ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ዛሬ እንኳን አደረሳችሁ ብዬ ልጀምር አይደል? ምክንያቱም አዲስ ዓመት ላይ ስንሆን ዋና ሰላምታችን ይህ ነው ።ክረምቱ አልፎ ሰማዩ የሚጠራበትን እለት አምላካችን ስለሰጠን የምናመሰግንበት ጊዜም ነውና እንኳን አደረሳችሁ መባባል አለብን ።ለመሆኑ ይህንን በዓል እንዴት ለማሳለፍ አስባችኋል፤ መጪውን የትምህርት ዘመንስ በምን መልኩ ለማሳለፍ አቅዳችኋል? እርግጠኛ ነኝ ብዙዎቻችሁ ዝግጅታችሁን ጨርሳችሁ የመግቢያ ቀናችሁን እየጠበቃችሁ ነው ።ምክንያቱም ይህ ጊዜ የናፈቋችሁን የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁን የምታገኙበት ነው ።በዚያ ላይ ከትምህርት ተለይታችሁ ቆይታችኋልና ያንን የናፈቃችሁትን ትምህርት መማር የምትጀምሩበትም ነው ።
በዚህ ወቅት ዘመዶቻችሁን ጭምር የምትጠይቁበትም ሊሆን ይችላል ።ምክንያቱም ክረምቱ አልፎ መስከረም ይጠባልና ነው ።በዚያ ላይ ሜዳው በሙሉ በአበባ የሚያሸበርቅበት ጊዜ ስለሆነ እንደልባችሁ ለመቦረቅና ከጓደኞቻችሁ ጋር ለመጫወት የምትችሉበት ወቅትም ነው ።እናም ይህ አዲስ ዓመት ሲመጣ ብዙዎቻችሁ እንደተደሰታችሁ ይሰማኛል ።ለመሆኑ ልጆች አዲስ ዓመት፤ እንቁጣጣሽ፤ ቅዱስ ዮሐንስና አውደ ዓመት የሚባለው ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ ? ለዛሬ ስለዚህ ነገር ትንሽ ልበላችሁ ።
አዲስ ዓመት ለምን ተባለ ከተባለ መልሱ ይህ ነው። በሰኔ ወር የገባው የክረምት ወቅት እየበረታ ሰማዩ በመብረቅ ብልጭታና በነጐድጓድ ድምፅ የሚታጀብበት፤ ከላይ የዝናብ ዶፍ ከሥር ጐርፍ የሚጨምርበት፤ አልፎ ተርፎም በረዶ የሚዘንበብት ጊዜ ነው። መስከረም ሲሆን ግን ሁሉ ነገር ይለወጣል ።ምድሪቱ በልምላሜ ትሞላለች ።አስፈሪዎቹ ከሰኔ እስከ ነሐሴ ያሉ ወራት ይለወጡና ምድሪቱን በበረከት ይሞሏታል ።በምድር ላይ አዲስ የሆኑ ነገሮች በስፋት ይታያሉ ።አንዱ ፀሐይ መውጣቷ ሲሆን፤ የበረደው ይሞቀዋል፣ የጨለመውም ብራ ይሆናል፤ የረጠበውም ይደርቃል ።በክረምቱ ዝናብ ረግፈው የነበሩት አበባዎች ሳይቀሩ ዳግመኛ ሕይወት ያገኛሉ። ንቦች በየጋራው በየሸንተረሩ ፈክተው የምናያቸውን አበባ ለመቅሰም ይሯሯጣሉ ።ቢራቢሮዎች በየመስኩ ይንሽራሸራሉ ።የመስቀል ወፍና የተለያዩ ወፎችም ከተደበቁበት ጐጆዎቻቸው ይወጣሉ ።በውሃ ሙላት ምክንያት የተራራቀ ዘመድም ይገናኛል ።በአጠቃላይ በመስከረም ስፍራው ሁሉ ለምለም፤ ፍጥረታት ሁሉ ደስታ ያገኛሉ ።በዚህም አዲስ መሆናቸውን አብስረው አዲስ ዓመት በማለት ያከብራሉ ።
እንቁጣጣሽ ማለት ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች ያሉት ስያሜ ነው ።የመጀመሪያው እንቁጣጣሽ ማለት ምድሪቱ በአበባ የምትንቆጠቆጥበት በመሆኑ ማሸብረቅ እንደማለት ነው ይሉታል። አንዳንዶች ደግሞ እንቁጣጣሽ ማለት እጽ አወጣሽ የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል ይላሉ ።በምክንያትነት የሚያነሱትም በመስከረም ወር እጽዋትና አዝርዕት ያብባሉና እጽ አበቀልሽ እንደማለት ይወስዱታል። እንቁ የሆኑ አበቦችና እጽዋትን አፈራሽ እንደማለትም ነው። ሌላው እንቁጣሽ ማለት እንቁ እጣ ወጣሽ የሚለውን ይይዛል። ይህ ማለትም በትውፊት የተቀመጠልን ሲሆን፤ የኖህ ልጅ ካም በእጣ አፍሪካ ስለደረሰቺው መልካም ዕድልን መረጥህ እንደማለት እንደሆነም ይነገራል ።ሌላው እንቁ እጣ አመጣሽ የሚለው ሲሆን፤ ንግስት ሳባ ለሰለሞን የሰጠችው ከሀርና እንቁ የተሠራውን ስጦታ ያመለክታል። የመጨረሻው ደግሞ ለሳባ እንቁ ለጣቷ መሰጠትን የሚይዝ ነው።
ቅዱስ ዮሐንስ የሚባለው ደግሞ በነቢዩ ዘካሪያስ ልጅ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሲሆን፤ መጥምቁ ዮሐንስ በብሉይና ሃዲስ መካከል የተፈጠረ እና «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ የኖረ፣ በመጨረሻም በሄሮድስ ትዕዛዝ ጭንቅላቱን የተቆረጠ ትልቅ ሰማዕት ነው ።በዚህም ምክንያት የቤተክርስቲያን አባቶች የበዓላትን ስርአት ሲሰሩ፣ ይህ በዓል ለመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ መታሰቢያ እንዲሆንና በእሱ ስምም እንዲጠራ በመወሰናቸው ነው ።
በመጨረሻ ለምን አውደ ዓመት እያልን እንጠራዋለን የሚለውን እንመልከት ።ዘመናት ዘመንን እየወለዱ ሰዓታት ደቂቃ ወይም ሰከንድን እየሰፈሩ፤ እለታት ሳምንታትን ሳምንታት ወራትን ወራት ደግሞ ዓመታትን እየተኩ አሁን ያለንበትን ጊዜ ይሰጡናል ።በእነዚህ መካከል የሚከወነውን ኡደት ደግሞ የምናየውና የምንገልጸው የዓመቱን ዙረት በማየት ነው ።እናም አውደ ዓመት ማለት የዓመት ዙረት የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል ።ለዚህም ነው አውደ ዓመት እያልን እንድናከብር የሆነው ።
ልጆች መስከረም የዘመን መለወጫ ወርም በመባል ይጠራል ።ዘመን መለወጫ የተባለውና ለምን መስከረም ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንት እንዲህ በማለት ያብራሩታል። ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው ።ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል ።በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም ።በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር ጭምር ነው ።ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወትም የሚለወጥበት ጊዜ ነው ።ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው የክረምቱን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን የበጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚያይበት ሌላም ሌላም ክስተቶች የምናይበት ነው ።ስለዚህም እነዚህ ሁሉ ክስተቶችን እያየን ስንሄድ ዘመን ተለወጠ እንላለን ።
ልጆች በአባቶች ምርቃት ልሰናበታችሁ ።ምክንያቱም ይህ ዘመን ሲከበር ምርቃቶች በየአቅጣጫው ይጎርፋሉ። እናም እኔም እንዲህ ልላችሁ ፈለግሁ ።አሜን ማለቱን እንዳትረሱ እሺ ‹‹ዝናሙን ዝናመ ምሕረት፣ እህሉን እህለ በረከት ያድርግልን፣ ሰላም ይስጠን፣ እህል ይታፈስ፣ ገበሬ ይረስ፣ አራሽ ገበሬውን፣ ሳቢ በሬውን ይባርክ፣ ቁንጫን፣ አንበጣን፣ ትልን… ያጥፋ፣ ምቀኛን ሸረኛን ያስታግስልን፣ ወጡ ገቡ ሰቡ ረቡ የሚለውን ሁሉ እግሩን ቄጠማ ዓይኑን ጨለማ ያድርገው ››። መልካም አዲስ ዓመት!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን 2015 ዓ.ም