አገልጋይነት በብዙ መልኩ ይገለፃል። አገልጋይነትና ቅንነት፤ አገልጋይነትና ታማኝነት፤ አገልጋይነትና አርአያነት ወዘተርፈ የሚለያዩ ባህርያትና ተግባራት አሉት። ከአገልጋይነት ጋር በተያያዘ ብዙ ማለት የሚቻል ሲሆን፤ ከወቅታዊነቱና ከአገራዊ አቅጣጫነቱ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስለ አገልጋይነት ከሰጡት ብያኔና ማብራሪያ እንጀምር።
እንደ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አህመድ አስተያየት “አገልጋይነት ታላቅነት ነው። ክብር የሚገኘው ከማገልገል ነው። ፈጣሪን፣ አገርን፣ ሕዝብን፣ ከማገልገል ውጭ ምን ሕይወት አለ። ሁላችንም በአንድ ቦታ አገልጋዮች በሌላም ቦታ ተገልጋዮች ነን። አገልጋይነት የሁላችንም ባህልና ሥነ ምግባር ከሆነ የትኛውም መ/ቤት መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ይሆናል። የሆኑ አካላት ብቻ እንዲያገለግሉን ከጠበቅን ግን በአንዳንድ ቦታዎች ተፈልጎ የሚገኝ ብርቅ ሀብት ይሆንብናል። በቂና ብቁ አገልጋዮች የሌሏት አገር፣ በዕድገት መራቅና መምጠቅ ይቸግራታል።”
”አገልጋይነት የሁላችንም ባህልና ሥነ ምግባር ከሆነ የትኛውም መስሪያ ቤት መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ይሆናል።” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለፃቸውም እንዲሁ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ሆኖም የሆኑ አካላት ብቻ እንዲያገለግሉን ከጠበቅን አገልጋይነት በአንዳንድ ቦታዎች ተፈልጎ የሚገኝ ብርቅ ሀብት ይሆንብናል። በቂና ብቁ አገልጋዮች የሌሏት አገር፣ በዕድገት መራቅና መምጠቅ ይቸግራታል።” ያሉትም እንዲሁ።
ጉዳዩ መሰረታዊ ነውና ከሀይማኖት አስተምህሮ አኳያም ብናየው ጉዳዩ ሩቅ አይደለም። አንድ ምሳሌ ወስደን እንመልከት።
በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ ዕርሻ፡ ቍፋሮ፤ ማንኛውም ሥጋዊና መንፈሳዊ የማገልገል ሥራ፤ ዕንጨት መስበር፡ ውሃ መቅዳት፡ እንጀራ መጋገር፡ ወጥ መቀቀል፡ ጠላ መጥመቅ፡ ሰፌት መስፋት፤ ቅዳሴ፡ ውዳሴ፤ የመሰለው ኹሉ (2ዜና 8፡14) የአገልግሎት ተግባራት መሆናቸው ተዘርዝሮ ይገኛል። ከዚህ አኳያ የአገልግሎት ወሰን ምን ያህል ሰፊ እንደ ሆነ የምንገነዘብ ሲሆን፤ በሌሎች ሀይማኖቶችም ከዚህ የሰፋ ቢሆን እንጂ አንሶ የሚገኝ አይመስልም።
አገልጋይነትን ከጊዜና ቦታ አኳያም ማየት ይቻላል።
አገልጋይነት በጊዜና በቦታ የመወሰኑ ጉዳይና ከዛውም ጋር ተያይዞ የመታወሱ፤ የመዘከሩ ጉዳይ ሲሆን፤ ይህም ”የካቲት ወር የአፍሪካውያን ወር ይባላል፡፡ ይህን ወር የአፍሪካውያን ወር ያሰኘው ብቸኛ ምክንያት የዓድዋ ድል ነው፡፡ ነጮች አፍሪካውያንን በግፍ በሚረግጡበት፣ በባርነት በሚገዙበት፣ ያሻቸውን ያለከልካይ በሚፈፅሙበት በዚያን ወቅት “እምቢኝ! አገሬን በቅኝ አላስገዛም” ብሎ በጀግንነት የተነሳ፣ ተነስቶም የቅኝ ገዢዎችን በትር በሀይል መስበር የተቻለበት ወር ይህ የካቲት ወር ነው፡፡” ከሚለው ክፍለ ዘመን የተሻገረና ከአገርም አልፎ አህጉርን ያጠቃለለው ድል ነው።
ለማንም ግልፅ በሆነ መልኩ ይህ ድል ባለቤት አለው። ባለቤቶቹም ባለ ድሎቹ ናቸው። የዛሬውን ቀን አስመልክተን እየተነጋገርነው ባለው ”የአገልግሎት ቀን” መሰረት ደግሞ ለዚህ ሁሉ ድል የበቁትና እኛንም ለዛሬው ቀን ያበቁን አያት ቅድመ አያቶቻችን ጀግኖች ብቻ ሳይሆኑ፤ አገልጋዮቻችንም ናቸው ማለት ነውና ዛሬም፣ በዚህ የአገልጋይነት ቀን ሊታወሱና ሊዘከሩ ይገባል ማለት ነው።
ከዚሁ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ የእቴጌይቱ ተግባር ነው። እቴጌ ጣይቱ ለፋሽስቱ ‹‹የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን አገሬን እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ! እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር አስጥቶ ደሙን ለአገሩ ፍቅር አፍስሶ ለአፈሩ ክብር ለብሶ እሱ ወድቆ አገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ! ሂድ! የኢትዮጲያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለአገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ግዜ ተመለስ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፡፡ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ግዜ እናየዋለን ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፡፡›› ነበር ያሉት። በቂና ብቁ አገልጋዮች የሌሏት አገር እንደ አገር መቀጠል ይከብዳታል፡፡ አገልጋዮች ያሏት አገር ደግሞ ከራሷ አልፎ ለሌሎችም መከታ ትሆናለች፡፡ ለዚህ ደግሞ የአድዋ ጀግኖች ከጀግነነትም አልፈው አገልጋይም እንደነበሩ አመላካች ነው፡፡ በሌላ ጎኑ እቴጌ ጣይቱ ታላቅ የጦር መሪ ብቻ ሳይሆኑ ብቁ የኢትዮጵያና ህዝቦቿ አገልጋይ ነበሩ እያልን ነው። ወደ ዘመናዊው ቢሮክራሲ እንምጣ።
በአሁኑ ዘመን ቢሮክራሲ ውስጥ ጎልቶ የሚታየው በየደረጃው ባሉ የስራ ሃላፊዎች ዘንድ ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል የሌብነት አመለካከትና ድርጊት መስፋፋት፤ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር መጓደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄዶ የስልጣን ባለቤት የሆነውን ህዝብ ማስቆጣት ነበር። በቅድመ ዐቢይ የህዝብ ተቃውሞዎች ውስጥ ሲታይ የነበረው ይኸው አይነት የማጋለጥ እንቅስቃሴ እንደ ነበር ይታወሳል። በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ መሰረታዊ ምክንያትም በየደረጃው የአገልጋይነት ስሜት መጥፋት የፈጠረው መሆኑ አይዘነጋም።
ይህን በወቅቱ በነበሩት የመንግስት ባለስልጣኖች ዘንድ የጠፋው የህዝብ አገልጋይነት ተግባር መጓደል የነበረውን መንግስት ወደ ደርዝ እንዲገፋ ምክንያት ሆኖ እንደ ነበር ማንም ያውቃል። የወቅቱ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግም በሚገባ ተረድተውታል። ህዝብ በውክልና ስልጣን ሲሰጣቸው የጣለባቸውን አደራ መወጣት እንዳልቻሉም ተገንዝበዋል። እናም የህዝብ አገልጋይነት ጉድለቱን ለማስተካከል ቃል ገብተው እርምጃ ለመውሰድ ቢሞክሩም መሽቶ ነበርና አልተሳካም። በመጨረሻም ስርዓቱ ተንኮታኩቶ ወደቀ፡፡
ይህ የሚያሳየን፣ ወይም ከነበረው አጠቃላይ ሁኔታ የምንረዳው በተለያየ ደረጃ ሃላፊነት የተሰጣቸው ግለሰቦች ወይም ባለስልጣኖች የህዝብ አገልጋይነት አመለካከት እንዲኖራቸው በቅድሚያ ስልጣናቸው አገልግሎት ፍለጋ ወደ መስሪያ ቤታቸውና ቢሯቸው በሚመጡ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በሚፈልጉና በሚጠይቁ ሁሉም ዜጎች በውክልና የተሰጠ መሆኑን መገንዘብ ያለባቸውና በዛው ልክም ማገልገል ያለባቸው መሆኑን ነው። ካልሆነ ያው ከላይ እንደተባለው ተንኮታኩቶ መውደቅ ይመጣል ማለት ነው።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ሲሉ እንደ ሚሰማው የህዝብ አገልጋይነት ‘ሀ’ ‘ሁ’ የሚጀምረው ሀላፊነትን ከማወቅና ውክልናን በአግባቡ ከመረዳት ነው። ይህ ከታወቀ አገልጋይነት ከባድ አይሆንም።
በዚህ ብቻም አይወሰንም። ተገልጋይ የአገልጋይን ተገቢ አገልግሎት ማወቅ ይጠበቅበታል። በማያውቀው አይፈርድምና የሚያውቅበት መንገድ ሊኖር የግድ ይሆናል። ይህ ማለት ከዚህ ባሻገር ህዝብ በውክልና ስልጣን ላይ ያስቀመጠውን አካል የሚከታተልበት፣ የሚያርምበትና ውክልናውን የሚያነሳበት ስርአት ሊኖር ይገባል ማለት ይሆናልና ይህም ሊታሰብበት ይገባል እያልን ነው። ይህንን ትንሽ ሰፋ አድርገን ማየት ይኖርብን ይሆናል።
በየሰነዱ ላይ ሰፍሮ እንደሚነበበው፣ የሚመለ ከታቸውም ሲናገሩ እንደሚሰማ በዴሞክራሲያዊ ስርአት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ህዝብን በአግባቡ እንዲያገለግሉ ቁጥጥር ማደረግና ማረም የሚያስችሉ ስርአቶች አሉ። አንደኛው ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትና ይህ መብት እውን የሚሆንበት የፕሬስ ነጻነት መረጋገጥ ነው። ፕሬስ የመንግስት አሰራር ላይ ያሉ ድክመቶችን በማጋለጥ እንዲሁም የህዝብን ፍላጎት ለመንግስት በማሳወቅ የህዝብ ድምጽ ሆኖ ያገለግላል። በሌላ በኩል የመንግስትን ክንውንን ለህዝብ ይገልጻል። የፕሬስ ነጻነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ የመንግስትን የህዝብ አገልጋይነት መቆጣጠርና ማረም አይቻልም። የመንግስት የህዝብ አገልጋይነት የፕሬስ ነጻነት ባደገበት ልክ ይወሰናል። እናም የመንግስትን የህዝብ አገልጋይነት ለማጎልበት በሀላፊነት የሚመራ ነጻ ፕሬስን ማጎልበት አማራጭ የለውም። የሲቪክ ማህበራትንም ከዚሁ ጋር አያይዞ ማሰብ ያስፈልጋል።
ሌላው አገልጋይነት የሚጠቀስበት መንገድ ከላይ ካለነው ትንሽ ወጣ ያለ ሲሆን፤ እሱም የህዝብን ጥቅም ለተወሰነ ቡድን ወይም ቡድን አባላት አሳልፎ ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው። ለለምሳሌ ያህልም ከአንድ ፅሁፍ ውስጥ የተወሰደን፤ ይህንን አንቀፅ እንመልከት። ”አገልጋይነት …”፣ ”መገልገያነት …” እና የመሳሰሉትን ቃላት ልብ እንበል።
በጥቅሉ ከ2008 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በመላ አገሪቱ ተስፋፋ። ከ2009 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ ኦህዴድ እና ብአዴን በኦሮማራ ጥምረት አማካኝነት ራሳቸውን ከሕወሓት አገልጋይነት ነፃ አወጡ። በ2010 አጋማሽ ላይ የሕወሓት የስልጣን የበላይነት ተወግዶ አዲስ አመራር ወደ ስልጣን መጣ። አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣበት ግዜ ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ አምስቱን አጋር ድርጅቶች እና ደህዴንን ከሕወሓት ተፅዕኖ እና መገልገያነት ነፃ አወጣ። በዚህ ረገድ የአብዲ ኢሌ ከስልጣን መወገድ፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ አፋርና ድሬዳዋ የተደረጉት የአመራር ለውጦች ይጠቀሳሉ።
በወቅቱ ተፅፎ ከነበረ ፅሁፍ ቆንጥረን እዚህ ያመጣነው አንቀፅ እንደሚያሳየው ቅድመ ዐቢይ አስተዳደር አይደለም የአገልጋይነት ፍላጎትና ተግባር ሊኖረው ቀርቶ መንፈሱ እንኳን እንዳልነበረው ያሳያል። በዚሁ ምክንያትም ውጤቱ ሊገለገል የሚገባው ህዝብ አለመገልገሉ በፈጠረበት ተቃውሞ መንበሩን ነቀነቀው፤ ነቅንቆም ጣለው።
ሌላው ከአገልጋይነት አኳያ ብዙ ጊዜ ፀያፍ የሚሆነው፣ ቢሮክራሲው ህዝብን በማገልገል ፋንታ ህዝብ እሱን እንዲያገለግለው የመፈለጉ ጉዳይ ነው። ለዛ ማሳያ ይሆነን ዘንድ እሩቅ ሳንሄድ አሁንም ቅድመ ዐቢይ አሕመድ አስተዳደርን ማየት እንችላለን።
በቅድመ ዐቢይ አስተዳደር ወቅት ጮክ ብለው ይሰሙ ከነበሩት ድምፆች መካከል “በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚመራ ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ እንደ አገር ትፈርሳለች፣ ህዝቦቿን በጦርነት ያልቃሉ”፤ “እኔ ከሌለሁ አንተ አትኖርም”፤ “… በኢህአዴግ መቃብር ላይ ነው” የሚሉትና የመሳሰሉት ነበሩ። እነዚህ ደግሞ በምንም መልኩ ህዝብን የማገልገል፤ ህዝብን የማዳመጥ፤ ህዝብን የማሳተፍ ወዘተርፈ ተግባራት አይደሉምና በወቅቱ አገልጋይነት አለ ለማለት ያስቸግራል። (ካስፈለገ እነዚህን ሰፋ አድርጎ ወደፊት በሌላ ፅሁፍ በተንተን አድርጎ በማሳየት ምን ያህል ”አገልጋይ” ሳይሆኑ ”አግላይ” እንደ ነበሩ ማሳየት ይቻላል። በተለይም ከ”ወካይ”፣ ”ተወካይ”፤ ”መራጭ” ”ተመራጭ … አኳያ ብዙ የሚያወያዩ፣ የሚያነጋግሩ ከመሆናቸው አንጻር)
ባጠቃላይ፣ “አገልጋይነት ታላቅነት ነው። ክብር የሚገኘው ከማገልገል ነው። ፈጣሪን፣ አገርን፣ ሕዝብን፣ ከማገልገል ውጭ ምን ሕይወት አለ። ሁላችንም በአንድ ቦታ አገልጋዮች በሌላም ቦታ ተገልጋዮች ነን። አገልጋይነት የሁላችንም ባህልና ሥነ ምግባር ከሆነ የትኛውም መ/ቤት መልካም አስተዳደር የሰፈነበት ይሆናል። የሆኑ አካላት ብቻ እንዲያገለግሉን ከጠበቅን ግን በአንዳንድ ቦታዎች ተፈልጎ የሚገኝ ብርቅ ሀብት ይሆንብናል። በቂና ብቁ አገልጋዮች የሌሏት አገር፣ በዕድገት መራቅና መምጠቅ ይቸግራታል።” ያሉትን እዚህ መድገሙ አስፈላጊ ነውና በዚሁ እንሰናበት።
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2014