ዘመን በራሱ ሲፈሸን
ኢትዮጵያውያን አዲስ ዘመን በመጣ ቁጥር ይዋባሉ። ታዲያ ውበታቸው በተፈጥሮም ይደምቃል። ምድር በአዲስ ዓመት ትዋባለች። በአዲስ ዓመት ኢትዮጵያ ላይ ሰው ብቻ ሳይሆን ዘመን በራሱ ይፈሽናል። ወቅቱ በራሱ አዲስነት ይላበሳል። ሜዳና ጋራው አረንጓዴ ለብሶ፣ የለመለመ መስኩ በአደይ አበባ ደምቆ ልዩ ውበት ይላበሳል። ልክ እንደ ፋሽን ወቅቱም የውበት ሰገነት ይለብሳል። በዚህ ጊዜ ክረምት ያደመነው ሰማይ ይጠራል፤ በጎርፍ የደፈረሰው ውሃ ፀድቶ ኩልል እያለ ይወርዳል።
ሰዎች በዚህ ወቅት አዲስ መንፈስ ይላበሳሉ። በአዲስ ዓመት የአዲስ መንፈስን ለመላበስ ዘመን ባፈራው አልባስ አጊጠው፤ ጊዜው በፈጠረው የውበት ማድመቂያ ተውበው ከዘመድ አዝማድ ጋር ይገናኛሉ። የኢትዮጵያውያን የጥበብ ባለሙያዎች እጅ ያረፈባቸው አልባሳት ማጌጫ፤ ለበዓሉም ልዩ ድምቀት ይሆናቸዋል። ዲዛይነሮች የሰሩዋቸው አዳዲስ ማራኪ አላባሳት የፍስሀ ቅባቸው ማድመቂያ ያደርጉታል። አገሬውም ይህን አስመልክቶ ዘመኑን በራሱ መንገድ ይቀበላል።
አዲስ ዘመን በልጃገረዶች
በአዳዲስ ልብስ ተውበው፣ፀጉራቸውን ሹሩባ ተሰርተው፣ ከሌላ ጊዜ በተለይ ሹሩባ የተሰሩት ፀጉራቸው ላይ አደይ አበባ ወይም አደይ አበባን በሚመስል ቀለምና ቅርፅ የተሰራ የፀጉር ማጌጫ ደምቀው በየቤቱ እየዞሩ በውብ ዜማ የአዲሱን ዓመት ብስራት ያጋራሉ።
ቀደም ብለው ሕፃናት የራሳቸውን አልባሳት አጥበው ወይም ደግሞ የተገዛላቸው ልብስ ለብሰውና አጊጠው አባበአየወሽን ያሳልፉት ነበር። ዛሬ ላይ አዲስ ነገር ተለምዷል። ተመሳሳይ የሆነ ዲዛይን ያለው የአገር ባህል ልብስ አሰፍተው መልበስ ተለምደዋል። በተለይ አሁን ላይ እየተለመደ የመጣው የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት ተጎናፅፈው አዳዲስ የዲዛይን ለውጦች የተደረገባቸው ባህላዊ ልብሶች ለብሰው የዘመን መለወጫውን ጥዑም ዜማ እያንቆረቆሩ በየቤቱ ይዞራሉ። አሁን ላይ ልጃገረዶች በእጃቸው አደይ አበባ ይዘውና የተለያዩ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት መግለጫ ካርዶችም ይዘው መዞር ጀምረዋል።
አዲስ ዘመን በወንድ ልጆች
በእርግጥ ከሌላው ዓውዳመት የሚለዩበት የአለባበስ ሥርዓት ወይም ልምድ ባይኖርም አሁን ላይ የተለያዩ የአገር ባህል አልባሳት ተውበውና በተለያዩ ዲዛይኖች አምረው በዓሉን ያሳልፋሉ። ሙሉ ነጭ በነጭ የሀበሻ አልባሳት ከታች ሱሪና ከላይ በሚያማምሩ ዲዛይኖች የተሰሩ የሸሚዝ ቅርጥ አልያም የክናቴራ መልክ ያለው የባህል አልባሳት በሕፃናቱ የሚዘወተር ነው።
በእርግጥ ከለበሱት የዓውዳመት ልብስ ጋር በመልክና በዲዛይን የሚመሳሰሉ ጫማዎች በሕፃናቱ አልፎ አልፎ የሚዘወተር ነው። የተለየ የጫማ አለባበስ ሥርዓት በሕፃናቱ አይታይም። ከአልባሳት ባለፈ የሚጫሙት ጫማ ለበዓሉ በተለየ መልኩ በፋሽንነት የሚጠለቅ ሳይሆን መደበኛ ወይም በአዘቦት ጊዜ የሚደረጉ የጫማ አይነቶች ይደረጋሉ። ወንድ ሕፃናት ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት እንደሚያደርጉት ሁሉ፤ አበባ ስለውና በየዘመድ አዝማዱ ቤት አልያም ጎረቤት የሚዞሩበትና አበባውን የሚሰጡበት ነው አዲስ ዓመት።
አዲስ ዘመን በወጣቶች
ዛሬ ላይ ትውልዱ ለአገሩ ባህል ትኩረት የሰጠ ይመስላል። በተለይ በበዓል ወቅት ይሄ ይገለጣል። ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እንደቀደመው ጊዜ የተዘጋጁ የውጭ ሀገር ልብሶች በበዓል ሰዓት አይለብሱም። የአገር ባህል አልባሳት በተለያየ መልክና በሚፈልጉት ዲዛይን አሰርተው መልበስ ልምዳቸው አድርገዋል። ለአዲስ ዓመትም ይህንኑ ባህላዊ አልባሳት በተለያየ ዲዛይን አሰርተው ይለብሳሉ።
ይበልጥ በሕፃናት ወጣቶች አልባሳትና ዜማ የሚደምቀው አዲሱ ዓመት ለአዋቂዎችም እንደ መስኩ ሁሉ የራሱን አዲስ ውበት ያላብሳል። ዛሬ ላይ ለባህሉ ልዩ ትኩረት የሰጠ ትውልድ ተፈጥሯልና ባህላዊ አልባሳት በብዙዎች ይዘወተራሉ።
ዛሬ ላይ ሀበሻ ልብስ ዋንኛ መታያ ጊዜው የበዓል ወቅት በተለይም እንዲህ ሰማይ ምድሩ በሚፈካበት አዲስ ዓመት ነው። ሀበሻዊ አልባሳት የሚነግሱበት በዓል ነውና የሀገር ባህል አልባሳት ከተሞቻችን ያጥለቀልቃሉ። የአገር ባህል አልባሳቱን የተጎናፀፉ ሰዎች መንገዶች ሞልተው ይታያሉ። ተጣጥፎ ከተቀመጠበት ሳጥን ተሸጉጦ ከከረመበት ቅርጫት ወጥቶ ታጥቦና ተተኩሶ ከሰው ጋር ይቀላቀሉበታል።
ኢትዮጵያውያን የራሳችን የሆነ ከሌሎች የሚለየን በራሳችን ጥበብ ተቃኝቶ ከአኗኗር ዘይቤያችን ተቀድቶ ተጎናጸፍነው የሚያምርብን ጥበብ ተላብሰነው የምንደምቅበት የባህል ልብሳችን መለያችን ነው። በተለይ እንዲህ በበዓል ወቅት እምር ብለን የምንታይባቸው የባህል ልብሶቻችን ባህሎቻችንን ያንፀባርቁልናል።
ሀበሻ ጠቢብ አይደል በራሱ ሸማ አዲሱን ዓመት በጥበበኞቹ በተሰሩ አልባሳት ይደምቃል። ቀድሞ የነበረውን የተለመደ የባህል አልባሳት ዛሬ ላይ በበዙት ዲዛይነሮቻችን ከሁሉ ጋር በልክ የተሰፋ ያህል ልዩ ውበት እንዲላበስ ማድረግ ችለውበታል። የፋሽን ዲዛይነሮች ዘመኑ የሰጣቸውን እውቀትን ተጠቅመው ቀድመው በልምድ ያገኙትን ክህሎቱ ጋር አዋዶ ጥበብ ላይ ጥበቡን ድርቦ ለልብስነት ያበቃዋል። አገሬው ደሞ ከራሱ ጋር የሚሄደውን መርጦ አዲሱን ዓመት አዲስ ሆኖ ይቀበልበታል።
እንዲህ አውዳመት በተለይ ሰማይ ምድሩ በሚፈካበት አዲስ ዘመን ላይ የባህል አልባሳት በማህበረሰቡ መዘውተሩ የላቀ ጠቀሜታ አለው። አጋጣሚው አገራዊ አልባሳት ወደገበያው በዝተው እንዲቀርቡ በማድረግ የኢኮኖሚና የባህል እድገቱ ላይ ታላቅ አዎንታዊ ሚና በመጫወትም ላይ ይገኛል። በሙያው ዘርፍ ያሉ ተዋንያንም ተጠቃሚና በብዙ መልኩ እራሳቸው የመለወጥ እድሉን ያሰፋላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ማህበረሰቡ ለራሱ ባህል ልዩ ትኩረት እንዲሰጥና ለአገራዊ ምርቶች የተሻለ ቦታ እንኖረው ያደርጋል። በዚህም እንደ አገር ይህ በጎ ልማድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ሊያስገኝ መቻሉ እሙን ነው።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 / 2015 ዓ.ም