ሰሞኑን የኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር ገጽን እያየሁ ነበር። ብዙ የሚያስገርሙ ነገሮች አነበብኩ። መቼም የወንጀል አይነቱ እና ምክንያቱ ብዙ ነው። የግድያው ፤ የሙስናው፣ የማጭበርበሩ የሌላው ብቻ ምኑ ቅጡ። ለዛሬ እኔን የገረመኝን አንዱን ብቻ እንይ። የግድያውን። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከተለጠፉት የፍርድ ዜናዎች የግድያውን ብቻ ጥቂቱን እንመልከት፤-
“ባለትዳር ለሆነች የስራ ባልደረባው ያቀረበውን የፍቅር ጥያቄ ባለመቀበሏ የገደላት ጌታቸው አለምፀሀይ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት”
“ለምን ከስራ ቦታየ እቀየራለሁ?” በሚል ምክንያት የቅርብ አለቃውን በክላሽ ተኩሶ የገደለው የፌዴራል ፖሊስ በእስራት ተቀጣ።”
“የራይድ አሽከርካሪውን የገደሉት ጓደኛማቾች በእድሜ ልክ ፅኑ አስራት ተቀጡ።”
“ጨቅላ ህፃን ልጇን በጭካኔ አንቃ የገደለችው ተከሳሽ በጽኑ እስራት እንድትቀጣ ተወሰነ።”
“አንተ ለምን ትንበቀበቃለህ?” ብሎኛል በሚል ምክንያት የስራ ባልደረቦቹን የገደለው እና ያቆሰለው የፌዴራል ፖሊስ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጣ”
አስገራሚ ነው። 5 ግድያዎች 5 የተለያዩ ምክንያቶች። አንደኛው ከፍቅር ጋር ይያያዛል ፤ ሌላኛው ከስራ ጋር ፤ ሌላኛው የውንብድና ፤ ሌላኛው የምቾት ፤ ሌላኛው ደግሞ የክብር ናቸው። ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ጉዳዮች እንዴት ነፍስ ሊያጋድሉ እንደደረሱ ለመገመት እንኳ ከባድ ነው። አስቡት እስኪ “አንተ ለምን ትንበቀበቃለህ?” የምትል ተራ ንግግር ቃታ ስታስብ ፤…. በዚህ ዘመን ባለትዳር ሴት አላገባም አለችኝ ብሎ ሲገድልም ይታያችሁ… ብቻ አስገራሚ ነው። እነዚህ እንግዲህ በ15 ቀን ውስጥ ብቻ
የሰማኋቸው የፍርድ ውሳኔዎች ናቸው። በየፍርድ ቤቱ ሚዲያ ሳያየው የሚከናወን የፍርድ ዜና ቢጨመር ደግሞ ሌሎችም ከዚህ የከፉ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው።
የሆነ ሆኖ ዛሬ መጻፍ የፈለግኩት ስለ ግድያ ምክንያቶች አስገራሚነት አይደለም። ነገር ግን የግድያዎቹ መነሻ እና ድርጊቱ የሚያሳየው አንድ ነገር ቢኖር ጉዳዩ ጠለቅ ያለ ጥናት እንደሚፈልግ ነው። በኔ እምነት ጉዳዩ ከአእምሮ ጤና ጋር የተያያዘ ነው። ምክንያቱም የሰው ልጅ በጤነኛ አእምሮው ሌላ ሰውን ለመግደል እንዳይችል ተደርጎ ነው የተፈጠረው። ይህም ማለት ገዳዩ ለመግደል አንዳች የጤና መጓደል ሊኖርበት ያስፈልጋል። ይሁንና እኛ ጋር ይህ ጽንሰ ሃሳብ የሚታወቅ አይመስልም። አንድ ሰው ሌላ ሰውን ከገደለ የሚገድለው አንድም እብድ ስለሆነ ነው አልያም ጨካኝ ስለሆነ ነው። እብድ እና ጨካኝ የሚሉት መግለጫዎች ግን በራሳቸው ገላጭ አይደሉም ፤ እንዲያውም አሳሳች እና አደገኛ ናቸው።
ምናልባትም ከነዚህ 5 ግድያዎች የተወሰኑት የተፈጸሙት የሥነ ልቡና ባለሙያዎች ሳይኮፓት በሚሏቸው አይነት ሰዎች ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች ደግሞ የራሳቸው መገለጫዎች አሏቸው። ያን ማወቅ ደግሞ ወደፊትም የሚከሰቱ እንዲህ አይነት ግድያዎችን ለመቀነስ ይረዳል። አልያም ግን ሞቱንም ሳናስቀር ማረሚያ ቤቱን በመሰል ሰዎች እንሞላውና ከውጭ ይልቅ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚኖረው ግድያ የሚያሰጋ ይሆናል። ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ጥናት ያስፈልጋል።
ነጮቹ በዚህ ዙሪያ ብዙ ሰርተዋል። በትምህርት ተቋማቶቻቸው ፤ በሚዲያዎቻቸው ፤ በፊልሞቻቸው ወዘተ… ሕዝብን ስለ ጉዳዩ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ችለዋል። ዛሬ ላይ እንዲህ አይነት የጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች ቀድሞው በመለየት እና ህክምና እንዲያገኙ በማድረግ ብዙ ችግሮችን ማስቀረትም ችለዋል።
እስኪ ከሰሯቸው ስራዎች መካከል አንዱን እንመልከት። በ2014 እ.ኤ.አ ቤልጄማዊው የሳይካትሪ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሌስቴድ እና ሌሎች 10 የሙያ አጋሮቹ ከዚህ ቀደም ሳይኮፓት ገጸ ባህሪያትን የያዙ ፊልሞችን ሊመረምሩ እና የትኛው ፊልም በትክክል ይህን የሥነ ልቡና ቀውስ አሳስቷል የሚለውን ሊለዩ ተነሱ። በዚህም መሰረት ከ1915 እስከ 2010 እ.ኤ.አ ባሉት 95 ዓመታት ውስጥ በተሰሩ 400 ፊልሞች ውስጥ ያሉ 126 ሳይኮፓት ገጸ ባህርያትን ለዩ። በዚህም መሰረት ዝነኛው ሀቪየር ባርጉዌን በተወነበት ኖ ካንትሪ ፎር ኦልድ ሜን ፊልም ላይ ያሳየው የሳይኮፓት ባህሪ እስከዛሬ ከታዩ ገጸ ባህርያት መካከል ለእውነታው የቀረበ ነው ብለው ደመደሙ።
አጥኚዎቹ በጥናታቸው ያሳኩት ዋነኛ ቁምነገር ግን ምርጡን ገጸ ባህሪ መለየታቸው ሳይሆን ከዚህ ቀደም ሳይኮፓት ስለሚባሉ ሰዎች የነበረው የገጸ ባህሪ አሳሳል የተሳሳተ እንደነበር ማስተዋላቸው ነው። ድሮ ይህ የሥነ ልቡና ቀውስ ያለባቸው ሰዎች ሲሳሉ ያልተረጋጉ ፤ ብስጩ ፤ የማይገመቱ ፤ በትንሽ በትልቁ ጠብ ውስጥ የሚገቡ ፤ በየቦታው የተለየ የፊት ገጽታ የሚያሳዩ ፤ እንደ ጅል የሚገለፍጡ ወዘተ ተደርገው ነው የተሳሉት። ሰዎቹም በአብዛኛው አመጸኛ ወይም እብድ ዶክተር ተደርገው ነበር የሚገለጹት። ይህ ግን ስህተት ነው።
ብዙውን ጊዜ የዚህ ችግር ሰለባ የሚሆኑት ሰዎች በፊልሞቹ ላይ እንደሚታየው እውቀት ያሳበዳቸው ዶክተሮች ወይም ሀሺሽ ያሰከራቸው የመንደር ጎረምሶች ብቻ አይደሉም። ሰዎቹም ሁልጊዜ ብስጩ ፤ ስሜታዊ ፤ የማይገመቱ ፤አንዳንዴ እንደ ቂል የሚቃጣቸውም ብቻም አይደሉም።
እንዲያውም ብዙውን ጊዜ ከዚህ በተቃራኒ ሆነው ይገኛሉ። የተረጋጉ ፤ ብልህ ፤ አስተዋይ የሚመስሉ ብቻ በጥቅሉ ለመገመት የማይመቹ ናቸው። ሀቪየር ባርደምም በፊልሙ ላይ ማሳየት የቻለው እና በሥነ ልቡና ባለሙያዎችም ዘንድ ችግሩን በትክክል አሳይቶታል ተብሎ የተደነቀው በዚህ የተረጋጋ ባህሪ ነው።
የእኛም ሀገር ወንጀለኞች ጉዳይ ሲታይ መታየት ያለበት በዚህ መነጽርም ሊሆን ይገባል። እስኪ አስቡት የፌዴራል ፖሊስ አባል ተናገራችሁኝ ወይም ቦታ ቀየራችሁኝ ብሎ የስራ አጋሮቹን ሲገድል… የመንግሥት ሰራተኛ ባለትዳር ሴት አላፈቀረችኝም ብሎ ነፍሷን ሲነጥቅ ፤… እናት ገና አይታ ያልጠገበችውን የገዛ ስጋዋን አንቃ ስትገድል … ይሄ ከስሜታዊነት በላይ የሆነ ችግር ነው።
ምናልባትም እነዚህ ሰዎች ያልታወቀላቸው የአእምሮ ጤና መታወክ ሳይኖርባቸው አይቀርም። እኛ ግን ስለ ሁኔታው ያለን ግንዛቤ አናሳ እና የተሳሳተ በመሆኑ እንዲህ አይነት የአእምሮ ጤና መታወክ ያለባቸውን ሰዎች እየጠበቅን ያለነው ድሮ ፈረንጆቹ ፊልም ላይ በሰሯቸው ገጽታ ጨርቅ የጣሉ እብዶች አድርገን ነው።
ሳይንሱ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር ደግሞ ዛሬ ላይ የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በብዙ መልክ እንደሚመጡ ነው። እንደምናስበው ብስጩ እና ጠብ ጠብ የሚላቸው ብቻ ሳይሆን ጠብን የሚቆጣጠር ጸጥታ አስከባሪ ፤ ጸብን የሚያወግዝ የሃይማኖት መምህር ፤ ጠብን የሚሸመግል የሀገር ሽማግሌ ፤ ጠበኞችን የምታክም ነርስ ወዘተ… ሆነው ሊከሰቱ ይችላሉ። ስለዚህም ሕዝባችንን ስለ ችግሩ በዚህ መልክ ማስተማር እና ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል። አልያም ከላይ የሰማናቸው አይነት ግድያዎች እየተበራከቱ ይመጣሉ። ዛሬ ላይ የፖሊሱን ብንሰማም ነገ የሀኪሙን ፤ የሰባኪውን ፤ የነጋዴውን ፤ የባለሥልጣኑን ወዘተ እየሰማን እንቀጥላለን። እዛ ላይ እንዳንደርስ ደግሞ ካሁኑ እይታችንን እናስተካክል። ሳይንስን ተመርኩዘን እናጥናው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2014