አለም አቀፍ የጤና ስጋት እየሆኑ ከመጡ በሽታዎች ውስጥ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ኩላሊት፣ የመተንፈሻ አካላት፣ የልብና የደም ቧንቧን የመሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዛሬ ድረስ የብዙዎች ራስ ምታት ሆነዋል።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ ባይሆኑም ስር የሰደዱ፣እድሜ ዘለቅና የረጅም ጊዜ ክትትል የሚፈልጉ ናቸው። ምንም እንኳን እነዚህን በሽታዎች የሰውነትን ጤና በመከታተልና መድኃኒቶችን በመውሰድ መቆጣጠር የሚቻል ቢሆንም በዘላቂነት ግን ማዳን አይቻልም። በዚህም ችግራቸው እጅግ ውስብስብ ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች 31 ከመቶ፣ ካንሰር 16 ከመቶ፣ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች 7 ከመቶ፣ የስኳር በሽታ 3 ከመቶ እንዲሁም ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች 15 ከመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ።
ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚከሰቱ 57 ሚሊዮን ሞቶች ውስጥ 71 ከመቶውን ድርሻም ይሸፍናሉ። እድሜያቸው በ30 እና 70 መካከል የሚገኙ ሰዎችም በየሁለት ሰከንዱ በእነዚሁ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ይሞታሉ።
በኢትዮጵያም ቢሆን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የወቅቱ የጤና ፈተና ከሆኑ ሰነባብተዋል። በእነዚህ በሽታዎች የሚያዘው የሰው ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል። እ.ኤ.አ 2016 በተሰራ ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ 43 ነጥብ 5ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች የሞት መንስኤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሆኑ ተረጋግጧል።
በጠቅላላው በሀገሪቱ ከምከሰተው ሞት ውስጥ ደግሞ 52 ከመቶ ያህሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት እንደሆነ በጥናቱ ተመላክቷል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 54 ከመቶ ያህሉን የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎችና ካንሰር እንደሚሸፍኑ በጥናቱ ተጠቁሟል።
ከግማሽ በላይ ማለትም 51 ከመቶ በላይ የሚሆነው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰተው ሞት እድሜያቸው 40 ባልሞላቸው ሰዎች ላይ ሲሆን፤ 63 ከመቶ ያህሉ ደግሞ በ50ና በ70 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ የሚከሰት ነው።
በኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መያዝና ሞት ዋነኛ መንስኤ እየሆኑ ከመጡት ውስጥ አንዱ ታዲያ ጤናማ የአመጋገብ ስርአትን ያለመከተል ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2009 እና በ2019 በተሰራ ጥናት ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ በ17 ነጥብ 9 ከመቶ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መከሰት ቁልፍ ምክንያት እንደሚሆን ተረጋግጧል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ሞት አጋላጭ ምክንያት ስለመሆኑም ጥናቱ አሳይቷል።
በጤና ሚንስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ፕሮግራም ባለሙያ ዶክተር ሙሴ ገብረ ሚካኤል እንደሚናገሩት፤ጤናማ አመጋገብ የተመጣጠኑ ምግቦችን መመገብ ነው። ይሁንና ይህንን ማግኘት ባለመቻሉ በዚህ ዘመን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ እንዲመጡ አድርጓቸዋል። ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን ማለትም እንደጨው፣ስኳርና ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን መመገብም ተላላፊ በሽታዎችን እንዲጨምሩ ከአደረጋቸው መካከል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በቂ አትክልትና ፍራፍሬ አለመመገብም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚያጋልጡ ምክንያቶች ናቸው።
ሌላው ለተላላፊ በሽታዎች መከሰት ምክንያቱ የከተሞች መስፋፋት፣ ግሎባላይዜሽን፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ያለማድረግ፣ድህነትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቂ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያለመመገብ፣ በተፈጥሮ ከሚመረቱ ምግቦች ይልቅ የፋብሪካ የምግብ ምርቶችን መመገብ፣ ከፍተኛ ቅባት፣ጨውና ስኳር የበዛባቸውን ምግቦች መመገብና ሌሎችም በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።
እንደ ባለሙያው ገለፃ፤ በኢትዮጵያ 96 ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች ከልክ ያለፈ ጨው በምግባቸው ውስጥ ይጠቀማሉ። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ በአማካይ 8 ነጥብ 3 ግራም ጨው ሰዎች ይጠቀማሉ እንደማለት ነው። ይህ ደግሞ የአለም ጤና ድርጅት በቀን ካስቀመጠው 5 ግራም ጨው መጠን ከፍ ያለ ነው። በሌሎች ምግቦች ላይም በተዘዋዋሪ ጨው እንዳለና ጨው የመጠቀሙን ልክ ይበልጥ ከፍ እንደሚያደርገው መረጃዎች ያሳያሉ።
ጨው ከልክ በላይ መመገብ ለከፍተኛ የደም ግፊትና ለልብ ህመሞች ይዳርጋል። በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየገደለ ያለው ደግሞ የልብና የደም ቧንቧ በሽታ ሲሆን፤ 16 ከመቶ ያህሉን ይሽፍናል። በአጠቃላይ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ 33 ከመቶው ዋነኛ የልብ ህመም ለሆኑት ለድንገተኛ የልብ ህመም፣ ስትሮክና በከፍተኛ የደም ግፊት ለሚመጣ የልብ ህመም ያጋልጣል።
በልብና የደም ስር በሽታዎች ለሚሞቱ ሰዎች አንድ ሶስተኛ መንስኤ የሚሆኑት ደግሞ ጤናማ ያልሆኑ አመጋገቦች ናቸው። ጤናማ ካልሆነ አመጋገብ ውስጥ ጨውን በብዛት መመገብ አንዱ ሲሆን፤10 ነጥብ 94 በመቶ የሚሆነውን የልብና የደም ስር በሽታዎችን ወደ ሞት የሚቀይር እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ 97 ከመቶ ያህሉ ኢትዮጵያውያን አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንደማይመገቡም ጥናቶች ያሳያሉ። ይህም በራሱ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ይዳርጋል።
ማህበረሰቡ ወደ ጤናማ የአመጋገብ ስርአት ውስጥ እንዲገባ በቅድሚያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና በሚመለከታቸው አካላት አማካኝነት በስፋት መሰራት አለባቸው። ለአብነትም በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አነሳሽነት የተጀመረውን የጓሮ አትክልትና ችግኞችን የመትከል ተግባር ማስፋትና ህብረተሰቡ ይህንኑ ልምድ በማድረግ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲመገብ ጠንከር ያሉ ስራዎችን መስራት ይገባል።በዚህ ደግሞ በተፈጥሮ እርሻ የሚገኙ ምግቦችን በማዘውተር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል።
የግንዛቤው ሥራ በመገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካኝነትም መጠንከር ይኖርበታል። ይህም ህብረተሰቡ አትክልትና ፍራፍሬን መመገብ ባህሉና የእለት ተእለት ህይወቱ አካል እንዲያደርገው ያስችለዋል። በተጨማሪም ህብረተሰቡ ያልተፈተጉ የጥራጥሬ ምግቦችን፣ ባቄላ፣ ምስር፣ አተርና የመሳሰሉትን ምግቦች እንዲያዘወትር ተመሳሳይ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል።
ከስጋ ምርቶችም በተለይ ጤናማ የሆኑትን የአሳ ምርቶችን እንዲመገብ መስራት ይጠይቃል። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ምላሽ የሚያስፈልግ በመሆኑ የአሳ ምርቶችንም ማምረት ያስፈልጋል። ቅባት ያልበዛበት የዶሮ ምግብ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ መመገብም ለጤና አስፈላጊ ነው። እነዚህና መሰል ተግበራትን ማከናወን ከተቻለ ህብረተሰቡን ወደጤናማ የአመጋገብ ስርአት ውስጥ ማስገባትና ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ የሚከሰተውን የበሽታ ስርጭት መቀነስ ይቻላል።
የፋብሪካ የምግብ ምርቶችም በሰዎች እንዳይዘወተሩ ተጨማሪ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት ይገባል። በዋናነት ለጨው ከፍተኛ መንስኤ የሆነው በርበሬና ሚጥሚጣ በመሆኑ ህብረተሰቡ እነዚህን ሲጠቀም ተጨማሪ ጨው ማስገባት እንደሌለበት የማስገንዘብ ስራዎችም ሊሰሩ ይገባል።
ባለሙያው እንደሚሉት፤ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ለጤና ከፍተኛ አደጋ አለው። በኢትዮጵያም ለሞት ከሚዳረጉት ከአምስት ዋነኛ መንስኤዎች ውስጥ አንዱ ነው። ነገር ግን እንደ አልኮልና ትምባሆ ሱስ የማስያዝ ባህርይ አይኖረውም። ከዚህ አንፃር የባህሪይ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል። መጠነ ሰፊ የባህሪ ለውጥ ዘመቻ በማድረግም መከላከል ይቻላል።
የጤና ሚንስቴርም ከጠቅላይ ሚንስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር ጤናማ የሆኑ ዘይቶችን ስለመመገብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መስራት ጀምሯል። ከዚህ አንፃር ህብረተሰቡ ጤናማ፣ የማይረጉና ከአትክልት የሚሰሩ ዘይቶችን በመመገብ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል አለበት። የሱፍ፣ አኩሪ አተር፣ የወይራ ዘይቶችን በስፋት በማምረትና በመመገብ በልብና በደም ስር አማካኝነት የሚመጡ በሽታዎችን መቀነስ ይቻላል።
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብን ለመከላከል የስነ ባህሪ ለውጥ ብቻ ማምጣት በቂ ባለመሆኑ ዘርፈ ብዙ ምላሽም ያስፈልገዋል። በተለይ በፋብሪካ የሚቀነባበሩ ምግቦች ላይ አዋጆችን ማዘጋጀትም ያስፈልጋል። በተመሳሳይ የቁጥጥር ስራዎችንም ጎን ለጎን መስራት ይገባል። ይህን ማድረግ የማይቻል ከሆነ ግን ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2030 ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በአንድ ሶስተኛ ለመቀነስ ያሰበችውን እቅድ ማሳካት አይቻልም። ከዚህ አንፃር የፖሊሲ ማእቀፎችንና አዋጆችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
አቶ አክሊሉ ጌትነት በጤና ልማትና ፀረ ወባ ማህበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ባለፉት ዓመታት ማህበሩ ይበልጥ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ የቆየው ወባና ኤች አይ ቪ ኤድስ በመሰሉ ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ላይ ነበር። ለማህሩም መቋቋም ምክንያት የሆነው ከሀያ አራት ዓመት በፊት በሀገሪቱ ተከስቶ የነበረው የወባ ወረርሽኝ ነው። ሆኖም እ.ኤ.አ በ2016 በኢትዮጵያ የተሰራ አንድ ጥናት 52 በመቶ ከሚሆነው የሞት ምጣኔ 52 ከመቶ በላይ የሚሆነው የሚከሰተው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ አረጋግጧል። ከዚህም ወደ 43 ከመቶውን የሚይዘው ቀጥታ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ነው። ሌለው ድርሻ ደግሞ በአደጋ ምክንያት የሚከሰቱት ናቸው። ከዚህ አንፃር ማህበሩ ጤንነቱ የተጠበቀ ማህረሰብን መፍጠር እንደራእዩ በመሰነቅ ተላላፊ በሆኑትና ተላላፊ ባልሆኑት በሽታዎች ላይ እየሰራ ይገኛል። በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ መስራት ጀምሯል።
በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ የማህራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጤና ተፅእኖ እያሳደሩ ይገኛሉ። ለአብነትም 71 ከመቶ የሚሆነው የሞት ምጣኔ በአለም አቀፍ ደረጃ ሲታይ በዓመት ውስጥ የሚከሰተው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ነው። በሌላ አባባል 57 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በዓመት ይሞታሉ። ከዚህ ውስጥ 41 ሚሊዮን ሰዎች የሚሞቱት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ነው። ከዚህ አኳያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ታዳጊ ወደሆኑ ሀገራትም እየተስፋፋ መጥቷል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ መንስኤዎች ዋናዎቹ ሲጋራ ማጨስ፣ የአልኮል መጠጦችን አብዝቶ መጠቀምና በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ያለማድረግ ናቸው። በዚህም ማህበሩ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ስራ የጀመረው በትንባሆ ቁጥጥር ስራ ላይ ነበር። ላለፉት አራት ዓመታትም ይህንኑ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። ኢትዮጵያ በትንባሆ ቁጥጥር ዙሪያ የተሟላና ጠንካራ ህግ እንድታወጣ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የድርሻውን ተወጥቷል። አሁንም ህጉ በተሟላ መልኩ ተግበራዊ እንዲሆን ግንዛቤ የመፍጠርና ተቋማት ህጉን ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማነቃቃት ስራዎች እየሰራ ይገኛል።
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽተታዎች የሚያጋልጥ ሌላኛው ምክንያት ነው። ከዚህ አኳያ ማህበሩ ህብረተሰቡ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ምን እንደሆነ በትክክል እንዲገነዘብና ጤናማ የአመጋገብ ስርአትን እንዲከተል ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ማህረሰቡን የማስተማርና የማንቃት ስራ የሚሰሩት የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ባለሞያዎች በመሆናቸው የግንዛቤ ማዳበርና አቅማቸውን የማጎልበት ሥራ እየተሰራ ነው። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተለይ ደግሞ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብን የሚመለከቱ መልእክቶች በሬዲዮና በቴሌቪዥን እንዲተላለፉም ይደረጋል። በራሪ ፅሁፎችን በማዘጋጀት ለህዝቡ ተደራሽ እንደሚያደርጉም ያስረዳሉ።
ቢልቦርዶችን በማዘጋጀትና ሊነበቡ በሚችሉ ቦታዎች ላይ በመለጠፍ መልእከቶች እንዲተላለፉ ማድረግንም በቅርቡ የጀመሩ ቢሆንም በቀጣይ ግን አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ስራውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ ጤናማ ያለሆነ አመጋገብ መንስኤ ከሆኑት ውስጥ አንዱ በፋብሪካ የተቀነባበሩና የታሸጉ ምግቦች ናቸው። እነዚህ ምግቦች እንዲጣፍጡና ረጅም ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ ንጥረ ነገሮች ይጨመሩባቸዋል። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ለጤና ጎጂዎችና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎችም ያጋልጣሉ። ከዚህ አኳያም በከተሞች አካባቢ እንደስልጣኔ በመቁጠር እነዚህን ምግቦች የመመገብ ባህል እየጨመረ መጥቷል። ስለሆነም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ከእነዚህ ምግቦች ራሱን እንዲያርቅ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል። በዚህ ዙሪያ ለህብረተሰቡ ተከታታይ መረጃዎችን መስጠትም ያስፈልጋል።
ማህበሩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለው በፋብሪካ የተቀነባበሩና የታሸጉ ምግቦች ዙሪያ የህግ ማእቀፍ እንዲዘጋጅና በዚሁ የህግ ማእቀፍ መሰረት ማንኛውም ሰው የሚመገበውን ምግብ ይዘት በትክክል እንዲረዳ ገላጭ ነገሮች እንቀመጡበት ለማድረግ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም የግንዛቤ ማዳበሪያ ስራዎች ይሰራሉ። በተለይም የጨው አጠቃቀም በኢትዮጵያ ከፍተኛ በመሆኑና የአለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት በላይ በመሆኑ ተከታታይ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል። ማህበሩም ይህንን አስመልክቶ በቀጣይም ከዚህ በፊት የነበረውን ልምድ ተጠቅሞ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚሰራበት ይሆናል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28 /2014