በተፈጥሮዬ ችኩል ነኝ ። በዚህ ላይ አስተዳደጌ ነፃ ነው።ሁሉንም መሞከር እፈልግ ነበር። ከትምህርት ቤት ከቀሰምኩት እውቀት ይልቅ በሕይወት ተሞክሮ ያገኘሁት ልምድ ይበልጣል። ባልቸኩልና እድሜዬ ለጋብቻ ሳይደርስ ባላገባ ኖሮ ምን አልባት አባቴ የሚፈልገውን ፤እኔም እንደተመኘሁት ለራሴና ለሌሎችም የምተርፍ ሰው እሆን ነበር ብዬ አስባለሁ።
ሆኖም ችግር ብልሃትን ይፈጥራል እንዲሉ ከሕይወቴ በመማሬ በላሰብኩት መንገድ ያሰብኩት ተሳክቶልኛልና የምቆጭበት የለኝም። ደግሞም በትዳሬ ያፈራኋትና በሄድኩበት ይዣት በመዞር በጥርሴ አንጠልጥዬ ያሳደግኳት እኩያ ልጄ ደስታዬና ሀብቴ ናት። ለእሷ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ለብዙ መሰል የጾታ አጋሮቼ ምሳሌ ለመሆን አብቅቶኛል።በዚህም ዛሬ ላይ አብዝቶ ደስ ይለኛል። በራሴም እኮራለሁ።
ይሄን ያለችን ወጣቷ ሥራ ፈጣሪና የ Gelancrafts’ company ባለቤትና መሥራቿ ገላዬ ደያስ ናት።በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት ከተማ ውስጥ ተወልዳ ያደገችው ገላዬ ስለ እናቶቼ ፤ ስለ እህቶቼ በአጠቃላይም የጸታ አጋሮቼ ስለሆኑት ሴቶች ይመለከተኛል ይገደኛል የሚል አስተሳስብ የፀነሰችው ገና በልጅነቷ ነበር። ዕድገቷ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጃገረድ ቢሆንም ወላጆቿ በተለይም አባቷ ከአብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ልጃገረዶች በተለየ ሁኔታ በራሷ መወሰንና መንቀሳቀስ የሚያስችል ሰፊ ነፃነት ሰጥተው ያሳደጓት መሆኗ ኃላፊነት የሚሰማት ሴት ሆና አድጋለች።
ነፍስ ካወቀች በተለይም 10ኛ ክፍልን ካጠናቀቀች በኋላ የአገሯን ባህል፤ ወግና ልማድ ብሎም የአኗኗር ዘይቤ አውቃ ለአለም ለማስተዋወቅ ከቦታ ቦታ ፤ከክልል ክልል ትንቀሳቀስ የነበረው በራሷ ተነሳሽነት ነበር። ነፃነቱ ከራሷ ሕይወት እየተማረች እንድታድግና እንድትንቀሳቀስ ብሎም ዛሬ ላይ ደርሳ አለኝታ የሆነችላቸውን እናቶቿን፤ እህቶቿንና የጾታ አጋሮቿን ችግር እየተገነዘበች እንድታድግ ሰፊ ዕድል እንደሰጣት ታወሳለች።
የኔ ልጅ የአገሯን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሴቶችን ችግር በዘላቂነት የምትፈታ የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ነው የምትሆነው›› ሲሉ ተስፋ ጥለውባትና ሲያበረታቷት የነበሩትን አባቷን ህልም ዕውን ለማድረግ ስትጥር ቆይታለች። ገና በልጅነቷ አባቷ የጣሉባት ተስፋ ጉልበት የሆናት ገላዬ በነቀምት ከተማ እስከ 10ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን የተማረችውም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ነው።
ገላዬ ኢትዮጵያ ውስጥ የአገር ውስጥ የእናቶች ችግር በዛው በአገር ውስጥ የጥጥ፤ የስንደዶ ፤የቀርከሃ፤ የፋብሪካ ተረፈ ምርት ግብዓት በቀላሉ መፍታት የሚያስችል ዕድል መኖሩን እያሰበች ቆይታለች።ለገላዬ ግብዓቶቹ የአየር ብክለትን የሚከላከሉና ከአካባቢ ጋር የሚስማሙ መሆናቸውም ፍንትው ብሎ የተገለፀላት ያኔ በታዳጊነት ዘመኗ ነው። ግን ደግሞ ግብዓቶቹ የተሻሻለ ምርት እንዲሰጡ የሚያደርግ የቴክኖሎጂ ዕውቀት አስፈላጊ መሆኑም ያኔውኑ ነው የታያት። ከዚህ በኋላ ከራሴ አልፌ ለአገሬና ለዓለም ሴቶች ዘላቂነት ያለው ለውጥ ማምጣት ያስችለኛል ብላ ወዳሰበችው አዲስ አበባ ከተማ በመምጣት እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን አጠናቃለች።
ገላዬ ይሄኔ ድንገት ሳታስብ በትዳር ተጠለፈች። ከትዳሯ አንዲት ሴት ልጅ ልትወልድም በቅታለች። ባለፈርጀ ብዙ ህልሟ ወጣት ከችኩልነቷ ጋር ተዳምሮ በሰዎች ግፊት ጭምር በገባችበት በትዳር ሕይወቷ የአባቷን ህልም ዳር ማድረስ የሚያስችላትን ነፃነቷን ብታጣምና ብዙም ደስተኛ ባትሆንም ከፍተኛ ልምድ ቀስማበት ነው ያለፈችው። በትዳሯ ውስጥ ከነበሩ ችግሮች ትልቅ ትምህርት ልትቀስምባቸው ችላለች። እንደውም ‹‹ችግር መፍትሄን ይወልዳል ››እንዲሉት ተረት የተሻለ ነገር እንድታስብ አድርጓታል። ካሰበችበት ለመድረስና ራሷን ለማውጣት ከፊቱ እየተማረች ለወደፊቱ በመጠንቀቅ በትጋት እንድትገሰግስ የሚያስችልም ከፍተኛ አቅም እንደገነባላት ትመሰክራለች እንጂ ትዳሯን ስታማርርና ስትወቅስ አትደመጥም ።
‹‹እንደውም ከራሴ አልፌ ተርፌ ሌሎች በርካታ ባለ ትዳር ሴቶች በትዳራቸው ውስጥ የሚገጥማቸውን ችግር በማወቅ አሁን ላይ እየሰራሁት ባለው ሥራ የበኩሌን ድጋፍና እገዛ እንዳደርግላቸው አስችሎኛል›› ትላለች ። ወጣቷ ትዳርን ራሱን እንደቻለ የሕይወት ትምህርት ቤት በመቁጠር ከቆመችበት ለመነሳት ጊዜ አላጠፋችም። አባቷ በእሷ ላይ ያለሙት ህልም ጉልበት ሆኗት ጭምር በፍጥነት ወደ ራሷ በመመለስ አንዲት ሴት ልጇን በብብቷ፤ የተቋረጠ ትምህርቷን በቀኝ እጇ ጨብጣ ለመጀመርያ ጊዜ ከኢትዮጵያ በመውጣት ወደ አገረ ህንድ አቀናች። በዚሁ በህንድ አገርም ከትምህርቷ ጎን ለጎን ለሀገሯ ብሎም ለዓለም ሴቶች ዘላቂ ጥቅም ይሰጣል ብላ የምታስበውን የራሷን ሥራ ለመፍጠር የሚያስችላትን ልምድ ስትቀስም ኖራለች።
የኔንም ሆነ የሌሎች የአገሬን እና የዓለም ሴቶችን ሕይወት የሚለውጠው ዘላቂ ሥራ ነው የሚል ዕምነትን ገና ከብላቴናነቷ በውስጧ ያሳደረችው ወጣቷ በዚህ በህንድ አገር ዛሬ ላይ Gelancrafts’ company የተሰኘውንና በውስጡ ብቻ ለ30 ሴቶች የሥራ ዕድል የፈጠረችበትን የራሷን ሥራ ፈጠራ ለመጀመር ያስቻላትን ተሞክሮ ለዓመታት ስትቀስም መቆየቷ አላረካትም። ግን ደግሞ ውቦቹ የህንድ እጅ ሥራ ውጤቶች ማርከዋት እንደነበር አትሸሽግም ። የገበያ ሁኔታቸውም ቢሆን የሳባት መሆኑን አልካደችም።የመንፈሳዊውን ስነመለኮት ትምህርቷን በአገረ ህንድ በአጥጋቢ ሁኔታ አጥንታ ካጠናቀቀች በኋላ ወደ አገሯ ኢትዮጵያ ተመለሰች።
በኢትዮጵያ በትዳር ውስጥ፤ በሌጣነት፤ በሴት አዳሪነትና በጎዳና ያሉ ሴቶችን እንዲሁም በትምህርት ገበታ ያሉ ልጃገረዶችን ፤ በተጨማሪም በትምህርቸው ብዙ ገፍተው መሄድ ያልቻሉትን ተገድደው የተደፈሩና የተለያየ ጥቃት የደረሰባቸው፤ ዕድሉን ቢያገኙ ለሀገር የሚጠቅም ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍታት ይችላሉ የምትላቸውን አካል ጉዳተኛ ሴቶች የሚኖሩበትን ሁኔታ በተለያየ መልኩ ስታጠና ሰነበተች። ችግሮቻቸው ከሥር መሰረታቸው በዘላቂነት መፈታት አለባቸው የሚል እምነት ያላት ገላዬ ችግሮቹን በመለየት ለዘላቂ መፍትሄው ተጨማሪ ልምድ ለመቅሰም በድጋሚ ከኢትዮጵያ ውጪ ወደ ሆኑ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት አመራች።
‹‹እንደ ሥራ ፈጣሪ ችግርን ነው የምመለከተው ። በተለይ የእኛ ሀገር ገና በማደግ ላይ ያለች እንደመሆኟ በማሕበረሰባችን ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የምንመለከትበት አጋጣሚ ብዙ ነው ›› የምትለው ወጣቷ ሥራ ፈጣሪ ከኬንያ ጀምሮ በርካታ የአፍሪካ አገራትን ተሞክሮ ጎብኝታ ከተመለሰች በኋላ በሀገር ቤት ቆይታዋ በስደት ያሉ የነበሩና አካላዊና ስነ ልቦነናዊ ጥቃት የደረሰባውን ሴቶች ስትመለከት አንጀቷን በሏት። ሴቶቹ አቅም ያላቸው መሥራት የሚችሉ ነበሩ። ግን ደግሞ አይችሉም ወይም አይለወጡም ተብለው በማህበረሰቡ ተገልለዋል። ተገፍተዋል። በዚህም ጎዳና ለመውጣት ተገድደዋል። ለራሳቸው፤ ለልጆቻቸውና ለቤተሰባቸው የሚሆን የዕለት ጉርስ አጥተው ተሰደዋል። ብዙዎቹ እናቶች ፤እህቶች ይሄም ሳይሆንላቸው ቀርቶ ታርዘው፤ተራቁተውና ተርበው ሕይወታቸውን ለመግፋት ተዳርገዋል።
ሥራ ፈጣሪዋ እንደ ብዙዎቻችን ከንፈሯን መጥጣ አላለፈቻቸውም።እንደውም ከዚህ ከንፈር ከመምጠጥ ካለፈ በአንደበቷ እንዳወጋችን እያሽከረከረች በአምስት ኪሎ አካባቢ ስታልፍ የገጠማት አንድ ገጠመኝ አላት።ወጣቷ እዚህ አካባቢ ስትደርስ አንድ ራሱን ስቶ የወደቀ ወጣት ትመለከታለች።ቦርሳ ይዟል።በኪሱ ውስጥ የኢንሱሊን መውጊያ መርፌ ይዟል።ከዚህ በመነሳት በርካታ ሰዎች ስኳሩ ወርዶ ነው በማለት ከንፈራቸውን እየመጠጡ ሳንቲም ጥለውለት ያልፉ ነበር። የወጣቷ ሥራ ፈጣሪ አእምሮ ግን ሳንቲም መፍትሄ እንደማይሆነው የገባው ፈጥኖ በመሆኑ እንደደረሰች በሰዎች እርዳታ ወጣቱን ወደ መኪናዋ ውስጥ አፋፍሳ አስገባችና በፍጥነት ሆስፒታል በማድረስ ሙሉ ወጪዎቹን ሸፍና ሕክምና እንዲያገኝ አደረገችው።
ምንም እንኳን ወጣቱ በሕክምና ስኳር የሌለበት መሆኑ ቢታወቅና አንድ ነገር ቢፈጠር ብላ ጭናቸው ከነበሩት ፖሊሶች እጅ ሮጦ በማምለጡ አታላይ መሆኑ ቢረጋገጥም መፍትሄው የታመመውን ወጣት ማዳን እንጂ ከንፈር መምጠጥና ሳንቲም መጣል እንዳልሆነም አሳይታለች።በተለይም ከመስራት ይልቅ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ሲባል ሰዎችን አታሎ ገንዘብ የመሰብሰብ ክፉ ባህል በመንሰራፋቱ ወጣቱን ወደ ስራ መመለስ እንደሚገባ የልጁ ሁኔታ ትምህርት ሆናት።
ከዚህ ተነስታ ለእንዲህ ዓይነቱ በሽታም ሆነ ሴቶች ለሚደርስባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄው አስቀድሞ ሰው አመለካከትና ባህርይ ላይ መሥራትና የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥተው ወደ ትክክለኛው ማንነታቸው እንዲመለሱ ማድረግ መሆኑን ሳታሰልስ ትመክራለች።ታድያም ወደ አገር ቤት በተመለሰችበት ወቅት አይችሉም ተብለው በተገለሉት፤ በተገፉት፤ጎዳና በወጡት፤በትዳራቸውም ሆነ በአንድ የሕይወት አጋጣሚ በውጣ ውረድ ውስጥ እያለፉ ያሉትን ሴቶች አውጥታ ካላቸው ነገር በመነሳት እንዴት ነው ሕይወታቸው ላይ ለውጥ ማምጣት የምችለው በሚል የዛሬ 14 ዓመት የራሷን ሥራ በመፍጠር የ Gelancrafts’ companyን መሥርታ መንቀሳቀስ ጀመረች።
በጥናት እንደተረጋገጠው አሁን ካለንበት ወቅታዊና የፀጥታ ሁኔታ ጋር በትግራይ ክልል ያለው ባይታወቅም 700 ሴቶችን በተለያየ የእጅ ሥራ ሙያ አሰልጥና ከ450 በላይ የየራሳቸውን ማህበር በመመስረት ጥሪት በማፍራት ሕይወታቸውንና ቤተሰባቸውን ለዘለቄታው እንዲመሩ አስችላለች።ለውጥ የሚመጣው ችግርን ከሥር መሰረቱ በዘላቂነት በመፍታት ነው።ወጣቷ በተጨማሪም ከ100 ዓመት በላይ ባለመበስበሱ የአፈርን ለምነትንም ሆነ ምድራችንን እየጎዳ ያለውን ፌስታል የሚተኩና ከአካባቢ ጋር የሚስማሙ የገበያ ቦርሳዎችን ታመርታለች።በዚህም ላይ ከደንና አካባቢ ጥበቃ ከዩኤን ዲፒ ጋር የቀረፀችውን ፕሮጀክት በመጠቀም አራት ክልሎችና ሁለት ወረዳዎች ላይ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎች ላይ መስራት አለብን በማለት አሳምናም የሰራችው ሥራ ተጠቃሽ ነው።
በዚህ ዙርያም በብዙ መቶ የሚቆጠሩና ዩኒቨርሲቲን ብሎም ቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የሚቀላቀሉ ልጃገረድ ተማሪዎች አሰልጥናለች።ልጃገረዶቹ በፊናቸው ማህበረሰቡ የፕላስቲክ ጎጂነትን እንዲረዱ የሚያስችል ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በማህበረሰቡ ዘንድ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ግንዛቤ ፈጥረዋል።አሁን ወላጆቻቸው በየገበያው ሲሄዱ የራሳቸውን አካባቢ የማይበክል ከረጢት ይዘው ነው ። የኔ ትውልድና ቀጣዩ ትውልድ ፕልስቲክን አይፈልግም የሚል አስተሳሰብ መገንባት ችላለች።በአለምና በአፍሪካ ስኬታማ ሥራዎች ከሰሩ ሴቶች መካከል አንዷ በመሆኗ ታሪኳ በድህረ ገጽ ጭምር የተለቀቀው ወጣት ገላዬ ይሄን የሥራ ፈጠራ አስተሳሰብና ተግባር ለማስፋት 50 ሚሊዮን የአፍሪካ ሴቶች ይናገሩ የሚለውን እንዲሁም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2040 ከፕላስቲክና ከተለያዩ የአካባቢ ብክለቶች ነፃ የሆነች ዓለም ለመፍጠር የሚንቀሳቀሰውና ሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮችን በመጠቀሙ ረገድም ወደር አልተገኘላትም።
ችግርን ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ከስር መሰረቱ መፍታት በተለይ እንደኛ ባሉ ሥራ አጥነት በተንሰራፋባቸው፤ የምግብ ዋስትና በቤተሰብ ደረጃ ባልተረጋገጠባቸው እንዲሁም በርካታ ሌሎች ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ባሉባቸው አገሮች ሀገር በቀል ዕውቀትን መጠቀም ከድህነት ወደ ብልጽግና ሊያሻግር የሚችል አይነተኛ መፍትሄ ነው ትላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ችግሮቻችንን በዚህ መልኩ መፍታት የሚያስችል መሰረት መጣላቸውንም ታነሳለች።ይሄን ተከትሎ በስንዴ ምርቱና በሌሎች መስኮች የተጀመሩት ጅምሮች አበረታች መሆናቸውንም ታወሳለች።
የትኛውም ሥራ ፈጣሪም ሆነ የለውጥ ሀዋርያ ነኝ የሚል አካል ችግርን በዘላቂነት የማይፈታ ከሆነ ባይጀምረው እንደሚመረጥም ትመክራለች። ሴቶች ላይ የሚሰሩ መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሴቶች ጀርባ ልጆች ቤተሰብ ብዙ ታሪክ ሀገር እንዳለች ማሰብ እንዳለባቸው ታስገነዝባለች። እንዲህ ተደረገና ሆነ ለሪፖርት ወይም ለሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ መሥራት የለባቸውም ባይ ናት ። በተጨባጭ በሁለት በሦስት አመት ውስጥ ይህችን ሴት ከዛ ጋር አንስቼ እዚህ ላደርሳት ችያለሁ የሚል የሚታይ ተጨባጭ ሥራ በሴቶች ላይ መሥራት እንዳለባቸውም ታሳስባለች።
እናም እሷ በጥቂት ሴቶች ላይም ቢሆን ዘላቂ ለውጥ ማምጣት የቻለችው በዚህ መልኩ እንደሆነም ታወሳለች። የሀገር ውስጥ ችግር በሀገር ውስጥ መፍታት አለብን በሚል ማሳመን ችላለች። የማንንም እርዳታ ሳይፈልጉ እንችላለን በማለት በራሳቸው የተለያዩ ዓይነት የእጅ ሥራዎች ስልጠና በመውሰድና እንደ ስንደዶ ፤ጥጥ፤ ቀርከሃና የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን በግብዓትነት በመጠቀም የሚያማምሩ ቦርሳዎች፤ስፌቶች፤የአንገት ልብሶች፤ወንበርና ጠረጴዛዎች፤ቅርጫቶችና የተለያዩ ምርቶች እንዲያመርቱ የሚያደርጋቸውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስልጠና እንዲወስዱ በማስቻል ለእራሳቸው እንዲበቁ አድርጋለች።ለራሳቸው ፤ለልጆቻቸው ብሎም ለቤተሰቦቻቸው ዘላቂ ዳቦ መግዛት የሚያስችል አቅም እንዲፈጥሩ እንዲለወጡ ማድረግ ችላለች።
በትምህርታቸው ብዙ ገፍተው የሄዱ ስለ ትምህርታቸው ፤ ብዙ ችግር ደርሶባቸው የተቀመጡ ሴቶች መሥራት ከቻሉ ብዙ የተማሩ ያወቁ ራሳቸው ላይ ብዙ የሰሩ ወጣቶች ደግሞ ሥራ ፈጥረው የሀገሪቱን ችግር ወደ መፍትሄ በመለወጥ ብዙ ሥራ መሥራት ይችላሉም ትላለች።ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ100 ካሬ በላይ የነበረው ማምረቻ ቦታዋ በ20 ካሬ ብቻ ተወስኖ ነው ያለው።ይሄ በየቤታቸው ሴቶች የሚያመርቱትን የእጅ ሥራ ማሳያ ብቻ በመሆኑ የግድ መንግስት የማምረቻ ቦታ በመስጠት ትብብር ሊያደርግላት እንደሚገባ ገላዩ የመንግስት ትብብር ትሻለች።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 /2014