አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች በርካታ ትምህርት ቤቶችን በማፍረስ ትምህርት ጠል መሆኑን አሳይቷል። በዚሁ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። ቡድኑ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ አማራና አፋር ልዩ ሃይልና ፋኖ ተመቶ ከያዛቸው ቦታዎች ለቆ ከወጣ በኋላ ያወደማቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ የመገንባት ሥራ በመንግሥት፣ በግለሰቦችና ባለሀብቶች ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
ቡድኑ በትምህርት ቤቶች ላይ ካደረሰው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንፃር ግን ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ተግባር አሁንም የበርካቶችን ድጋፍና ርብርብ ይጠይቃል። በተለይ ደግሞ በውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ሀገር ወዳድ የውጭና የሀገር ውስጥ የልማት ድርጅቶችንና ሌሎችም በሀገር ውስጥ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመልሶ ግንባታው ድጋፋቸው አስፈላጊ ስለመሆኑ አያጠያይቅም።
የትምህርት ሚኒስቴርም የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ አካሄድ የመገንባት መርሃ ግብር በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመሰረት ድንጋይ የማኖር ተግባሩን ቀጥሏል። ትምህርት ቤቶቹን በመገንባት ሂደት ውስጥ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ተሳታፊ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደሚሉት፤ በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት 1 ሺ 222 ትምህርት ቤቶች ወድመዋል። በሸኔ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የወደሙትን ሲጨምር ቁጥሩ ወደ 1 ሺ 300 ከፍ ይላል። በዚሁ መነሻነት በቀጣዩ 2015 በጀት ዓመት እስከ 200 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ተይዟል። ይህም ግንባታ የሚከናወነው የተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶችን በማሳተፍ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተለያዩ መንገዶች በሚያሰባስባቸው ፈንዶች፣ ከረጂ ድርጅቶችና ከዲያስፖራ ፈንድ ነው።
በዚህ ክረምት ማገባደጃ የትምህርት ቤቶቹ ዲዛይን ይጠናቀቃል ተብሎ ይታሰባል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ወደ 50 የሚሆኑ ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ይገነባሉ። እነዚህ ግን ቀደም ብለው የፈረሱትን የሚያካትት ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገነቡ ናቸው። በተጨማሪም 13 አዳሪ ትምህርት ቤቶችን በሁሉም ክልሎች አንዳንድ ለመገንባት መታቀዱን ይናገራሉ።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሃርቡ ወረዳ መርሳ ከተማ መልሶ ከሚገነባው የመልካ ጨፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተጨማሪ ሁለት ትምህርት ቤቶች ይገነባሉ። እንደ ዞን ደግሞ እስከ ሰላሳ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች የሚሰራ ይሆናል። በደቡብ ወሎም በተመሳሳይ ይህን ያህል ቁጥር ትምህርት ቤት ይገነባል። በጎንደርና ሰቆጣም የሚሰሩ ትምህርት ቤቶች አሉ።
በአማራ ክልል 1 ሺ 160 ፤ በአፋር ክልል 65 በጥቅሉ 1 ሺ 225 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። ከዚህ አንጻር እነዚህን ጨምሮ በሁለቱ ክልሎች የወደሙ የትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታም በቀታዮቹ አምስት ዓመታት የሚጠናቀቅ ይሆናል።
ትምህርት ሚኒስትሩ እንደሚያብራሩት፤ ትምህርት ቤቶች ላይ የደረሰው አደጋ በጦርነት ብቻ የመጣ አይደለም። በተለይ ከታችኛው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ በትምህርት ጥራት ላይ ሆን ብሎ የተሰራው ሥራ ትምህርቱን ጎድቶታል። ለአብነትም በትምህርት ሚኒስቴሩ በተሰራ ምዘና ሶስተኛ ክፍል ጨርሰው ማንበብ የማይችሉ ተማሪዎች ከ60 በመቶ በላይ መሆናቸው ተረጋግጧል። በእንግሊዝኛ ቋንቋም በኩል ያሉ ችግሮች ይታወቃሉ።
የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ትምህርት የሚሰጠው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው ቢባልም በትክክል ትምህርቱ በቋንቋው እየተሰጠ ነው ለማለት ያስቸግራል። ለዚህ ደግሞ በመምህራን፣ በትምህርት ቤቶች ርእሰ መምህራን በኩል ያለው የብቃት ማነስ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ይህም በተደረገው ምዘና ውጤት መረጋገጡን ያስረዳሉ። ከዚህ አኳያ ትምህርት ጥራት ችግሩ ቀደም ብሎ የጀመረ እንደነበርም ያነሳሉ።
ይህም አልበቃ ብሏቸው ወያኔዎች ሀገሪቷን ለመበተን ባደረጉት ወረራ ሆን ብለው የትምህርቱን ዘርፍን በጦርነት አዳክመዋል፤ ትምህርት ቤቶችን ሳይቀርም አውድመዋል። ከዚህ አንፃር ችግሩን ከስር መሰረቱ በማየት የሚገነቡት ትምህርት ቤቶች ዝም ብለው በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሳይሆን የትምህርት ጥራትን በሚያሻሽል መልኩ ነው። ይህም ከትምህርት ቤቶቹ መሰረተ ልማት ጀምሮ እስከ ካሪኩለም፣ የመምህራን ብቃትና ተማሪዎች የሚማሩት የትምህርት አይነትን የሚያካትት እንደሚሆንም ይናገራሉ።
ተማሪዎች የቀለም ትምህርት ብቻ ሳይሆን በመጠኑም ቢሆን ተግባራዊ የእርሻና የእጅ ሥራ ትምህርት የሚማሩበት፤ ትምህርታቸውን ቢያቋርጡ እንኳን በማሕበረሰቡ ውስጥ ገብተው መስራት የሚያስችላቸው አካሄድንም ይከተላል። የቤተሰብና የተማሪዎችን ግንኙነት የሚያጠናክር የጋራ መሰብሰቢያ አዳራሾችና የጋራ መገበያያ ቦታዎችን በማካተትም ማሕበረሰቡን ማእከል ያደረገ የትምህርት ቤቶች ግንባታ እንደሚከናወንም ያስረዳሉ።
አዲሱ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ተብሎ የተጀመረው አካሄድ በአንድ ቦታ ላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራን፣ ማሕበረሰቡና ተማሪዎች የሚገናኙበት አዳራሽ፣ የእጅ ሙያ መስሪያ፣ የእርሻ ቦታ፣ ከእርሻው ደግሞ የሚመረተውን እዛው ተማሪዎችን ማብላትና ትምህርት ቤቱ ውስጥ እንዲቆዩና እውቀትን መከታተል የሚችሉበትን አካባቢን መፍጠር እንዲችሉም ይደረጋል። የሚቀጥለው ትውልድ የትምህርት መሰረትም ይህ ነው።
እንደሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው ጥናት ከአንድ እስከ አራተኛ ደረጃ ባለው ውስጥ አራተኛና ጥሩ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሱ ትምህርት ቤቶች 0 ነጥብ 001 ከመቶ ናቸው። ይህም ማለት 6 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው በበቂ ሁኔታ የመሰረተ ልማት ያሟሉት። በሌላ አባባል ከ99 በመቶ በላይ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማታቸው ደካማ ነው ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ግን የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች ይህንን መምሰል እንደማይችሉ ተወስኗል፤ ወደ ተግባርም ተገብቶበታል።
ኢንተርኔትን ጨምሮ ሌሎች የውሃ፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ መብራትና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን በበቂ ሁኔታ ማሟላት ያልቻሉ ትምህርትቤቶች ከዚህ በኋላ አይገነቡም። ለዚህም ነው አሁን ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባት ፕሮጀክት ዝምብሎ ትምህርት ቤቶችን መገንባት አይደለም የተባለው። በመሰረታዊነት የትምህርት ጥራትን ማሻሻል በሚችሉበት ሁኔታም ይቃኛሉ። ያልፈረሱት ትምህርት ቤቶችን ጭምር የአካባቢው ማሕበረሰብ እየተባበረ እንዲያሻሽልም በቅርቡ አዲስ ፕሮጀክት ይጀመራል።
እንቅሰቃሴው የትምህርቱን ሥርዓት ትርጉም ባለው መልኩ መቀየር ነው። ይህ ሥራም ዩኒቨርሲቲዎችንም ይጨምራል። በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ አንዱና ዋነኛው የትምህርት ሚኒስቴር ተግባር ይሆናል። ከዚህ አኳያ እነዚህን ትምህርት ቤቶች መገንባት የዚህ አጠቃላይ ፕሮጀክት አካል እንደሚሆንም ይናገራሉ።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ በአሸባሪ ቡድኑ ትምህርት ቤቶቹ እንደወደሙ ትምህርት ሚኒስቴር ባገኛቸው መሳሪያና ድንኳን ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው የነበሩ ተማሪዎችን ሲያስተምር ቆይቷል። ግን ትምህርቱ በፊትም ከነበሩበት የባሰ ሁኔታ ላይ ነበር። ይህንን በቶሎ መቀየር ያስፈልጋል። ሀገር አቀፍ ጉዳት ነው። በአንድ ጊዜም ሊሰራ የሚችል አይደለም። ስለሆነም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ትምህርት ቤቶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አቅዷል።
ፕሮጀክቱ እውን እስኪሆን ድረስ ባለው የትምህርት መሳሪያና የሰው ኃይል ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንደሚቀጥሉ ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ለዚህ ሥራ ተግባራዊ መሆን የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ለትምህርት ቤቶች የሚከፋፈል ይሆናል። 1 ሺህ የሚሆኑ ኮምፒዩተሮችንም ለትምህርት ቤቶቹ ለማከፋፈል ዝግጅት ተጠናቋል። መጽሃፍቶችም እየተዘጋጁ ነው። በተቻለ መጠን የትምህርት ሂደቱ እየቀጠለ የሚፈለገው ቦታ ላይ ለመድረስ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ይገልጻሉ።
ለትምህርት ቤቶቹ ግንባታ የሚወጣው ዋጋ ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት ይለያያል። የግንባታ አይነትም እንዲሁ ከቦታ ቦታ ይለያያል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ራሱን የቻለ ዲዛይን እየተሰራ ነው። ነገር ግን ከሃምሳ እስከ ስልሳ ሚሊዮን ብር በአማካይ ወጪ ሊሆን ይችላል። በዚሁ ስሌት ወደ 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል። የግንባታ ግበዓት ዋጋና ሌሎችም እየጨመሩ ሊሄዱ ስለሚችሉ ወጪው ከዚህም በላይ ከፍ ሊል ይችላል። ነገር ግን ይህ ገንዘብ አስኪገኝን ቁጭ ብሎ መጠበቅ የለም። ባለው ገንዘብ ሥራው ይቀጥላል። የሀገር ውስጥና የውጭ ኢትዮጵያውያን ማሕበረሰብን በማሳተፍ የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ እንዳይቋረጥም ይደረጋል።
ሚኒስትሩ እንደሚሉት፤ ከአዲስ አበባ ውጪ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ ተማሪዎች የምገባ ተጠቃሚ ሆነዋል። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ቢያንስ 1 ሚሊዮንና ከዛ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ለመጨመር ታስቧል። አንዱ የዚህ አዲሱ ትምህርት ቤቶች ዲዛይን ለየት የሚያደርገውም በጊቢው ውስጥ እርሻ እንደሚኖር ታሳቢ መደረጉ ነው። የእርሻ ቦታ እንዲኖር የሚታሰበው ከእርሻው የሚገኙት ፍራፍሬዎች ተመልሰው እዛው ትምህርት ቤት ውስጥ ለተማሪዎች ምግብነት እንዲውሉ ነው። ትናንሽ የከብት ርቢዎች፣ ዶሮ ርባታ፣ እንቁላል እንዲኖርና የእነዚህ ተዋጽኦዎች ተማሪዎች እንዲመገቡ ይፈለጋል።
ቀስበቀስ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በርሃብ ምክንያት ወይም በምግብ እጦት መማር የማይችል ተማሪ እንዳይኖር እድሉ ይፈጠራል። ሀገሪቱ እያንዳንዱን ችሎታ ያለው ልጅ ስለምትፈልግ በድህነትና በማጣት ምክንያት በትምህርታቸው ትልቅ ቦታ ሊደርሱ የሚችሉ ልጆች እንዲባክኑ ወይም ወድቀው እንዲቀሩ አትፈልግም። እናም የምገባ ፕሮግራም በጣም ውድ ቢሆንም በተቻለ መጠን ይህን እንደ አንድ ሥራ በመውሰድ ለማስፋት ሙከራዎች ይደረጋሉ እየተከናወኑም መሆናቸውን ይናገራሉ።
በተቻለ መጠን ተማሪዎች አልሚ ምግብ ተመግበው ትምህርት ለመቀበል ችግር የሚሆንባቸውን ችግሮች ለመፍታት ነው ሙከራ የሚደረገው። ነገር ግን ይህ በአንዴ የሚያልቅ አይደለም። ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በቶሎ የሚፈለገው ነገር ላይ ለመድረስ የሁሉንም ተሳትፎና ርብርብ እንደሚጠይቅም ያነሳሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2014