ያለማንም ከልካይ ከከርሰምድር ውስጥ ፈንቅሎ በመውጣት ሜዳውን አቋርጦ ወንዝ ውስጥ ይቀላቀላል:: የአካባቢው ነዋሪ ለላምባ ይጠቀምበት እንደሆን እንጂ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት እየቻለ ሀብቱ እንደወራጅ ውሃ ሲወርድ እንደዋዛ እየታየ አመታት ተቆጥረዋል::
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ውስጥ ለገሂዳና ወረኢሉ ወረዳዎች ድንበር ላይ መቸላ ወንዝ አቅራቢያ ስለሚገኘው የተፈጥሮ ጋዝ ነው የምናወራው:: ሀብቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖረው በደቡብ ወሎ ዞን በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሥር የሚገኘው የማዕድን ዘርፍና በጥናትና ምርምር ከተሳተፈው ወሎ ዩኒቨርሲቲ ከጥቂት ወራት በፊት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሀብቱ ስለመኖሩ እንጂ ትክክለኛው ጊዜ አይታወቅም:: መኖሩ የተረጋገጠውም በአካባቢው አርሶአደሮች ጥቆማ ነው::
ይሁን እንጂ በ2000 ዓ.ም ትኩረት አግኝቶ እንቅስቃሴ ተደርጓል:: ሳልኮም ፔትሮሊየም የተባለ ኩባንያ በ2005 ዓ.ም ከማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ አግኝቶ በአካባቢው ላይ የጥናት ሥራ ለማካሄድ እንቅስቃሴ ጀምሮ ነበር:: ኩባንያው ይህ ነው የሚባል ሥራ ሳይሠራ አካባቢውን ጥሎ መውጣቱን በዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የማዕድን ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ጀማል እድሪስ ይገልጻሉ::
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል በኢንጂነሪንግ ጂኦሎጂ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ደሳለኝ ገዛኸኝ እንደተናገሩት፤ ወሎ ዩኒቨርሲቲ 2011 ዓ.ም የጥናት ቡድን በማቋቋም ጥናቱን አካሂዷል:: የጥናት ቡድኑም በስፍራው ተገኝቶ ያረጋገጠው ከመሬት እየወጣ የሚፈስ ነዳጅ መኖሩን ነው:: የመንደድ ባህሪ ማሳየቱም ነዳጅ ስለመሆኑ አንዱ ማረጋገጫም ስለነበር በዚህ መንገድም ተፈትሾ ተረጋግጧል:: የጥናት ቡድኑ ናሙና ይዞ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመመለስ በቤተሙከራ ውስጥ በተከናወነው የምርምር ሥራ ከፍተኛ የሆነ (98 በመቶ) የነዳጅ ድፍድፍ መኖሩ ነው የተረጋገጠው::
ዩኒቨርሲቲውም ሀብቱ ስለመኖሩ ከማረጋገጥ በላይ ብዙ ርቀት አልሄደም:: በወሎ አካባቢ በጥናት የተደገፈ በከርሰ ምድር ውስጥ የተፈጥሮ ነዳጅ ስለመኖሩ ለአብነት አነሳን እንጂ ኢትዮጵያ ከኦጋዴን እስከ ኦሞ፣ ከኦሞ እስከ ጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብና ምሥራቅ አካባቢዎች የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ዘይት ሀብት ክምችት ባለቤት ስለመሆኗ በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ ቆይቷል:: በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ነዳጅ ፍለጋ ሥራ የተጀመረው እኤአ በ1950ዎቹ ሲሆን፣ ፍለጋውም በምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ኦጋዴን አካባቢ የተካሄደ መሆኑን ማዕድን ሚኒስቴር፤ የተፈጥሮ ጋዝ ምንነትና በኢትዮጵያ ያለበት ደረጃ በሚል በድረገጹ ያስነበበው መረጃ ያስረዳል:: አገሪቱም በነዳጅ ፍለጋ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ፈቃድ በመስጠት የፍለጋውን ሥራ ስታከናውን ቆይታለች:: በተለይም እ.እ.አ ከ2003 ጀምሮ በተለያየ ሁኔታ የዓለምአቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በነዳጅ ፍለጋ ሥራ ተሰማርተዋል:: ማዕድን ሚኒስቴርም ከነዚህ ኩባንያዎች ጋር እስከ 25 አመት የሚቆይ የነዳጅ ምርት ሽርክና ስምምነት፣ ከሁለት አመት ያልበለጠ የጥምር ጥናት ስምምነት፣ በሚሉ የስምምነት ዓይነቶች በመፈራረም ሲሠራ ቆይቷል:: በዚሁ መሠረትም 16 የስምምነት ሰነዶች ተፈርመዋል:: ባለፉት 10 አመታትም ሰፋ ያለ የጥናት ሥራ ተሠርቷል:: በጥናት ሥራውም ኦጋዴን ውስጥ በካሉብ፣ በሂላላ እና በገናሌ አካባቢዎች ወደ 4ነጥብ7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ፊት የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መኖሩ መረጋገጡን የሚኒስቴሩ የቆየ መረጃ ያመለክታል::
በኢትዮጵያ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እና የነዳጅ ፍለጋ ሥራ ለማጠናከርና ወደ ምርት ለማስገባት እንዲያስችል የነዳጅ ሥራዎች ፖሊሲና አዋጅ መውጣቱም ይታወሳል::በፖሊሲው ከተካተቱት ዓላማዎች መካከል በክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተቀናጀ አሠራር ለመዘርጋት፣ ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የአገር ውስጥና የቀጠናውን የገበያ ዕድል በመዳሰስ የተሻለ የገበያ አማራጭ ለመፈለግና ተወዳዳሪ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት የሚሉት ይጠቀሳሉ:: እነዚህ ሁሉ የመንግሥት ጥረቶች በሀብቱ ለመጠቀም የተከናወኑ ተግባራትን ያሳያሉ:: መንግሥት ቢለዋወጥም ከሀብቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚደረገው ጥረት እንደቀጠለ ነው:: በማዕድን ልማት የሚታወቁ የውጭ ኩባንያዎችን ወደ አገር በማስመጣት የፍለጋና የአዋጭነት ጥናት እንዲያካሂዱና ወደ ልማቱም እንዲገቡ እንዲሁም ዘርፉ ላይ የነበሩ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችል የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ ጭምር ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ይገኛል::
የነዳጅ ሀብት ፖለቲካዊ አንደምታም ያለው በመሆኑ ከሀብቱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን ተግዳሮቶች ያጋጥማሉ:: ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለችውን የከርሰ ምድር ሀብቷን ለኢኮኖሚ ጥቅም እንዳታውል ፀጥታ በማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሚያደርሱት ተጽእኖ ሌላው ተግዳሮት ነው:: በሶማሌ ክልል በደገሃቡር ዞን አቡሌ በተባለ ቦታ በነዳጅ ፍለጋ ላይ ተሰማርተው እያሉ በፀረሰላም ኃይሎች 65 ኢትዮጵያውያንና ዘጠኝ ቻይናውያን ሕይወታቸውን ያጡበትን ጊዜ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሚያዝያ 18 ቀን 1999 ዓ.ም እትሙ ያስታውሰናል::
አሁንም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ መደፍረስ የማዕድን ዘርፉን እየፈተነው ይገኛል:: የፀጥታ ችግር የተለያዩ ኩባንያዎችና የማዕድን አካባቢዎች ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉን ማዕድን ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል:: ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጋር በመተባበር የፀጥታ ስጋቱን ለመፍታት የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑንም ነው ያስታወቀው:: በክትትልና ቁጥጥር ቁርጠኛ ሆኖ መሥራት ላይ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ሁኔታው ያስገነዝባል::
አሁን ባለው ዓለምአቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ያሻቅብ እንደሆን እንጂ ይቀንሳል የሚል ግምት የለም:: ነዳጅ ደግሞ ከዕለት እንቅስቃሴ ጀምሮ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ እጅግ ይፈለጋል::
በአሁኑ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ኢኮኖሚያዋ ላይ ጫና እየተፈጠረባት ላለው ኢትዮጵያ ደግሞ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ነገሮችን አዳጋች ሊያደርጋቸው ይችላል:: በመሆኑም ኢትዮጵያ ምድር የሰጠቻትን ሀብት ወደ ጥቅም መለወጥ ላይ መሥራት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም::
የኢኮኖሚ አቅሟን ማዕከል አድርገው ሊያጠቋት የሚነሱ ኃይሎችን ማሸነፍ የሚቻለው ያለውን ሀብት በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ሲቻል ነው:: የውጭ ተጽዕኖ ለርስበርስ ግጭትና ሙስና መስፋፋት መንስኤ ስለመሆኑም አሁን ካለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ አያዳግትም:: መንግሥትም ይህንን ታሳቢ በማድረግ በማዕድን ዘርፉ በተለይም በተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ማልማት በኩል ወደ ውጤት የተቃረበ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል::
ከእንቅስቃሴ ተግባራቱ አንዱ በማዕድን ዘርፉ ላይ የነበሩ ክፍተቶችን እየተጠናቀቀ ባለው 2014 አመት የመሙላት እርምጃዎችና እስከ ቅርብ ጊዜ በተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ፍለጋ ጥናት ላይ የተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች ይዘውት የመጡት የጥናት ውጤት ለ20015 ዓ.ም አዲስ አመት መልካም የምሥራችና ተስፋን የሰነቀ ሆኗል::
በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ዘይት አሳሽና አልሚ ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም አድርገናል ያሏቸው ጥናቶች ማዕድናቱ በምን ያህል መጠን እንዳሉና ለማልማት ያላቸውን አዋጭነት ያላመላከቱ ነበሩ:: በጥናትና በማልማት ስም የገቡ ኩባንያዎች ለአመታት ለውጤት ያለመብቃታቸውን ጉዳይ በመለየት መንግሥት ፈቃድ እስከመሰረዝ የደረሰ እርምጃ እንዲወስድ ተገዷል::
የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን የ2014 በጀት አመት የዘጠኝ ወር አፈፃፀም ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፤በተለያየ የማዕድን ዓይነቶች ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው ውጤት ያላስገኙ ፈቃድ የተሰረዘባቸውና በማስጠንቀቂያ የታለፉ መኖራቸውን ማስታወቃቸውን ከዚሁ አኳያ መመልከት ይቻላል::
ከነዚህ ውስጥም ፖሊ ጂሲኤል የተባለው ኩባንያ ይጠቀሳል:: ኩባንያው አራት የፍለጋ አንድ ደግሞ የልማትና ምርት ፍቃድ አግኝቶ ለዘጠኝ አመታት ሲቆይ የሚጠበቅበትን እንዳላከናወነ ለምክርቤቱ ገልጸዋል:: ኩባንያው ባለመስራቱ መንግሥትና ሕዝብ ከፍተኛ ተስፋ የጣለበትን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት በተያዘለት ጊዜ እውን እንዳይሆን እንቅፋት መፍጠሩን ተናግረዋል:: ኩባንያው ያለበትን የፋይናንስና የቴክኒክ አቅም ውስንነት እስከ በጀት አመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ካላሟላ ስምምነቱ የሚቋረጥ መሆኑን ሚኒስቴሩ በደብዳቤ ማሳወቁንም ለምክርቤቱ አሳውቀዋል::
ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ በቅርቡ ደግሞ ሌላ ምስራች ይዞ መጥቷል:: ነሐሴ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ የተደረገው የምስራች አገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ነዳጅ ክምችት በሚገባ ያመለካተ ነው::
ከአራት ወር በፊት ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ የአሜሪካ ኩባንያ የሆነው ኤልሲኤአይ (LCAI) በኦጋዴን አካባቢ የነዳጅና የተፈጥሮ ሀብት አቅም አዋጭነት ጥናት የውል ስምምነት ተፈራርሞ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል:: ኩባንያውም በውሉ መሠረት ሥራውን አጠናቅቆ ለሚኒስቴሩ አስረክቧል::
ማዕድን ሚኒስቴር አዲስ ባስጠናው በዚህ ጥናት በኦጋዴን አካባቢ 7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ጥልቀት ያለው የተፈጥሮ ጋዝ መኖሩ ተረጋግጧል:: የአሜሪካ ኩባንያ የሆነው ኤልሲኤአይ (LCAI) የጥናትና ውጤቱን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ርክክብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በተገኙበት ለሚኒስቴሩ ማስረከቡን ከሚኒስቴሩ የፌስቡክ ገጽ የተገኘው መረጃም ያመለክታል:: መረጃውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንም ይዘውት ወጥተዋል::
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በርክክቡ ወቅት «እስከ ዛሬ አለ እየተባለ በአባቶቻችን ሲነገረን የቆየውን የተፈጥሮ ጋዝ ሀብታችን የወደፊት ዕጣ ፈንታችንን የሚወስን አንዱ የአገራችን የኢኮኖሚ ዋልታ እንዲሆን እንሠራለን» ብለዋል። የተፈጥሮ ጋዝ ለአገር ምርት እና ለውጭ ንግድ የምንጠቀምበት ይሆናል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሰርተፍኬቱ ምን ያክል የተፈጥሮ ጋዝ እንዳለን ያወቅንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል። ‹‹የሰርተፊኬቱ ሚና አገራችን ያላትን የተፈጥሮ ሀብት፣ እውቀት ልምድና ፍላጎት ሳይኖራቸው አንቀው ከቆዩት በመላቀቅ ሊሠሩና ሊያለሙ የሚችሉ ትላልቅ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ያስችላል›› በማለት የማረጋገጫ ሰነዱ የተፈጥሮ ጋዝ እና ድፍድፍ ነዳጅ የማልማት አገራዊ እቅድን አንድ እርምጃ እንደሚያራምድ ጠቅሰው፣ በትልቁ የመንግሥት ቁርጠኝነት የታየበት ሥራ እንደሆነም አመልክተዋል:: እንደሚኒስትሩ ገለጻ ይህ የሰርተፊኬት ሰነዱ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ መጠንና የኢኮኖሚ አዋጭነት ማረጋገጫ ነው:: ይህን ሰርተፊኬት በመያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስ እና በዘርፉ የኢንቨስትመንት አቅም ያላቸው ኩባንያዎች መጋበዝ ይቻላል:: የተዛባ መረጃ ይዘው ሀብታችንን እስረኛ እያደረጉ ላሉ ኩባንያዎችም ጥሩ የማንቂያ ይሆናል ብዬ አምናለሁ ብለዋል ሚኒስትሩ:: ሰነዱን ወደ ተግባር ለመቀየርም ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንና ወደተግባር የመቀየሩ ጉዳይም እንደአሠራራችን ፍጥነት የሚወሰን ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል::
የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ከማጥናት አንስቶ ከምድር በታች ያለውን ሀብት ቆፍሮ ማውጣት፣ ግዙፍ የጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧዎችን መዘርጋት ከፍተኛ ቴክኖሎጂ፣ ባለሙያና መዋዕለነዋይ የሚጠይቅ ነው:: ይህን ሂደት አልፎ ምርቱን ከፈገር ውስጥ ተጠቃሚነት ባሻገር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ረጅም ጉዞን የሚጠይቅ መሆኑ የማይደርስበት ሊመስል ይችል ይሆናል:: ግን ደግሞ ‹‹ህልም አለ ተብሎ ሳይተኛ አይታደርም›› እንደሚባለው ሀብት ላይ ቁጭ ብሎ የሚያጋጥሙ ስጋቶችን በማሰብ ወደ ማልማት አለመግባት ሁሌም ከድህነት የማይላቀቅ ሕዝብን ይዞ መጓዝና ከሌሎች ጥገኝነትም የማትላቀቅ ጠባቂ አገር መምራት ይሆናል::
ከዚህ አኳያ መንግሥት አሁን የደረሰበት የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ መጠንን እና የማልማት አዋጭነትን በዘርፉ በሚታወቅ ኩባንያ ማስጠናቱ የአገሪቱን የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ለማልማት ትልቅ ተስፋ ተደርጎ ይወሰዳል፤ በቀጣይም ወደ ልማቱ በመግባት የአገሪቱንና የሕዝቧን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መሥራት ይገባል እንላለን::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27 /2014