ኔልሰን ማንዴላ እንዲህ ብለው ነበር ‹‹ስፖርት ዓለምን የመለወጥ ኃይል አለው ፡፡ ሰዎችን የማስተባበር ፣ የማነቃቃት ኃይል አለው … የዘር መሰናክሎችን ለማፍረስ ከመንግስታት የበለጠ አቅም አለው››፡፡ እናም የቀድሞውን የደቡብ አፍሪካ መሪና የነፃነት ታጋይ ቃል በመቀላቀል የተባበሩት መንግስታትም የ2030 ዘላቂ ልማት አጀንዳ መግለጫ ስፖርት ለልማት፣ ለሰላምና አንድነት ግቦች ለሚጫወተው ሚና ልዩ ቦታና እውቅና ይሰጣል፡፡
ስፖርት በተመሰረተባቸው አዎንታዊ እሴቶች የተነሳ ለአንድነት፣ ለሰላምና ለልማት ሁነኛ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በርካታ አገራትም ይህን የስፖርት ትሩፋት በአግባቡ የተጠቀሙበት ብዙ አጋጣሚዎች በታሪክ ይታወቃሉ።
አገራት ብቻም ሳይሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ስፖርትን ለአንድነት ይጠቀሙበታል። የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭትን ለመፍታት ተመድ ከተጠቀመባቸው ዋነኛ መንገዶች ስፖርት አንዱ ነበር። ስፖርቱን እንደ መፍትሄ ለመጠቀም ምክንያት የነበረው አጋጣሚ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በደቡብ ሱዳንና በጋቦን መካከል የተደረገው ጨዋታ እንደነበር ብዙዎች አሁንም ድረስ አይረሱትም። ደቡብ ሱዳን ተጋጣሚዋን 1ለ0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ውጤቱ በአገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት የቆሸሸው የአንድነት ስሜት ከተቀበረበት ገንፍሎ እንዲወጣ አደረገ። የአገሪቱ ህዝቦች በብሔር፣ በጎሳ ተመዳድበውና በጠላትነት ተፈራርጀው እርስ በእርስ ከመጋደል በአንድነት ስለ አገራቸው እንዲያዜሙ ያደረገ ክስተት ተፈጠረ። የልዩነት ቀለም ደብዝዞ የአንድነትና የወንድማማችነት ስሜቱን ከፍታ ያስመለከተ ክስተት በተግባር ተገለጸ።
ከስፖርታዊ ድሎች የሚቀዳ ድብቅ የብሔራዊ ስሜት ሲፍለቀለቅ ማየት አዲስ አይደለም። ዛሬ የአንድነት ቀን ነውና የሩቁን ትተን በዚህ ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ባገኘቻቸው ድሎች በፖለቲካ፣ በዘውግና በተሳሳተ ትርክት ተከፋፍለው በማህበራዊ የትስስር ገጾች ዘወትር ሲቆራቆዙ የሚስተዋሉ አካላት ሳይቀሩ ስፖርታዊ ድሎች በፈጠራቸው ስሜቶች እንዴት ወደ አንድነት እንደመጡ አስተውለናል። በነዚህ ድሎች እየተሸረሸረ የመጣው አገራዊ ስሜት እንዴት ገንፍሎ እንደወጣም አንዘነጋውም።
እንዳጋጣሚ ሆኑ ዛሬ የምንሸኘው የ2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ካለፉት በርካታ ዓመታት በተለየ በዓለም አቀፍ የተለያዩ ስፖርት መድረኮች ጣፋጭ ድሎችን ያገኘችበት ነው። ኢትዮጵያ እንዲህ በጦርነት ፈተና ውስጥ በገባችበት ወቅት፣ ሕዝቦቿም በመፈናቀል፣ በንጹሃን ዜጎች ግድያ፣ በኑሮ ውድነትና በፖለቲካ ውጥረት አንድነታቸውን ለመሸርሸር ፈተናዎችን በሚጋፈጡበት ወቅት በስፖርት ያገኘችው ያልተለመደ ስኬት ብዙ ትርጉም አለው። እነዚህ ድሎች በኢትዮጵያ ተስፋ የቆረጡ ተስፋቸው እንዲለመልም ሆኗል፣ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም የሚሉ ሳይቀሩ ወደ ኢትዮጵያዊነት ለመመለስ ሲቀምጡ ታይተዋል፣ ክፉዋን የሚመኙም በነዚህ ድሎች አንገታቸውን ደፍተዋል፡፡
ባለፈው መጋቢት በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ አሜሪካንን አስከትላ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ የሁልጊዜም የኩራት ምንጭ በሆኑት ብርቅዬ አትሌቶቿ ድል ያልፈነጠዘ የለም። በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ ግብጽን ከ60 ዓመት በኋላ ሲያሸንፉ ስለ ኢትዮጵያ ጮቤ ያልረገጠ፣ ብሔራዊ መዝሙሯ የተለየ ስሜት ያልፈጠረበት የለም። ከወራት በፊት በኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና እንዲሁም በኮሎምቢያ ካሊ የወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ብርቅዬዎቹ አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያ አፍሰው የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ ደጋግመው ሲያስጠሩ በአገሩ ያኮረፈ ሳይቀር ውድድሮችን በጥፍሩ ቆሞ ተመልክቷል። እነዚህ ድሎች ለወትሮው በፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮች ተወጥረው የከረሙ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ አጀንዳቸው ስፖርትና ስፖርት ብቻ እንዲሆን አድርገዋል። ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካ፣ አመለካከት፣ ጾታና እድሜ ሳይለይ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል አንድ የሆነበት አጀንዳ ቢኖር እነዚህ ድሎች ናቸው።
እነዚህ ድሎች ኢትዮጵያውያንን በአንድ ያስደሰቱ ብቻ አይደሉም። ድሎቹ በራሳቸው በአንድነት የተገኙ ናቸው። ለነዚህ ድሎች የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የትኛውም ብሔር፣ የትኛውም ወገን ተጠሪ አይደለም። እነዚህ ድሎች ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ እንቁ ስፖርተኞቿ በአንድነት ያስመዘገቧቸው ናቸው። ውጤቶቹም በየትኛውም መንገድ ከመለያየት ይልቅ እንደ አገር አንድ ሆኖ የመቆም ሚስጥሮች ነበሩ።
ከብዙ በጥቂቱ የተጠቀሱት ማሳያዎች ስፖርት አገራዊ አንድነትን ለመፍጠር፣ ሰላምን ለማስፈን ያለውን ጉልህ ድርሻ ለመጠቆም ያህል እንጂ ብዙ መናገርና ብዙ መጻፍ ይቻላል። ስፖርትን ለአንድነትና ለሰላም አሳንስር አድርጎ መጠቀም ኢትዮጵያን ካለችበት በርካታ ችግሮች ለማውጣት የሚደረገው ጥረት በእጅጉ እንደሚረዳ ተገንዝቦ መንግስትም በአግባቡ ሊጠቀምበት እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ ማስታወስም ተገቢ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ከገጠሟት ፈተናዎች አኳያ በህዝብ ዘንድ ያለውን መተማመን ለማጠንከር፣ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች አንድነትን እንዳይሸረሽሩ ድልድይ እንዲሆን የስፖርት ዘርፍን እንደ ቁልፍ መፍትሄ የመጠቀም ጥረት በአዲሱ ዓመት እንደ አዲስ ልንጠቀምበት ይገባል። በተለይም በህዝቦች መካከል መቻቻልን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን…የሚሰብኩ የውድድር መድረኮችን ቀርጾ ወደ ተግባር መግባት ቢቻል የሸፈተውን ብሄራዊ ስሜት መመለስ እንደሚቻል በአንድነት ቀን ላይ ልናስብና ልንተገብረው እንደሚገባ ማስታወስ አስፈላጊ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም