በዚህ ሳምንት ከአንጋፋው ደራሲ እና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ ጋር በተያያዘ አንድ ዜና ተሰምቷል:: በመከላከያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ በሰቆጣ ከተማ የደራሲና ተርጓሚ ማሞ ውድነህ መታሰቢያ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ዛሬ አስቀምጧል የሚል ነበር ዜናው።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ ተገኝተው ነበር። በእውነቱ ደራሲው ለኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ ካበረከቱት አስተዋጽኦ አንጻር ይህ ቤተ መጻህፍት ቢያንስ እንጂ አይበዛባቸውም:: እኛም ይህን ዜና ተንተርሰን እኚህን የብዙዎችን የንባብ ልምድ በተለይ ስለላ ላይ ባተኮሩ መጽሐፎቻቸው ያሳደጉ ታላቅ ሰው በአጭር ጽሁፍ ልናስታውሳቸው ወደድን:: ጽሁፎቹ ከተለያዩ ምንጮች የተሰበሰቡ ናቸው::
በቀድሞው የወሎ ክፍለ አገር ዋግ አውራጃ አምደወርቅ ከተማ ውስጥ በ1923 ዓ.ም ተወለዱ። ወላጅ እናታቸውን በሞት አባታቸውን ደግሞ በአርበኝነት ያጡት ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፤ የልጅነት ሕይወታቸውን ያሣለፉት እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ነበር:: በተወለዱበት አካባቢ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ደሴ ከተማ ድረስ በመሄድ በወ/ሮ ስህን ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረዋል:: ከዚያም በመቀጠል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ኑሮአቸውን ለማሻሻልና ትምህርታቸውን ለመከታተል ጥረት አድርገዋል:: በ1948 ዓ.ም. ልብወለድ ጽሁፎች መጻፍ የጀመሩት ደራሲ ማሞ ውድነህ የመጀመሪያ ጽሑፋቸው ባለ 160 ገጽ የሆነውና በትያትር መልክ የተተወነው “የሴትዋን ፈተና አለፈ በደህና” የሚል ነበር::
ማሞ ውድነህ የቴአትር ደራሲ፥ ጋዜጠኛና ለ12 አመት (ከ1985 – 1997 ዓ.ም ድረስ) የቀድሞው የኢትዮጵያ ደራሲዎች ማኅበር ሊቀ መንበር ነበሩ። የ54 መጻህፍት ደራሲና ተርጓሚ የነበሩት አቶ ማሞ በማስታወቂያ ሚኒሰቴር ስር በሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔ ቶች በጋዜጠኝነት የሰሩ ሲሆን የፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ መስራችና ተባባሪ ዋና አዘጋጅ ነበሩ:: በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆነው በተመደቡበት የጋዜጠ ኝነትና የፖለቲካ ስራ በተጨማሪ ህብረት በተሰኘው ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣ ዘገባዎችና ትንታኔዎች ያቀርቡ ነበር።
አቶ ማሞን ይበልጥ ታዋቂና ተወዳጅ ያደረጋቸው በሥነ ጽሑፉ መስክ ያበረከቱት መጠነ ብዙና ዘርፈ ሰፊ የድርሰት ሥራ ዎቻቸው ናቸው:: 53 መጻሕፍት ያሳተሙ ሲሆን ሥራዎቻቸው በስለላ፣ በታሪክ፣ በልብለወድና በተውኔት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት፤ የደቡብ ሱዳን ብጥብጥ፤ የሴቷን ፈተና፤ ብዕር እንደዋዛ፤ ከወንጀለኞቹ አንዱ፤ ሞንትጐመሪ፤ ቬኒቶ ሙሶሊኒ፤ የኤርትራ ታሪክ፤ የገባር ልጅ፤ የኛው ሰው በደማስቆ፤ ሁለቱ ጦርነቶች ፤ የ፪ ዓለም ሰላይ፤ አደገኛው ሰላይ፤ ምጽአት- እሥራኤል፤ ዲግሪ ያሳበደው፤ ሰላዩ ሬሳ፤ ካርቱም ሔዶ ቀረ?፤ የ፲፯ቱ ቀን ጦርነት፤ የ፮ቱ ቀን ጦርነት፤ የካይሮ ጆሮ ጠቢ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ጽሁፋችንን ከመጠቅለላችን በፊት ግን ከታላቁ ደራሲ ጋር የሚገናኝ አንድ አስገራሚ ታሪክ ጀባ እንበላችሁ:: በደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ተዘጋጅቶ በ1981 ዓ.ም “ዮሐንስ” በሚል ርዕስ የታተመው መጽሐፍ የህትመት ታሪክ አስገራሚ ነው::
ነገሩ የተከሰተው ከ31 ዓመታት በፊት ነው። በወቅቱ አፄ ዮሐንስ አራተኛ የተሰውበት መቶኛ ዓመት የደረሰበት ወቅት ነበር:: በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ፣ ታላቁን ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህን በእንግድነት ጋበዘ:: ጋሽ ማሞ ከደርግ/ኢሠፓ ዘንድ ቀርበው ጉዳያቸውን አስረዱ፤ “በእንግሊዝ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አፄ ዮሐንስ አራተኛ የተሰውበትን መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባዘጋጁት ክብረ-በዓል ላይ እንድገኝ ጋብዘውኝ ነበር::”አሉ::
ከደርግ/ኢሠፓ የተሰጣቸው ምላሽ አስደንጋጭም አስገራሚም ነበር:: “ስለ አፄ ዮሐንስ አንድ መጽሐፍ ያዘጋጁና በዓሉን እዚሁ እናክብረው::” የሚል ምላሽ!…:: ጋሽ ማሞ ይህን ትዕዛዝ ሲቀበሉ፣ አፄ ዮሐንስ የተሰውበት መቶኛ ዓመት ሊከበር ሠላሳ የማይሞሉ ቀናት ነበር የቀሩት:: ሠላሳ በማይሞሉ ቀናት ውስጥ አንድ መጽሐፍ አዘጋጅቶ ለሕትመት ማብቃት::.. ሆኖም ሰውዬው ማሞ ውድነህ ናቸውና “ዮሐንስ” የተሰኘ መጻሕፍ በሃያ ምናምን ቀናት አዘጋጅተው ለሕትመት አበቁ::
ከ60 በላይ መፃህፍትን የደረሱትና የተረጎሙት አንጋፋው ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም. በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 /2014