የዓለም ምግብ ፕሮግራም ንብረት የሆነና ለሰብአዊ እርዳታ ማመላለሻ በመቀሌ መጋዘን ውስጥ የተቀመጠ 570 ሺህ ሊትር በህወሓት መዘረፉና የእርዳታ ሰራተኞች ላይ እንግልት መድረሱን ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ድርጊቱ ኢትዮጵያውያን ሲቪሎችን ለመመገብ የሚደረገውን ጥረት ማደናቀፍ እጅግ የጭካኔ ተግባር ነው ሲሉም በርካቶች አውግዘዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ከሚገኝ የዓለም የምግብ ድርጅት መጋዘን በህወሓት ኃይሎች የተዘረፈው 570ሺ ሊትር ነዳጅ እንዲመለስ ጠይቋል። ዓለም አቀፉ ህብረሰብም ወደ ትግራይ የሚገባው ሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖረው ህዝብ እየደረሰ መሆኑን እና ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማስተማመኛ እንዲሰጥም ጥያቄ ማቅረቡም የሚታወስ ነው። በዚህ የስርቆት ሚና የተካነውን ህወሓት ግን ውግዘቱንም ርክሰቱንም የፈራው አይመስልም። ይባስ ብሎ ዘረፋውን በፈጸመ ሁለተኛው ቀን ጀምሮ ወደ አማራ ክልል እና አፋር ክልለ በመሄድ ጦርነት ቀስቅሷል።
ህወሓት በዝርፊያ ውስጥ ሲሰማራ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜው አይደለም። በ1977 ዓ.ም በሀገር ድርቅ ተከስቶ በነበረበት ወቅትም ለተረጂዎች የመጣን የሰብአዊ እርዳታ ሀገር ውስጥ ሳይገባ በጉዞ ላይ እያለ አየር በአየር ሸጦ የጦር መሳሪያ መግዣ አውሎት እንደነበር ይታወሳል። እንዲሁም በተለያየ ጊዜ ጦርነት ሲያካሂድባቸው በነበረባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች ለሰብአዊ እርዳታ የመጣን ምግብ፣ መድሀኒት እና የህጻናት አልሚ ምግቦችን ጭምር በመዝረፍ ለወታደራዊ ዓላማው ማስፈጸሚያ ሲያውል መቆየቱን ዓለም አቀፍና ሀገራዊ መገናኛ ብዙሀን ሲዘግቡት ከርመዋል።
አሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) የሆኑ የእርዳታ መጋዘኖችን መዘረፋቸው ቀደም ሲል የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳሬክተር ሾን ጆንስ፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ መናገራቸው ይታወሳል። የህወሓት አማጺያን በየደረሱባቸው ስፍራዎች የሚገኙ የእርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈው ነበር። ‹‹ወታደሮችና የታጠቁ ሰዎች ከዜጎች ምግብ ሰርቀዋል። በተለይ ህወሓት በገባባቸውና ጦርነት በከፈተባቸው ሁሉም የአማራ አካባቢዎች መጋዘኖችንና ተሽከርካሪዎች ዘርፏል። ውድመት ፈፅሟል›› ብለው ነበር። መጋዘኖቻችን በመዘረፋቸውና ባዶ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ አለን ነበር ያሉት። ‹‹ህወሓት ሁኔታዎችን ያለአግባብ እየተጠቀመ እንደሆነ አምናለሁ። ከተረጂዎች ላይ በኃይል እርዳታ እየነጠቀ እንደሆነ ይሰማናል፤ የምናውቀው ሃቅ ግን የህወሓት ኃይሎች በገቡባቸው አካባቢዎች ሁሉ የእርዳታ መጋዘኖቻችን ዘርፈዋል›› ማለታቸው ይታወሳል።
በደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ሀሳቡ ተስፋው እንዳሉት ፤ ህወሓት ዘረፋን የተካነበት እና ከምስረታው ጀምሮ የመጣበት ታሪክ ስለመሆኑ ሁሉም የሚያውቀው እንደሆነ ያብራራሉ። ህወሓት ነዳጁን ለምን ሰረቀ ከሚለው በፊት [[ሰላማዊ መንገድ ይበጃል፤ ድርድር ይቅደም]] ሲል ቆይቶ ወደ ጦርነት የገባው ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ይገባል ። ህወሓት በባህሪው በሚደግፉት ዘንድ ቅቡል ለመሆን ጦርነትን እንደ መለኪያ አድርጎ ይመለከተዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ የክልሉን ህዝብ በአግባቡ ለመምራት ብዙ ነገሮች የሚጎድሉትና ለራሱ ህልውናም በመጥፋት ላይ በመሆኑ አጀንዳ እየፈጠረ ህዝቡን ጠፍንጎ ለመያዝ የሚያስብ እና ኃላፊነት የጎደላቸው ስብስብ ነው።
አሸባሪ ህወሓት ከሌሎች ጋር እኩል ሆኖ መኖርን እንደ ነውር የሚያይና የበላይ ለመሆን ብዙ ግፎችን ሲፈጽም የኖረ፤ እያደረገ የነበረ እና አሁንም በመፈፀም ላይ የሚገኝ ነው። ይህ በመሆኑም ይህ ቡድን ለማድረግ የማይመኘው ነገር የለም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ስለተገፋ ብዙ ነገሮች ግራ ገብተውታል። በመሆኑም ሠላምን ማወክ እንደጀብድ ይቆጥረዋል። ይህ ሁሉ ጥረት ደግሞ ድርድሩ ህወሓት በሚፈልገው መንገድ እንዲሄድለት በማሰብ ነው። ህወሓት ከኋልዮሽ ታሪኩም ሆነ አሁንም ፀረ-ሠላም ሆኖ የቀጠለ ቡድን መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።
ታዲያ ህወሓት የሠላም ፍላጎት የሌለው ቡድን በመሆኑም በተገኘው አጋጣሚ ደግሞ አቅም ለመፍጠር ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን ይፈጽማል፤ ዘረፋም ያካሂዳል። ሰሞኑን ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ተብሎ ወደ ትግራይ ክልል የተላከውንና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ንብረት የሆነውን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ በህወሓት መዘረፉና የእርዳታ ሠራተኞች ላይ እንግልት መድረሱን የቀድሞ ታሪኩን የበለጠ ለዓለም ያሳየበት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ህወሓት ይህን ሁሉ ዘረፋ እና ወንጀል እየፈጸመ ዝምታው የመረጡ ኃያላን ሀገራትም ዓላማቸውን በእጅ አዙር እያሳኩ በመሆኑ ደስተኛ ስለመሆናቸው አመላካች ሁኔታዎች አሉ የሚሉት አቶ ሃሳቡ፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢትዮጵያ ጎልታ እንድትወጣ አይፈለግም። ይህም በመሆኑ በህወሓት ላይ የመረረ አቋም መያዝ አይፈልጉም። ህወሓትም የእነርሱን ፍላጎት ሲያስተናግድ የቆየ፤ በተመሳሳይም ትዕዛዛቸውን ሲፈጸም የነበረ በመሆኑ ህወሓትን ተሸክመውታል። ይህ በመሆኑም መንግስትን ቅርቃር ውስጥ ማስገባት ቀዳሚ አጀንዳቸው ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ጨምሮ ቀጣናው የተረጋጋ መሆን የለበትም የሚለው የማይናወጥ አቋማቸው ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያን መዳከም ይፈልጉታል።
ይህ እውነት መሆኑን ለማሳየት ብዙ ርቀት መጓዝ አይገባም የሚሉት አቶ ሃሳቡ፤ ሰሞኑን ለሰብዓዊ እርዳታ ተብሎ የቀረበን ነዳጅ ህወሓት ሲዘርፍ ቀለል ያለ መግለጫ ከመስጠት የዘለለ አንዳችም እርምጃ እንዲወሰድ አልፈቀዱም። በህግም ተጠያቂ አላደረጉትም። ይህም ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የሚመጡ ጫናዎችም መንግስት ላይ የሚያነጣጥሩ ስለመሆናቸው አመላካች ነው። በቀጣይ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማትም የኢትዮጵያ መንግስት ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ እያደረገ ነው በሚል ወቀሳቸውን ይቀጥላሉ፤ ይሄ የፌደራል መንግስቱንም ለከፋ ጫና ይዳርገዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ድርድሩ አድርጉ እያሉ የሚወተውቱ ሲሆን፤ ይህ ሁሉ የሚሆነው የኢትዮጵያን ህልውና እስከመጨረሻው አደጋ ውስጥ ለማስገባት በማሰብ ነው። ያም ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም በሮችን አልዘጋም” አሁን የሰላም እጆቹን ዛርግቶ በሰላም ዙሪያ ለመወያያት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።
ህወሓት ሰብዓዊነት የሚጎድለው ቡድን ቢሆንም ለሰው ልጆች ሰብአዊ መብት መከበር የሚሰሩ ድርጅቶች ህወሓት ለእርዳታ የመጣን 570ሺ ሊትር ነዳጅ ሲዘርፍ ነውር መሆኑን ከማውገዝ በዘለለ እርምጃ መወሰድ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ አካላት የህወሓት የዘረፋ ታሪክም በቅጡ የሚረዱ ሆኖ ሳለ አንዳችም እርምጃ እንዲወሰድባቸው አለማድረጋቸው እነሱንም ትዝብት ላይ የሚጥላቻው ነው። ይሄ ዝምታቸውም የተባባሪነታቸው ማሳያ ነው የሚል እምነት እንዲያድርባቸው ማድረጉን ይናገራሉ -አቶ ሐሳቡ።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህር ቤት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር እንዳወቅ ፀጋው፤ ልክ እንደ መምህር ሀሳቡ ሁሉ የእሳቸውም አስተያየት ህወሓት በዘረፋ ላይ የተሰማራና የቀደመ ታሪኩም ይሄንኑ የሚያሳይ መሆኑን ይናገራሉ። ህወሓት ለኢትዮጵያ ሠላም እና አንድገት ነቀርሳ ሆኖ የቆየ፤ ሲፈጠር ጀምሮም ስርቆትን የተካነበት ስለመሆኑም ያስረዳሉ። የዚህ ቡድን ስርቆት በቁሶች ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ታሪክ፤ እውነትንና ሀቅን በአንድ ላይ ያካተተ እና ክህደትን ጭልጥ አድርጎ የተጎነጨ ስለመሆኑም ይጠቁማሉ።
ህወሓት ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ተብሎ የተጓጓዘውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ንብረት የሆነውን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ በህወሓት ቡድን መዘረፉና የእርዳታ ሰራተኞች ላይ እንግልት ማድረሱ፤ ቀደም ሲል የነበረውን ልምድ የበለጠ በገሃድ ያሳየበት እንጂ የተለየ ነገር የለውም ባይ ናቸው። ይልቁንም የዚህ አስናዋሪ ሥርቆት የተወገዘበት መንገድ አሳዛኝ ነው። ለወትሮ ሰብዓዊ መብት መጠበቅ አለበት፤ ለንፁሃን እንቆማለን የሚሉ ወገኖች በሁለት መስርመር ድርጊቱን አግባብ አይደለም ከማለት የዘለለ አንዳችም አለፍ ያለ መልዕክት ማስተላለፍ አልፈለጉም። ይህም የነገሩን መባባስና በመንግስት ላይ ጫና የማሳደሪያ መንገዶች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ስለመሆናቸው ፍንትው አድርጎ ያሳያል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ ህወሓት ከስርቆትም ሆነ ሌሎች አስነዋሪ ድርጊቶች ራሱን ያቅባል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ለሀገራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የመገዛት ዕድሉ የጠበበ ነው። በአሁኑ ወቅት ህወሓት እንደ መፍትሄ ብሎ የሚያስበው ደግሞ ጦርነትን ነው። ቡድኑ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ በመሆኑም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ነውሮችን ከመፈፀምና ከመስረቅ እንደማይመለስ ማወቅ ይገባል ባይ ናቸው።
የህወሓት ነዳጅ ስርቆት ከዓለም አቀፍ ህጎች፤ ከሰብዓዊ እርዳታ አሰራሮችና መርሆዎች፤ ከሰው ልጅ ሞራሊዊ ግዴታዎች አኳያ ሲመዘን በፍጹም ተቀባይት የሌለው ነው። በመሆኑም ዓለም አቀፍ ተቋማት በቀጣይ ቡድኑ መሰል ድርጊቶችን ከማድረግ እንደማይመለስ በመገንዘብ፤ አስፈላጊውን የተጠያቂነት እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ። በተለይም ደግሞ የተራድኦ ድርጅቶች ለሰብዓዊነት ተብሎ የሚላኩ ምግቦችና ነዳጅን ጨምሮ በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉም ለፌዴራል መንግስት ማረጋገጫና ማስተማመኛ የመስጠት ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ህወሓት በስርቆትና ሀሰተኛ መረጃዎች ተደላድሎ እንዲሰነብት ዕድሎችን ማመቻቸት ይሆናል።
ህወሓት የስርቆትም ሆነ የዘረፋ ታሪኩን ማቆም የማይፈልግ ቡድን በመሆኑ መፍትሄው ላይ ማተኮር እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ሀሳቡ ተስፋው ኢትዮጵያ ይህ ጦርነት እስከመጨረሻው በአሸናፊነት መውጣት አለባት ይላሉ ። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የምንገነዘበው የዓለም ፖለቲካ ከአሸናፊዎች እንጂ ከእውነት ጋር አለመሆኗን ነው። በተለይም ደግሞ ህወሓት የሚከተለውን የውሸት ዲፕሎማሲ እና ጫና በመረጃ ላይ በመመስረት ማክሸፍ ይገባል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ከመሆኗ ባሻገር በርካታ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች እና ድርጅቶችም የሚገኙበት በመሆኑ እድሉን ከተጠቀመች የአሸባሪውን ህወሓት የስርቆት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅም የትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርሰው እያደረገ ስለመሆኑ በሚገባ ለማስረዳት በር ይከፍታል፤ ጫናዎችንም ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ይቻላል። ይሁንና ህወሓት ስርቆት እየፈጸመ ነው በሚል መግለጫ ብቻ ማለፍና የህወሓትን ነውር መናገር በቂ አለመሆኑንም ይጠቁማሉ።
በመንግስት በኩልም የህወሓት የኋልዮሽ ታሪክ በመረዳት ለሠላማዊ ውይይት ዝግጁ አለመሆኑን ማሳያ ምልክቶች መሆናቸውን ማወቅ ይገባል። በመሆኑም የህወሓትን አስነዋሪ ድርጊቶች በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶችና ተቋማት በሚገባ ደጋግሞ ማሳወቅ ያስፈልጋል። በሀገር ውስጥ አደረጃጀትና ሀገራዊ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማጠናከር ይገባል። ህዝብና መንግስት በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ማተኮር ለነገ የማይባል ጉዳይ ስለመሆኑም ረዳት ፕሮፌሰር እንዳወቅ ያሣስባሉ።
ምሁራኑ በሰጡት አስተያየት ለማረጋገጥ የተቻለው የህወሀት ቡድን ከተፈጠሩ ጀምሮ በስርቆትና በዝርፊያ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው። ሰላምን ማደፍረስ እንዲሁ መገለጫ ባህሪው ነው። በመሆኑም መንግስት የህወሓትን ባህሪ ጠንቅቆ ማወቅ እና መዘጋጀት ያስፈልጋል። እንዲሁም ዓለምአቀፍ ተቋማት በሰብአዊ እርዳታ፣ በመድሀኒትና በነዳጅ ላይ በተደጋጋሚ የሚያደርገውን ዘረፋ ከማውገዝ በተጨማሪ በህግ ተጠያቂ ማድረግ አለባቸው።
ክፍለዮሐንስ አንበርበር
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24 /2014