ስፖርትን በተለይም እግር ኳስን በዘመናችን ከውድድርነት ባለፈ አርቆ አለመመልከት አላዋቂነት ነው፡ ፡ ይህ የዓለማችን ቁጥር አንድ ተወዳጅ ስፖርት እግር ኳስ ተሰባስቦ ቂሪላ ከማልፋት በእጅጉ የተሻገረ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው እየጎላ ስለመምጣቱ የማይረዳ አለ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ዘወትር የትችት ናዳ በሚወርድበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንኳን ስፖርቱ ከሚፈስበት ረብጣ ገንዘብ አንፃር ውጤቱ አገርን ባይመጥንም ፋይዳው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕዝብ የሚመጥነውን ውጤት ባለማግኘቱ ምክንያት የስፖርቱ ማህበራዊ ፋይዳ ብዙ ጊዜ ጎልቶ ሲነገር አይታይም፡፡ የዛሬው እለት የበጎ ፍቃድ ቀን ነውና በዚህ አጋጣሚ መመስገን ያለባቸው ሁለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቀንዲሎች የበጎ ፍቃድ ተግባራትና እንቅስቃሴ መነሳቱ የግድ ነው፡፡ ይህም በስፖርቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚገኙ ለሌሎች አርአያ ከመሆኑ ባሻገር እንደ አገርም በሌሎች ዘርፎች ትኩረት እንዲሰጠው ያስችላል፡ ፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርትና የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴ ጉዳይ ሲነሳ የስፖርት ቤተሰቡ በተመሳሳይ ድምፅ የሚመሰክረው አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች በተናጠል በመሰረቱት ማህበርም ይሁን ከማህበራቸው እንቅስቃሴ ውጪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በመስጠት ረገድ ከእነሱ ልቆ ሊጠቀስ የሚችል የስፖርት ቤተሰብ የለም፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና እንደ ክለብ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዋልታና ማገር ሆነው ማገልገላቸውና እያገለገሉ እንደሚገኙም ይታወቃል። ሁለቱ ክለቦች እንደ ተቋም የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ለማህበረሰቡ ያበረክታሉ፡፡ ከዚያ በዘለለ ግን የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች በማህበራቸው በኩል የሚያደርጉት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በገንዘብ የማይተመን ለሌሎችም ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ የደጋፊ ማህበራቱ በስራቸው በሚገኙ በርካታ ውብ ደጋፊዎች አማካኝነት ባለፉት በርካታ ዓመታት የስራቸውን ያህል አልተነገረላቸውም እንጂ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ያላደረጉት ነገር የለም፡፡
የአንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በታላቁ የክለባቸው አርማና የኢትዮጵያ ስፖርት አባት ‹‹ዝክረ ይድነቃቸው ተሰማ›› በሚል በየዓመቱ የደም ልገሳ መርሃግብር ያደርጋሉ፡፡ ሰኔ 17/2010 ዓ.ም ላይ በ9ኛ ዙር የደም ልገሳ መርሀ ግብራቸው በአንድ ቀን 1025 ዩኒት ደም በማሰባሰብ ግንባር ቀደም የሆኑበት ታሪክ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚረሳ አይደለም፡፡ ይህ የበጎ ፍቃድ ተግባራቸው በየዓመቱም ቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችም በዚህ ረገድ የተለየ ታሪክ የላቸውም፡፡ ቡናማዎቹ በተለይም በየአመቱ በሚያካሂዱት የጎዳና ላይ የቤተሰብ የሩጫ ውድድር ላይ የደም ልገሳ መርሃግብርን ጨምሮ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ለማበርከት ሁሌም ከፊት ተሰላፊ ናቸው፡፡
የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ የዓለም ስጋት በነበረበት በዚያ በጨለማ ዘመን በተለያዩ በጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ከማህበረሰቡ ዘንድ የቆሙበት አጋጣሚ ታሪክ የሚዘነጋው አይደለም፡፡ በርካታ ገንዘብ በማዋጣት የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ገዝተው ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በየጎዳናው እጅ እያስታጠቡ ማህበረሰቡ ከወረርሽኙ ራሱን እንዲከላከል ተግተው ሰርተዋል፡፡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ስራዎች ጎን ለጎን ገንዘብ እያሰባሰቡ በወረርሽኙ ሳቢያ ድሃው ማህበረሰብ ለችግር እንዳይጋለጥ ጥረዋል፡፡ በዚህም የብዙዎችን ቀዳዳ ደፍነዋል፣ ለበርካቶችም የእለት ጉርስ ሆነዋል፡፡
ሁለቱ የኢትዮጵያ ሃያላን ክለቦች በሜዳ ላይ ተቀናቃኝ ሆነው ቢታዩም ውብ ደጋፊዎቻቸው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ብዙ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ አለ። ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በተጨማሪ የአረጋውያንና አእምሮ ሕሙማን የረድኤት ተቋማትን በተለያየ ጊዜ መደገፍ መለያቸው ነው። አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት መሳሪያ ቁሳቁስ በማሰባሰብ ድጋፍ ከማድረግ ጀምሮ በችግኝ ተከላና ሌሎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ለአገር አበርክተዋል። መቀመጫቸው ከሆነችው አዲስ አበባ ውጪም በተለያዩ ከተሞችና ገጠር ጭምር ዘልቀው የእንቦጭ አረምን ነቅለዋል፣ አንበጣን ለመከላከል ከገበሬው ጋር ሰብል ሰብስበዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከሁለቱ ታላላቅ ክለቦች ባሻገር በርካታ የከተማ ክለቦች በተለያየ ደረጃ በሚካሄዱ ውድድሮች ተሳታፊ ናቸው። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ክለቦች ጠንካራ የደጋፊ ማህበር በማቋቋም ረገድ ካለባቸው ክፍተት ጋር ተያይዞ ሊሆን ይችላል ደጋፊዎቻቸው እምብዛም የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ሲያከናውኑ አይስተዋልም። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ የበርካታ ክለቦች ደጋፊዎች እንደ ኢትዮጵያ ቡናና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሁሉ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች ብዙ ነገሮችን የመለወጥ አቅም አላቸው። በየአካባቢያቸው በተለያየ መልኩ የተቸገሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ህይወት መቀየር ይችላሉ። ጥቂት ቢሆኑም በርካታ ደጋፊዎች ያሏቸው አንዳንድ ክለቦች ወጥ ሆኖ ባይዘልቅም ጥሩ ጅምር አላቸው። የሚያስተባብር ጠንካራ የደጋፊ ማህበር የመፍጠር አቅም ላይ ሲደርሱም ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጡና የእግር ኳስን ትርጉም ከፍ እንደሚያደርጉም ይታመናል። ለዚህ ግን ከሁለቱ የበጎ አድራጎት ተምሳሌቶች ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ብዙ መማር ይጠበቅባቸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጳጉሜን 1 ቀን 2014 ዓ.ም