የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ከህብረተሰቡ ደረሰኝ ባለው ጥቆማና አካሄድኩት ባለው ጥናት በአምስት ፋብሪካዎች የፍሳሽ አወጋገድ ችግር ሳቢያ ከ1700 በላይ ደብረብረሃን ነዋሪዎች ለአደጋ ተጋልጠዋል ሲል አስታወቀ።
በዩኒቨርስቲው የህግ ኮሌጅ መምህር የሆኑት አቶ መሰለ ወንድማገኘሁ ዩኒቨርስቲው አካሄደው ባሉት ጥናት አምስት ፋብሪካዎች ባለባቸው የፍሳሽ አወጋገድ ችግር ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሚባል የጤና እክል እያደረሱ ናቸው ሲሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል። አቶ መለሰ አክለውም የክልሉ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ 15 ፕሮጀክቶች ፍሳሽ አጣርቶ መልቀቅ ላይ ችግር ያለባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
መምህር መለሰ፤ ማንኛውም ፋብሪካ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት አድርጎና ይሁንታን አግኝቶ ወደ ስራ መግባት ይኖርበታል ብለዋል። ይሁንና ይህ ባለመደረጉ ከ1700በላይ ነዋሪዎች አደጋ ውስጥ የገቡ መሆኑ ነው የታየው ብለዋል መምህሩ። ለዚህ ደግሞ ተናቦ አለመስራትና ቸልተኝነት አንዱ ችግር መሆኑን መምህሩ ጠቅሰዋል።
በከፍተኛ መጠን አደጋ እያደረሱ ያሉት የቢራ፣ ባህርዛፍን በመጭመቅ ለተለያየ አገልግሎት የሚያውለው ፋብሪካ፣ የአረቄና የቆዳ ፋብሪካዎች መሆናቸውን የሚያነሱት መምህር መለሰ፤ በነዋሪዎች ላይ የመተንፈሻ አካላት ችግር በብዛት ታይቷል። በተለይ ህጻናት አደጋ ውስጥ በመሆናቸው በማስረጃ ጭምር የተረጋገጠ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል። ከብቶችና ለአገልግሎት የሚውለው መሬታቸው ሳይቀር ከጥቅም ውጪ የሆነባቸው ነዋሪዎችም እንዳሉ ለማረጋገጥ መቻሉን አቶ መሰለ አንስተዋል።
እንደ መምህር መለሰ ገለጻ፤ ፋብሪካዎቹ ክሮም የሚባል አደገኛ የሆነ ኬሚካል በሁለት መቶ ሜትር የቱቦ መስመር ከወንዞች ጋር እንዲቀላቀል በማድረግ ለውሃ አካላቱም ሆነ ለማህበረሰቡ ትልቅ አደጋ ፈጥረዋል። አንዳንድ አካባቢ ላይ እያደረሰ ከመጣው ትልቅ አደጋ በመነሳትም የውሃ ሀብትን መጠቀም አስፈሪ ሆኗል ብለዋል አቶ መሰለ።
በቤተሙከራ በምን ያህል መጠን ፍሳሹ እየጎዳ እንዳለ ባይታይም፤ በተገኘው ምላሽና በታየው ማረጋገጫ ግን ነዋሪዎቹ በጤና፤ በንብረትና በውኃ አካላት ላይ በሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን መምህር መለሰ አስረድተዋል።
የሰላሳ ቀን ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውና ሂደቱን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን እየተከታተለው መሆኑን የገለጹት መምህር መለሰ፤ በሁለት ወር ውስጥ ፋብሪካዎቹ ወደሚፈለገው መስመር የማይገቡ ከሆነ ክሱ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል መምህሩ።
አዲስ ዘመን 2011 ዓ.ም
በጽጌረዳ ጫንያለው