በልዩነት ውስጥ አንድ ሆነው የሚዘልቁባት አገር ናት ኢትዮጵያ። በመተሳሰብ እና መቻቻል የሚያድሩባት አገራችን ከሁሉ ጉዳዮች ከፍ ያለች ናት። ጉዳዮቻችንን ተቀምጠን እንድናወራ አለመግባባታችንን ተነጋግረን መቅርፍ እንድንችል ቀድመን አገር ያስፈልገናል። ይህቺ አገር ደግሞ አንድነትዋ የፀና መሆን ይኖርበታል፤ ያንን የምናፀናው ደግሞ እኛ ነን። ስለ አገር ብለን ሁሌም አንድ ሆኖ መቆም ግድ ይለናል። የፀናች እና በሌላው የማትደፈር አገር የሚገነባው ደግሞ አንድ ሆኖ በመቆም ነው።
አንድነትና አንድ አይነትነት የተራራቁ ናቸው። ሁለቱ እጅግ የተለያዩ ትርጓሜ ያላቸው ሃሳቦች ቢሆኑም ልዩነታቸውን በቅጡ የሚረዱት ግን ቁጥራቸው ያንሳል። አንድ መሆን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ይገባንና፤ አንድ ለመሆን ግን አንድ አይነት መሆን ያለብን ይመስለናል። በዚህም ምክንያት አንድ ለመሆን ሁሉንም አንድ አይነት ማድረግ አለብን እንላለን። ነገር ግን አንድ ለመሆን አንድ አይነት መሆን ፈፅሞ አያስፈልግም።
እኛ በአንድነት ፀንተን የምንኖር፤ ስለእርስዋ ለውጥና ህዳሴ አንድ ሆነን የምንቆም ሁላችንም የምንጋራት አንዲት አገር አለችን። ይህቺን አንድ አገር ጠንካራ ለማድረግ አንድ መሆን ግድ ይለናል። ለውጧን ለማቅረብ መተሳሰርና ህብረታችን ወሳኝ ነው። ነገር ግን እኛ ብዙ ነን። የተለያየ ቋንቋ፣ ባህል፣ ብሄር፣ እምነት እና ማንነት ያለን እጅግ ቁጥራችን የበዛ ሕዝቦች ነን።
ታዲያ እዚህ ላይ ነው ዋንኛው ጉዳይ እነዚህ ልዩነቶች ወደ አንድ አይነት ማቀራረብ ፈፅሞ አይቻልም፤ግን አንድ ሆነ አንዲት አገራችንን ማፅናት ይችላሉ። የአገራችንን አንድነት ለማፅናት አንድ ሆነው ለመቆም አንድ አይነት መሆን አይጠበቅባቸውም።
ስለምን አንድ አይነት ስላልሆንን አንድ መሆን ያቃተን ይመስለናል? እስኪ የእጃችንን ጣቶች እንመልከት አንድ እጃችን ላይ ያሉ ነገር ግን አንድ አይነት ያልሆኑ። አጭር ረጅም መካከለኛ ናቸው። በውፍረትም አንዱ ካንዱ ይለያያሉ። ነገር ግን የተለያዩ ተግባራት ስንከውን አንዱ ለሌላው ረዳት ሆኖ በአንድነት አንድን ተግባር እንድንፈፅም ያግዙናል። በልዩነታቸው ውስጥ ህብረት ፈጥረው ተግባራችንን በወጉ እንድንወጣ ይረዱናል።
አንድ መሆን ከአንድ አይነትነት ጋር ፍፁም ይራራቃል። እንኳን ሌላው እንደኛ ካላሰብክ አላቀርብህም ማለት ቀርቶ፤ እኛ ሌላ ውጫዊ አካል በሌለበት ሁኔታ የተለያየ ሃሳብ ወደ አዕምሮአችን ይፈልቅና ሙግት ውስጥ እንገባ የለ?
ኢትዮጵያ በአንድነትዋ ፀንታ ትኖር ዘንድ አንድ የሆነ የጋራ አቋም ሊኖረን ግድ ይላል። እርስዋ ውስጥ የምነገኝ እኔ አንተ እና አንቺ ወይም እኛ ሁላችንም አንድ ሆነን መቆም እንችላለን አንድ አይነት መሆን ግን አንችልም። የየራሳችን መልክ፣ አመለካከትና ባህሪ ተላብሰን እንድ የሆነችዋን አገራችን በአንድነት ቆመን ማፅናት እንችላለን። እኛ አንድ ሆነን ሺህ መሰናክሎችን ማለፍ የምንችል ነን።
የአንድነት ታላቅነት ከአያቶቻችን በላይ ያስተማረን እውነት የለም። አንድ ሆነው ትልቅዋን አገራችንን ያስረከቡን ጀግኖች ዛሬ ተፈጥሮአዊ የሆነው ልዩነት ምክንያት ልናለያየው ከቶም አይገባም። ብዝሀነት ያከበረ ጠንካራ አንድነት ከእርነሱ መማር ይገባናል።
አንድነት ጥንካሬ ያላብሳልና ለአሸናፊነት ያቀርባል። አሸናፊ የሚያደርገን አንድነት ለመላበስ ግን የግድ አንድ አይነት ሆነን መገኘት የለብንም። በፖለቲካ አመለካከት በባህል በሃይማኖትና በተለያዩ ማሕበራዊ ክፍፍሎች ውስጥ መገኘታችን እውነት ነው። ይህን መቀበል ግድም ይለናል። መልመድ ያለብን እነዚህን እንዴት እናስታርቅ፤ እንዴትስ ለአንድነታችን ጥንካሬ እንጠቀምባቸው የሚለው ነው።
በፖለቲካ አቋማችን ብንለያይ፣ በእምነትና በአስተሳሰባችን ብንራራቅ ምንም አዲስነት የለውም። አንድ ሆኖ ለመቆማችን ምንም አይነት እንቅፋት አይፈጥርም። በተገኘንበት ማንነት አንድ አይነት ባንሆንም አንድ ሆነን በመቆም አንዲት የፀናች አገር መመስረት እንችላለን። አባቶች ችለውም አሳይተውናል።
አንድ ትልቅ የጋራ ጉዳይ አለን። እስዋም አገራች ናት። ጉዳዮቻችን ሁሉ ታላቅ ከሆነችው ኢትዮጵያ በታች ናቸው። በየጊዜው እዚህና እዚያ እያነሳን የምንጫቃጨቅባች፣ የማያግባቡን የሚመስሉ ሃሳቦችና አመለካከቶች ሁሉ ከዚህች አገር እጅግ በጣም ያነሱ ናቸው። ምክንያቱም ሁሉም ሃሳቦች ያሉት እስዋው ውስጥ ነው። ከሚለያዩ ነገሮች ከፍ የሚሉት የሚያቀራርቡን ናቸው። ለኢትዮጵያ ግዝፈት ልዩነቶቻችን አሳንሰን ብናያቸው ያግባቡናል። ለአገር ጥንካሬና ህልውና ስንል ተቀራርበን ብናወራባቸው እጅጉን ይቀሉናል።
ብዝሀንት የበረከተባት ኢትዮጵያ ሰፊ አገር ናት። ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባት። መቶ ሚሊዮኑ አንድ አይነት አቋም ሊያንፀባርቅ ፈፅሞ አይችልም፣ መቶ ሚሊዮኑም አንድ አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ሊኖረው ከቶም አይቻለውም። ነገር ግን መቶ ሚሊዮኑም በአንድነት የሚኖርበት አንድ አገር አለው። የቁጥሩ ያህል እንኳን የተለያየ አመለካከትና እምነት ቢኖረውም አገር በሚለው እሳቤ ግን መፅናት፤ አንድ ሆኖ መቆም ግድ ይለዋል።
ኢትዮጵያ በደስታችን ወቅት የቦረቅንባት፣ በኀዘናችንም ጊዜ አንባችንን የምናብስባት በቸገረን ጊዜ የምንጠለልባት ለሁላችን የምትበቃ ሰፊ ጎጆ ናት። ስለዚህም ፀንታ እድትኖር ማድረግ ግድ ይላል። ስናኮርፍም ስንደሰትም እስዋ አገራችን ናት። በቅሬታችን ወቅት ትተናት በደስታችን ጊዜ አለሁ የምንላት እርስታችን አይደለችም።
ኢትዮጵያ ጽኑ የሆነች አንዲት አገር በመሆንዋ ላይ ፈፅሞ የአቋም ለውጥ ሊኖረን አይገባም። በድሎታችን አገራችን እዳልነው ሁሉ፤ በመከፋታችን ጊዜ አገሬ ማለት ግድ ይለናል።
የፖለቲካ አመለካከታችን ስለተለያየ እና የፖለቲከኞች ተግባር ስላልጣመን አገር የምንጠላ፤ በአንፃሩ ደግሞ ስለተመቸን ኢትዮጵያዬ የምንል ዜጎች መሆን ፈፅሞ አይገባም። በመከፋትም በመደሰትም ወቅት አገር አገር ናት። መልካም አይደለም ብለን የምናስበውን ውሳኔና ተግባር በሰከነ መልኩ እኛ ጋር ያለውና የተሻለ ነው የምንለው መፍትሄ አቅርበን መፍታት እንጂ የራስን ፅንፍ ይዞ የሌላን መገፍተር ተገቢነት የለውም።
ዛሬ ላይ መጥፎ ልማድ ተፀናውቶናል የመስጠት እንጂ፤ የመቀበል ልምዱ የለንም። የእኔን እንካ ያንተን እንዳታመጣ የሚለው ስሌት ጋር ተጋብተናል። የእኔ ሃሳብ መልካም ነው፤ የአንተ ግን የሚያሻግር አይደለም ብሎ ማሰብ ልክ አይደለም። ሁሌም መዘንጋት የሌለብን አንድ ለመሆን የግድ አንድ አይነት መሆን እንደሌለብን ነው።
ኢትዮጵያ የበርካታ ባህልና ማንነት መድረክ ናት። ለዘመናት ሕዝቦችዋ አንድ ሆነው ቆመው ሉዓላዊነትዋ አስከብረው ዘልቀዋል። ዛሬ ላይ አዲስ የተፈጠረ የአመለካከት ልዩነት አልያም ደግሞ የእምነት መለያየት የለም። ባይሆን እምነትና አመለካከታችን የምንተረጉምበትና በተሳሳተ መንገድ የምንተገብርበት ሁኔታ ነው የንትርካችን ሰበቡና ያለመግባባታችን መነሻው። ሰፊ አገር ላይ የሰፋ ሃሳብ ይዞ ቀርቦ መሞገት የተሳሳተው ማርም እንጂ የሚገባው ጉዳዮችን አጣቦ ይዞ መፍቻ መንገዶቹን መዝጋት አይገባም።
ያለችን አንዲት አገር ናትና በእስዋ ጥቅምና ህልውና ፈፅሞ ልንደራደር አንችልም። ጉዳዮቻችን ከእስዋ ማነሳቸው ተረድተን ጉዳዮቻችን ሁሉ ከእስዋ ጥንካሬና መፅናት ጋር ማያያዝ ይገባል። ሁላችንም በጋራ አቅፋ የያዘች የጋራ ቤት ናት። እንደኔ ለምን አላሰብክም አያሻግርም፤ ለምን እኔ እንደፈለኩ አትሆንም የትም አያደርስም። አዎ ብዙ ነን ግን አንድ መሆንና አንድ ሆነን መቆም ግድ ይለናል።
ተፈጥሮአዊ በሆነው ልዩነት ማመን አንድ አይነት ካልሆንን ለምንለው እኛ መፍትሄ ነው። ተለያይተን በብቸኝነት መጓዙ አቅም ቢያሳጣ እንጂ አያፀናም። ፍፁም አንድ የሆነ ማንነትና አንድ አይነትነት የለም። ምን አልባትም እንደምናስበው አንድ አይነትነት መርጠን የምንመሰርተው ቡድን በራሱ የተለያየ አመለካከትና ማንነት የተላበሰ መሆኑ ይገባናል።
በአንድ አይነት ፍላጎት ለመመስረት ከምናስበው ቡድን ይልቅ፤ የአንድነት ጥንካሬ ገብቶን በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ አተኩረን በአንድነት የምንቆምበት ፅናትና ለውጡን እንመለከታለን። ብዙ ነንና አንድ አይነት አመለካከት ልንላበስና ተመሳሳይ አቋም ልናፀባርቅ አንችልም። እንደ ብዝሀነታችን አመለካከታችን ሊለያይ፤ አቋማችን ለየቅል፤ ሃሳባችን የማይጣጣም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአንዲት አገር ውስጥ የምንገኝ አንድነት የምንጋራ ዜጎች ነን።
በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የአቋም ልዩነት ሊኖረን ይችላል፣ ብዙዎች የተስማሙበት በግለሰብ ደረጃ ላንቀበልም እንችላለን። ነገር ግን የራስን አቋም ማንፀባረቅና የሌሎችን ሃሳብ ማክበር ልማዳችን ሊሆን ይገባል። ከእኛ ፍላጎት ውጪ በሆነ ልንቆጣ፣ ከቁጥጥራችን ውጪ በሆነው ልናዝን አልያም ደግሞ እጅጉን አምርረን ልንቃወም እንችላለን። ነገር ግን አገር ልንጠላ ወይም ለኢትዮጵያ አገራች ያለንን ስሜት ሊለወጥ ፈፅሞ አይገባንም።
ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከእኛ ስሜት የገዘፈች ናት። ስናኮርፍ የምንተዋት፤ ስንታረቅና በሃሳብ ስንግባባ አለሁልሽ ብለን የምንቆምላት ብቻ አደለችም። ስንስቅ ኢትዮጵያ እንዳልነው ሁሉ በመከፋታችን ውስጥ ከስሜታችን ከፍ ያለችው ታላቅዋን አገር አገሬ ማለት ይገባል።
አንድ እንዳንሆን መለያያ አጀንዳ ፈብርከው ሌሎች ያቀብሉናል። ደካማ እድንሆን ስለሚፈልጉ የሚያለያየንን ጉዳይ ይሰብኩናል። ያኔ ከአንድነት ይልቅ መለያየታችን ይጎላብናል። ይህ ግን የተሳሳተ እሳቤ ነው። ኢትዮጵያ የተፈጠረችው አንድ አይነት ስለሆነች አይደለምን ግን አንድ የሆነ አቋም ባላቸው ሕብረትና ትስስር በገባቸው ታላላቅ አሳቢዎች ነው።
እኛ እየፈጠርን ለአገራችን ሰላም የማይበጅ ለሕዝባችን አንድነት እንቅፋት የሚፈጥር አመለካ ከትና ተግባር ውስጥ በተደጋጋሚ እንወድቃለን። ነገር ግን በመስከንና አገሬ በማለት እስዋን በማሰብ ከስሜታችን በመስከን ነገሮችን በስክነት መፈተሽ ደጋግሞም ማሰብ ይበጃል።
ብዝሀነት የእኛ መገለጫ ነውና ያንን አክብሮ በሰለጠነ መንገድ መራመድ ይገባል። በዚያ ልዩነት ውስጥ ወደ አንድነት የሚያቃርቡ ጉዳዮችን ማጉላት የሚያስተሳስሩት ላይ መስራት የእኛ ድርሻ ነው። የተለመደ ነውና፤ በፖለቲካ ልዩነት አልያም ደግሞ በእምነት መለያየት ምክንያት ልንኳረፍ እንችላለን። ነገር ግን በመኮራረፋችን የማንተዋት ታላቅ የሆነች የጋራ አገር አለችን።
ልዩነታችንን አጥበን አልያም ደግሞ ተቻችለን የምንዘልቅባት አንድ ሆነን የምናድርባት ከተፋቀርን ለሁላች የምትበቃ ውብ አገር አለችን። ሁሌም ትኩረታችን ሊሆን የሚገባው ልዩነቶችን በምን መልክ ማቻቻል ወይም ማቀራረብና አብሮ ማስኬድ ይቻላል የሚለው ላይ ነው። በእርግጥ ልዩነትን አጥብቦና መነቃቀፎችን ቀንሶ፤ ሰላማዊ የሆነ አካታች ውይይት ማድረግ አን ድአይነት መሆን ሳይሆን አንድ አድርጎ የሚያኖር መቻቻል መላበስ ይቻላል። ቸር ያሰማን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም