በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በማተኮር በተለይም አሸባሪው ሕወሓት በመንግስት በኩል የተዘረጋውን የሰላም እጅ በመግፋት ሰሞኑን በአማራ እና አፋር ክልሎች በኩል ጦርነት መክፈቱን አስመልክቶ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የሀረሪ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት፣ የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግሥት እና የሲዳማ ክልል ያላቸውን አቋም ገልጸዋል፡፡ ተግባሩንም አውግዘው በአገር ውስጥ ጦርነቱን ቀልብሶ ሰላምን እውን በማድረግ ሂደት ሕዝቦች ሊኖራቸው የሚገባውን ዝግጁነት እንዲሁም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ሊገነዘብና ሊያደርግ የሚገባውን ጉዳይ በመልዕክትነት በማካተት ያወጡት መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
***
ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ፤
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት የክልሉ ሕዝብ በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ሥር ተጠቃሚ የሚሆንበትን ወሳኝ ተግባራት አከናውኗል።
ይህን ሁኔታ የተረዳው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የአማራ ሕዝብና መንግሥት የራሱን የመልማት ዐቅም ተጠቅሞ የራሱን ዕድገት የሚያረጋግጥበትን ዕድል ለማጨናገፍ ከመነሻው ዓላማ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል።
በቀጥተኛ እና በተዘዋዋሪ መንገድ በመላ ኢትዮጵያ በሚገኘው የአማራ ሕዝብ ላይ የተጠኑ፣ ተከታታይነት ያላቸው፣ አሰቃቂ ዘር ተኮር ጥቃቶችን፣ ግድያዎችን፣ ዝርፊያና መፈናቀል እንዲደርስበት በማድረግ አማራን ማኅበራዊ ዕረፍት የመንሣት ስልትን ሲከተል ከርሟል፡፡
በዚህ የጥፋትና የእልቂት ድርጊቱ ያልተገታው ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ክህደት ፈጽሟል። በዚህም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ወታደራዊ ጥቃት አድርሷል። ከዚህም አልፎ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጡም ሆነ በባህላዊና ሃይማኖታዊ መስተጋብሮቹ ከትግራይ ሕዝብ ጋር የሺ ዓመታት የአብሮነት ታሪክ ባለው የአማራ ክልል ሕዝብ ላይ ወረራ በመፈጸም ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳቶችን አድርሷል።
ከ288 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መሠረተ ልማቶችና ተቋማትንም አውድሟል፡፡
የክልሉ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ የህልውና አደጋ ጋርጠውበት የነበሩትን እነዚህን ሁሉ ግፎች ለመከላከል ጥረት ከማድረግ በዘለለ ወደለየለት መጠፋፋት እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ የተፈጠሩት ግጭቶች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን አማራጮች በማስቀደም ከሁሉም በፊት እና ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ለሰላም የተከፈተውን በር በሚፈጽማቸው የጦርነት ትንኮሳዎችና ወረራዎች ስለዘጋው የጋራ ታሪካችን እና ስለ መጪው አንድነት፣ ዕድገትና ተስፋ ስንል ቅድሚያ የሰጠነውን የሰላም ዕድል በተደጋጋሚ አምክኗል፡፡
ዛሬም ቢሆን የትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የክልላችን አካባቢዎች ላይ ለአራተኛ ጊዜ ወረራ በመፈጸም ከወራት በፊት በክልላችን ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ሁለንተናዊ ጥቃት ለመድገም እየተክለፈለፈ ይገኛል፡፡
ይህ ጦር ናፋቂ የሽብር ቡድን በንጹሐን ዜጎች፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ላይ የፈጸማቸው ጥቃቶች የቡድኑን እውነተኛ ማንነት አጋልጠውታል።
በመሆኑ መላው ሰላም ፈላጊ የሰው ዘር እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሽብር ቡድኑን ሊያወግዝ እና ለፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን ግፊት ሊያደርጉ ይገባል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሁሉንም ዓይነት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ የሰነቀው ልባዊ መሻት ጽኑ ነው። ነገር ግን በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን እምቢተኝነት ምክንያት የሰላም አማራጮች የተዘጉ በመሆናቸው የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት የማስጠበቅ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ አስገድዶታል።
ስለዚህም በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን የተቃጣበትን ወረራ ለመቀልበስ የሚያስችል አስፈላጊና ተመጣጣኝ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በመሆኑም መላው የአማራ ሕዝብ የክልሉ መንግሥት የሚያቀርበውን ጥሪ በንቃት እንዲጠብቅና ተገቢውን ሁሉ ዝግጅት እንዲያደርግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከወዲሁ ያሳስባል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም.
ባሕር ዳር
***
ከአፋር ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ፤
አሸባሪው ሕወሓት የጀመረውን ህዝባዊ እልቂት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዝ ይገባል!
አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል እና በአማራ ክልል በኩል በከፈተው በከባድ መሳሪያ ህዝብን በማሸበር የጀመረውን አረመኔያዊ ህዝባዊ እልቂት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዝ ይገባል።
ቡድኑ ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ ለሶስት ዙር በአፋር ክልል በኩል በከፈተው ጦርነት ንፁሀን ሴቶችን፣ ህፃናት፣ አዛውንቶችን ያለምንም ርህራሄ በጅምላ ጨፍጭፏል፣ ህዝባዊ ተቋማትን፣ ሃይማኖት ተቋማትን አውድሟል፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ንፁሀን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል ለስቃይ፣ ለርሃብ፣ ለእንግልት እና ሞት ዳርጓል፡፡
በንፁሀን ዜጎች የጭካኔ አይነቶችን እያፈራረቀ የፈፀመው አሸባሪው ሕወሓት ለዘመናት ተጋምዶ የኖረው የአፋር እና ትግራይ ጎረቤት ህዝቦችን አብሮነት የሚያሰናክለው ባለመሆኑ፣ አሸባሪ ቡድኑን እንደ ቡድን ነጥሎ በማየት፣ የተከበረው የትግራይ ህዝብን ለመታደግ መድረስ የሚገባቸው የሰብአዊ እርዳታ በአፋር በኩል እንዲያልፍ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለህዝብ እርዳታ እንዲደርስ የአፋር ህዝብና መንግስት ከፌዴራል ተቋማት፣ ሰብአዊ ድርጅቶች እና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋር ሲሰሩ ቆይተዋል።
በቀጣናው አሸባሪው ሕወሓት የከፈተው አስከፊ ጦርነት እንዲቆም መንግስት የሰላም አማራጭ ቢያቀርብም ሰላም የማይመቸው አሸባሪው ሕወሓት በመንግስት በኩል የቀረቡ የሰላም አማራጮችን ወደ ጎን በመተው በአፋር ክልል በኩል በፈንቲረሱ ዞን ያሎ ወረዳ በኩል ለአራተኛ ዙር በአፋር ህዝብ ላይ ጦርነት ከፍቷል።
በተመሳሳይም በአማራ ክልል በኩል ጦርነት ከፍቶ ህዝባዊ እልቂት በማስከተል ላይ ይገኛል፡፡
አሸባሪው ሕወሓት ከአሁን በፊት ጦርነት በከፈተባቸው ግንባሮች እንዳደረገው ሁሉ አሁንም በከፈተው ጦርነት ንፁሀን ዜጎችን ኢላማ ያደረገ የሰው ማዕበልን በመጠቀም ጦርነት ከፍቷል። በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ ዞን በያሎ ወረዳ በኩል ከባድ መሳሪያ ወደ ንፁሀን አርብቶ አደሮች በመተኮስ ህፃናትና ሴቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፣ ከባድ የሆነ ጉዳትም ደርሷል፡፡
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ በአፋር ክልል እና በአማራ በኩል በከፈተው ጦርነት ከዚህ የከፋ ህዝባዊ እልቂትን ለማስከተል እየሰራ በመሆኑ ይህን ፈፅሞ ከሰብአዊነት የራቀ አረመኔያዊ በጭካኔ የተሞላ ድርጊት በማውገዝ ከሰብአዊነት ጎን ሊቆም ይገባል!
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ነሐሴ 21/2014 ዓ.ም
ሰመራ
ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ፤
አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያን ሀገረ መንግስት ስልጣን ተቆናጦ በነበረበት ዘመን፣ የአገራችን አንድነት ለመናድና ህዝቦቿን እርስ በርስ ለማናከስ ያልዘራው ጥላቻ፣ ያልሸረበው ሴራ አልነበረም። ከትናንት እስከ ዛሬ ይሄ አሸባሪ ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የተሰጠውን ተልዕኮ እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያንን በብሔርና በሐይማኖት ከፋፍሎ ሲያባላ ኖሯል።
ለዘመናት የኖርንበትን የመቻቻል እና ሀገራዊ አንድነታችንን ለመሸርሸር ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዘረፋዎችን አካሂዷል፣ ታሪክ ይቅር የማይለውን በደል በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ ፈፅሟል።
ከምንም በላይ ደግም ሀገራዊ አንድነትን ለመናድ ያመቸው ዘንድ ሆን ብሎ የታዛቡ ታሪካዊ ኩነቶችን በመድረስ እና በመተረከ ኦሮሞና አማራን እሳትና ጭድ አድርጎ ሳለ። አንዱን ጠባብ ሌላውን ትምክህት ብሎ ሰየመ። እርስ በርስ በማናከስና ጥርጣሬን በማስፈን ከፋፍሎ መግዛትን የአገዛዙ ስልት አድርጎ ሲጠቀምበት ኖረ።
ይሄም ብቻ ሳይሆን አሸባሪው ሕወሓት በስልጣን ዘመኑ መባቻ ላይ ተዋልዶና ተጋምዶ ለዘመናት አብሮ የኖረውን የኦሮሞና የሶማሌ ህዝቦች አንድነት ለመናድ በሸረበው ሴራ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎችን በማፈናቀል የጭካኔውን ጥግ አሳይቷል፤ የሀገራችንን አንድነትም አደጋ ላይ ጥሎ ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ስሪትና የህዝቦቿ አንድነት የተገመደበት እሴት የፍርሰት ሴራን ተቋቁሞ የቡድኑን የከፋፍለህ ግዛ ስርዓትን አሽቀንጥሮ በመጣል ነፃነት፣ እኩልነት፣ወንድማማችነትና የህብረብሔራዊ አንድነት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር እውን እንዲሆን አደረገ።
ኢ-ፍታዊነትና የበላይነትን የለመደው አሸባሪው ሕወሓት እኩልነትን እንደ በደል በመቁጠር አሻፈረኝ በማለት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ እንደሚጓዝ ግልፅ በማድረግ ባንዳነቱን አረጋገጠ። የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አጀንዳን እውን ለማድረግ በአማራና አፋር ክልሎች ቀጥተኛ ጥቃት በመፈፀም የንፁሃን ዜጎቻችንን ደም አፍስሷል፣ ንብረት አውድሟል፤ የትግራይ ወጣቶችን በእሳት ማግዷል።
በምስራቅ ኢትዮጵያ በኩል ከአልሸባብ ጋር በመሆን፣ በኦሮሚያ ክልል በአምሳሉ የፈጠረውን ሸኔን በመጋለብ፣ በቤንሻንጉልና በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ጭፍሮቹን በማሰማራት ኢትዮጵያን እረፍት ነስቶ በሂደት ለማፍረስ ያላደረገው ጥረት አልነበረም።
ከግጭትና ጦርነት ውጪ መኖር የማይችለው አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ መንግሥት የተዘረጋለትን የሰላም እጅ አሻፈረኝ በማለት በአማራና አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በፅኑ ያወግዛል፤ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከአማራና አፋር ህዝቦች ጎን ሆኖ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።
አለማቀፉ ማህበረሰብም አሸባሪው ቡድን ህዝባዊ መዓበልን እንደወታደራዊ ስልት በመጠቀም እየፈፀመ ያለውን አስነዋሪና አረመኔያዊ ድርጊትን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግስት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበል አስፈላጊውን ግፊት ማሳደር አለበት። አሸባሪው ሕወሓት አሁን እየተከተለ ያለው ኋላቀር የህዝባዊ ማዕበል ወታደራዊ ስልት የትግራይ ወጣትን በመማገድ ኢትዮጵያን ለመበታተን ቆሮጦ መነሳቱን በተግባር ያረጋግጣል።
ይህ ቡድን በዚህ ጭካኔ በተሞላበት ተግባር የጀመረውን መጠነ ሰፊ ማጥቃት ካላቆመ አልያም ለተሰጠው የሰላም አማራጭ ይሁንታን ካላሳያ ለዜጎች ደህንነት፣ ለሀገራዊ ሉዓላዊነት እና አንድነት ሲባል የፌዴራል መንግስት የሚወስደውን ህጋዊና ሞራላዊ እርምጃዎችን በፅኑ የሚደግፍ መሆኑን የኦሮሚያ ብሐራዊ ክልላዊ መንግስት ያረጋግጣል።
ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ነሐሴ 22, 2014
ፊንፊኔ
ከሐረሪ ክልል የፀጥታው ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ፤
የሐረሪ ክልል የፀጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ ክልላዊ የጸጥታ ጉዳዮች ተወያይቷል።
በሐረሪ ክልል እየተስተዋለ የሚገኘው አንፃራዊ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ የፀጥታ ሀይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ሀይል እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል።
ምክር ቤቱ በክልሉ የተከናወኑ የሠላምና ጸጥታ ሥራዎች ፍሬያማ መሆናቸውን የገመገመ ሲሆን፤ በቀጣይም በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
በተለይም የህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ህገ ወጥ ግንባታ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ኮንትሮባንድን እና ህገ ወጥ ንግድን ከመቆጣጠር አንፃር እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ይበልጥ በማጠናከር ህዝብን ባሳተፈ መልኩ በቁርጠኝነት ይሰራል።
ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆኖ የጥፋት ተልእኮ የሚፈጽሙ አካላትን በማጥራት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ በትኩረት የሚሰራ ይሆናል።
በክልሉ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በሚያደርጉ ስግብግብ ነጋዴዎች እና በመልካም አስተዳደር ችግር ህዝብን የሚያማርሩ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጫው አመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ የማህበራዊ ሚዲያን ለእኩይ ዓላማ በማዋል ህዝብን ከመንግሥት የሚያጋጩ መልዕክቶችን በመቅረጽ የሚያሰራጩና፣ እምነትን መነሻ በማድረግ ግጭት የሚቀሰቅሱ አካላት እንዲሁም እውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ በየማህበራዊ ሚዲያው የሚደረግ ዘመቻ የፀጥታ ምክር ቤቱ በምንም መልኩ እንደማይታገስ ያስታውቃል።
ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ዛሬም እንደ ትናንቱ የክልላችን ህዝቦች ለሰላም ዘብ እንዲቆም ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የፌዴራል መንግስቱ ለሰላም ያሳየውን ዝግጁነትና ያቀረበውን ጥሪ ወደ ጎን በመተው ጦርነት በመጀመሩ የትግራይ ክልል ሕዝብና በተለይም ወጣቶችን ለጦርነት እየማገደ እና በአጎራባች ክልሎች የለመደበትን ጥቃት እያደረሰ ይገኛል።
ስለሆነም የክልሉ ፀጥታ ም/ቤት የፌዴራል መንግስት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት እና ተጨባጭ እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ የመደገፉ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ለመግለፅ ይወዳል።
የሐረሪ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት
ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም
ሐረር
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ፤
አሸባሪው ሕወሓት ባለፉት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት የብዝሃ ብሔር፣ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ባለቤት የሆነችውን የኢትዮጵያን አንድነት ለመናድ እና ብሔር ብሔረሰቦችን እርስ በርስ ለማፋጀት ሌት ከቀን ሲሠራ ቆይቷል። በዚህ ክፉ ሴራው በርካታ ንጹሃንን ህይወት በመቅጠፍ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥቁር ጠባሳ ፈጽሟል።
ይህ አሸባሪ ቡድን በስልጣን ላይ በነበረባቸው ዓመታ በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈጠረው ጥርጣሬ፣ መከፋፈልና እልቂት ሳያንሰው የጥፋት ሴራ ሁነኛ ዋነኛ መገለጫው ማድረጉን ደጋግሞ አሳይቷል። በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ከፈጸመው ክህደት ጀምሮ የትግራይ ወጣቶችን ወደ ጦርነት በማስገባት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ግልጽ ጦርነትና ወረራ ያደረሰው እልቂት አሸባሪ ቡድኑ ለሰብዓዊነት ምንም የማይራራ አረመኔ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት ተላላኪዎቹን በመጠቀም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሀገራችን አካቢዎች ንጹሃንን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል። በርካታ ውድመትንም ፈጽሟል።
የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮነት እንቅልፍ የሚነሳው ይህ አሸባሪ ቡድን ተላላኪዎቹን ተጠቅሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሕዝብ ከወንድም የኦሮሚያና የአማራ ክልል ሕዝቦች ጋር ለመነጠል በክልሉ ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች ጋር የሚዋሰኑ የመተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ ዞኖች እንዲሁም የማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ አካባቢዎችን የጦርነት ቀጣና የማድረግ ክፉ ሴራውን ሲፈጽም ቆይቷል።
አስቸጋሪ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ግን የዚህ አሸባሪ ቡድን ባንዳነት የበለጠ አጠነከራቸው እንጂ በጋራ እንዳይቆሙ አልገደባቸውም። ለህዝብ ሠላም ኃላፊነት የሚሠማው የኢትዮጵያ መንግስት ግልጽ የሠላም አማራጭን ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ተጨባጭ ሂደት ገብቷል።
ነገር ግን ያለፈው ጥፋት አልበቃው ያለው አሸባሪው ሕወሓት ወትሮም ቢሆን ከጦርነትና እልቂት ውጪ መኖር እንደማይችል ያሳየበትን ተግባሩን አሁንም በድጋሚ ቀጥሎበታል። አሸባሪ ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበውን የሠላም ጥሪ በእምቢታ ረግጦ የትግራይን ወጣት ለጥፋት በመጠቀም በአማራና አፋር ክልሎች ዳግም ጦርነት ማወጅን ምርጫው አድርጓል።
መፍትሔው በሠላም ተወያይቶ መፍታት ሆኖ እያለ አሸባሪው ሕወሓት አሁን የጀመረው ዳግም ጦርነት ለሕዝብ ሠላም ከመጨነቅ ይልቅ የብዝሃነት ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ መቼም የማይተኛ መሆኑን ደጋግሞ ያረጋገጠበት መሆኑን ያሳያል።
አሁንም ቢሆን አሽባሪው የሕወሓት ቡድን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የቀረበውን የሠላም አማራጭ በአግባቡ ሊጠቀምበት ይገባል።
ዓለማቀፉ ማኅበረሰብም በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ዳግም ወረራ ከማውገዝ በተጨማሪ ለህዝቦች ሠላም ሲባል በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን የሠላም አማራጭ አሸባሪ ቡድኑ እንዲቀበል አስፈላጊውን ትብብርና ግፊት የማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት አሸባሪው ሕወሓት ህጻናትን ጨምሮ ህዝባዊ ማዕበልን በመጠቀም በአማራና አፋር ክልሎች እያካሄደ ያለውን ወረራ በጽኑ ያወግዛል።
የክልሉ መንግስት አሸባሪው ሕወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ወረራ ለመቀልበስና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ጥረት እንደከዚህ ቀደሙ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።
አሸባሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ እየቀረበለት ያለውን የሠላም አማራጭ በድጋሚ በማጤን የማይቀበል ከሆነ እና ወረራውን አጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ ለህዝብ ደኅንነት እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ሲባል በፌዴራል መንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችን የሚደግፍ እና ኃላፊነቱን የሚወጣ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ለማረጋገጥ ይወዳል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ 22/2014 ዓ.ም
አሶሳ፣
በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ፤
አሸባሪው ሕወሓት የመንግስትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ጦርነት ማወጁ ለሰላም ቦታ የማይሰጥ መሆኑን ማረጋገጫ ነው። ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለመበታተን ወደ ኋላ እንደማይል በግልጽና በአደባባይ ያሳየበት እንደሆነም በመግለጫው አመልክቷል።
የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በመግለጫው እንዳለው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መንግስት የጀመረውን የሰላም አማራጭ በመተው አሸባሪው ሕወሓት ሰላም እንደማይፈልግ አረጋግጧል።
በቅርቡም በጋምቤላ ከተማ በተላላኪዎቹ በጋ.ነ.ግ እና በሸኔ የሽብር ቡድኖች ሊደርስ የነበረውን የከፋ ጥቃት በፀጥታ ሀይሉ እና በህብረተሰቡ የተቀናጀ ጥረት ማክሸፍ ተችሏል።
አሸባሪ ቡድኑ በተለይም የትግራይ ክልል ወጣቶችና አጠቃላይ ህዝቡን ለማያባራ እልቂትና የከፋ ችግር በመዳረግ የራሱን ህልውና ለማስቀጠል እየሰራ ይገኛል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰላም ወዳድ በመምሰል የሚያሰራጨው መረጃ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት የሚጠቀምበት ስልቱ እንደሆነም በመግለጫው አመልክቷል።
አሁን ላይ የመንግስትን የሰላም አማራጭ ባለመቀበል ጦርነት መክፈቱ የቡድኑን አረመኔያዊነት ያመላክታል። ወገናችን የሆነው የትግራይ ህዝብ የሰላም አማራጭን ባለመቀበል ዳግም ጦርነት የከፈተውን ቡድን በአንድነት ሊያወግዘውና ሊቃወመው ይገባል።
አሸባሪው ሕወሓት ዳግም በከፈተው ጦርነት ሳንሸበር የአንድነትና የመተሳሰብ እሴታችን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል።
የዜጎች ደህንነትን ለመጠበቅ ሲል የፌዴራል መንግስት የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃዎችን በፅኑ የሚደግፍ መሆኑን የጋምቤላ ህዝቦች ብሐራዊ ክልላዊ መንግስት ያረጋግጣል።
የሽብር ቡድኑ የከፈተውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የጋምቤላ ክልል ህዝብና መንግስት የሚያደንቅ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በመሆን የሚጠበቅበትን ይወጣል።
የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት
ነሀሴ 22/2014 ዓ.ም
ጋምቤላ
ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት የተሰጠ መግለጫ፤
አሸባሪው ሕወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ወረራ በተባበረ ክንድ ለመቀልበስ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ዝግጁ ነው።
ከሰላም ይልቅ ጦርነትን መርጦ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመዳፈር አልሞ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የሽብር ቡድን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የክልሉ መንግስት ዝግጁ ነው።
መላው የክልላችን ህዝቦች ሀገር በጠላት በተወረረች ጊዜ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ ጀግኖቻችን በስንቅ ዝግጅት፣በሞራል፣ከዚህ ባለፈም ወደ ግንባር በመዝመት አለኝታቸውን አሳይተዋል።
ሰርተን መለወጥ የምንችለው ሀገር ሰላም ስትሆን እንደመሆኑ መጠን አሸባሪው ሕወሓት ህዝባዊ ማዕበል በመጠቀም የተቃጣብንን ወረራ በአስተማማኝ ደረጃ ለመመከት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል።
አሸባሪው ሕወሓት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት በህዝብ ደም ሲነግድ ቆይቷል።እኔ ያልመራኋት ሀገር መፍረስ አለባት በሚል እሳቤ ለሰላም የተዘረጋውን አማራጭ ወደ ጎን በመተው ለጋ ህጻናትን በማሰለፍ ግልጽ ወረራ መጀመሩን መላው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊገነዘብ ይገባል።
የሽብር ቡድኑ በንጹሀን ዜጎቻችን ላይ ካደረሰው ጭፍጨፋ በተጓዳኝ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመተባበር ኢኮኖሚያችን እንዲዳከም ጥረት አድርጓል። ከዚህ ቀደም ተዋደው እና ተግባብተው በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ግጭት እንዲኖር የዘወትር ተግባሩ አድርጎ ቆይቷል። በሌላ በኩል የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት በመፍጠር ሀገሪቱን የትርምስ ቀጣና ሲያደርግ እንደነበርም ልብ ሊባል ይገባል።
አሸባሪው ሕወሓት ተላላኪዎቹን በመጠቀም የህብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት የሆነውን ክልላችንን በማወክ ለብዙኃን ሞት፣መፈናቀል፣የንብረት ውድመት እና የአካል ጉዳት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።
የሀገርን ዳር ድንበር እየጠበቀ ባለው በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ከፈጸመው ክህደት ጀምሮ የትግራይ ወጣቶችን ወደ ጦርነት በማስገባት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ግልጽ ጦርነትና ወረራ ያደረሰው እልቂት አሸባሪ ቡድኑ ለሰብዓዊነት ምንም የማይራራ አረመኔ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።
መላው የሀገራችን ህዝብ ሀገር በጠላት ስትወረር ከዳር እስከ ዳር ሆ ብሎ በመነሳት ጠላትን አሳፍሮ መመለስ ከጀግኖች አባቶቻችን የወረስነው አኩሪ ታሪክ አለን። ይህም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአሁኑ ትውልድ የሚደገም ይሆናል።
በአማራና አፋር ክልሎች የደረሰውን ወረራ የክልሉ መንግስት የሚያወግዝ ሲሆን መንግስት ተገዶ የገባበትን ህግ የማስከበር እርምጃ የምንደግፍ ይሆናል።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት
ነሐሴ 22/2014 ዓ.ም
ከሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ፤
ትዕግስትን ለሚንቅ ፣የሰላም ጥሪን ለማይቀበል ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ለሚዳፈር የሀገር አፍራሽ ቡድን ግብአተ መሬቱ እስኪረጋገጥ የሲዳማ ህዝብና የክልሉ መንግስት እንቅልፍ የለውም።
የአሸባሪው ሕወሓት መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን ትቶ ለሦስተኛ ጊዜ በሀገራችን ላይ ጦርነት ከፍቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜያት አማራጭ የሰላም መንገዶችን ቢያቀርብለትም ድብቅና ስውር አላማው ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ስለሆነ የሰላምና የዕርቅ ጥያቄዎችን ሊቀበል አልቻለም ።
ሕወሓት ሀገር ለማፍረስ ወደ ኋላ የማይል በጥላቻ የታወረ አሸባሪ ቡድን በመሆኑ በሀገራችን ላይ በተደጋጋሚ ጦርነት ከፍቷል። ይህም ለሰላም ምንም አይነት ቦታ የሌለው ለሀገርና ለህዝብ ጠንቅ ተልዕኮ እንዳነገበ ያመላክታል ።
ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜ በሀገራችን መንግስትና ንፁሃን ህዝብ ላይ የከፈተው ጦርነት ታሪክ ይቅር የማይለው መጠነ ሰፊ የህይወትና የንብረት ውድመትን አድርሷል።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት ለኢትዮጵያና ለንፁሃን የትግራይ ህዝብ ያለውን ንቀት አሳይቷል።
ከዚህ ቀደም በከፈተው ጦርነት የትግራይን ህዝብ በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመደለልና አልደለል ያለውን በማስገደድ አላስፈላጊ የህይወት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ አድርጓል።
ከስህተቱ የማይማረው ሕወሓት ዳግም ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የከፈተው ጦርነት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያለውን ጥላቻ ያሳየበት ነው። ይህም ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ በቁጣ የሚያነሳሳና በተባበረ ክንዳቸው ሕወሓትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱን እንዲያፋጥኑ የሚያደረግ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሕወሓትን ሀገር አፍራሽ ተልዕኮ፣ ከፋፋይነት፣ ጥላቻና ነጣጣይነት ዕኩይ ሴራ ጠንቅቆ የተረዳ በመሆኑ ዳግም በሀገራችን ላይ የከፈተውን ጦርነት በአስተማማኝ ሁኔታ ይቀለብሱታል።
የሲዳማ ህዝብና የክልሉ መንግሥት የአሸባሪውን የሕወሓትን ሴራ ጠንቅቆ የሚያውቅ ለ27 አመታት ሲታገል የቆየና ሕወሓት ማን እንደሆነ በደንብ የተረዳ ህዝብ በመሆኑ የሕወሓት ግባተ መሬት እስኪፈጸም ድረስ ለክልሉ ህዝብና መንግሥት ላፍታም ቢሆን እረፍት የለውም።
የሲዳማ ህዝብና መንግስት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን የክልሉ መንግሥት ያረጋግጣል።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት
ነሐሴ 22/2014 ዓ.ም
ሀዋሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2014