ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በስፖርቱ ዓለም በማስጠራት ጀምራ ለኅብረሰተብ ፍቅርና አንድነት መጎልበት ለምትተጋው ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የዓመቱን የክብር ዶክትሬት ትናንት አበርክቶላታል።
ለእንቁዋ አትሌት ለአገሯ ላበረከተችውና እያበረከተች ለሚገኘው አስተዋጽኦም ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ይህን ክብርና እውቅና ሲሰጣት የመጀመሪያ አይደለም። ከዚህ ቀደም የጅማ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ የክብር ዶክትሬት አበርክቶላታል።
አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በአትሌቲክስ ሕይወቷ ላበረከተችው አስተዋጽኦ የተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝታለች። ከደቡብ አፍሪካው ዌስተርን ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ እኤአ 2015 ላይ የክብር ዶክትሬት ማግኘቷም አይዘነጋም። በጣልያን በተካሄደ ዓለም አቀፍ ሽልማት የሕይወት ዘመን የስፖርታዊ ጨዋነት ዘርፍ ተሸላሚ የሆነችው ደራርቱ፣ በባርሴሎና ኦሊምፒክ በአስር ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ የመጀመሪዋ ሴት አፍሪካዊት አትሌት በመሆኗ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የክብር ሽልማቶች በየጊዜው ማግኘቷን ቀጥላለች።
በአዳማ አውራ ጎዳና ላይ የሚገኘው ትልቁ አደባባይ በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ተሰይሟል። በአዲስ አበባ ከተማ ሀያት አካባቢ የሚገኘው የሀያት አደባባይም በቅርቡ በስሟ ተሰይሟል። በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም 350 ግራም የወርቅ ኒሻን እንዲሁም የ2021 ሞዴል ሌክሰስ ቪ8 መኪና ከኦሮሚያ ክልል እንደተበረከተላትም ይታወሳል።
ደራርቱ በውድድር ዘመኗ አጠቃላይ ከ13 በላይ ወርቆች፣ 2 ብሮች፣ የነሃስ ሜዳሊያ እና 3 ዲፕሎማዎችን ለአገሯ ኢትዮጵያ አበርክታለች።
የኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ፈለግ በመከተል በ10ሺህ እና በ5ሺህ ሜትር ርቀቶች ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ሴት አትሌቶች መካከል አትሌት ጌጤ ዋሚ፣ ጥሩነሽ ዲባባ እና መሰረት ደፋር ተጠቃሾች ናቸው።
አሁን ላይ ደራርቱ በአዲስ አበባ እና አዳማ ከተሞች በሆቴል እና የንግድ ህንፃ ግንባታ ተሰማርታ ትገኛለች። አትሌቷ ስለ አሁናዊ ሁኔታዋ ስትናገር፣ “ከአትሌቲክስ ባፈራሁት ገንዘብ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራሁ ነው፤ ራሴንና ቤተሰቤን ከመርዳት አልፌ ማለት ነው። በርካታ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሌን አስተዋፅኦ እያበረከትኩ ነው” በማለት ትናግራለች።
አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል፣ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ዞን ምክትል ፕሬዝዳንትነት፣ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ የአካባቢው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና እያገለገለች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆና በማገልገል ላይ የምትገኘው አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈፃሚም አባል ነች።
ደራርቱ በአትሌትነት ዘመኗ አፍሪካዊያን ጭምር ብዙ ገፍተው ባልወጡበት የረጅም ርቀት ውድድር ፈንጥቃ በመውጣት ከሷ በኋላ ለመጡ ሴት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችም ፈር ቀዳለች። ከአትሌትነት ወደ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳትነት ስትመጣም ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ታሪክ ከፍተኛውን 4ወርቅ ጨምሮ በ10 አጠቃላይ ሜዳሊያ ኢትዮጵያ ወደ ስኬት ጫፍ እንድትደርስ ሚናዋን ተጫውታለች።
አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ስኬቷ ከአትሌቲክስ የመም (track ) ውድድሮች እስከ ፌዴሬሽን አመራርነት የዘለቀ ነው በሚል ትውልድ ከፍ አድርጎ እንዲዘክረው ተደርጎ የተጻፈው አበርክቶዋ አገራዊ ምልክትነቱ እና አርዓያነቱ በጉልህ ቀለም የተጻፈ ታሪክ እንዲሆን አድርጎታል።
ኮማንደር ደራርቱ በ1984 ዓ.ም. በስፔን በባርሴሎና ተዘጋጅቶ በነበረው ኦሎምፒክ በ10ሺህ ሜትር ተወዳድራ ድል አስመዝግባ ወደአገሯ እንደተመለሰች የሻለቃነት ማዕረግ አግኝታለች። ደራርቱ ስለ ባርሴሎና ኦሎምፒክ ስትናገር፣ “የባርሴሎና ኦሎምፒክ የሕይወቴን አቅጣጫ የቀየረ ነበር። ከአስራ አለቃነት ወደ ሻለቃነት ደረጃ አደግኩኝ፤ ደመወዜ ከ200 ብር ወደ 600 ብር አደገ፤ ዝናዬም ናኘ” ስትል ድሉ ያመጣላትን በረከት ትናገራለች።
በባርሴሎናው ኦሎምፒክ ያገኘችው የወርቅ ሜዳሊያ የእርሷ እና የአገሯ ብቻ ሳይሆን የመላ ጥቁር ህዝቦች ድልም ነበር። ከዚህ የደራርቱ ድል በኋላም በእርሷ አሸናፊነት መንፈስ የተቃኙ በርካታ ሴት ኢትዮጵያዊያን ሯጮች ለመታየት በቅተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ደራርቱ በ37 አመቷ የኒውዮርክ ማራቶንን ማሸነፍ የቻለች ምርጥ እና ፋና ወጊ ኢትዮጵያዊ አትሌት ነች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 /2014