ኢትዮጵያ ከ31 አመታት በኋላ እኤአ 2013 ላይ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፏን ተከትሎ በእግር ኳሱ ከፍተኛ መነቃቃት ነበር። የዚያ ትውልድ ታሪካዊ ተጫዋቾችና የዋልያዎቹ አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ከአፍሪካ ዋንጫው ማግስት በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ ላይ በተካሄደው የቻን ዋንጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳተፉ። ለዚህ ተሳትፎም የመጨረሻውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር ከሜዳቸው ውጪ ተፋልመው ማለፋቸው አይዘነጋም። በተለይም በዚያ የመጨረሻ የማጣሪያ ፍልሚያ የዋልያዎቹ ቋሚ ግብ ጠባቂ የነበረው ጀማል ጣሰው ጨዋታው በመለያ ምት እንደሚጠናቀቅ ከአሰልጣኙ ጋር ቀደም ብለው በመግባባት የመለያ ምት የማዳን የተሻለ ብቃት ያለው ግብ ጠባቂ ሲሳይ ባንጫ ተቀይሮ እንዲገባ አደረጉ። ሲሳይም አላሳፈራቸውም። ተቀይሮ ገብቶ ሁለት የመለያ ምቶችን በማዳን ዋልያዎቹን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቻን ዋንጫ አበቃቸው።
ከዘጠኝ አመታት በኋላ ዋልያዎቹ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመሩ በቀጣይ አመት በአልጄሪያ አዘጋጅነት በሚካሄደው የቻን ዋንጫ ለሦስተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ባለፈው ቅዳሜ ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር የመጨረሻውን የዘጠና ደቂቃ ፍልሚያ ከሜዳቸው ውጪ አደረጉ። ዋልያዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፍቸውን ያረጋገጡት በተመሳሳይ ሩዋንዳን በሜዳዋ ገጥመው ሲሳይ ባንጫ ባዳናቸው ሁለት የመለያ ምቶች ነበር። ዘንድሮም ዋልያዎቹ የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከሩዋንዳ ጋር አድርገው ካለ ግብ አቻ እንደመለያየታቸው ታሪክ ራሱን ይደግማል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አድሮ ነበር።
ዋልያዎቹ በቅዳሜው የሩዋንዳ ወሳኝ ፍልሚያ ወደ መለያ ምት አላመሩም እንጂ ያለፈውን ታሪክ በመድገም ወደ ቻን አምርተዋል። ከቅርብ አመታት ወዲህ በታላላቅ ጨዋታዎች ለዋልያዎቹ ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር ታሪክ እየሠራ ያለው የአጥቂ መስመር ተጫዋች ዳዋ ሆጤሳ ገና በጨዋታው 22ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ግብ ኢትዮጵያን በቀጣዩ ጥር በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ውድድር ለማሳለፍ በቂ ነበረች።
በመጨረሻው ዙር ማጣሪያ ሩዋንዳን የገጠመው ብሔራዊ ቡድናችን ከሜዳው ውጪ ባሳካው ድል በድምር ውጤት 1-0 አሸንፎ የቻን ማጣሪያ ጉዞውን ምንም ሽንፈት እና ጎል ሳያስተናግድ በድል አጠናቋል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እና የጽሕፈት ቤት ኃላፊም በዋልያዎቹ ውጤት የተሰማቸውን ደስታ አጋርተዋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ «ለመላው ኢትዮጵያውያን በተገኘው ውጤት እንኳን ደስ አለን። ይህ ትውልድ ማኩራቱን ቀጥሏል። በቀጣይ በቻንም ሆነ በሌሎች ውድድሮች ከዚህ የበለጠ ውጤት በማስመዝገብ ማኩራቱን እንደሚቀጥል እምነቴ ከፍ ያለ ነው።» ብለዋል።
ዋና ፀሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በበኩላቸው «ብሔራዊ ቡድናችን ለአልጄሪያው ውድድር በማለፍ ውጤታማ ጉዞውን አስቀጥሏል። ለመላው የቡድናችን አባላት እና ከቡድናችን ጀርባ ሁሌም ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አለን።» የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዋልያዎቹ ከስድስት አመት በፊትም ለሁለተኛ ጊዜ በቻን ውድድር ላይ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እየተመሩ በጋቦን በተካሄደው ዋንጫ ላይ መሳተፍ ችለዋል። በሁለቱም የተሳትፎ ታሪካቸው ግን ከምድባቸው ሳያልፉ ቀርተዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም