በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በተለያዩ አገራት በተካሄዱ የጎዳና ላይ የሩጫዎች ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል። አትሌቶቹ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡባቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የአንትሪም ኮስት ግማሽ ማራቶን ነው። በሰሜን አየርላንድ በሚካሄደውና በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና ባለው በዚህ ውድድር በርካታ ዝነኛ አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነቱን በመያዝ አጠናቀዋል።
በሴቶች በኩል በተካሄደው ውድድር ባለፉት ጥቂት አመታት በግማሽ ማራቶን የተለያዩ ድሎችን በመጎናጸፍ ከፍተኛ ልምድ ያካበተችው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ውድድሩን ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ማሸነፍ ችላለች። ያለምዘርፍ አምና ውድድሩን ስታሸንፍ ያስመዘገበችው ሰዓት የግማሽ ማራቶን የዓለም ክብረወሰን ቢሆንም፤ ርቀቱ በድጋሚ ተለክቶ ጉድለት ስለተገኘበት ክብረወሰን ሆኖ ሳይመዘገብላት መቅረቱ ይታወሳል። ይሁን እንጂ አትሌቷ በዚያው ዓመት በቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን 1:03:51 የሆነ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች። በአወዳዳሪው አካል ስህተት ያስመዘገበችው ክብረወሰን የተሻረባት ያለምዘርፍ ይህንን ቁጭት ለመወጣት ዘንድሮ በተመሳሳይ ውድድር ተመልሳ 5 ኪሎ ሜትሩን በ14 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ በማገባደድ አስደናቂ ብቃት አሳይታ ነው ያሸነፈችው።
ይህም ያለምዘርፍ በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ለተሰንበት ግደይ የተያዘውን የርቀቱን ክብረወሰን ዳግም ለመረከብ በእጅጉ አቅርቧት ነበር። ይሁንና ውድድሩን አጠናቅቃ የመጨረሻዋን መስመር የረገጠችበት ሰዓት 1:04:22 ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም በአንድ ደቂቃ 30 ሰከንድ የዘገየ ሆኖ ተመዝግቧል። ያለምዘርፍን በመከተልም ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ፀሐይ ገመቹ 1:05:01 በሆነ ሰዓት በመግባት ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽማለች።
ያለምዘርፍ ከድሏ በኋላ ‹‹ይህንን ውድድር በማሸነፌ በጣም ደስተኛ ነኝ። አስብ የነበረው የዓለም ክብረወሰን ስለመስበር በመሆኑ የመጀመሪያውን 10 ኪሎ ሜትር በፍጥነት ነበር የሮጥኩት፤ ይሁንና የመጨረሻውን 5ኪሎ ሜትር ዘግይቻለሁ። በቀጣይ ግን ክብረወሰኑን መስበሬ አይቀርም፤ ይህንን ውድድር ስለምወደው በድጋሚ እሮጣለሁ›› በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
በተመሳሳይ በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር ያለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊው አትሌት ጀማል ይመር ባለድል ሆኗል። ኬንያውያን አትሌቶችን አስከትሎ የገባው ጀማል የገባበት ሰዓት 59፡04 ሆኖ ተመዝግቦለታል። ይህም በውድድሩ ከተሳተፉ አትሌቶች ሁሉ የፈጠነ ሰዓት ነው። አትሌቱ አምና ውድድሩን ያጠናቀቀው በ1ሰዓት ከ30ሰከንድ ሲሆን፤ የዘንድሮውን በፈጣን ሰዓት መግባት ችሏል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ተስፋሁን አካልነው ደግሞ ኬንያውያኑን ተከትሎ 1:01.43 በሆነ ሰዓት አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በሌሎች አገራትም የተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነቱ ይዘዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ በአውስትራሊያ የተደረገ የግማሽ ማራቶን ውድድር ሲሆን፣ በሴቶች በኩል አትሌት በቀለች ጉደታ አሸናፊ ሆናለች። አትሌቷ አሸናፊነቷን ያረጋገጠችውም 1:08.05 በሆነ ሰዓት በመግባት ነው። በወንዶች በኩል በተካሄደው ውድድር ደግሞ አትሌት ኪሮስ አሸናፊ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ፈጽሟል። አትሌቱ ርቀቱን ለመፈጸም የፈጀበት ሰዓትም 1:05.51 ሆኖ ተመዝግቧል።
በሜክሲኮ በተካሄደ የማራቶን ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያን በሴቶች የወከለችው አትሌት አማኔ በሪሶ አሸናፊ ሆናለች። አትሌቷ ርቀቱን 2:25.05 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ በመሆን ስትገባ፤ ሌላኛዋ አትሌት ሙሉዬ ደቀቦ ደቂቃዎችን ዘግይታ በመግባት ሦስተኛ ደረጃ መያዟን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 /2014