ኢትዮጵያዊቷ ዓለም አቀፍ ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫን ለመምራት ከተመረጡ ዳኞች መካከል አንዷ ሆናለች። በህንድ አዘጋጅነት በሚካሄደው ዓለም ዋንጫ 58 ሴት ዳኞች ውድድሩን እንዲመሩ በፊፋ ተመርጠዋል።
የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት በሚመራው ፊፋ አዘጋጅነት ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል አንዱ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ነው። ይህ ውድድር በመጪው ጥቅምት/2015ዓም የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ የሚካሄድ ሲሆን፤ ጨዋታዎቹን የሚመሩ ዓለም አቀፍ ዳኞችም ከወዲሁ ተሰይመዋል። ፊፋ ይፋ ባደረገው የዳኞች ዝርዝር መሰረት ዳኞቹ ከየአህጉራቱ የእግር ኳስ ማህበራትና ኮንፌዴሬሽኖች የተወጣጡ ሲሆኑ፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 8 ዳኞችን አስመርጧል። ከእነዚህ ዳኞች መካከል አንዷ ደግሞ ኢትዮጵያን ለበርካታ ጊዜያት በመወከል ዓለም አቀፍ ውድድሮችን መምራት የቻለችው ኢትዮጵያዊቷ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ናት።
ፊፋ እንዳስታወቀው ከሆነም ለውድድሩ 14 ዋና ዳኞች፣ 28 ረዳት ዳኞች እንዲሁም በቪድዮ ዳኝነት ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ 16 ዳኞችን ሰይሟል። በዚህ ውድድር ላይ በቪድዮ የታገዘ ዳኝነት የሚተገበር ሲሆን፤ ፊፋ በእድሜ ገደብ በሚያካሂዳቸው የወጣት ዓለም ዋንጫዎች ቴክኖሎጂውን ሲጠቀም ይህ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ነው የታወቀው። ይፋ በሆነው የዳኞች ዝርዝር መሰረትም ከአፍሪካ ሁለት የቪዲዮ ዳኞች (VAR) ተካተዋል። ኢትዮጵያዊቷ ዳኛ ሊዲያ ታፈሰም ከአፍሪካ ከተመረጡ ሁለት የቪዲዮ ዳኞች መካከል አንዷ ሆናለች። ሌላኛዋ የኢስዋቲኒ ዜግነት ያላት ሊቺያ ቪያና የቪዲዮ ዳኝነት ግልጋሎትን ከሊዲያ ጋር የምትሰጥ ይሆናል።
ዓለም አቀፍ ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ተመራጭ ከሆኑ ዳኖች መካከል አንዷ ስትሆን፤ እአአ በ2019 ፈረንሳይ ባስተናገደችው የሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይ ጨዋታዎችን በመምራት ብቃቷን ማስመስከሯ የሚታወስ ነው። በአፍሪካ ዋንጫ፣ በቻን፣ በአፍሪካ የሴቶች ቻምፒዩንስ ሊግ እንዲሁም በሌሎች አህጉራዊ ውድድሮች ላይ ጨዋታዎችን መምራትም ችላለች።
በመድረኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የታገዘ ዳኝነት ሲተገበር በሴቶች እግር ኳስ በተለይም ለሴቶች ዓለም ዋንጫው በስፋት ለመተግበር የልምድ መቅሰሚያ ይሆናል በሚልም ይጠበቃል።
ጨዋታውን ለመምራትም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) 8 ዳኞችን ያስመረጠ ሲሆን፤ ሁለቱ በዋና ዳኝነት፣ አራቱ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ሁለቱ በቪድዮ ዳኝነት ላይ ተሳታፊዎች ይሆናሉ። በዚህ ውድድር ላይ ብቃታቸውን ማስመስከር የሚችሉ ዳኞችም በመጪው ዓመት በአውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ አዘጋጅነት በሚደረገው የሴቶች ዓለም ዋንጫ በቀጥታ የመመረጥ ዕድላቸው የሰፋ እንደሚሆንም ታውቋል።
ከወደ ጅማ በቅርጫት ካስ ተጫዋችነት የተጀመረው የሊዲያ የስፖርቱ ዓለም ጉዞ በመጨረሻም መክሊቷ ከሆነው የእግር ኳስ ዳኝነት ሕይወት ውስጥ አደላድሏታል። በኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ታሪክ የወንዶች ውድድር ላይ መዳኘት የቻለች የመጀመሪያዋ እንስት ነች። የፊፋ የዳኞች ዝርዝር ውስጥ የተካተተች የመጀመሪዋዋ ምስራቅ አፍሪካዊት እንስትም ነች።
እ.ኤ.አ በ2006 የመጀመሪያ ኢንተርናሽናል ጨወታዋን በአቡጃ ናይጄሪያና ላይቤሪያ ያደረጉትን ጨወታ በዳኝነት መምራት የጀመረችው ሊዲያ፣ 2007ና 2011 የመላው አፍሪካ ጨወታዎች ላይ ዳኝታለች። አራት ተከታታይ የሴቶች አፍሪካ ዋንጫን በዳኝነት አገልግላለች (2012, 2014, 2016,2018)።
የፊፋ ከ17 ዓመት በታች በ2016 ፣ ከ20 ዓመት በታች ደግሞ በ2018 በዳኝነት ተመርጣ ሰርታለች። በ2015 እና 2019 የሴቶች አለም ዋንጫን ዳኝታለች።
በፋርማሲስት ሙያ ተመርቃ የህክምና ዕውቀቷን ያዳበረችው ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በሀገርም ሆነ በአህጉር ደረጃ ከባድ የሚባሉ ጨወታዎችን እንድትመራ ኃላፊነት ተጥሎባት በብቃት እየመራች ትገኛለች።
ካፍ ካሜሮን በ2020 ባዘጋጀችው የወንዶች የቻን ውድድርን እንድትዳኝ ሲመርጣት በአህጉራዊ የወንዶች ውድድር ላይ የዳኘች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ስትሆን፣ ‹‹ዳኝነትን ስጀምር በጣም ከባድ ነበር ምክንያቱም አልፎ አልፎ አንዳንድ ሰዎች ሌሎች ሴቶች በሌሉበት መስክ ለምን ሴት ሆኜ ዳኝነትን ለመምረጥ እንደወሰንኩ ይጠይቁኛል›› ስትል በአንድ ወቅት ከካፍ ኦንላይን ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ተናግራለች።
በመጀመሪያው የሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜን ለመዳኘት ካፍ ከባዱን ኃላፊነት ለኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ሰጥታል። 40 ዓመታት በዘለቀው ሕይወቷ ግማሽ ዕድሜዋን ያሳለፈችው በዳኝነት ህይወት ውስጥ ነው። ፆታዊ ስነ ልቦና ያስከተለባትን ትችት ተቋቁማ ፣ አልበገር ባይነትን በተግባር ማሳየት የቻለችም ለብዙዎች ምሳሌ የሆነች ብርቱ ሴት ነች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26 /2014