እንደ አገር የትምህርት ተደራሽነቱ የሰፋ ቢሆንም የጥራቱ ጉዳይ ግን ሁሉንም እያሳሰበ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ ችግሩን የተረዳው የትምህርት ሚኒስቴርም የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወን ጀምሯል፡፡ ከእነዚህ መካከልም የትምህርት ጥራትን ሊያመጣ ይችላል የተባለለትና በብዙ መልኩ ለውጦችን እያስመዘገበ ያለው የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህንን ሥራ በስፋት ከከወኑ ክልሎች መካከል ደግሞ የኦሮሚያ ክልል አንዱ ነው፡፡ ስለሆነም ደረጃውን የጠበቀውን ትምህርት ቤት በመገንባት ውስጥ ምን አይነት ችግሮች ነበሩ፤ ውጤቶቹስ እንዴት ይታያሉና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት የክልሉን ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶን አነጋግረናል፡፡ እርሳቸው ያሉንንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ክልል በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ የምታደርጉት እንቅስቃሴ ለብዙዎች ትምህርት የሚሰጥ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ለመሆኑ ከሌሎቹ አዳሪ ትምህርትቤቶች የእናንተን ምን ይለየዋል?
ዶክተር ቶላ፡- በክልሉ ያለው አዳሪ ትምህርት ቤት አንዱ የሚለይበት ምክንያት በፊት የነበሩ ትምህርት ቤቶች ችግር ምን ነበር የሚለውን በሚገባ አጥንቶ ዳግመኛ ችግሩን ላለመድገም የተሰራበት መሆኑ ነው፡፡ ተማሪዎቹ በአዳሪ ትምህርት ቤት ቆይታቸው ምን አገኙና ምን ሊጨመርበት ይገባል የሚለውንም ለይቷል፡፡ በዚህም መሰረት ቀለም ላይ ብቻ ሳይሆን ሙያም እንዲቀስሙ ተደርጎ እንዲማሩ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቷል፡፡ በስነምግባር የተገሩና አርአያ የሚሆኑ ተማሪዎች የሚወጡበት ተቋም እንዲሆንም የምክር አገልግሎት እንዲሰጣቸው ሁሉ ጭምር ተደርጎ ተዘጋጅቷል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ክልል ልዩ ትምህርትቤት የሚባልም እንደፈጠራችሁ ሰምተናል፡፡ ምን ማለት ነው፤ ምን አይነት ተማሪዎችንስ ይቀበላል?
ዶክተር ቶላ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ እንደምናውቀው አዳሪ ትምህርት ቤት ማለት መኖሪያቸውም እዚያው ትምህርት ቤት ውስጥ የሆነ ነው፡፡ ልዩ ተማሪዎች የሚባሉት ግን ማደሪያቸው ቤተሰባቸው ጋር የሆነ ነገር ግን ትምህርቱ እንደ አዳሪ ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ የሚሰጣቸው ተማሪዎች ናቸው፡፡ የሚገቡት ተማሪዎችም ልክ እንደ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ጎበዝ የሆኑ ናቸው፡፡ ልዩነቱ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ላይ በጣም ጎበዝ ሲሆኑ፤ ሁሉንም በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ማካተት ስለማይቻል ያላካተቱትን በመያዝ የሚያስተምር ነው፡፡ ይህ ማለት አዳሪ ትምህርት ቤቱን የሚያግዝ ትምህርት ቤት ነው፡፡
አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የሚቀበሉት ተማሪ በዛ ከተባለ 280 ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ጎበዝ ተማሪዎች በቦታ ውስንነት ምክንያት ዕድሉን እንዳያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለሆነም ብዙ አቅም ያለው ተማሪ ለማፍራት ያግዝ ዘንድ ይህ ትምህርት ቤት ሊከፈት ችሏል፡፡ ትልቅ ውጤት እንደሚመጣበትም ይታመናል፡፡ አሁን ላይ 33 የሚሆኑ ልዩ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፤ ከ5ሺ700 በላይ ተማሪዎችን አካቶ ያስተምራል፡፡ እነዚህንም በሚቀጥለው ዓመት እጥፍ የምናደርግ ይሆናል፡፡ በዚህም 10 ሺህ የሚጠጉ ጎበዝ ተማሪዎችን የማፍራት እቅድ ተይዟል፡፡
የአዳሪ ትምህርት ቤቶችና ልዩ ትምህርት ቤቶች መስፋፋታቸው እንደችግር የሚነሳበት አጋጣሚ ይኖራል። ከአሉት አጠቃላይ ተማሪ የተወሰኑትን ብቻ መልምሎ ማስገባቱ ሌሎችን ለመጉዳት ታስቦ እንዳልሆነም ይታሰባል። ነገር ግን አስተሳሰቡ ትክክል አይደለም።ከዚህ አንጻር ግቡን ማወቅ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው።ዋና ግቡ ሁለት ነው፡፡ የመጀመሪያው ጎበዝ ተማሪዎች አንድ ላይ ሲሆኑ የመረዳዳትና የተሻለ የመሆን ነገርን ያመጣሉ፡፡ይህ ደግሞ ለአገር አስተዋትኦ እንዲያበረክቱ ያደርጋቸዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ አዳሪ ወይም ልዩ ትምህርት ቤት ለመግባት የሚደረገው የተማሪዎች ፉክክር ሲሆን፤ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ላይ ያለው ውጤታማ የመሆን አቅም ያሳድጋል።ይህ ፉክክር ለተማሪው ብቻ ሳይሆን ለመምህሩ ጭምር የሚሆን ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚገቡ መምህራን የተመረጡና አቅም ያላቸው መሆን ይገባቸዋል፡፡ እናም መምህራን ሌሎችን በማገዝ ውስጥ ከፍ ሲሉ ተማሪዎችም የተሻለ አቅም እየፈጠሩ እንዲመጡ ያደርጋል፡፡ ይህ እድል ደግሞ ልዩና አዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚገባ ተማሪን ቁጥር ከፍ ያደርጋል፡፡ ከዚያም አልፎ ሰራተኛ ትውልድ በሁሉም መስክ እንዲፈጠር ያግዛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ምን ያህል አዳሪ ትምህርት ቤቶች አሉ፤?
ዶክተር ቶላ፡- ቀደም ሲል በክልሉ የኦሮሚያ ልማት ማህበር የመሰረታቸው ሁለት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ብቻ ነበሩ፡፡ እነርሱም ቢሆኑ በርካታ ችግሮች ነበሩባቸው። ለአብነት ከፍተኛ ውጤት የሚመጣባቸው ተቋማት አለመሆናቸው አንዱ ነው፡፡ እንደውም አንድ ተማሪ ብቻ ነበር ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግበው፡፡ እናም በአዲስ መልኩ እንዲቃኙ ለማድረግ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ለምሳሌ፡- የመማር ማስተማር ሥርዓቱን እንዲከለስና ለዚያ የሚመጥን ተደርጎ እንዲቀረጽ ማድረጉ አንዱ ነበር። በተመሳሳይ የትምህርት ቤቶቹ ሁኔታ እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተሻሉ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩ ግንባታዎች ተደርገዋል፡፡ በተጨማሪነት ሰባት ትምህር ቤቶች ተገንብተው ለ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመንም ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ለአብነት ዶዶላ፣ ሐረምያ፣ ነገሌ ቦረና፣ ያቤሎ፣ በደሌ የመሳሰሉት ላይ የተጀመሩትም ያለቁትም በዚህ ዓመት ቢሆንም ለማስተማር ግን ዝግጁ ናቸው፡፡
አዳሪ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚኖረው ውጤት እንደ አገር ጭምር አርአያነት ያለውና ለአገር ትልቅ አበርክቶን የሚያደርግ እንደሆነ ከእነዊንጌት መረዳት ይቻላል፡፡ ብዙ ሚኒስትሮች የተማሩበት ተቋም ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ከፍተኛ ውጤቶችን የምንመለከተው ከዚያ በወጡ ተማሪዎች ነው። በዚያ ላይ ውጪ የትምህርት እድል አግኝተው እንኳን አገራቸውን ማስጠራት የሚችሉት ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ የወጡ እንደሆነ ነጋሪ አያሻውም፡፡ እናም እንደ ኦሮሚያ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋት ብዙ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎችን ማፍራት ነው ተብሎ ይታመናልና ትልቅ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
እነዚህ ትምህርት ቤቶች የቋንቋ ቤተሙከራ ሳይቀር የተሟላላቸው ናቸው፡፡ የትምህርት አቀባበላቸው ከፍ ያለ ስለሆነ የትምህርት ስርዓታቸው የተለየ እንዲሁም የመጸሐፍት ዝግጅቱ ሳይቀር ልዩ ተደርጎ ተዘጋጅቷል። በዚያ ላይ የቤተሰብን ወጪ ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር ነው፡፡ እንደ አገር ትምህረት ሚኒስቴር 50 የሚሆኑ አዳሪ ትምህርትቤቶችን በየክልሉ ለመስራት አስቦ ቦታዎቹ ተመርጠዋል፡፡ 13ቱ እየተሄደበቸውም ነው፡፡ ለዚህ ግብዓት መሆን መቻል ደግሞ እጅግ የሚያስደስተን ነው፡፡
የአዳሪ ትምህርት ቤት መኖር በርካታ ጠቀሜታን እንደአገር ይሰጣል፡፡ በተማሪም ላይ የውድድር ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ ምክንያቱም ወደዚያ የሚገቡት በክልሉ ከሁሉም ቦታዎች ላይ ተወዳድረው ጎበዝ የሆኑት ናቸው። ስለዚህም የበለጠ ጎበዝ ለመፍጠርና በእውቀት የተሻሉ ተማሪዎችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታን ያድላል፡፡ የማንበብ ልምዳቸውም በዚያው ልክ ይጨምራልና የፈጠራ አቅማቸውን ያሳድግላቸዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው ቀደም ብለው በሁለቱ አዳሪ ትምህርትቤቶች ብቻ ብዙ ተግባራት በመከናወናቸው በየዓመቱ የውጤት ልዩነት እየታየ መጥቷል፡፡
ከዓመት ክትትልና መሻሻል ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች ቁጥርም ወደ ስድስት እንዲያድግ ሆኗል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ዘጠኝ መድረስ ችሏል። ዘንድሮ 266 ደርሷል።ሰባቶቹ ሲጨመሩ ደግሞ ምን ያህል ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎች እንደሚኖሩ መገመት አያዳግትም፡፡ እንደውም አዳሪ ትምህርትቤቶችን የማስፋት ዘመቻ የተጀመረውም ይህንን ውጤት ከአየን በኋላም ነው፡፡ ስለዚህም አሁን በአዲስ መልክ የተገነቡትን ሰባቱን ጨምሮ ዘጠኝ አዳሪ ትምህርትቤቶች ላይ የደረስን ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው 250 በላይ ተማሪ ይዘው ትምህርቱን የሚጀምሩ ይሆናልም፡፡
በአጠቃላይ አሁን ላይ በዘጠኙም አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1ሺ522 ተማሪ የሚገኙ ሲሆን፤ በቀጣይ ዓመት ግን ይህንን እጥፍ ለማድረግ ታስቧል፡፡ በአራት ዓመት ውስጥም በእያንዳንዳቸው 1000 ሺህ ተማሪዎችን መቀበል እንደሚኖርብን ታምኖበታል፡፡ ይህ ማለት 10 ሺህ ተማሪዎችንም እንደ ክልል በአዳሪ ትምህርት ቤት ብቻ አካተን የምናስተምር ይሆናል።ነገር ግን ትምህርት ሚኒስቴር ከሚገነባው ውጪ ትምህርት ቤት የመገንባት አላማ የለንም።
አዲስ ዘመን፡- ክረምት ከገባ ጀምሮ በርካታ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን እያስመረቃችሁ እንደሆነም ይታያል፡፡ ይህ የትምህርት ቤት ምረቃ ከደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክት ጋር ይተሳሰራል ወይስ ለብቻው የሚከናወን ተግባር ነው?
ዶክተር ቶላ፡- ሁሉም የትምህርት ቤት ግንባታ ደረጃውን የጠበቀ ከሚለው ፕሮጀክት ጋር ይተሳሰራል፡፡ ደረጃ መጠበቅ ሲባል ደግሞ የትምህርት ቤቱን ጥራት ብቻ አይደለም፡፡ ቀጣይ ለሚሰራው ሥራ የሚያግዙ ነገሮችን ጭምር የሚያካትት ነው፡፡ ማለትም ኮንትራክተር መረጣ፣ የሥራ እድል ፈጠራ፤ የአማካሪዎች አቅምን ሁሉ ያማከለ ደረጃ የመለየት ጉዳይን የያዘ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚገቡ ተማሪዎች በምን መስፈርት የተመለመሉ ናቸው?
ዶክተር ቶላ፡- እንደ ሀገር ያሉ መስፈርቶችን ተይዞ ነው ምልመላው የሚደረገው፡፡ እነዚህን መስፈርቶች ያሟሉ የዕድሉ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። የመጀመሪያው ነገር ውጤት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ትክክል ነወይ ከተባለ መሻሻል እንዳለበት አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም የሌሎች አገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው ተማሪዎች እነዚህ አይነት ትምህርት ቤቶችን የሚቀላቀሉት በውጤት ብቻ ሳይሆን በአላቸው ችሎታም ጭምር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአገራቸው የተሻለ ነገርን ከማበርከት አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋል፡፡ ያልተማሩ ግን ልምድ ያላቸው ጭምር የሚያበረክቱት ነገር እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ እኛ ጋር ግን ይህንን ለማድረግ ብዙ ሥራንና በጀትን ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም ይህንን ማድረግ አልተቻለም፡፡ በቀጣይ ግን የሚታሰብበት ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዳሪ ትምህርት ቤቶችንና ልዩ የተባሉትን ትምህርት ቤቶች ስትገነቡ ያጋጠሙ ችግሮች ምን ምን ነበሩ?
ዶክተር ቶላ፡- ችግሩ ሰፊ ነው፡፡ ዋናው ግን እነርሱን የሚቀበል ዩኒቨርሲቲ በአገር ደረጃ አለመገንባቱ ነው። እናም እንደ ሀገር ይህ ነገር ታሳቢ ካልተደረገ ማስተማሩ በራሱ ዋጋ አይኖረውም፡፡ በውጪ የትምህርት እድል ብቻ ይህንን ማሳካት ይቻላል ተብሎም አይታመንም፡፡ እናም በየሙያው መስክ መሥራት ይገባል፡፡ ይህም እንደሚሆን ትምህርት ሚኒስቴር አምኖበት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ እኛም እንደ ኦሮምያ ክልል የልማት ማህበሩ እነዚህን ሊያስገነባ የሚችልበትን አቋም ፈጥረን ተንቀሳቅሰን ነበር፡፡ ነገር ግን በብዙ መንገዶች ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ አይሆንም ብለን አናሳብምና አሁንም እንቀጥልበታለን።
አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ተመራጭ የሚደርጋቸው ምንድን ነው?
ዶክተር ቶላ፡- ባለፈው ዓመት 52 ነጥብ ስምንት በመቶ ተማሪ ከክልሉ በማለፉ ብዙ ጫጫታ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ችግሩ እኩል መሥራት አለመቻል ነው፡፡ እንደ አገር አዳሪና ልዩ ትምህርት ቤቶች ሁልጊዜ ከፍ ያደርጉናል ተብሎ የማመኑ ምጣኔ በክልሎች ላይ ክፍተት ይታያል፡፡ እንደ ኦሮሚያ ክልል ግን ይህ ልዩ ትኩረት የተሰጠውና ወደፊትም በትልቁ የሚሰራበት ነው፡፡ እንደ ክልል ችግሮች ቢኖሩም ከችግሩ ጎን ለጎን የትምህርት ዘርፉን ማሳደግ ላይ ይሰራል፤ እየተሰራም ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ የምንቀጥልና እንደ ኦሮሚያ ክልል እየሰሩ መራመድ ካልተቻለ አሁንም ልዩነቱ መጉላቱ አይቀሬ ነው፡፡
የአዳሪም ሆነ የልዩ ትምህርት ቤቶች አበርክቶ በአንድ ክልል ሥራ የሚወጣም የሚታይም አይሆንም፡፡ ሁሉም ተሞክሮውን በመውሰድ በተቻለው ልክ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ለመስራት የሚፈልጉ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓመት ብቻ ሰባቱን አዳሪ ትምህርትቤቶች ስናስመርቅ ከሦስት ክልሎች በላይ መገኘት አልቻሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ መንፈሳዊ ቅናት ኖሮባቸው ክልሎች በዚህ ልክ አስበው መንቀሳቀስ እንደማይፈልጉ ነው። እናም መልዕክቴ የሚሆነው ለሀገራችን እድገት ሁላችንም እየተመካከርን እንራመድ፤ እንስራ ነው።ለዚህ ደግሞ እንደ ክልል ድጋፋችንን ለሚፈልግ ሁሉ በራችን ክፍት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡ ስለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን፡፡
ዶክተር ቶላ፡- እኔም እንግዳ ስላደረጋችሁኝና የተቋማችንን ሥራ እንድገልጽ እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም