ሕወሓት ገና ከምስረታው ጀምሮ የሚታወቅበት አንዱ መገለጫው ዘረፋ ነው። ከተመሰረተበት ካለፉት 50 ዓመታት ጀምሮ ለትግራይ ሕዝብ ነጻነት ቆሜያለሁ ቢልም በተግባር ግን ለተቸገረውና ለተራበው የትግራይ ሕዝብ በተለያየ ጊዜ የመጣን እርዳታ ሲዘርፍ እና ሲሸጥ ቆይቷል። በቅርቡም ይህንኑ የዘረፋ ተግባሩን በጠራራ ጸሀይ ፈጽሟል ሲል የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዳስታወቀው፤ ሕወሓት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ የነበረ ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ ዘርፏል። የዘረፈውንም ነዳጅ በአፋጣኝ እንዲመልስ አሳስቧል። በነዳጁ መዘረፍ ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታዎች ለማሳለጥ መቸገሩን ገልጿል። እንዲሁም ቡድኑ የፈጸመው እጅግ አስነዋሪ ተግባር መሆኑን ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር ያወገዙት ሲሆን ከእነዚህም መካከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ እና በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ይገኙበታል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ፤ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ፤ በመጋዘኑ ውስጥ የነበረው የምግብና የነዳጅ ክምችት በአስችጋሪ ሁኔታ ለነበሩ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ነበር። በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግር ሰለባ ለሆኑ የትግራይ ማሕበረሰብ መድረስ የነበረበት እርዳታ በሽብር ቡድኑ መዘረፉ ተቀባይነት የሌለውና አስነዋሪ ተግባር ነው ማለታቸው ይታወሳል። ዘራፊዎቹ ነውረኛ ድርጊታቸውን ክደው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የትግራይ ሕዝብ ለችግር ተዳርጓል የሚል የተለመደ ልፋታቸውን እንደሚቀጥሉና የሕዝብ ተቆርቋሪ ለመምሰል እንደሚሞክሩም ነው የገለጹት።
ከዚህ ቀደምም ሕወሓት በወረራ በቆየባቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች ለተረጂዎች የተላከን ምግብ፣ መድሃኒት እንዲሁም የሕጻናት አልሚ ምግብ በመዝረፍ ለወታደራዊ አገልግሎት እንዲውል ማድረጉ ይታወሳል። በነሃሴ ወር 2014 ዓ.ም ወያኔ የዩኤ ስ ኤ አይዲ (USAID) መደብሮች ውስጥ በመግባት የእርዳታ የምግብ እህል ዘርፏል። የእርዳታ ምግብ ጭነው ወደ ትግራይ የገቡ ከ 100 በላይ የጭነት መኪናዎችን ከነጫኑት ቁሳቁስ ዘርፏል።
ይሄ ተደጋጋሚ የሕወሃት የዘረፋ ድርጊት እንደምታ ምንድነው? የቡድኑን ባህሪ ቁልጭ አድርጎ አያሳይም ስንል የጠየቅናቸው የሕወሓትን ባህሪ ከመሰረቱ የሚያውቁትን የቀድሞ የሕወሓት ታጋይ አቶ ሊላይ ሃይለማሪያምንና የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ትዴፓ) የሕዝብ ግንኝነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሌ ናቸው።
አቶ ሊላይ እንደሚሉት ፤ ሕወሓት ሲፈጥረው የሰው ሀብትና ንብረትን ለመቀማት የተፈጠረ የአንድ ቤተሰብ ስብስብ ድርጅት ነው። ይህ ሲባል ሕወሓት ከዓድዋ አካባቢ የመጡ የአንድ ቤተሰብ ስብስብ ቡድን ነው። በዝምድናና በዘር ግንድ የተሳሰረ በአካባቢ ልጅነት የተዋቀረ ቡድን ነው።
ለመዝረፍ ሲፈልጉ ተቀናጅተው ነው ። ለአብነት በ1977 ዓ.ም ለእርዳታ የመጣውን እህል ከተራበው የትግራይ ሕዝብ ጉሮሮ ነጥቀው ለሠራዊታቸው ቀለብ አውለውት እንደነበር ዓለም የሚያውቀው ሃቅ ነው። በሌላ በኩልም በ 1984 ዓ.ም የወልቃይትን መሬት ለመዝረፍ ሲያቅዱ ከአራት መቶ ሺ በላይ ነዋሪዎች አፈናቅሎ የራሴ የሚላቸውን ሲያሰፍር እንደነበር ያስታውሳሉ። በሃያ ሰባት ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ሀገርና ሕዝብን ሲዘርፉ እንደነበር ይናገራሉ። እዛው ትግራይ እንደርታ ውስጥ ወደ ሶስት መቶ ሃምሳ ሺ ሰው አምጥተው አስፍረው የነበረ ሲሆን አንድ የዓድዋ ተወላጅ የሆነ የእነሱ ቤተሰብ ሁመራ ቦታ አለው፤ ወልቃይት፤ ሽሬ፤ እንደርታና ራያ ላይ ቦታ አለው። አንድ ሰው ቢያንስ አምስት ስድስት ቦታ ይዞ ከመሬት እስከ ንብረት ሲዘርፉ መኖራቸው የቀደመ ማንነታቸውም ከዘረፋ ጋር የተቃኘ መሆኑን እንደሚያሳይም ነው የሚያብራሩት።
ይሄ ቡድን ባህሪው ዘረፋ ነው፤ የሌብነት ነው። 27 ዓመት በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜም ይህንኑ ሲያደርግ ቆይቷል፤ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ለመመስረት የታቀደው እነ ስብሃት ነጋ፤ እነ አባ ፀሀየ በአጠቃላይ የሕወሃት ቤተሰብ አዲስ አበባ ከተማ ተቀምጠው ቦታ ተመርተው ፋብሪካው ሊመሰረት ሲል በባለቤትነት ብዙ ገንዘብ ስለመቀበላቸው ይገልጻሉ።
ሕወሓት የደም ድርጅት ነው። በሰው ላብ በሰው ደም መክበር ይፈልጋል። አሁን እራሱ እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ መጥተው ዘርፈዋል። በዘረፉት ገንዘብም መቀሌ ላይ የተለያዩ አይነት ሱቆች መክፈታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑን ያብራራሉ።
አሁን ላይ መንግሥት ለተቸገረው ለስድስት ሚሊዮን የትግራይ ሕዝብ የሚሆን እርዳታ አስገብቷል፤ ይህ የእርዳታ እህል በሕወሓት መጋዘን ተቆልፎበት ነቀዝ እየበላው ይገኛል። ሕወሓት ከድሀ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ የሚነጥቅ ድርጅት መሆኑ ሳያንሰው አሁን ደግሞ ከሕዝብና ከመንግሥት አልፎ የዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶችን ንብረት መዝረፍ መጀመሩ ምን አይነት የሞራል ዝቅጠት ላይ እንዳለ ማሳያ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
እንደ አቶ ሊላይ ገለጻ፤ መቀሌ ውስጥ ነዳጅ ጠፋ በማለት ያላቸውን ለሕዝብ የሚያካፍሉ የትግራይ ሕዝብ አሳቢ መስለው ለመታየት ይሞክራሉ። በተግባር ግን ነዳጅም ሆነ ሌሎች የእርዳታ ቁሳቁሶች ሕዝቡ ጋር ሳይሆን እየወሰዱ ያሉት ለእነሱና ላሰለፉት ሃይል ነው ። የትግራይ ሕዝብ በመድሃኒትና በምግብ እጦት እየሞተ ነው። ከ2010 ዓ.ም እስካሁን ድረስ የትግራይ ሕፃናት ክትባት አላገኙም ። ነገር ግን ይህ በሕዝብ ስም መነገድ ነው። ይሄም የሚታወቅ የኖረበት ባህሪው ነው። አሁንም ለሕዝቡ የመጣውን መድሃኒት በሕገ ወጥ መንገድ መድሃኒት መደብሮችን በመክፈት ለሕዝቡ በውድ ዋጋ እየሸጠ መሆኑ በማስረጃ አረጋግጠናል።
ሕወሓት የትግራይ ሕዝብን እንደ ሕዝቡ አያየውም። ቢያየው ኖሮ ሕፃናትን ለጦርነት እየማገደ ትውልድ አይሰርቅም ነበር። ሌብነቱ ሕዝብን፤ ወጣቶችን፤ የሰውን እድሜ ሳይቀር እየሰረቀ መሆኑን አብራርተዋል። አርባ ሃምሳ የማይሞሉ ወሮበሎች የትግራይ ወጣቶችን ሕይወት ለሥልጣን ጥማታቸው ማርኪያ ሲሉ እየሰረቁ መሆኑ አሳፋሪ ተግባር ነው ይላሉ አቶ ሊላይ ።
አቶ ሊላይም በዚህ ሃሳብ በመስማማት በአሁኑ ሰአት የትግራይ ሕዝብ የሕወሓት አመራር አንገሽግሾታል። በየቀኑ ተቃውሞ በማድረጉ በየቀኑ እየተገደለ መሆኑ ይታወቃል፤ ሕዝባችንን እንደ ኢትዮጵያዊ የምናየው ከሆነ ልናግዘውና ነፃ እንዲወጣ ይገባል ይላሉ። የዚህ ሁሉ ችግር መፍትሄው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይህንን ሃይል ማጥፋት ነው የሚሉት አቶ ሊላይ በመላው ሀገሪቱ ያለውን አለመረጋጋትና ጦርነት ለማስቀረት የግድ መጥፋት ይኖርበታል። የትግራይ ሕዝብም ስብሰባ ሲጠራ ባለመሄድ፤ ልጆቹን በመጠየቅ እየታገለ ይገኛል።
የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ትዴፓ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ሃይሌ በበኩላቸ፤ የሕወሓት አመራር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የዝርፊያ ወንጀሎችን እየሰራ የመጣ ቡድን መሆኑን ይናገራሉ። ቀደም ሲል ለ17 ዓመታት በተደረገው የትግል ወቅት ጭምር በተራበው የትግራይ ሕዝብ ስም የመጣ የእርዳታ እህል እየሰረቀ እና እየሸጠ ለግል ጥቅሙ ሲያውል መቆየቱንም ያስታውሳሉ።
በሥልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ በሴፍትኔት፣ በእርዳታ ምግብ በሚኖር ወቅት በርካታ ሕዝብ እየተቸገረ እያለ እንኳን ለካድሬዎችና ደጋፊዎቹ የተዘረፈ ሀብት እንዲያካብቱ ሲያደርግ መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑን ያስታውሳሉ።
አሁን ደግሞ ሕዝቡን በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ መክተቱ ሳያንስ ለዚህ ሕዝብ በእርዳታ የሚገባ መድሃኒት ለራሱ ካድሬዎች እንዲጠቀሙበት ፣ አዳዲስ መድሃኒት ቤቶችን በመክፈት እየሸጠ መሆኑን ይናገራሉ። ይህ የትግራይ ሕዝብ ጠላት የሆነው ሕወሓት ጦርነቱን በጀመረ ዋዜማ በረሃብ ምክንያት በሞት አፋፍ ላይ ያሉትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ለመድረስ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የተሰበሰበውን ከ 570ሺ ሊትር በላይ ነዳጅ ከሚያጣጥሩት ረሃብተኛ ወገኖች አፍ መንጠቁ ከፍተኛ ውግዘት አድርሶበታል ይላሉ።
ይህ ሁሉ በሥልጣንም ላይ እያለና ከሥልጣን ከወረደም በኋላ እያደረጋቸው ያሉት ተግባር የቡድኑን የዝርፊያ ታሪክ እንዲሁም ነጥቆ መብላት ባህሪው እንደሆነና አብሮት አድጎ አብሮት ያረጀ እኩይ ተግባሩ ስለመሆኑ ለመረዳት አያስቸግርም ። ሕወሓት አሁንም ከ 500ሺ በላይ ወጣቶችን ጨርሶ፤ የቀረው ተዳክሞ ተስዶ ባለበት ሁኔታ፤ ሕዝቡ በረሃብ፣ በመድሃኒት እጦት ለማለቃቸው ምክንያት መሆኑ የማያሳስበው እኩይ ቡድን መሆኑን ይናገራሉ።
የትግራይ ሕዝብ ችግር በሕወሓት የማይፈታ መሆኑን ሕዝቡ ማመን እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ሙሉብርሃን ይህንን እምነት ይዞ ለውጥ ሊያመጣ ይህንን ሃይል ለማስወገድ የሚችል የሚመጥን ትግል ሊደረግ እንደሚገባም ነው የሚናገሩት ።
ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ በማስገደድ ወደ ጦር ግንባር እንዲዘምት፣ እንዲዋጋ ለማድረግ በሚተጋበት ጊዜ መንግሥት ግን ለሕዝቡ የተገኘውን ያህል ሰላም በመመኘት ያለ ቅድመ ሁኔታ ለመደራደር እንደሚፈልግ የሰጠውን የሰላም አማራጭ በመመልከት ሕዝቡ በቃኝ ሊለው ይገባልም ባይ ናቸው።
የትግራይ ሕዝብ ለሰላሙና ለአንድነቱ ሲል ይሄንን ቡድን ከላዩ ላይ መንግሎ መጣል አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የሀገሪቱ መንግሥትም ሆነ የሕወሓት ተቃዋሚ ሃይሎች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ትልቅ ግፊት ግን ከሕዝቡ ሊነሳ ይገባል ይላሉ።
እርግጥ ነው በርካታ አካባቢዎች ተቃውሞዎች አመፆች መኖራቸውን አይካድም ያሉት አቶ ሙሉብርሃን ሕዝቡ ይሄንን ለሀገርም ለወገንም የማይጠቅም ሃይል በቃኝ ብሎ ከራሱ ማውረድ ይኖርበታል። የትግራይ ወጣት ወንጀለኞችን ሕዝብ ውስጥ ለመደበቅ ሲባል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች መስዋእት መሆን እንደሌለባቸው ተረድቶም አፈሙዙን ወደ ሕወሓት ማዞር አማራጭ መሆኑን አስረድተዋል።
ሁለቱም ፖለቲከኞች እንደሚስማሙበት ፤ የሕወሓት ዋነኛ መገለጫ ባህሪው ዝርፊያ ነው። ከትግል ወቅት ጀምሮ በሥልጣን ላይ እያለም ይሄው ባህሪው በተለያየ መልኩ ታይቷል። አሁንም ከሥልጣን ቢባረርም ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳሉ እንዲሉ ለተረጂዎች የመጣን ሰብአዊ እርዳታ ፣ መድሃኒትና የእርዳታ ማጓጓዣ ነዳጅ ጭምር ሲዘርፍ ታይቷል። በአጠቃላይ ይሄ ቡድን ለትግራይ ሕዝብ የቆመ ሳይሆን በትግራይ ሕዝብ ቁስል ላይ ጨው እየነሰነሰ የትግራይን ሕዝብ ለስጋይ ለሰላም እጦት የሚዳርግ ነው። ዝርፊያውም በታሪክ የሚታወቅበት መገለጫው ነው።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2014