ብዙ ኢትዮጵያውያን በደስታ ካነበቧቸው እና ሌሎችም እንዲያነቧቸው ከሚጋብዟቸው መጻህ ፍት መካከል የአና ማስታወሻ አንዱ ነው፡፡ ይህ በመላው ዓለም እጅጉን ተወዳጅ የሆነ መጽሐፍ ኢትዮጵ ያውያንም እንዲያነቡት እና እንዲማሩበት ያደረገው ሰው ደግሞ ስሙ አዶኒስ ይባላል፡፡ ይህ ታላቅ ደራሲ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ እነሆ 2 አመት ሆነው፡፡ ዜና እረፍቱ የተሰማውም በዚህ ሰሞን ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር፡፡
እውነተኛ ስሙ አድነው ወንድይራድ ይባላል። ግሩም ደራሲ ነው፡፡ ሆኖም የመጀመሪያ ሙያው ግን ደራሲነት አልነበረም፡፡ የመጀመሪያ ስራው አርክቴክቸር ነው፡፡“ትምህርቴ ከኪነጥበብ ጋ ግንኙነት ባይኖረውም ብዙ አንብቤአለሁ፡፡ አሁንም አነባለሁ፡፡ በኪነጥበብ ውስጥ ራሱን እንዳስተማረ ሰው ነው ራሴን የምቆጥረው!” የሚለው አዶኒስ እውነተኛ ስሙ አድነው ወንድይራድ ነው፡፡ የንባብ ሱሰኛ የሆነው አዶኒስ በ1979 ዓ/ም የአርክቴክቸር ትምህርቱን ያጠናቀቀ ቢሆንም ነፍስያው ወደ ድርሰቱ ዓለም ነውና ሌት ከቀን ይደክም ነበር፡፡ አንጋፋው ደራሲ ሃይሉ ጸጋዬም ወንድሙ ስለነበር ብርታት እንደሆነውም ጠቅሶ ነበር “ሃይሉ ወንድሜ ስለሆነ በአንዳንድ ስራ እንተጋገዛለን!” ሲልም በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር፡፡
አዶኒስ በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ ስሙ ከፍ ብሎ ይነሳል፡፡ “ገመና” ቁጥር አንድ ለየት ያለ የታሪክ ፍሰትና ቴክኒክ ኖሮት የየቤታችንን ገመና ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነበር፡፡ የአንድ አመት ቆይታ የነበረው “ገመና” ቁ 1 በርካታ አድናቂና ተመልካችም አግኝቶ ነበር፡፡ ሌላኛው ስራው ደግሞ “መለከት” የቲቪ ተከታታይ ድራማ ነው፡፡ በሃይሉ ከበደ ድርጅት በሮኆቦት ፕሮዲውስ የተደረገ ሲሆን የ104 ክፍል ቆይታ ነበረው፡፡ በፊልም ዝግጅቱም ቢሆን “አንድ አድል” የተሰኘውን የገዛ ጽሁፉን ራሱ ያዘጋጀ ሲሆን በብሩክ አምባቸው የተዘጋጀም “መንትዮች” የተሰኘ ፊልም ነበረው፡፡
አዶኒስ ከትርጉም የተውኔት ስራዎቹ ሶስቱን እንጥቀስ ቢባል አንደኛው በኢትዮያ ብሄራዊ ቴአትር የቀረበው ክሊዮ ፓትራ ነው፡፡ በራስ ቴአትር የአና ማስታወሻና በሀገር ፍቅር ቴአትር ደግሞ ጣውንቶቹ የተሰኘው የመድረክ ተውኔትን ማንሳት ይቻላል፡፡ የራሱ ወጥ የሆነውን ቴአትርም ቀስተ ደመናን በባህል አዳራሽ አቅርቦ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የአና ማስታወሻንም በመጽሐፍ መልክ ጥሩ አድርጎ የተረጎመልን አዶኒስ ነው፡፡
የ“ገመና” ቁጥር አንድ የቴሌቪዥን ድራማ የሽልማት ስነስርአት እለት ነው፡፡ የአዶኒስ ስም ተጠራና ካሜራዎቹ ሁሉ ወደ መድረኩ አነጣጠሩ፡፡ ግና አዶኒስ የለም፡፡ ሽልማቱን ልትቀበል የወጣችው ባለቤቱ ነበረች፡፡ “…እኔን ወክላ ሽልማት የተቀበለችው ባለቤቴ ነበረች፡፡ እኔ ግን እዚያው ነበርኩኝ!” አዶኒስ በመልክ የማይታወቅ ግን ግዙፍ ስም ያለው ደራሲና ተርጓሚ ነበር፡፡ ምስሉ እንዲታይ አለመፈለጉን አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር “ይሄን የማደርገው በቀላሉ በነጻነት መኖር ስለምፈልግ ነው! ሚዲያ ላይ መውጣት አልፈልግም!” ይል ነበር፡፡
የሁለት ልጆች አባት የነበረው አድነው ወንድይራድ /አዶኒስ/ በገመና ቁጥር አንድ የቴሌቪዥን ድራማ ብቃቱን አስመስክሯል። መለከትን (በ204 ክፍል) የቴሌቪዥን ድራማ አበርክቶልናል። በመድረክ ደግሞ፦ “ክሊዮ ፓትራ”፣ “የአና ማስታወሻ”፤ “ቀስተ ደመና”፤ “ጣውንቶቹ”፣ “አጋምና ቁልቋል”፣ “ሞትና ትንሳኤ” ከትርጉምና ከወጥ ስራዎቹ ይጠቀሱለታል። .
በፊልሙ ዘርፍም፦ “መንትዮቹ”፤ “አንድ እድል”፣ “የማይታረቁ ቀለማት”፣ “መልኅቅ” የተሰኙትን እነሆኝ ብሎናል። ከትርጉም መጽሐፉ፦ “የአና ማስታወሻ”፣ “አዶልፍ ሄክማን”ን ጀባ ብሎናል። በአጭር ልቦለድም የሰላ ብዕር ነበረው። “ፕሮፌሰሩ” አስደማሚ ስራው ነው። አስገራሚ የዘፈን (ጃን ስዩም ሔኖክ የተጫወተውን) እና የሕፃናት ውብ መዝሙሮችን ግጥሞችም አቋድሶናል።
አዶኒስ በሕይወት ዘመኑ መጨረሻ (የ52 ሳምንት) የአንድ ዓመት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ጥንቅቅ አድርጎ ፅፎ ጨርሶ ነው እስከወዲያኛው ያሸለበው። በኒሞኒያ በሽታ ተጠቅቶ የሞተው አዶኒስ ነሐሴ 19 ቀን ሞቶ ስርአተ ቀብሩ ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 /2014