይወት በበኩላቸው፤ የሕወሓት የማያልቅ ዲስኩር እና ውሸቱ ከአፈጣጠሩ እስከሞቱ አብሮት የሚሄድ ስለመሆኑ ይናገራሉ። ይህም ብቻ ሳይሆን አሸባሪው ሕወሓት የትግራይ ህዝብን እንደግል ንብረቱ የሚመለከት አድራጊ እና ፈጣሪ ቡድን ነው። ይህ ቡድን የክልሉን ህዝብ በሙሉ በሚፈልገው የፕሮፓጋንዳ መስመር ውስጥ ለማስገባት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፤ ቃላትን መጠቀም እስከቻለ ድረስ ደግሞ የማይዋሸው አንዳችም ነገር አይኖርም ሲሉ የሕወሓትን የውሸትና የንቅዘትን ታሪክ መለስ ብለው ያስታወሳሉ።
ታዲያ ሰሞኑንም፤ ‹‹የትግራይ ክልል ከሌሎች ጦርነት ካላገኛቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚታየው ችግር አንፃር ሲታይ እንደሚባለው ሰፊ ችግር የለም›› በሚል ህዝቡን ሊያደናግር የሚሄድበት መንገድ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና የቀድሞውኑ የመጣበት ውሸት ታሪክን መድገም ነው ይላሉ። ሕወሓት ከሞራልም ሆነ ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን ሲል ጥቂት እውነት እንኳን መቀለቀል አይፈልግም፤ ዕድሜ ዘመኑንም እንደዋሸ ይኖራል ባይ ናቸው።
ይህ ቡድን ሁልጊዜ አታላይ እና አጭበርባሪ ነው። አሁን ሕዝብ እንዲረጋጋ ለማድረግ ነው። ሌላው ቀርቶ ከረድዔት ድርጅቶች የሚላከውን እርዳታ የሚሰጠው ለራሱ ታጣቂዎች ነው። መንግስት ነኝ ብሎ በህዝቡ ዘንድ በሰፊ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ይሰራል። ሌላው ቀርቶ ማህተሙ ‹‹የትግራይ መንግስት›› ነው የሚለው። ይሄ ህዝብን እያጭበረበረ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
ለመሆኑ አሸባሪው በጦርነት ላይ የከረመ ማህበረሰብ እንዴት የተትረፈረፈ ምርት ሊኖረው ይችላል ሲሉም ይጠይቃሉ? እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሕወሓት የሚለው ሳይሆን ከዚህ በተቃራኒ ነው። ከጥንትም ጀምሮ ሕወሓት ከኢትዮጵያ መንግስት፣ አማራ፣ አፋር፣ ኢህአፓ፣ ኢሰፓ፣ እና ሌሎች ዘመኑን በሙሉ ጦርነት ላይ የኖረ ነው። በክልሉ የመድሃኒትና የምግብ እጥረት ስለመኖሩም በርካታ መረጃዎች እየወጡ ነው። መድኃነት በማጣት ጭምር ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች አሉ። እርዳታውን እንኳን በፍትሀዊነት እየሰጡ ሳይሆን ልጅ ለሰጠ በሚል ልዩነት እያደረጉ ጭምር ነው። የከፋ ችግር ባይኖር ነው የዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶችን ወደ መዝረፍ የተገባው ሲሉ ይጠይቃሉ። ይሄ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር የተረጋገጠ ዝርፊያ ነው።
ሕወሓት ለዘመናት ሲዋጋ የሚኖረውም ለትግራይ ህዝብ በማሰብ ብቻ ሳይሆን፤ በዘመናት ውስጥ ሲፈፅሙት የነበረው የታሪክ ጠባሳ ይፋ እንዳይሆንና በህግ እንዳይጠየቁ ለመሸፋፈን ነው። ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ወቅት በጀመረው ጦርነት ብቻ አንድ ሚሊዮን የሚሆን የትግራይ ወጣት ሞቷል፤ተፈናቅሏል፤ ተሰዷል። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም በ100ሺዎች ሞተዋል። ሕወሓት የጦርነት ታሪኩ የትግራይ እናቶች በርካታ ሚሊዮን ወጣቶችን ገብረዋል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ግን ሕወሓት መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።
ሕወሓት ሲመሰረት 1967 የነበሩ አመራሮች አሁንም በርቀት የድሃ ልጅ ያዋጋሉ የሚሉት የሠላም አምባሳዳር አቶ ምዑዝ፤ የአሸባሪው የሕወሓት ስብስቦች አስገራሚ ፍጥረት ስለመሆናቸው መረጃን በማጣቀስ ይናገራሉ። የደርግ መንግስትንም ሲዋጉ የነበሩት አመራሮች አሁንም ትግራይን እንመራለን ብለው ከአማራ እና አፋር ህዝብ ጋር እያዋጉ ያሉ ናቸው። ሕወሓት አካሄዱ የሽፍታ በመሆኑም ብዙም አይገርምም ሲሉ ታሪኩን ዋቢ በማድረግ አሁናዊ ቁመናውን ይጠቅሳሉ። 1981 ዓ.ም እና 1982 ዓ.ም የተማረኩ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የነበሩበትንና ብሎም ሰሜን ግንባርን በሌሊት በተገኙበት ሲወጓቸው የያዛቸውን ሰራዊት ፎቶ እየተጠቀሙ የብልጽግና ወታደር ምርኮኛ ነው ብለው ህዝብ ያሞኛሉ። በመሆኑም ሕወሓት ዕድሜ ልኩ ይዋሻል፤ ሰላምን ሳይሆን ጦርነት ይናፍቃል። ይህን ሁሉ የሚደርገው ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን ነው።
እንደ ሠላም አምባሳደሩ ከሆነ፤ ሕወሓት አብሮት የተፈጠረውን ውሸትና የሀሰት ትርክት የመተው ፍላጎት አንዳች የለውም። ይልቁንም ከዚህ በበለጠ አዳዲስ ውሸቶችን በመፈብረክ የትግራይ እናቶች ልጆቻቸው ለጦርነት እንዲማገዱ ለማባበል ይሞክራል። ይህም ካልሆነ ግን ኃይል መጠቀሙን አይተውም ባይ ናቸው። ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን የትግራይ እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች ኢ-ዲሞክራሲዊ አካሄድ በቃህ የሚሉበት ጊዜ መሆኑንም መገንዘብ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ።
ሕወሓት በሚዋሸው ልክ ስኬታማ እየሆነ ባለመሆኑ፤ ከፍተኛ ሞራላዊ ኪሣራ እየገጠመው ነው። ሰሞኑንም ከሌሎች ጦርነት ካላገኛቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚታየው ችግር አንፃር ሲታይ በትግራይ ክልል የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የሄደበት መንገድ ለመላው ትግራይ ያለውን የወጣ ጥላቻና ጠላትነት የገለፀበት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይህም በመሆኑ በሀገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጪ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ሊያወግዙት ይገባል። መንግስትም ኃላፊነት በተሞላው አኳሃን የክልሉን ነዋሪዎች መታደግ ይጠበቅበታል ሲሉ ያሳስባሉ።
ሁለቱም ሐሳብ ሰጪዎች፤ ህወሓት በዘመኑ የመጣበት የውሸት ትርክትና የተዛባ እውነት ጋር መነጣጠል አለመቻሉን ነው። በትግራይ የኑሮ ውድነቱ ሰማይ መድረሱን ብዙዎች እየተናገሩና እየመሰከሩ ባለበት ሁኔታ አሸባሪው ሕወሓት ግን ይሄን አይን ያወጣ ውሸት መዋሸቱ የቆየ ባህሪው መገለጫው ነው። አሸባሪው ሕወሓት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ውሸትን ስልቅጥ አድርጎ የዋጠ በመሆኑ ሰሞኑን ከሌሎች ጦርነት ካላገኛቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚታየው ችግር አንፃር ሲታይ፤ በትግራይ ክልል የተሻለ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ይስተዋላል ማለቱ አሁንም ለትግራይ ህዝብ ደንታ ቢስ ስለመሆኑና ውሸት እስከዕለተ ሞቱ የማይለየው ቡድን ስለመሆኑ የተገለፀበት ባህሪው ነው። ሆኖም የአሸባሪው ቡድን መገለጫዎች ውስጥ ውሸት ቀዳሚው ቢሆንም፤ በችግር ውስጥ ያለው የትግራይ ህዝብ ግን የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነውና ይሄንን ቡድን በቃህ በውሸትና በጦርነት መገዛት አንፈልግም ሊለው ይገባል።
አዲስ ዘመን መስከረም 3/2015 ዓ.ም