ዓመታዊ የጤና ምርመራ ወይም (Annual health checkup calendar) እንዳለ ምን ያህሎቻችን እናውቃለን? ጥቅሙስ ምን እንደሆነ እንረዳለን? ለመሆኑ ይህ ቀን እንደ አገር መቼ ይከበራል? ዛሬ ስለዚህ ጉዳይ ልናወጋችሁ ወደናልና ተከተሉን:: ዓመታዊ የጤና ምርመራ አዲሱ ዓመት መጣሁ በሚልበት ወቅት ጳግሜን ተንተርሶ የመጨረሻው ቀን ላይ ይከናወናል:: ጤናማ ሆነን እንድንሻገር ማለት ነው::
ይህ የዛሬው እለት ማለትም ጳግሜን 5 ዓመታዊ የጤና ምርመራ ቀን ብለን እናከብረዋለን:: ስንቶቻችን አድርገነዋል ቢባል መልሱ ጥቂቶች የሚል ይመስለኛል:: ምክንያቱም ሙሉ ምርመራ ወይም ዓመታዊ የጤና ምርመራ እንደ አገራችን የተለመደ ባለመሆኑ ::
በእርግጥ እንደባህል አድርገን የምንናገራቸው በርካታ ንግግሮች ነበሩን አልተጠቀምንባቸውም እንጂ:: ለአብነት ቀድሞ መመርመር ያለውን ጠቀሜታ ከማጉላት አንጻር ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› እንላለን ተግባሩ ወዲያ ንግግሩ ወዲህ ሆኖ ሳይገናኙ ቢቀሩም:: ለማንኛውም ይህ ቀድሞ መመርመር ወይም ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ ምን ይጠቅማል? ዓመታዊ ምርመራ ማለትስ ምንድነው? እንዴት ምርመራው ይከናወናልና መሰል ነጥቦችን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘነውን አብነት በማድረግ እናውጋችሁ::
አጠቃላይ የጤና ምርመራ ሲባል ምን ማለት ነው ?
ሰዎች ገና ከመታመማቸውና አልጋ ይዘው ከመተኛታቸው እንዲሁም በበሽታው ምክንያት ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት፤ በሽታዎችን በመመርመር የተወሳሰበ የጤና ችግር ከመድረሱ አስቀድሞ ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ ነው:: በተጨማሪም የግለሰቡን ለተለያዩ በሽታዎች የተጋላጭነት ደረጃውን ለመለየት የሚያገለግል ምርመራ ማለት ነው::
የዓመታዊ ምርመራ ጥቅም
ሰዎች ከመታመማቸው አስቀድሞ የሚያደርጉት አጠቃላይ የጤና ምርመራ የሚሰጠው ጠቀሜታ በግለሰብና በሀገር ደረጃ የሚታይ ነው:: ግለሰቦች ከመታመማቸው አስቀድሞ የጤና ሁኔታቸው በምን ደረጃ እንዳለ ማወቅ ይችላሉ:: የጤና ችግር ካለ ህመሙ ስር ሳይሰድና የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ተገቢውን ህክምና በማድረግ ፈጣን መፍትሄ ማግኘት የሚችሉበትን ዕድል ይሰጣል:: በተጨማሪም የአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ በማድረግ ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ ያስችላቸዋል::
እነዚህ ጥቅሞች የሚገኙት በአነስተኛ ወጪ መሆኑ ሲታይ ደግሞ አስቀድሞ በሚደረግ ምርመራ፣ የጤና ሁኔታን በየጊዜው መከተል ጠቀሜታው በምንም ሊተካ የማይችል መሆኑን መገንዘብ ይቻላል:: በተጨማሪም የተሟላ ጤና፣ ጠንካራና በራሱ የሚተማመን ማሕበረሰብ ለመፍጠር ያስችላል::
በሌላ በኩል ጠቀሜታው ከሀገር አንፃር ሲታይ፣ ማሕበረሰቡ አስቀድሞ የመመርመር ባህሉን ቢያዳብር፣ በቀላል ምርመራ ህመምተኛውን በመለየት በወቅቱ የማከም ዕድልን ስለሚፈጥር በጤና ተቋማት ላይ የሚታየውን የህክምና ፈላጊ ጫና ይቀንሳል:: ህሙማን በሽታው ከተባባሰባቸው በኋላ በመምጣት ለከፍተኛ ወጪና እንግልት የመዳረጋቸው ጉዳይ ያጠፋዋል:: ይህ ደግሞ ሀገሪቱ በጤናው ዘርፍ አክሞ ለማዳን የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ ያግዛል::
የግድ ቅድመ ምርመራ ሊደረግባቸው የሚገቡ የጤና ችግሮች
ሰዎች ከመታመማቸው አስቀድሞ በየጊዜው ቅድመ ምርመራ ሊያደርጉባቸው የሚገቡ የጤና ችግሮች በርካታ ናቸው:: ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የበለጠ ትኩረት የሚሹ በሽታዎችን ማንሳት ተገቢ ነው:: እነዚህ በሽታዎች የማህፀን፣ የጡት ካንሰር፣ የፊኛ፣ የዘር ፍሬ፣ የአንጀትና የጨጓራ ካንሰር፣ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ኮሌስትሮልና ኤች.አይ.ቪ፣ የልብና ከልብ ጋር ተያያዥነት ላላቸው ህመሞች ትኩረት ሰጥቶ ቅድመ ምርመራ ማድረግ ይገባል:: ከእነዚህ የጤና ችግሮች በተጨማሪ ለዓይን፣ ለጥርስ፣ ለጆሮ፣ ለውፍረትና በደም ውስጥ የስብ መጠን መብዛትን ተከትሎ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል::
ለቅድመ ምርመራ የተለየ ትኩረት መስጠት ለምን ያስፈልጋል ?
የሞት መጠንን ለመቀነስ፣ የአካል ጉዳትን ለመከላከል፣ ደስታ ማጣትን ለማስቀረት፣ በምንም ነገር ላይ ያለመርካት ስሜትን ለመለወጥ፣ ምቾት አለመሰማት ካለ ችግሩን ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት፣ ድህነትንና በማሕበረሰብ ደረጃ የሚከሰቱ ጫናዎችን ለመቀነስ እንዲሁም በሽታው ሳይባባስ ከተገኘ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ይረዳል::
የቅድመ ምርመራ ባህል
በዓለምአቀፍ ደረጃ በተለይም በምዕራቡ ዓለም ሁሉም ሰው የጤናውን ሁኔታ አስቀድሞ የመከታተል ባህሉ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው:: ለምሳሌ፡- አሜሪካን ብንወስድ ለማህፀን፣ ለጡትና ለአንጀት ካንሰር የሚረገው ቅድመ ምርመራ ከ50 እስከ 70 በመቶ ደርሷል:: በሀገራችን ያለው ሁኔታ ግን እዚህ ግባ አይባልም:: ነገሮች ከከበዱ በኋላ የሚመጡት ናቸው የሚበዙት:: በዚህም የሞት ምጣኔ እንጂ የመዳን ምጣኔው በስፋት አይታይም:: ስለሆነም በጣም ብዙ መስራት ይጠበቃል::
በዓመታዊ ምርመራ ወቅት የሚካሄዱ ዋና ዋና ምርመራዎች
በመጀመሪያ ደረጃ የሚደረገው ምርመራ የተመርማሪውን ታሪክ ጠይቆ መረዳትና እሱን ተከትሎ ደግሞ አካላዊ ምርመራ ማድረግ ነው:: ከዚህ ቀጥሎ እንደ አስፈላጊነቱ የሽንት፣ የደምና የሰገራ ምርመራን ጨምሮ የላቦራቶሪና በተለያዩ የመሳሪያ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የተለያዩ ምርመራዎች ይደረጋሉ:: ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ጤና ላይ ለውጦች ይኖራሉ:: ስለዚህም በተለያዩ የሕይወት ደረጃዎች ውስጥ ለተለያዩ በሽታዎች የበለጠ ተጋላጭ ይሆናሉ። እነዚህም በርካታ የካንሰር ዓይነቶችን ፣ የደም ግፊት ፣ የስኳር በሽታ እና የደም ቧንቧ መጥበብ ችግሮችን ያጠቃልላል። በመሆኑም ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ የራስንም ሆነ የቤተሰብዎን መልካም ጤንነት ለመጠበቅ አይነተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ሊታመንበት ያስፈልጋል:: እንደውም ይሄን ተግባር በሕይወት ዘመንዎ በቁርጠኝነት ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ውስጥ ማካተት አለብዎት።
አብዛኛዎቹ የውጭ ሆስፒታሎችን ከዓመታዊ የጤና ምርመራ አንጻር ብናያቸው ዕድሜን መሰረት ያደረጉ ተግባራትን የሚከውኑ ናቸው:: ማለትም ዓመታዊ የጤና ምርመራዎችን ሲያደርጉ ዕድሜ-ተኮር ተግባርን በመከወን ነው:: ምክንያቱም በእነእርሱ እሳቤ ዓመታዊ የጤና ምርመራዎች በዚህ ሁኔታ መከናወናቸው የዕድሜ ጤንነትን ከመጠበቅ አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ብለው ያምናሉ:: እናም ምርመራቸውን ሲያደርጉ በእድሜ ደረጃ ከፋፍለው ነው:: ለአብነት ከታዳጊዎች ጀምረን እንመልከተው:: ለታዳጊዎች የሚደረጉ የጤና ምርመራዎች ዋነኛ ትኩረታቸው ዋና ዋና የሰውነት ክፍሎቻቸው በመደበኛነት እንደሚሰሩ ማረጋገጥ፣ ቅድመ መከላከል ህክምናዎች እና ህመምተኞች ምንም አይነት የሚያስጨንቅ ምልክት እንዳያሳዩ ማረጋገጥ ላይ ነው:: በዚህም ዶክተሮች በእያንዳንዱ ምርመራ ወቅት የተሟላ በሰውነት ውስጥ ያለ የስብ መጠን (lipid profile) ምርመራ ያካሂዳሉ። ይህም ጥሩ ኮሌስትሮል (HDL) እና መጥፎ (LDL) ኮሌስትሮልዎን እንዲሁም የትራይግሊሰሪድ ደረጃ የሚመረምር ሲሆን፤ ዕድሜያቸው እየገፋ ለሚሄዱ ሰዎች የስትሮክ ፣ የልብ ህመም እና የደም ቧንቧ መጥበብ ተጋላጭነትን ቀድመው ለማወቅ ይረዳቸዋል::
በመካከለኛው የእድሜ ክልል ሲሆኑ ደግሞ ከመከላከል እና አጠቃላይ የጤና ምርመራ ከማድረግ ትኩረቱ የተለያዩ በሽታዎች እና የጤና ችግሮች መኖራቸውን ወደ መለየት ይቀየራል:: ከ35 ዓመት እድሜ በኋላ ያሉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ከደም ውስጥ ያለ ካንሰርን ለመለየት ያነጣጠረ የጠቅላላ የካንሰር ላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል:: እነዚህ ጠቅላላ ምርመራዎች እንደ ዕድሜዎ መጠን እየሰፉ ይሄዳሉ። አብዛኛዎቹ በሽታዎች እና ሥር የሰደዱ ችግሮች በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ የሚከሰቱት ከ35 እስከ 60 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ነው::
ደም መመርመርም የግድ ነው:: በርካታ የጉበት ምርመራዎች እና የካንሰር አመላካች ምርመራዎችም እንዲሁ ያደርጋሉ:: ምክንያቱም እድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዶክተሩ የሆርሞንዎን መጠንና የቫይታሚን፣ የማዕድን፣ እና የካልሲየም መጠንን በትኩረት ይከታተላል:: በተፈጥሮ እርጅና ሂደት ምክንያት የሚከሰቱትን መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለመተካት ተጨማሪ ምግቦች ወይም የሆርሞን ቴራፒን ሊያዝልዎት ይችላል::
በሰውነት ውስጥ ያለ የካልሲየም መጠን መቀነስ ወደ አጥንት መሳሳት ችግር ሊያመራ ይችላል። ሐኪሙ የአጥንትዎን ጥንካሬዎን ወደ ሰውነት ምንም አይነት መሳሪያ ማስገባት ሳያስፈልግ ኤክስሬይ በሚመስል የ DEXA ስካን አማካኝነት የአጥንትን ጥንካሬዎትን እና የአጥንት መሳሳት ችግሮችን በትክክል ይለካል:: ይህ የዕድሜ ክልል ዶክተሩ ለልብ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥበት ነው:: የደም ቅዳ በሽታን ለመመርመር ሐኪሙ የተለያዩ የልብ ምርመራዎችን ማለትም የልብ ተግባርን የሚያፋጥኑ ተግባራትን እያከናወንን የሚደረግ ምርመራ ፣ EKG እና CCTA ጨምሮ የተለያዩ የልብ ምርመራዎችን ሊያደርግ ይችላል::
በሌላ በኩል ዓመታዊ የጤና ምርመራ ሲያደርጉ በጾታም የሚያዩበት ሁኔታ አለ:: ለምሳሌ፡- ለሴቶች የቤተሰቡን ያለፈ የህክምና ታሪክ መናገር ለዶክተርዎ ዓመታዊ የማሞግራም ምርመራ መጀመር ያለብዎትን ዕድሜ ለመወስን ይረዳዋል፣ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ዶክተሮች ሴቶች ከ50 ዓመት ጀምሮ እንዲጀምሩ ይመክራሉ::
የጤና ምርመራ ሳይደረግ የቤተሰብ ታሪክ ለምን ያስፈልጋል?
ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ ከእድሜ ጋር በሚዛመዱ በሽታዎች እና ሁኔታዎች ችግር የሌለብዎት ቢሆንም ሐኪሙ ስለ አኗኗር ሁኔታዎ እና ስለቤተሰብዎ የህክምና ታሪክ ይጠይቃል:: ለወደፊት ለእነዚህ ችግሮች ከፍተኛ የመጋለጥ እድል እንዳለዎት ወይም እንደሌለዎት እርስዎ የሚሰጧቸው መልሶች ይነግራቸዋል። ከዚያም በመልሶችዎ እና በዓመታዊ የጤና ምርመራ ውጤቶችዎ መሰረት ላይ በመመርኮዝ ሐኪሙ በኑሮ ዘዴዎት ላይ አንዳንድ ለውጦችን እንዲያደርጉ ይመክሮታል:: እነዚህን ምክሮች ደግሞ ለጤናዎ መጠበቅ የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል:: ምክንያቱም ዶክተሩ ምክሮችን የሚሰጠው ገለልተኛ እና ክሊኒካዊ ከሆነው ምልከታ አንፃር ነው:: የሳይንስ እና የሕክምና ዕውቀት ላይ ተመስርተው ነገሮችንም ያደርጋሉ:: እናም በተገቢው መልኩ ይህንን ማድረግ ከቻሉ ጥቅሙን በቀላሉ የሚገልጹት አይሆንም::
ዓመታዊ ምርመራ ባለማድረግ የሚመጣ ጉዳት
የህመም ምልክቶች አለመታየት ማለት አለመታመም ማለት አይደለም:: በሽታዎች ምንም አይነት ምልክት ሳያሳዩ ለረጅም ጊዜ በውስጣችን ሊኖሩ ይችላሉ:: በቅድመ ምርመራ የጤና ደረጃችንን ባለማወቃችን፣ በሽታዎች ስር እንዲሰዱና እንዲሰራጩ በማድረግ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን በማይድኑበት ሁኔታ እንዲጎዱ ጊዜና ዕድል እንሰጣቸዋለን:: ለምሳሌ፡- አንድ ሰው ያጋጠመው የጤና ችግር ከሦስት ዓመት በኋላ ቢታወቅለት በቀላሉ መዳን የሚችልበት ሁኔታ የለም:: ወይም ደግሞ አንዱን አካሉን መልሶ ሊያገኘው በማይችለው መንገድ ሊያጣው ይችላል:: ስለዚህ ቀድሞ የጤናን ሁኔታ ማወቅ ከተወሳሰቡ ችግሮች ያድናል::
የጤና ምርመራ ባህልን እንዴት
ማሳደግ ይቻላል?
በመጀመሪያ ደረጃ ሕብረተሰቡን ስለጤናው ሁኔታ ያለውን ግንዛቤ እንዲያድግ የማስተማር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል:: ለዚህ ደግሞ በማሕበረሰቡ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ተደማጭነት ያላቸው ግለሰቦችን፣ በየጊዜው ዓመታዊ ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው:: በተለያዩ መንገዶች አርአያ ሆነው ሕብረተሰቡን እየደገፉ እንዲያስተምሩ ማድረግም ያስፈልጋል::
በሌላ በኩል የምርመራ አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ ደረጃ በደረጃ በሕብረተሰቡ ውስጥ የጤና ሁኔታን የመከታተል ባህል እየዳበረ የሚመጣበት ዕድል መፍጠርም ተገቢ ነው:: ለአብነት የተጀመረው የጤና መድህን ብዙውን የማሕበረሰብ ክፍል የሚያነቃቃና ወደ ህክምናው እንዲሔድ የሚያግዝ በመሆኑ ተግባሩን ማስፋትና ግንዛቤ መፍጠር ላይ መንቀሳቀስ ይገባል::
የጤና ጉዳይ በጤናው ዘርፍ ላይ የሚሰራ አካል ጉዳይ ተደርጎ መታየት የለበትም:: ከዚያ ይልቅ ዓመታዊ ምርመራ አድርጎ የተጠቀመ ሰው መድረኮች ባይሰጡት እንኳን ለጎረቤቶቹ በማስተማር ባህሉን ማዳበር ይቻላል:: ስለዚህም ከግለሰብ የጀመረ ተግባር መከናወን ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም