ኦሎምፒክ ቁርስ ቤት ሰፈራችን አስፓልቱን ተሻግሮ ያለ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የተቀባ ብቸኛው ቁርስ ቤት ነው። የቁርስ ቤቱ ባለቤት አቶ አብዱቃድር ሁሴን ይባላሉ። ሰፈር ውስጥ ማንም አብዱቃድር ብሎ የሚጠራቸው የለም። ጋሽ አብዲ ነው የሚላቸው። በረጅም ጢም ያጌጠ ጠይም ሩህሩህ ፊት አላቸው። ጉንጫቸው ዘውትር በጫት ተጎስሮ እንዳረገዘ ነው። ከወገባቸው ላይ ሽርጥ፣ ከብብታቸው ስር ጫት አይጠፋም። እግራቸው ሁሌም በነጠላ ጫማ ነው። የልጅነቴ ትልቁ ትዝታዬ ጋሽ አብዲና ኦሎምፒክ ቁርስ ቤት ነው። ጠዋት ማልጄም ሆነ ከሰዓት አርፍጄ ወዳሉበት ስሄድ የሚሰማኝ ደስታ ልኬት የለውም። በልጅነቴ ኦሎምፒክ የሚለውን ቃል ለማንበብም ሆነ ለመጥራት እንገዳገድ ነበር። ከሰፈራችን ከናሆም በቀር ኦሎምፒክ የሚለውን ቃል በትክክል የሚጠራ እኩያ አልነበረኝም። አብዛኛው የሰፈር ልጅ የጋሽ አብዲን የቁርስ ቤት ስም በመጥራት ነበር ጉብዝናውን የሚለካው። አንድም ቀን ግን ሳንሳሳት ጠርተነው አናውቅም ነበር።
በልጅነቴ ጋሽ አብዲ ስላሉበት ብቻ ሰፈራችን ገነትን ይመስለኝ ነበር። ቁርስ ቤቱ ሰማይ ቤት ጋሽ አብዲ ደግሞ እግዜርን ይመስሉኝ ነበር። እናቴ ዛሬም ድረስ ያልበላሁትን ጣት የሚያስቆረጥም ቁርስ ሰርታልኝ እንኳን የጋሽ አብዲን ሳንቡሳና ጮርናቄ ያክል አይጣፍጠኝም ነበር። እናቴ ብስኩት እንዳልበላ ያልነገረችኝ ተረት የለም። ዘይት ሆድ ያማል፣ ከትምህርት ሰነፍ ያደርጋል እያለች ሳንቡሳና ጮርናቄ እንድሸሽ የለፋች ቢሆንም አልተሳካላትም። ዞሬ ዞሬ መገኛዬ ጋሽ አብዲ ቁርስ ቤት ጋ ሆነ። ፈልጋ የምታገኘኝ በር ላይ ቆሜ በበላተኛ ርካታ ምራቄን ስውጥ ሆነ። ከጮርናቄ ፍቅር የተነሳ እናቴን ትምህርት ቤት ሄድኩ እያልኩ ውሎዬ እዛ ነበር።
በልጅነቴ እንደ እኛ ሰፈር ልጅ የሚበዛበት ሰፈር አልነበረም። የሆነ ደመነፍስ አለን መሰለኝ የሰፈር ልጆች ሁሉ ሳናውቀው መገኛችን ጋሽ አብዲ ቁርስ ቤት በር ላይ ነበር። የጋሽ አብዲ ቁርስ ቤት ከዳቦና ሻይ ባለፈ ብቸኛው ቴሌቪዥን ያለበት ቤትም ስለነበር ከዛ ቤት አንጠፋም። በልጅነታችን ኃይሌንና ቀነኒሳን፣ ደራርቱንና ጡርዬን የተዋወቅናቸው እዛ ቤት ነው። ልጅነቴ ያለቀው እዛ ጮርናቄ ቤት ነው ብል አበልኩ አልልም። አይ ጋሽ አብዲ..ለዛ ሁሉ የሰፈር ልጅ የሚሆን ደግነት ነበራቸው። ጋሽ አብዲ በር ላይ ቆሞ ሳንቡሳና ጮርናቄ ሳይበላ ቤቱ የሚገባ ልጅ አልነበረም። ከደግነታቸው የተነሳ ቁርስ ቤቱን የከፈቱት ድሆችን በነጻ ለመመገብ ይመስለን ነበር። ዛሬ ነው ጋሽ አብዲ ለዛ ሁሉ ለሰፈራችን ድሀ ማህበረሰብ የእግዜርን ያክል ዋጋ ያላቸው አባት እንደሆኑ የገባኝ። አድጌ ያን የልጅነት ሰፈሬን እስከለቀኩበት ጊዜ ድረስ እናቴ እጄን አንጠልጥላ ወደ ቤት የምትወስደኝ ከጋሽ አብዲ ቁርስ ቤት በር ላይ ነበር።
ማልጄ ወይም አርፍጄ ብቻ በቀናኝ በአንዴ ጮርናቄ ቤቱ በር ላይ ሆኜ እቀላውጣለሁ። ጋሽ አብዲ እስኪያዩኝ ድረስ ወዲያ ወዲህ እላለሁ..እንዲያም ሆኜ አላይ ካሉኝ ጉንፋን ያለብኝ መስዬ እስላለሁ እንዲያም ብዬ አልሰማ ካሉኝ ወደ ውስጥ ገብቼ ያልጠማኝን በባዶ ሆዴ ውሃ እጠጣለሁ። ይሄ ሁሉ በዛ በልጅነቴ ጠዋት ውስጥ ጋሽ አብዲ እንዲያዩኝ የምከፍለው መስዋዕት ነበር። አዩኝ ማለት ወይ ጮርናቄ ወይም ሳምቡሳ ይሰጡኛል። ጋሽ አብዲ አይተውኝ ዝም ያሉኝ ጊዜ የለም። እንዳዩኝ ‹አንተ ትምህርት እንዴት ነው? አባትህ ተሻለው እንዴ? እናትህስ እንዴት ናት..እቁቡን ምነው ተወችው? አንዱንም ሳልመልስላቸው ሰላሳ ጥያቄ ይጠይቁኛል። ደስ የሚለው ነገር ጋሽ አብዲ ጥያቄ ጠይቀው መልስ አይፈልጉም። የነጻነቴ ስፍራ ናቸው። አባዬ እንደሳቸው ቢሆን ስል እመኝ ነበር። አባዬ ጥያቄ ጠይቆኝ መልስ ሳይጠብቅ ቀርቶ አያውቅም። ጥያቄዎች ሁሉ መልስ አላቸው ብሎ የሚያስብ ሞገደኛ አባት ነው። አንዳንድ ጊዜ ጠይቆኝ ካልመለስኩለት ንቀት ወይም ደግሞ ትዕቢት ይመስለውና መኝታው በላይ በሰቀላት አለንጋው ይጀልጠኛል። ጋሽ አብዲ እንዲህ አይደሉም..ከጥያቄ በኋላ እጃቸው ሳይዘረጋልኝ ቀርቶ አያውቅም። አባቴ ጠይቆኝ ዝም ካልኩ በአለንጋ ነው የሚጀልጠኝ ጋሽ አብዲ ደግሞ ጮርናቄ ነው የሚሰጡኝ። ‹ማነው የሚወደኝ አባቴ ነው ወይስ ጋሽ አብዲ? ስል አስባለሁ። በልጅነቴ አባቴን በጋሽ አብዲ ልለውጠው ትንሽ ነበር የቀረኝ። ቶሎ ባላድግና ሰፈር ባንቀይር ኖሮ አባቴ ጋሽ አብዲ ናቸው ስል አዋጅ አስነግር ነበር።
በልጅነቴ ብዙ ጮርናቄ ለመብላት የጋሽ አብዲ ልጅ መሆን ያጓጓኝ ነበር። አጠገባቸው ምንጣፋቸው ቁጭ ብዬ የሚሆኑትን መሆን፣ የሚያደርጉትን ማድረግ ይናፍቀኝ ነበር። በልጅነቴ ተመኝቼ ያጣሁት ወይም ደግሞ ቀረብኝ ብዬ የምቆጭበት የጋሽ አብዲ ልጅ ሆኜ አለመፈጠሬ ነበር። አቤት ብስኩት ስወድ..አቤት ጮርናቄ ስወድ። አንዳንድ ጓደኞቼ ዶክተር ወታደር ሲሉ ግን ሳድግ እንደ ጋሽ አብዲ ጮርናቄ ቤት ከፍቼ ለመኖር ነበር የምመኘው። የጋሽ አብዲ ቁርስ ቤት ልጅነቴ ተጀምሮ ያለቀበት ስፍራ ነው። መሽቶ የሚነጋልኝ እዛ ነበር። ሁልጊዜ ጠዋት ወደዛ ስሄድ ሳምቡሳው፣ ጮርናቄው ብረት በሚመስል ነገር ላይ በላስቲክ ተሸፍኖ ሳይ ከየት እንደመጣ የማላውቀው የምራቅ ጎርፍ አፌ ውስጥ ይጎርፍ ነበር። እንዴትና ከየት እንደሚያመጡት አላውቅም። ሲጠበስ ለማየት፣ ቆሜ ለመቀላወጥ ያላደረኩት ጥረት የለም። ግን ጠዋት ደጅ ላይ ስቆም ብስኩቱ ተጠብሶ ነው የማገኘው። ዛሬም ድረስ ባልነቃሁት ጠዋት ከነ አይናሬና ከነልጋጌ ነቅቼ ወደ ጋሽ አብዲ ቤት ስሄድ ሽርጣቸውን አገልድመው፣ ጫታቸውን ብብታቸው ስር ወሽቀው በላተኛ ሲያስተናግዱ አያለሁ። ያኔ ብዙ ሀሳቦች ይመላለሱብኛል። መቼና እንዴት እንደነቁ አላውቅ እላለሁ። በዛ ሌሊት በነቃና በበቃ ሰውነት ሳያቸው አስቤ አልደርስባቸውም። በዛ ውድቅት ሌሊት እሳቸውን ሳይ እኛ ብቻ የምንተኛ ይመስለኛል። በዛ ሌሊት ካልተኙ መች ተኝተው ነቁ? ያ ሌሊት እኮ የመተኛቸው ሌሊት ነበር.. እማዬና አባዬ እንኳን አልነቁም። ጠዋት..በጣም ጠዋት ማልደው በመነሳት ጸሎት የሚያደርሱት የእማዬ አባት እንኳን ለጸሎት አልተነሱም። ጋሽ አብዲ እንዴት ተነሱ? ተኝተው የማያድሩ ሰው ናቸው ስል ደመደምኩ።
ልጅነቴ አልቆ ጎለመስኩ..ነፍስ ሳላውቅ፣ ጋሽ አብዲንም ሆነ ጮርናቄ ቤታቸውን ሳልጠግብ አገር ቀየርን። ከብዙ አመት በኋላ ወደዛ ሰፈር ተመለስኩ። እውነት ለመናገር ጋሽ አብዲን አግኝቶ እንደ ማመስገንና ትላንትን አስታውሶ እንደማውጋት ምኞት አልነበረኝም።በልጅነቴ ውስጥ ያስቀመጡት ብዙ፣ እልፍ የራሮትና የደግነት ውለታ አለ። ያን ውለታ የምመልስበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ስለነበርኩ ላገኛቸው ቸኩያለሁ። በልጅነቴ የማውቃቸው ጓደኞቼ እንኳን የጋሽ አብዲን ያክል አልናፈቁኝም።
ወደ ልጅነት ሰፈሬ ደርሼ ወደጮርናቄ ቤቱ አመራሁ። ያ የማውቀው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የተቀባው ጮርናቄ ቤት አልነበረም። ትልቅ ሆቴል ተገንብቶበታል። በሆቴሉ ግራና ቀኝ የተለያዩ ዘመናዊ ሱቆች አሸብርቀውበታል። ወደውስጥ ገብቼ ስለጋሽ አብዲ ለመጠየቅ ወደ አንድ አስተናጋጅ ስንደረደር..በቅርብ ርቀት ላይ የሚያምር ሶፋ ላይ አንድ አዛውንት ተመለከትኩ። ሽርጥ ያሸረጡ፣ ረጅም ጢማቸው ቀይ ቀለም የተቀባ አዛውንት። ባለሁበት ቆምኩ ጋሽ አብዲ ስለመሆናቸው ቅንጣት ጥርጥር አልነበረኝም። እውነት እንባዬ መጣ..ሳያቸው እነዛ መስጠት የማይሰለቻቸው ደግ እጆቻቸው፣ ያቺ ለድሀ የማይቸግራት ነፍሳቸው ፊቴ ላይ አንጃበቡ። አስተናጋጁን ትቼ ወደእሳቸው ተራመድኩ። አጠገባቸው መመርኮዣ ምርኩዝ አየሁ።
አጠገባቸው ደርሼ ‹ጋሽ አብዲ? አልኳቸው። አልሰሙኝም..
ወደ ፊቴ ጎንበስ ብዬ ‹ጋሽ አብዲ? ስል ደገምኩላቸው።
ቀና ብለው አዩኝ። ያስታወሱኝ አይመስለኝም። ሁለት እጄን ሰድጄ እጃቸውን ጨበጥኳቸው። በዛ አላበቃሁም እጆቻቸውን ደጋግሜ ሳምኳቸው። በዚህም አላበቃሁም በእየሱስ እግር ላይ እንደተደፋችው መቅደላዊት ማርያም እጆቻቸው ላይ ተደፍቼ በእንባዬ አጠብኳቸው። ይሄ ሁሉ ሲሆን ምንም አላሉኝም።
ከሲቃዬ ጋር እየታገልኩ ‹አቡሌ ነኝ! አልኳቸው።
አላስታወሱኝም..ቢያስታውሱኝ እንዴት መልካም ነበር። የነፍሴን ብዙ አመት፣ የታሪኬን እልፍ ንጋት መልሼ ማን እንደሆንኩ ላስታውሳቸው ሞከርኩ። ድሮ ከድህነታቸው ላይ ቆርሰው በነጻ የሚሰጡኝን እነዛን መቼም ያልበላኋቸውን ጣፋጭ ጮርናቄዎች አስታውሼ ማን እንደሆንኩ ነገርኳቸው አላስታወሱኝም።
ሰው ደግ ልብ ሲኖረው እንዲህ ነው..ያደረገውንም የተደረገበትንም አያስታውስም።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2014