የዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ከ54 ዓመት በፊት የታተሙ ጋዜጦች ይዘው የወጡትን ዘገባ ያስታውሰናል፡፡ ማኅበራዊ፣ ወንጀል ነክና እንስሳት ሕክምና ላይ ያተኮሩ ዘገባዎችን ለትውስታ ያህል መርጠናል፡፡ የደብረ ዘይት የከብት ሕክምና ኢንስቲትዩት የተለያዩ የእንስሳት በሽታ መከላከያ መድኃኒት እየቀመመ ለእንስሳት ሕክምና በሥራ ላይ ማዋሉ ከመረጥናቸው ዘገባዎች ተጠቃሽ ነው፡፡ ባለፈው እሁድ በዚሁ ጋዜጣ ላይ የወጡት ዶክተር ተስፋዬ ቢፍቱ ለበርካታ በሽታዎች (ከ100 በላይ) መድኃኒት ግኝት ባለቤት መሆናቸውን የሚያስታውሰንን ዘገባም ይዘናል፡፡
ለ፮ ሚሊዮን እንስሳት የሚበቃ መድኃኒት ተቀምሟል
ደብረ ዘይት፤ (ኢ.ዜ.አ.)፤ ደብረ ዘይት የሚገኘው የከብት ሕክምና ኢንስቲትዩት፤ በዚህ ዓመት ለ፮ ሚሊዮን ፬፻፴፫ሺህ ፭፻፺፭ እንስሳት የሚበቃ ልዩ ልዩ የእንስሶች በሽታ መከላከያ የሚሆን መድኃኒት መቀመሙን አንድ የኢንስቲትዩቱ ቃል አቀባይ ገለጠ፡፡
ቃል አቀባዩ ከዚህ አያይዞ እንዳስረዳው፤ የተቀመመው መድኃኒት ፭ ሚሊየን ፫፻፴፰ ሺህ ፪፻ ዶዝ ለቀንድ ከብቶች፣ ለአሳማዎች በሽታ መከላከያ መሆኑን ገልጧል፡፡
እንደዚሁም፤ በተለይ የተዘጋጀ ፓስቴውሪላ ፩፻፸፯ ሺህ ፬፻፳፭ ዶዝ፣ አባ ጎርባ ለተባለው በሽታ መከላከያ፤ ፩፻፸፩ ሺህ ፪፻፶ ዶዝ፣ ለአባ ሠንጋ በሽታ መከላከያ ፬ሺህ ዶዝ፣ ፋውል ታይፎይድ ማለት (የዶሮ በሽታ) ፭ሺህ ፭፻ ዶዝ፣ ፋውል ኮሌራ (የዶሮ) በሽታ መከላከያ የሆኑ መድኃኒቶችን ቀምሞ በሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡
ቃል አቀባዩ አቶ ጌታሁን አበጀ ከዚህም በማያያዝ፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ መድኃኒቶችን ቀምሞ በየጠቅላይ ግዛቶቹ ታድለው በሥራ ላይ መዋላቸውን ከገለጡ በኋላ፤ የመከላከያ መድኃኒቱን ከውጭ አገር ስናስመጣ እዚሁ ስለሚቀመምና ስለሚዘጋጅ የከብት ሕክምና ዋና መምሪያ በሽታውን ለመከላከልም ሆነ፤ ፈጽሞ ለማስወገድ በየቦታው ያሠማራቸው ሠራተኞቹ መከላከያ መድኃኒት የማነስም ሆነ የማጣት ችግር አይገጥማቸውም፡፡
የመከላከያ መድኃኒቶቹን በላቮራቶሪ ውስጥ ቀምመው የሚያዘጋጁ አንድ ኢትዮጵያዊ ዶክተርና ሦስት የውጭ አገር ዶክተሮች ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በቂ ትምህርት ያላቸው ቴክኒሺያኖችና የዶክተሮቹ ረዳቶች መኖራቸውን ገልጠዋል፡፡
(ነሐሴ 11 ቀን 1960 ከወጣው አዲስ ዘመን)
በሬ የሰረቀው ፩ ዓመት
እሥራት ተቀጣ
አሰላ (ኢ.ዜ.አ)፤ በቀለ ቶልቻ የተባለው ሰው በተከሰሰበት የስርቆት ወንጀል በ፩ ዓመት እሥራት እንዲቀጣ የጭላሎ አውራጃ ፍርድ ቤት ግንቦት ፳፩ ቀን በዋለው ችሎት ፈረደ፡፡
ተከሳሹ ግንቦት ፲፪ ቀን የአቶ ጌታሁን ወልደማርያምን ሁለት በሬዎች ሰርቆ ሲነዳ ከነኤግዚቪቱ ተይዞ ተከስሶ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ፤ አድራጐቱን ራሱ ከማመኑም በላይ በሕግ ምስክሮች ተረጋግጦበታል፡፡ ስለዚህ ተከሳሹ በፈጸመው ወንጀል በ፩ ዓመት እሥራት እንዲቀጣ ሲበየንበት በእጁ የተገኙትም በሬዎች ለባለንብረቱ እንዲመለሱ ተወስኗል፡፡
በቀለ ቶልቻ ይህንን ወንጀል የፈጸመው፤ በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በጭላሎ አውራጃ በደራ ወረዳ መሆኑን ዐቃቤ ሕጉ አቶ ለገሠ መንግሥቱ ገለጡ፡፡
እንዲሁም በዚሁ አውራጃ ግዛት በኮፈሌ ወረዳ ሙዳ ሔይሳ የተባለ ሰው በፈጸመው የሥርቆት ወንጀል በ፩ ዓመት እስራት እንዲቀጣ የጭላሎ አውራጃ ፍርድ ቤት ግንቦት ፳፪ ቀን የፈረደበት መሆኑን ሕግ አስከባሪው በተጨማሪ ገለጡ፡፡
(ሐምሌ 10 ቀን 1960 ከወጣው አዲስ ዘመን)
የድርሰት ማኅበር ሽልማቱን
ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፡ (ኢ.ዜ.አ.)፤ የኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር ካወዳደረ በኋላ፤ አሸናፊ ለሆኑ አምስት ሰዎች ሽልማት እንደሚሰጥ ተገለጠ፡፡ ማኅበሩ ከልዩ ልዩ ደራሲያን የቀረቡለትን ፺፩ የግጥም ድርሰቶች በታወቁ የሥነጽሑፍ ሰዎች ዳኝነት አስመርምሮ ፹፱ የሚሆኑት የውድድሩ ተካፋይ ከሆኑ በኋላ፤ ለመጨረሻ ውጤት አምስት የድርሰት ባለቤቶች አሸናፊዎች በመሆናቸው የተዘጋጀውን ሽልማት እንደሚያገኙ የድርሰት ማኅበር የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አበራ ጀምበሬ እንደገለጡት፤ የድርሰቱ ውድድር ውጤት በተስተካከለ ዳኝነትና በምሥጢር የተጠበቀ ከመሆኑም በላይ፤ በጥንቃቄ የተመረመረ በመሆኑ ሽልማቱ በመጀመሪያ ደረጃ የተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ድርሰት ማኅበር የአሁኑን ሽልማት የሚሰጠው ወደፊት የተሻለ ድርሰት ለማግኘት፤ ደራሲያንን ለማነቃቃትና የሥነጽሑፍን ቅርስና የቅኔን ውበት ለተከታዩ ትውልድ ለማቆየት ሲሆን ማኅበሩ ወደፊት የተሻሉ ጽሑፎችን በመጠበቅ ላይ መሆኑን ምክትል ሊቀመንበሩ በተጨማሪ ገልጠዋል፡፡
(ሐምሌ 10 ቀን 1960 ከወጣው አዲስ ዘመን)
በጉርሱም አውራጃ የዝኆን መንጋ ጉዳት ማድረሱ ተገለጠ
ጅጅጋ፤ (ኢ.ዜ.አ.)፤ በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት የጅጅጋና የጉርሱም አውራጃ ግዛቶችን በሚያዋስነው ሰሰም ገብድሌይ በተባለው ቀበሌ የዝኆን መንጋ ጉዳት ማድረሱ ተገለጠ፡፡
ኰሎኔል ይልማ ተሾመ የአሥረኛ ብርጌድ ዋና አዛዥና የሰሜን ክፍለ ግዛት የበላይ አስተዳዳሪ ፊታውራሪ በሽር ሼክ አብዲ የጅጅጋ አውራጃ ገዢ እና ኰሎኔል ማሞ አስፋው የሰሜን ክፍለ ግዛት ፖሊስ ዋና አዛዥ ትናንት ወደዚሁ ሥፍራ ሔደው ሁኔታውን ተመልክተዋል፡፡
ባለሥልጣኖቹ እንደገመቱት የዝኆኑ መንጋ በአካባቢው ሕዝብ አዝመራ ላይ ያደረሰው ጉዳት ጐልቶ ባይታይም፤ ለወደፊት በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ባለው ሰብል ላይ ሕዝቡ ተገቢውን የሆነ ጥበቃ ካላደረገ ጉዳት እንደሚያደርስ ገምተዋል፡፡
እንዲሁም ባለሥልጣኖቹ በጅጅጋ አውራጃ ግዛት በተለይ የዝኆኑ መንጋ ወደሚገኝበት ወደ ጐላ አጆ ተጉዘው በዚያም የዝኆኑ መንጋ በሰብል ላይ ያደረሰውን ጉዳት በመመልከት ለወደፊት መፍትሔ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡
(ነሐሴ 11 ቀን 1960 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2014 ዓ.ም